Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ቀን:

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና ሆኗል፡፡ ሰዎች የተለያዩ ወጪዎቻቸውን ሸፍነው ለመኖር ፈጽሞ አልቻሉም፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮችን አሟልቶ ለመኖር ቅንጦት እስከመሆን ደርሷል፡፡ የኑሮ ውድነት የብዙኃኑን ሕይወት እያናጋ ነው፡፡ በመሠረታዊው ፍጆታዎችም ሆነ በሌሎችም ጓዞች የዋጋ ንረቱ ኅብረተሰቡን ከማማረርም አልፎ ተስፋ እንዲያጣ እያደረጉት ነው፡፡

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በኑሮ ውድነት ኃያል ክንድ እየተደቆሱ ከሚገኙት መካከል በተለይ ደመወዝተኛ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ምንዳ የሚከፈላቸው የቀን ሠራተኞች፣ ሥራ ፈላጊውን ጨምሮ አብዛኛው ኅብረተሰብ በኑሮ ውድነት በዋጋ ንረት ምክንያት አዘቅት ውስጥ ገብቷል፡፡  

አቶ ዓለሙ ሰሎሞን ይባላሉ፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤት በባለሙያነት በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ የሦስት ልጆች አባትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ዓለሙ፣ በአዲስ አበባ ያለው የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ስለመሄዱ ይገልጻሉ፡፡ ለቤት ፍጆታ የሚውሉ ምግብ ነክ ነገሮች ዋጋቸው በየዕለቱ በመጨመር ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ገቢያቸው ለቀለብ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ለማብቃቃት የማይችሉ ከቀጣይ ወር ገቢያቸው አስቀድመው የሚበደሩ ወገኖች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡

የዘይት፣ የሽንኩርት፣ የቲማቲምና መሰል የአትክልት ውጤቶች በየወቅቱ ገበያቸው እየጨመረ ነው፡፡ የታሸጉ ምግቦች፣ የሕፃናት ወተትና ለሕፃናት የሚውሉ ፍጆታዎች ዋጋቸው የሚቀመስ አይደለም፡፡ አንድ ለምለም እንጀራ እስከ 25 ብር ለመግዛት እየተገደዱ ነው፡፡ የቤት ኪራይና የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ ሲደማመር ሕይወታቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውና በመንግሥት መሥሪያ ቤት 13 ዓመታትን ያስቆጠሩት እኚህ ሰው፣ የሚያገኙት ወርኃዊ ደመወዝ ግብር፣ ጡረታና ሌሎችም ተቆርጠውለት ከ7,000 ብር አይዘልም፡፡

ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ከሚሄደው የዋጋ ንረት አንፃር በዚህ ደመወዝ መኖር ከባድ እንደሆነ፣ መንግሥት የደመወዝ ማስተካከያ ቢያደርግ፣ ችግሩ ይቃለላል የሚል እምነት እንደሌላቸውና ከደመወዝ ጭማሪ ውጪ ያሉ አማራጮች መፈተሽ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኛው አቶ ዓለሙ ሰሎሞን ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ የሚሉት አላቸው፡፡ ከተቀጣሪ ሠራተኞች የሚቆረጥ ግብር የሚሻሻልበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ሠራተኛው ጠንካራ አደረጃጀት እየፈጠረ በማኅበር ቦታና ቤት የሚያገኝበት ሁኔታ ቢፈጠርና ትንሽ ደመወዝ ለሚያገኙ ሠራተኞች የምገባ ፕሮግራም በመንግሥት ቢቀረፅ ችግሩ በተወሰነ መልኩ ሊቃለል ይችላል ይላሉ፡፡

በኑሮ ውድነት ምክንያት ‹‹ኑሮ›› የሚለው ቃልና ሕይወት በራሱ እንደሰለቻት የምትናገረው ሥራው ድንቅ አዳነ (ስሟ ተቀይሯል) ሌላዋ የመንግሥት ሠራተኛ ናት፡፡

የባለቤቷና የእሷ ደመወዝ ተደምሮ አሥር ሺሕ እንደማይሞላ፣ ለቤት ኪራይ ስድስት ሺሕ ብር እየከፈለች ሁለት ልጆቿን ይዛ ቀሪውን ገንዘብ ምን እንደምታደርገው ግራ እንደሚገባት ትገልጻለች፡፡

‹‹ከወር እስከ ወር መድረስ ፈተና ሆኖብኛል፡፡ ዝቅተኛ ወርኃዊ ገቢ ያላቸውና ያለ አባት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ጎረቤቶቼ የኑሮ ጫና ያሳደረባቸውን መከራ ስመለከት ከእኔም አልፎ ለእነሱ አዝናለሁ፤›› ትላለች፡፡

የኑሮ ውድነቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በሰዎች ማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይሆንም የምትለው ሥራው ድንቅ፣ ግለሰቦች ‹‹ሞታቸውን እስከመምረጥና እስከመመኘት›› ያደረሳቸውን የኑሮ ጫና መንግሥት በአፋጣኝ ማስተካከል እንደሚኖርበት፣ አሁን ያለውን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያ ለሠራተኛው እንደሚያስፈልግ ታክላለች፡፡

በቅርቡ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በፓርላማ በተደረገ ውይይት ላይ ስለኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ንረቱ ስላስከተለው ፈተና አስተያየት ተሰጥቶበት ነበር፡፡

አስተያየት ከሰጡት አንዱ የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ የቡድን መሪ የሆኑት አቶ አብርሃም ደግፌ ናቸው፡፡ የቡድን መሪው ‹‹የሠራተኛው ሕይወት እጀግ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛል፤›› ያሉትን በምሳሌ አስደግፈው ተናግረውታል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ አንድ ከፍተኛ ባለሙያ ያልተጣራ ደመወዙ 9,056 ብር መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ከዚህ ግብር ተከፍሎበት በእጁ የሚደርሰውን ገንዘብ አሥልታችሁ ድረሱበት፤›› ሲሉ ተሳታፊዎቹን ጠይቀዋል፡፡

በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ሠራተኞች አንዳንዴ ቢሮ መጥተው ምሳ የሚበሉበት እንደሌላቸው በግልጽ የሚናገሩ እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡ ወርኃዊ ደመወዛቸው አላዳርስ ያላቸው ሠራተኞች የምሳ ሰዓትን በቤተ እምነቶች እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡

በዚያው መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ይልማ በሰጡት አስተያየትም በደመወዝ አነስተኛነት፣ ‹‹መሄጃ እያጡ ቢሮ ምቹ ሁኔታ አለ በሚል እየተደበቁ የሚያድሩ›› መኖራቸውን መጥቀሳቸው የኑሮ ውድነቱ አስከፊ ገጽታ የሚያሳይ ነው፡፡  

እየባሰበት ስለመጣው አገራዊው የኑሮ ውድነት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የፖሊሲ አማካሪው ቆስጠንጢኖስ በርኸ ተስፋ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት የደረሰበት 30 በመቶ ከፍተኛ የሚባል ነው፤›› ካሉ በኋላ መንግሥት ግን የዋጋ ግሽበቱ ወደ 20 በመቶ ዝቅ ማለቱን ይናገራል ብለዋል፡፡

አሁን ለሚታየው የኑሮ ውድነት የዋጋ ግሽበቱ እንዳለ ሆኖ፣ የሰው ገቢ አብሮ አለማደጉ ሌላው ችግር ነው የሚሉት የፖሊሲ አማካሪው፣ የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት እያደገ ቢሆንም፣ በሰዎች ኑሮ ላይ ይህ ነው የሚባል የፈጠረው ለውጥ የለም ሲሉም ያክላሉ፡፡

እንደ አማካሪው፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያትና በዓለም በተፈጠረው የአቅርቦት ዋጋ መናጋት ምክንያት፣ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በመፈጠሩ በኢትዮጵያ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት የኢኮኖሚ ቀውሶችን ያስከተለ ነው፡፡

መንግሥት፣ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር በጥምረት የሚያወጣው ‹ሒዩውማን ዴቭሎፕመንት ኢንዴክስ› የሰዎችን የኑሮ፣ የትምህርትና ጤና ሁኔታ ከሚያመለክቱ ጥናቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

በትምህርት፣ በጤናና በኑሮ ሁኔታ አንድ አገር ያለበትን ደረጃ በሚለካው አመላካች መሠረት፣ ኢትዮጵያ ከዓለም 189ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህም ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ጤናማ አለመሆኑን የሚያመላክትና አሁን በኑሮ ውድነት ሳቢያ በዜጎች ላይ እየተከሰተ ላለው ችግር አስረጂ ሊሆን የሚችል ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት፣ በአፈጻጸም ላይ እንጂ የሰው ልማት ላይ ያተኮረ አለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹አሁን እየታየ ያለው የኑሮ ጫና በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስከትለው ቀውስ ከባድ ነው፤›› የሚሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ እንደ እነዚህ ዓይነት ችግሮች በምዕራብ አፍሪካ ባሉ ቡርኪናፋሶ፣ ማሊና ኒጀር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ቀውስ የፈጠሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

‹‹የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በሱዳን ያስከተለው ቀውስም የሚጠቀስ ነው፡፡ ከኑሮ ጋር በተያያዘ ዜጎች ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች እንደ አጠቃላይ የኅብረተሰብ አለመረጋጋትን የሚያመጡ ናቸው፡፡ ይህ አለመረጋጋት በራሱ ሌላ የፖለቲካ ተፅዕኖ ሊያስከትል የሚችል ነው፤›› ሲሉም ያሰምሩበታል፡፡

‹‹መንግሥት እስካሁን ሲያደርግ እንደነበረው ለሠራተኛው ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ሁኔታ ድጎማ ማድረግ ይኖርበታል፤›› የሚሉት አማካሪው፣ ይህ መሆን ካልቻለ ‹‹አገሪቱ ልትወጣው የማትችለው ቀውስ ውስጥ ልትገባ ትችላለች›› የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡  

በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የሠራተኛውን ሕይወት ያከበዱበት በመሆኑ፣ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈልግለት ከሚጠይቁት አገራዊ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ነው፡፡

ኢሠማኮ የዘንድሮውን የዓለም ሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) አስመልክቶ ሰጥቶት በነበረው መግለጫው፣ የሠራተኛው የሥራ ግብር ምጣኔው እንዲቀንስና የደመወዝ መነሻ እንዲወሰን ለመንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...