Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሕመምና ሥጋት!

ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ በሙሉ ሐሜቱ፣ አሉባልታው፣ መውጣቱ፣ መውረዱ፣ ልማቱ፣ ችግሩ፣ ሥጋቱ፣ ተስፋውና ሁለም ነገር እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ‹‹እንደ እንስሳ ሆዱን መቼ ይመለከታል፣ ሰው ፍቅር ካገኘ ምግብማ ሞልቷል…›› ያለው ነፍሱን ይማረውና የአገራችን ሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ትዝ እያለኝ እኔ እንዳለሁ አለሁ። ደብዳቤ አስመሰልኩት እንዴ? ምን ይደረግ ሰው በነገር ሆዱን ሲታመም ንግግሩ ሁሉ ብሶት፣ ብሶቱ ደግሞ ደብዳቤ መምሰሉ አይቀሬ ነው። ሰው ደግሞ እንደምታውቁት ነው። ቤት መሥራት ሲያቅተውና ለፍቶ አላልፍልህ ሲለው የነገር ጭቃ እያቦካ ሐሜት በሚባል ነፃ የሽርደዳ ሜዳ ላይ እርስ በርሱ ይለሳሰናል። የዘንድሮን ነገር እንጃልን ብቻ፡፡ እንደ አገር እያሰቡ መኖርን የሚያከብድብን አንዱ ችግራችን ክፍት ውሎ የሚያድረው ገመናችን መሆኑን አትርሱት። ‹‹እንደ እኛ በሰው እንጀራና በሰው ጎጆ ሚስጥር ሥራ የሚፈታ ያለም አይመስለኝ…›› የሚሉኝ እኮ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። እሳቸው ዕድሜ ብዙ ስላሳያቸው ስለሰው ብዙ ነገሮች ያውቃሉ። ስንቱ አለ ከዕድሜው የማይማር? ታዲያስ ባሻዬ አራት ትውልድ እያፈራረቁ በፈጣሪ ፀጋ በማስተዋል ኖረዋል። ቀላል ነው እንዴ? እሳቸው በማስተዋል ሲራመዱ ስንቱ ደግሞ የእንጨት ሽበት ሆኖ መቅረቱ መዘንጋትም የለበትም፡፡ ለምን ይዘነጋል!

‹ወዳጅ ጠላት ሲሆን ክፉ ትዝታ አለው› እየሆነ ነገራችን ሁሉ የኑሮ ግብግብ በ‹እህህ…› ሲወዘውዘን ዕድሜ አልመርጥ አለ እንጂ። ኧረ ተውኝ እባካችሁ፣ የወሬና የአሉባልታ ነገር አሞኝ አይደል ዛሬ የተገናኘነው? ‹‹አሉባልታ አገር ሊያፈርስ ምን ቀረው?›› ስል የሰማኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንተ ደግሞ በኮሪደር ልማት ሰበብ አፍርሶ መገንባት ላይ የተጠመድነው ለምን ሆነና?›› ይለኛል። እሱ መቼስ ከጀመረ አይለቅም አይደል? ‹‹ይልቅ እኔን የሚገርመኝ ይህ የወሬና የአሉባልታ ሥር የሰደደ ልማድ እያለ፣ ምሁራኑ አፉን እንደ ለጎሙት ፈረስ በ‹ዝም አይነቅዝም› ዘዬ ተደላድለው መቀመጣቸው ነው…›› ብሎ ጨመረልኝ። ‹እንዲያው ልፉ ብሎን እንጂ ምሁራኑ አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉት ወጀቡ ሲያልፍ ነው እንዴ?› ብዬ በውስጤ ታዘብኳቸው። ድሮም የሐሜት ትርፉ ትዝብት ነው አትሉልኝም? ‹‹የሆነስ ሆነና ሁሉ ነገር ሞልቶ በተረፋት አገር ውስጥ ምግብ ብርቅ ሆኖ የሰው ልጅ እየተራበ ነው እየተባለ እኮ ነው ምሁራን የታሉ እያልን የምንጨነቀው…›› ሲሉኝ የነበሩት አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ ጉድ እኮ ነው!

ሰሞኑን አንድ ሁለት የማሻሽጣቸው ቪትዝ መኪኖች እጄ ላይ ነበሩ። ወዲያ ወዲህ እላለሁ። አንዱ ዳቦ ሲሸጥ ሁሉም ተያይዞ ዳቦ ነጋዴ፣ አንዱ ካፌ ሲከፍት ሁሉም ካፌ መክፈት ልማድ ስለሆነ የዚህ አገር ሊሻር ያልቻለ የቢዝነስ ባህል፣ የመኪና ነጋዴው እንዴት እንደ አሸን እንደፈላ አትጠይቁኝ። ለነገሩ ሸማቹ በኑሮ ውድነት አቅሉን ቢስትም ገበያ መውጣቱ አልቀረም። አደራ ደግሞ የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰምቶኝ ‹የቪትዝ ሸማቾችና ሻጮች ማኅበር መጎልበት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ማሳያ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ አንበርብር ምንተስኖት ተናገሩ› ብሎ ዜና እንዳይሠራብኝ። ምን ይታወቃል? መጠርጠርና መጠራጠር መስሎኝ አከባብሮ እያኖረን ያለው። እንዲያው እኮ ምናለበት አሁን ክፉ ባታስወሩኝ? አንዱ በቀደም ዕለት ስለሰሞኑ ስለአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ እየተነተነ ነበር፡፡ እኔ ሰውየውን የማውቀው ከኮንትሮባንድ ነጋዴነት አሁን ደግሞ ወደ መሬት ደላላነት መሸጋገሩን ነው፡፡ በየት በኩል የፖለቲካ ተንታኝ እንደሆነ ስላልገባኝ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ስጠይቀው፣ ‹‹ዋርካ በሌለበት እምቧጮ አድባር ይሆናል ሲባል እየሰማህ አይደል እንዴ የኖርከው…›› ሲለኝ ሰውነቴ ከላይ እስከ ታች ቀዘቀዘ፡፡ ፍሪጅ ሆንኩ ለማለት ነው!

እንግዲህ አንዱ የሚለብስ የሚጎርሰው አጥቶ ሲንገላወድ፣ ሌላው ያማረውን ሲሸጥና ሲገዛ ማየቱ አድሮ እንደ አዲስ እያስደነቀኝ እንደለመደብኝ ተፍ ተፍ እላለሁ። ቪትዞችን የሚቀባበላቸው ሰው ብዙ ስለሆነ ሦስት አራቱን ካሻሻጣችሁ ደህና ዝግ ነው። ‹ዝግ የሚባል ቢዝነስ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አይቀርም› ያለኝ ማን ነበር? እና አንዲት ውብ ወጣት ሁለቱን ቪትዞች እንደምትፈልግ ነግራኝ ተገናኘን። መኪኖቹ ደህና ይዞታ ላይ ቢሆኑም ማስፈተሽ ግድ ነውና በባለሙያ ስታሳይ ዋለች። መላመድን የመሰለ ነገር የለምና አንድ አንድ ስንባባል ሳታስበው ከአፏ ያመለጣት አባባል ቀልቤን ሳበው። ምን አለችኝ መሰላችሁ? ስለኑሮና ስለትዳር እያወራን በአጠገባችን አንዲት ወጣት ልጇን ታቅፋ ስታልፍ፣ ‹‹ይኼውልህ ያደለው ልጅ ወልዶ የመኖር ምክንያት ያበጃል፣ እኔ ግን ለቆርቆሮ እንጦለጦላለሁ…›› አለችኝ። ከአንጀቷ መሆኑ ገብቶኝ፣ ‹‹ይኼንንስ ማን አየብሽ? አይዞሽ ሁሉም በጊዜው ይሆናል፣ ያውም አንቺን የመሰለች ልጅ…›› ስላት፣ ‹‹አይ አንተ ጊዜ ብቻውን ነው ብለህ ነው ሰውን እያነሳ የሚጥለው? ሰውም እኮ አመሉ ሲመች ነው ጊዜ ውለታ የሚውልለት። አመል ማክፋት እንደ ፋሽን ተይዞልን መስሎኝ የምናየውን እየካድን፣ የሆነውን አናምንም እያልን በችግር ላይ ችግር የምንደራርበው…›› ብላኝ በሐሳብ ከነፈች። ‹እኔን ያብረኝ ያክንፈኝ…› አልኩኝ በሆዴ፡፡ ሌላ ምን እላለሁ!

ውቢት ቪትዞቹን ተረክባ ኮሚሽኔን› በሞባይል ባንኪንግ ተቀባብዬ ተለያይተንም የማስበው ስለእሷ ነበር። ትዳር እንደ ኑሮ ተወዶባቸው ባላሰቡት የሚውሉና ባልጠበቁት የሚገኙ እህቶችን ኑሮ ስለማውቀው (አይ ደላላ መሆን ስንቱን እንደሚያሳይ እኮ)፣ በእሷ ውስጥ ስለእህቶቻችን ፈተና ሳላስብ እየተብሰለሰልኩ ዋልኩ። በኋላ ደግሞ ከአንድ ደላላ ወዳጄ ጋር ባለመቻቻል ሳቢያ በፈረሰ ትዳር ምክንያት እኔ ነኝ ያለ ዘመናዊ ቤት ልናሻሽጥ ስንዋከብ፣ ‹‹ኧረ ስማኝ እባክህ…›› አልኩት። ‹‹ምን ልስማህ?›› አለኝ። ‹‹ጎጆ እንደ ቀልድ ፈርሶ አንተ በድለላ ቤት ስታሻሽጥ የሚሰማህ ስሜት ምንድነው?›› ስለው፣ ‹‹እኔ ከሰው የኮንትራት ኑሮ ምን አለኝ? ቤቱ ቶሎ ገዥ አገኘ አላገኘ እያልኩ ላስብ ወይስ ሌላ? ምን ሆነሃል? እንዲህም ሆነን የምናገኘው ገንዘብ ረድኤት አልኖረው ብሎ አስመርሮናል አንተ ትፈላሰፋለህ…›› ብሎ የምሩን ተቆጣኝ። ለወዳጄ አብዛኛውን ጊዜ ሕግ የማይዳኘው፣ የማያመዛዝነውና የማይፈርደው ነገር አገር ሲያፈርስ መኖሩን ለማስረዳት ሰዓት አልነበረኝም። ዘንድሮ እኮ ሁሉም በተመቸው ጎዳና እየተመመ እውነቱን ከሐሰት እንዲለይ ማስረዳት ዳገት እየሆነ ነው፡፡ ዕድሜ ለቲክቶክና ለዩቲዩብ ወሬው ተሰልቆ የሚቀርበው ከዚያ ስለሆነ ምንጭ ሳያረጋግጡ መጋት ነው፡፡ ይብላኝ ለተበሉት!

ወዲያው ቀኑ ሊመሽ የቀረው ሰዓት የቤቱን ገዥ አፈላልጎ ለማግኘት እንደማይበቃን ተገንዝበን፣ የነገ ሰው ይበለን ተባብለን ስንለያይ ስልኬ ጠራ። ሳነሳው ከወር በፊት አንድ ከበርቴ ቤት ያስቀጠርኳት በሙያዋ አንቱ የተባለች የቤት ሠራተኛ ናት። ‹‹ሰላም አይደለም?›› ከማለቴ ሳታስጨርሰኝ፣ ‹‹እንዳስገባኸኝ ቶሎ መጥተህ አስወጣኝ…›› ብላ ጮኸች። ዋሷም እኔ ስለነበርኩ የሆነችው ነገር ካለ ብዬ ተጣድፌ ስሄድ፣ ጨርቋን ሰብስባ ወጥታ ጠበቀችኝ። ‹‹ይኼን የመሰለ ቤት ጥለሽ ወጥተሽ ምን ዓይነት ቤት እንዳስቀጥርሽ ትፈልጊያለሽ?›› ብላት፣ ‹‹ቱ… ይኼም እንጀራ ተብሎ፣ አገሬ ገብቼ አርሼ እበላለሁ። ዕድሜ ለጉልበቴ የትም ቢሆን ሠርቶ መኖር አያቅተኝም…›› ስትለኝ ስሜታዊ በመሆኗ የሆነችውን አጥብቄ ባልጠይቅ ይሻላል አልኩና ዝም አልኩ። በስንተኛው ቀን ታዲያ ደውላ፣ ‹‹ከሰው አመል ጋር የማያነካካ ሰጥቶ መቀበል የሆነ ሥራ ፈልግልኝ…›› ስትለኝ የምትፈልገውን ሊያገናኟት የሚችሉ ደላሎች ዘንድ ወስጄ አገናኘኋት። ዋል አደር ብዬ ሳጣራ የተከበረው ከበርቴ አባወራ ጨለማን ተገን አድርጎ ስላስቸገራት ተማራ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ስንቱ ይሆን ትልቅ መስሎ ቀሎ የሚገኘው አትሉም ታዲያ፡፡ ዘመኑ እኮ የማያሳየን የለም እናንተ!

ታዲያ ጨዋታም አይደል የያዝነው። ጥሎብን ከጨዋታም ስለአገርና ስለወገን ማንሳትና መጣል ይቀናናል። አገር ማለት ደግሞ ሰው ነውና ውሎዬንና ገጠመኜን ሳጫውታችሁ፣ በሰው አማካይነት ሁሉንም ነገር ብታዩ ብዬ ነው። ‹በእኔ የሕይወት ውስጥ ብታጮልቅ አገርህን ታያታለህ› ብሎ የጻፈውን ደራሲ ስም ጥሩልኝ እስቲ? ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር እየዋልኩ እኮ የማልሰማው የምሁራን አባባል የለም። ለነገሩ እንኳን የተማሩ የተመራመሩትን ሰዎች አባባል አይደለም፣ ሳይሠራ እዚያም እዚህም ብሎ ሀብት የሚያፍሰው ሳይቀር፣ ከእኔ በላይ ለአሳር እያለ ሲቀደድ ‹ቢል› ይከፍላል እያልን ስናዳምጥ እንውል የለ? ምነው ደበራችሁ እንዴ? ባይሆን እኛ እውነት እውነቱን እንጫወት እንጂ። ቀልድና ተረብ በበዛበት ዘመን ደግሞ ድብርት ሲያልፍም አይንካችሁ። የቀልዱስ ይሁን የተቃኘም ያልተቃኘም እየቀለዱ ሊያዝናኑን የሚጣጣሩ አሉ። የተራቢዎቹ ግን እንዴት ነው ነገሩ የሚያስብል ሆኖብኛል። ይኼ በመንጋ ሆ…ሆ…ሆ… የሚለውን ማለቴ ነው፡፡ መጠየቅ የለ፣ መሞገት የለ፣ ማፋጠጥ የለ፣ እንዲያው ግር ማለት፣ ዝም ብሎ መነዳት፣ በነፈሰበት መንፈስ ብቻ…፡፡ ዘንድሮ በርካታ የሥነ ልቦና አማካሪ ድርጅቶችና የአዕምሮ መታከሚያዎች ሳያስፈልጉን የሚቀሩ አይመስለኝም፡፡ ብዙዎቻችን በነገር እየጦዝን ነውና፡፡ ከባድ ሕመም!

በፖለቲካው ቡድን መሥርቶ ተያይዞ የሚነዳው፣ በሃይማኖቱ፣ በአለባበሱ፣ በአወራሩ፣ በአረማመዱ ሳይቀር ሆ… ባዩ ተያይዞ እያያያዘ ነገሩ ቀለጠ እኮ እናንተ፡፡ ኧረ ሆታ እስከ መቼ ጎበዝ? ጠልዘን ስናገባ በደስታ ተንጫጭተን፣ ተጠልዞ ሲገባብን በንዴት ጮኸን፣ ፈሩን በለቀቀ እሰጥ አገባ ውስጥ ሳንደማመጥ ትውልድ መጥቶ ትውልድ እየሄደ ዴሞክራሲያችንስ ምኑን በእግሩ ቆመው? እውነቴን እኮ ነው። መቼ ዕለት ነው ከባሻዬ ጋር ዕቁብ ጥለን ስንመለስ (ባሻዬ ብዙ ጊዜ ዕጣ ሳይደርሳቸው ስለሚቆይ የማይፈለፈል ዕንቁላል እየጣልኩ ይላሉ ሲቀልዱ)፣ ‹‹ምናለበት ይኼን በየቦታው እያናጀሰ እርስ በርስ የሚያጣላንን ዲያቢሎስ በጋራ ብናስወግድ አንበርብር? ዘለዓለም እንዲሁ በነገር መቆርቆዝ?›› ሲሉኝ ነበር። ‹‹ከፈጣሪ ሰው እየቀደመ ድሮስ ምን ልንሆን ነበር?›› የምትለው ደግሞ የእኔዋ ማንጠግቦሽ ናት። በዚህ በዚያም ነገሩን ስትደማምሩት በአጠቃላይ ተዛዝኖና ተባብሮ ከማደግ ይልቅ፣ ተቧድኖ እንዲራገጥ የተረገመ መንጋ የሚመስለው የበዛ ይመስለኛል። መጥኔ!

በሉ እስኪ እንሰነባበት፡፡ የዕለቱ ማሳረጊያ የተለመደው ግሮሰሪያችን ስለሆነ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር በጊዜ ተሰይመናል፡፡ ባለፈው ሰሞን እንደ በረዶ ቀዝቅዞ የነበረው ግሮሰሪያችን ምን እንደተገኘ አይታወቅም፣ ከተለያየ የኑሮ ደረጃና ማኅበረሰባዊ ጥንቅር የተሰባሰብን እንደ ምርጫችን አዘን እየተጎነጨን ነው፡፡ ‹ሒሳብ በግል ወሬ በጋራ› በሚባለው ያልተጻፈ ሕግ መሠረት፣ ቢራውንና አልኮሉን እየተጎነጨን ወሬ ስለቃው ቀጥሏል፡፡ ‹‹ጎበዝ ሰሞኑን በተከታታይ ለፓርላማ እየቀረቡ ያሉ ረቂቅ አዋጆች ምንን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው…›› እያለ አንዱ አብረውት ለተቀመጡ ወዳጆቹ ጥያቄ ሲያነሳ፣ ‹‹ዌል እንግዲህ ከዘመኑ ጋር የሚዋጁ ሕጎች በተለያዩ ዓውዶች መውጣታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር አዋጆቹ ለአገርና ለሕዝብ የሚሰጡት ፋይዳ ነው…›› ብሎ ሌላው ይመልሳል፡፡ በዚህ መሀል ነበር አንዱ ሞቅ ያለው፣ ‹‹ሕግና ሥርዓት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን በሕግ ስም ጥቃት እንዳይፈጸም መጠንቀቅ ካልተቻለ ስካራችን ተባብሶ ይቀጥላል…›› ብሎ በፌዝ ስሜት ሲስቅ ሌሎችም አብረውት መሳቅ ጀመሩ፡፡ ይኼን ጊዜ ምሁሩ ወዳጄ፣ ‹‹አንበርብር እንደ ዋዛ የሚነገሩና ቀልድ የሚመስሉ ንግግሮች ውስጥ ነው ሕመማችን ያለው…›› ሲለኝ ከሰዎቹ ንግግር በስተጀርባ ያለው ሥጋት ታየኝ፡፡ ሁሉም ነገር ሕመምና ሥጋት እንዳይሆን እያብሰለሰልኩ መሽቶ ወደ ቤታችን ስናዘግም ሐሳቡ ሰቅዞ ይዞኝ ነበር፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት