Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኢትዮጵያ በፓሪስ ባህላዊ ኦሊምፒያድ ትሳተፍ ይሆን?

ኢትዮጵያ በፓሪስ ባህላዊ ኦሊምፒያድ ትሳተፍ ይሆን?

ቀን:

ኦሊምፒክና ባህል ቁርኝት አላቸው፡፡ እርስ በርሳቸውም ይገላለጣሉ፡፡ የኦሊምፒክ ተሳታፊ አገሮች ባህላዊ መለያዎችም የሚታይበት መድረክ ነው፡፡

የመጀመርያው የኦሊምፒክ ጨዋታ በግሪኳ ከተማ ኦሊምፒያ የተከናወነው ከ2800 ዓመታት በፊት በ776 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ ነበር፡፡ ኦሊምፒያ የአገሪቱ የስፖርትና ባህል ማዕከል በመሆኗ ከጅምሩ ምርጥ አትሌቶችና ምርጥ ኪነ ጠቢባን (አርቲስቶች) መናኸሪያና መወዳደሪያ ነበረች፡፡

ዘመናዊውን ኦሊምፒክ  ፈረንሳዊው ባሮን ፒየር ደኩበርቲን (እ.ኤ.አ. 1894) ሲመሠርቱ የወሰዱት አቋም፣ ባህል የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ሁለተኛው ምሰሶ ሆኖ ከስፖርት እኩል መጓዝ እንዳለበት ነው፡፡ አዲሱ የኦሊምፒክ ጨዋታ የጥንቱን የግሪክ ትውፊት እንዲቀጥል በኦሊምፒክ ቻርተርም ተንፀባርቋል፡፡

የኦሊምፒክ ጨዋታን የሚያስተናግዱ ከተሞች ባህላዊ ፕሮግራሞች እንዲያዘጋጁና የአገራቸውን ባህልና ትውፊት ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸው ያሳስባል፡፡

ከ1912 እስከ 1948 የነበረው የባህል ኦሊምፒያድ፣ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውስጥ የኪነ ጥበብ ውድድርን በማካተት በኪነ ሕንፃ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በሥዕልና በኪነ ቅርፅ ጠቢባኑ ይወዳደሩ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የባህል ኦሊምፒያድ የተለየ መልክ ይዟል። ከተፎካካሪ ጥበብ ይልቅ፣ አስተናጋጁ አገር ከኦሊምፒክ ጋር ትይዩ የሆኑ አስደናቂ የባህል ዝግጅቶችን አስቀምጧል።

የኦሊምፒክን ባህልና ትምህርት ለማስተዋወቅ በሺዎች በሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች ለኦሊምፒኩና ለፓራሊምፒክ ጨዋታ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡

ሐምሌ 19 ቀን በሚጀመረው የፓሪስ ኦሊምፒክ ፈረንሳይ በመቶዎች በሚቆጠሩ ዝግጅቶች፣ ትርዒቶች፣ ዓውደ ርዕዮችና ሌሎችንም ዝግጅቶች ለማቅረብ እየተፋጠነች መሆኑን ዘገባዎች ይገልጻሉ፡፡

ተወዳጁ ኦሊምፒክ የአራት ዓመት ቀጠሮውን አጠናቆ ካለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክ አርማ የተቀበለችው ፓሪስ የ2024ቱን 33ኛ ኦሊምፒያድ ለማስተናገድ 33 ቀናት ብቻ ቀርቷታል፡፡

የፓሪስ ከተማ ልዩ መስህብ በሆነው ‹ኤፍል ታወር› የተሰቀለው የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ቀን ቆጠራ ሰሌዳ በየዕለቱ እየተቀያየረ ‹ኦሊምፒኩ ይህን ያህል ቀን ቀረው› እያለ ያመለክታል፡፡

 አገሮችን የሚያስተሳስረውና በባህላዊ መድረክ የሚታጀበው የኦሊምፒክ ጨዋታ ከ200 በላይ አገሮች የሚውጣጡ ከአሥር ሺሕ በላይ አትሌቶች ከነባህላዊ መገለጫዎቻቸው ጋር እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡ ፓሪስን በባህላዊ ገጽታ ኪነጠቢባኑ (አርቲስቶች) በኦሊምፒኩ ብቻ ሳይሆን በፓራሊምፒክ ጭምር ለማድመቅ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡

የፈረንሳይ ባህል ሚኒስቴር ከፓሪስ የኦሊምፒክና የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ጋር በተገናኘ የባህል ፕሮግራሞችን ለመሥራት እየሠራ ነው። በባህል ስፖርት መካከል ያለውን ግንኙነትና ትስስር የሚዳሰሱ ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት ሚኒስቴሩ ለባህል ኦሊምፒያድ መዘጋጀቱን አስታውቋል። ተካፋይ አገሮች በኦሊምፒኩ መንደር የየራሳቸው ባህላዊ መገለጫዎች እንደሚያቀርቡም እየተነገረ ነው፡፡

ኦሊምፒክን በሚያዘጋጁ አገሮች ሥነ ጥበብ፣ ባህልና የፈጠራ ሥራ የሚታዩባቸው ክብረ በዓላትም ይዘጋጃሉ፡፡ ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ 33ኛውን ኦሊምፒያድ የምታስተናግደው የፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ፣ የባህል ኦሊምፒያድን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ታከብራለች፡፡ የባህል ኦሊምፒያድ  ዘርፈ ብዙ የጥበብ እና የባህል ፕሮግራም ነው።

በባህል ኦሊምፒያድ ጥላ ሥር ሙዚቃ፣ ዳንኪራ፣ ዕይታዊ ጥበብ (ሥነ ሥዕል)፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ቴአትርና ፊልም ተካትተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፓሪስ ባህላዊ ኦሊምፒያድ ትሳተፍ ይሆን?

‹‹ምድረ ቀደምት›› (Land of Origins) የሚል መለያ ያላት ኢትዮጵያ፣ እ.ኤ.አ. በ2012 ለንደን ባዘጋጀችው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አጋፋሪነት በባህላዊ ኦሊምፒክ ተሳትፋ ራሷንም አስተዋውቃ ነበር፡፡ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷ ጎጆ ተዘጋጅቶላት ከተሳተፉት አገሮች መካከል የኢትዮጵያ መቀመጫ በርካታ ተመልካችና ልዩ አድናቆት ማግኘቱ በተለይ በኦሊምፒክ መንደር ውስጥ የኢትዮጵያ ቀን በታላቅ ሁኔታ መከበሩ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡

በአፍሪካ ሐውስ የኢትዮጵያ መቀመጫም ልዩ አድናቆትና ተመልካች አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩልም አትሌቶችን የማስተዋወቅ የባህልና የሙዚቃ ሥራ ቀርቧል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ መካነ መቃብር በመጎብኘትና ማንነትን በማሳወቅ ረገድ ልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓቶች ተካሂደዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤምባሲ በሃይድ ፓርክ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቀን፣ ባህላዊ ምግብና የቡና ሥነ ሥርዓት፣ ሙዚቃና ዳንስ ያካተተ የምሳ መሰናዶ እንዲሁም በገናናው ኦሊምፒን ኃይሌ ገብረሥላሴ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‹‹ጽናት›› ፊልም ለዕይታ በቅቶ ነበር፡፡

በሪዮ ኦሊምፒክ፣ በዓለም በቡና ምርት ቀዳሚ የሆነችው ብራዚል ከመካሄዱ አንፃር የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ፣ የቡና ሥነ ሥርዓቱን ጨምራ ልዩ ልዩ ባህላዊና ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊም መገለጫዎቿን በአፍሪካ ጎጆ ውስጥ ለማዘጋጀት አልታደለችም ነበር፡፡

ዘንድሮስ? ኢትዮጵያ ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ በቀጣይም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በነበሩት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከፈረንሳይ ጋር ከነበረ ቁርኝት አንፃር በባህል ኦሊምፒያድ ለመሳተፍ የታሰበ ነገር ይኖር ይሆን የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ባህልና የዕደ ጥበብ ምርቶች በፓሪስ ኦሊምፒክ ለማስተዋወቅ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሄዋን የፋሽንና የኤቨንት ሥራዎች፣ ከሲንቄ አድቨርታይዝንግና ፕሮሞሽን እና ፔሸንሲ ባይ ትዕግስት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ባለፈው ግንቦት መፈራረሙ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡

የስምምነቱ ዓላማ የጋራ ባህል እሴቶችን፣ የአገር በቀል ዕውቀትና የዕደ ጥበብ ሀብትን በፓሪስ ኦሊምፒክ በማስተዋወቅ ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር  የሚኖረውን ሚና ማሳደግ መሆኑ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጾ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1956 (ኅዳር 1949 ዓ.ም.) በሜልቦርን ኦሊምፒክ መካፈል የጀመረች ቢሆንም፣ ከ100 ዓመት በፊት በ1916 ዓ.ም.፣ የወቅቱ አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን ከ11 መሳፍንትና መኳንንት የተለያዩ የአውሮፓ አገሮችን መነሻቸውን የ1924 ኦሊምፒክ አዘጋጇ ፓሪስ አድርገው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን ከ1992 (1984 ዓ.ም.) የባርሴሎና ኦሊምፒክ ጨዋታ በስተቀር (የአውሮፓ ሱፍ እንዲለብሱ ተደርገዋል)፣ በሌሎቹ ኦሊምፒያዶች የተለያዩ የባህል አልባሳት ለብሰው በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በመገኘት አገራቸውንና ባህላቸውን ማስተዋወቃቸው ይታወሳል፡፡ ዘንድሮስ?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...