Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዛሬም ትኩረት የተነፈገው የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ

ዛሬም ትኩረት የተነፈገው የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ

ቀን:

ብሩክታዊት ስሜ፣ በተስፋ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ ብሩክታዊት እንደምትናገረው፣ በወር አበባ ወቅት ሴት ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይቀሩና ከዚህም ጋር በተያያዘ ከትምህርት ገበታ መራቅ እንዳይኖር አቅም ለሌላቸው ሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ፓድ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡

ዛሬም ትኩረት የተነፈገው የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኤድስ ሔልዝ ኬር ፋውንዴሽን ዳይሬክተር
መንግሥቱ ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)

እንደ ተማሪዋ ገለጻ፣ እሷ በምትማርበት ትምህርት ቤት ለሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ፓድ በነፃ እየቀረበ ይገኛል፡፡ በወር እስከ ሦስት እሽግ የሚደርሱ የንፅህና መጠበቂያ ፓዶች በማግኘት ላይ መሆናቸውንም ትገልጻለች፡፡ ይህ መሆኑም ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት ከትምህርት ቤት እንዲቀሩ የሚገደዱበትን ምክንያት ያስቀረ ነው፡፡

አንዲት ተማሪ የወር አበባዋ በሚመጣበት ወቅት ሕመም ይኖራታል፣ ጭንቀትም ይፈጠራል የምትለው ብሩክታዊት፣ ሕመሟን መቅረፍ ባይቻል የንፅህና መጠበቂያ በማግኘቷ ዩኒፎርሟ እንዳይበላሽና ከአሁን አሁን ምን ተፈጠረ ብላ እንዳትሳቀቅ፣ የሚደርስባትን የሥነ ልቦና ጫና በማቃለል በኩልም ትልቅ ድርሻ ስለሚኖረው ለሁሉም ሴት ተማሪዎች ተደራሽ የሚሆንበት አግባብ ሊፈጠር እንደሚገባ ትገልጻለች፡፡  

በተስፋ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዋ ኤልሳቤጥ ተረፈ በበኩሏ፣ በግብረ ሠናይ ድርጅቶች አማካይነት በትምህርት ቤታቸው የንፅህና መጠበቂያ ፓዶች በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡

ሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ፓዶችን ማግኘታቸው በራስ መተማመናቸው እንዲጎለብት፣ ሴቶች ተምረው ትልቅ ቦታ የመድረስ ተነሳሽነታቸው የሚጨምርና በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡

የተስፋ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ፍቃዱ ይገረሙ እንደገለጹት፣ በትምህርት ቤቱ ለሚማሩ ሴት ተማሪዎች ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ የኤድስ ሔልዝ ኬር ፋውንዴሽን የንፅህና መጠበቂያ ፓዶችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

የንፅህና መጠበቂያ ፓድ በትምህርት ቤቱ መቅረብ ከመጀመሩ በፊት በርካታ ተማሪዎች በወር አበባ ምክንያት ከአንድ ሳምንት ላላነሰ ጊዜ ከትምህርት ይርቃሉ፡፡ ተደጋጋሚ በመቅረታቸውም፣ በዚያው ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም፡፡ አሁን የንፅህና መጠበቂያ በትምህርት ቤቱ በመቅረቡ በዚህ ዙሪያ ያለው ችግር ተቀርፏል ብለዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች አካቶ ትግበራ ባለሙያ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ እንየው በበኩላቸው፣ የንፅህና መጠበቂያ እጥረት ለሴት ተማሪዎች ትልቅ ፈተና ነው፡፡

በወር አበባ ወቅት በንፅህና መጠበቂያ አለመኖር ምክንያት በልብሷ ላይ አንዳች ነገር ቢታይ የሌሎች ተማሪዎች መዘባበቻ ከመሆን ባሻገር፣ ዳግም ትምህርት ቤት እንዳትረግጥ ለሴቷ ምክንያት እስከመሆን የሚደርስ ነው፡፡

የንፅህና መጠበቂያ የሌላት ተማሪ ወደ ትምህርት ገበታ የመጣች እንደሆነም፣ የምትመጣው ከታላቅ ጫና ጋር ይሆናል ያሉት ባለሙያዋ፣ ይህም ለሥነ ልቦና ጉዳት የሚያጋልጥና በትምህርት ውጤታማነቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ፣ አንዲት ተማሪ በወር አበባ ወቅት በወር ሦስት ቀን በዓመት እስከ 30 ቀናት ከትምህርት ገበታ ልትርቅ ትችላለች፡፡ ይህ ደግሞ የትምህርት ተሳትፎዋ ላይ ተግዳሮት በመሆን የነገ እሷነቷ እንዲያጠላ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ለሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያዎችን በትምህርት ቤቶች ማቅረብ ሥር የሰደደውን ችግር ለመቅረፍ የሚያግዝ ነው፡፡

ሴቶች በወር አበባ ወቅት ሕመም ሊኖርባቸው ስለሚችል በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለእነሱ ማረፊያ ክፍል እንዲመቻች፣ የንፅህና መጠበቂያ ፓዶች አቅርቦት እንዲስፋፋና በማስገንዘቢያ ሥራዎች ዙሪያ ትምህርት ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡

 የሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ችግር እንደ አገር የት ደረጃ እንደሚገኝ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ባለሙያዋ ሲመልሱ፣ በትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዙሪያ የተጠና ጥናት የለም ብለዋል፡፡

የንፅህና መጠበቂያ ፓዶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ በኩል በሚኒስቴሩ ምን እየተሠራ ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹ጉዳዩ ከጤና ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴርን አይመለከተውም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የኤድስ ሔልዝ ኬር ፋውንዴሽን ካንትሪ ፕሮግራም ዳይሬክተር መንግሥቱ ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ድርጅታቸው በኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና ቁጥጥር እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ውጪ ያሉ ሴቶችን በመደገፍና ማኅበራዊ ጫናቸውን በማቃለል ዙሪያ የሚሠራ ነው፡፡

በወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ዕጦት ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንደሚስተጓጎሉ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍም በዩኒቨርሲቲና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ፓድ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ፓዶች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር እንዲገቡና ሴቶች በተለይም ሴት ተማሪዎች ምርቱን በአነስተኛ ክፍያ ማግኘት እንዲችሉ ድርጅቱ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት ላይ ነው፡፡

እንደ መንግሥቱ (ዶ/ር)፣ የሴት ተማሪዎችን የንፅህና መጠበቂያ ችግር ለማቃለል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምርቶቹን ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ተደርሶ፣ ግብዓቶችን ለማቅረብ በሒደት ላይ ይገኛል፡፡

ኤድስ ኬር ፋውንዴሽን፣ የወር አበባ ንፅህና ቀንን ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም.  በተስፋ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ፣ አጋር ድርጅቶችና የመንግሥት አካላት በተገኙበት አስክብሮ ውሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...