Monday, July 22, 2024

በውጭ ባንኮች መግባት ላይ የሚሰሙ የፖሊሲ ሙግቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአራት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ‹‹የዕድገትና ለውጥ ራዕይ በኢትዮጵያ ትልልቅ አገራዊ ግቦችና ፈታኝ ሁኔታዎች›› በሚል ርዕስ ተከታታይ የውይይት መድረኮች አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በመድረኮቹ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ወቅታዊ ቁመናና ለውጥን የመቋቋም ብቃት በሰፊው የውይይት አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ እንደ ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) ያሉ የምጣኔ ሀብት ምሁራን በመሩት ገብረ ሕይወት አገባ (ዶ/ር)፣ ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) እና አቶ ሚካኤል አዲሱን የመሳሰሉ የውይይት ጥናት አቅራቢዎች ባለሙያዎች በነበሩበት በዚያ መድረክ ላይ እጅግ ሞቅ ያለ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የባንክና ፋይናንስ ዘርፍ ውድድር የሌለበትና ውስን አገልግሎት ብቻ የሚቀርብበት ስለመሆኑ በዚህ መድረክ ተነስቷል፡፡ በኢትዮጵያ አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ባንኮች ጥቂቱን ሀብታም ማኅበረሰብ ያማከለ አገልግሎት ብቻ እንደሚያቀርቡ ተነግሮ ነበር፡፡ ደሃውና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእነዚህ ባንኮች አገልግሎት አካታችነት ውጪ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ሰፊው ማኅበረሰብ አማራጭ በማጣት ወይም በመገደድ ብቻ፣ የእነዚህ ንግድ ባንኮች ደንበኛ ከመሆኑ ባለፈ ባንኮቹ ኅብረተሰቡን ያማከለ አገልግሎት እንደማያቀርቡ ነበር ያለ ይሉኝታ የተነገረው፡፡

ለውጭ ኢንቨስትመንት ዝግ በተደረገ የቢዝነስ ከባቢ አየር ያለ ውድድር ሲሠሩ የቆዩት የግሉና የመንግሥት ንግድ ባንኮች፣ መያዣ ወይም ቋሚ ንብረት ለሌለው በአነስተኛ ገቢ ሕይወቱን ለሚገፋው ሰፊ ማኅበረሰብ ኑሮ መሻሻል መፍትሔ የሆነ አገልግሎት ባለመቅረባቸው በመድረኩ ሲወቀሱ ውለዋል፡፡

ከነጆ ከተማ እንደመጡ የጠቀሱትና ለሃያ ዓመታት በባንክ ሥራ ያገለገሉ አንጋፋ ባለሙያ የተናገሩት ንግግር የዚያን ቀኑን መድረክ ድባብ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ነጆ ከተማ ንግድ ባንክ 135 ቢሊዮን ብር በአንድ ዓመት ሰበሰበ፡፡ ለዚያ ከተማ የሰጠው ብድር ግን በዚያ ዓመት ከአሥር ቢሊዮን ብር በታች ነበር፡፡ በነቀምት ከተማ በአንድ ዲስትሪክት/ቅርንጫፍ ብቻ በዓመት አሥር ቢሊዮን ብር ባንኩ ሰብስቦ የሰጠው ብድር ግን ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ነበር፡፡ ንግድ ባንክ በመላው አገሪቱ ካሉ ደሃዎች ብር ይሰበስባል፡፡ ባንኩ ከሰጠው ብድር ውስጥ ግን 87 በመቶው ለአዲስ አበባ ከተማ የቀረበ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ደሃ ማኅበረሰብ አዲስ አበባ ለሚተከል የኮንክሪት ጫካ እየገፈገፈ ነው ማለት ነው፡፡ ነጆ እኔ በምሠራበት ጊዜ የተወሰደች 125 ሚሊዮን ብር ጠፋች፡፡ የራሴን ክትትል ሠርቼ ግማሹ ቻይና ሌላው ደግሞ ሆንግ ኮንግ መድረሱን አውቄያለሁ በማለት፤›› ነበር እኚህ ባለሙያ የተናገሩት፡፡

አንድ ሌላ ተወያይ በበኩላቸው የአማራ ክልልን ልምድ አንስተው ነበር፡፡ በአማራ ክልል ገንዘብ በመሰብሰብ ረገድ ቀዳሚው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው ቢሉም፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላለውም ሆነ ለክልሉ ሰፊ ሕዝብ ብድር በመስጠት ግን አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ያኔ እየተባለ የሚጠራውና አሁን ፀደይ ባንክ የተባለው ተቋም ቀዳሚ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች መያዣ ለሌላው ካለማበደራቸው ባለፈ ሐሳብ፣ ዕውቀትና ፈጠራ ይዞ ለሚመጣ ሥራ ፈጣሪም በራቸውን ዝግ ማድረጋቸው ሌላው በመድረኩ ተወቃሽ ያደረጋቸው ጉዳይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ማይክሮ ፋይናንሶችና ዲጂታል የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነታቸው ገና በውስን ደረጃ ላይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ከአገሪቱ ዕድገትና የፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ጋር አብሮ የሚሄድ አገልግሎት ገና አለመፈጠሩ ነው በጉልህ የተነሳው፡፡

ቁጠባን ለማሳደግ ለአሥር ዓመታት በተደረገ ጥረት የቁጠባ ምጣኔን ከዘጠኝ ወደ 24 በመቶ ማሳደግ መቻሉ፣ የፋይናንስ ተቋማትን ተደራሽነት ለማስፋት የባንክ ቅርንጫፎችን በጥቂት ዓመታት ወደ 5,000 ማድረስ መቻሉም ተነግሮ ነበር፡፡ አንድ የባንክ ቅርንጫፍ ለ150 ሺሕ ሰዎች አገልግሎት ይሰጥ ከነበረበት በማሻሻል አንድ ቅርንጫፍን ለ20 ሺሕ ሰው ማዳረስ መቻሉም ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉም ሆኖም በአዲስ አበባ እንኳ የባንክ ተደራሽነት 40 በመቶ ብቻ ነው የደረሰው በሚል የፋይናንስ ተቋማት ዕድገት አዝጋሚነት በሰፊው ተመላክቷል፡፡

ንግድና ቢዝነስ ሃይማኖትም ሆነ ብሔር የለውም የሚለው ብሂል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለው የፋይናንስ ሥርዓት በቡድናዊነት የታጠረ ስለመሆኑ የዚያን ቀኑ መድረክ ተስተጋብቶበታል፡፡ የባህል መድኃኒት ቀማሚዎች ሳይቀሩ ‹‹ብድር የሚያስረሳ መድኃኒት አለን›› ብለው እስኪያስተዋውቁ ድረስ የኢትዮጵያ ባንኮች በሰባት በመቶ የቁጠባ ወለድ የደሃውን ገንዘብ እየሰበሰቡ፣ ነገር ግን ለሚሰጡት ብድር እስከ 18 በመቶ የብድር ወለድ የሚያጋብሱ ያለ ውድድር በትርፍ የሚቀማጠሉ ናቸው ተብሏል፡፡

የዚያን ቀኑ መድረክ መሪ እዮብ (ዶ/ር) የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ይከፈታል መባሉን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹ጌታ ከመምጣቱ በፊት ይከፈታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን›› በማለትም በሚያስፈግግ ሁኔታ ዘርፉ ዝግ ሆኖ ረዥም ጊዜ መፍጀቱን ገልጸው ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ‹‹የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም›› ውይይት ከፖለቲከኞችና ከምጣኔ ሀብት ምሁራን ጋር የሚካሄድበት አጋጣሚ ደረሰ፡፡ በዚሁ ዕለትም በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ስለተመዘገበው ዕድገት፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ ማሻሻያው በትኩረት ስለሚሠራባቸው ዕቅዶች በሰፊው ተነሳ፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ስለመክፈት ጉዳይም ጥያቄ ቀረበ፡፡

ይህን በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሦስት ዓመቱ የአገር በቀሉ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ውስጥ ተካቶ የቀረበ ዕቅድ አለመሆኑን ተናገሩ፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፣ ጥልቅ ጥናት በማድረግ የሚገባበት እንጂ እንዲሁ ዝም ተብሎ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጫናን ለመቅረፍ በሚል የሚሠራ አለመሆኑን በአጽንኦት አስረዱ፡፡

ይህ ከሆነ አራት ዓመታት ተቆጠረ፡፡ በአጠቃላይ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ወዲህ ባለፉት ስድስት ዓመታት የውጭ የፋይናንሰ ተቋማት ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የመፍቀድ ጉዳይ በሰፊው ሲነገር ቢቆይም፣ በተጨባጭ የተወሰደ ዕርምጃ ሳይኖር ዘልቋል፡፡ መንግሥት የቴሌኮም ዘርፍን ክፍት ባደረገ ወቅት የባንክ ዘርፉንም ይከፍታል ተብሎ በሰፊው ተነግሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ ከሰሞኑ ‹‹የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ›› ለተወካዮች ምክር ቤት እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ የሚጨበጥ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ ወደ 94 አንቀጾች ያሉት አዲሱ አዋጅ በ11 ክፍል የቀረበ ነው፡፡ የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረግ ጉዳይን በተመለከተ የአዋጁ ቅድመ ማርቀቅ ምዕራፍ አካል የሆነ የፖሊሲ ሰነድ በብሔራዊ ባንክ በኩል እንዲዘጋጅ ተደርጎ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡንና መፅደቁን ያስታወሰው የአዋጁ መግለጫ፣ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ክፍት ማድረግ የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ መሆኑን ያወሳል፡፡

አዋጁ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ለበርካታ ዓመታት ዝግ ሆኖ በመቆየቱ የተነሳ፣ በአገር ውስጥ ባንኮች መካከል ፈጠራ የታከለበትና አዳዲስ አገልግሎቶች ያለው ውድድር እንዳይኖር እንቅፋት እንደፈጠረ በመጥቀስ ነው የሚንደረደረው፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ከውጭ ዓለም ገበያና ኢኮኖሚ ጋር እንዳይተሳሰር እንቅፋት መሆኑንም ይጠቁማል፡፡ የተደራሽነት ውስንነት፣ የግለሰቦችና የተቋማትን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች እጥረት፣ የፋይናንስ ገበያ መሠረተ ልማት ውስንነት የዘርፉ መገለጫዎች ሆነው ቆይተዋልም ይላል፡፡

ከባንክ ሥራ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ልምድና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አኳያ የአገር ውስጥ ባንኮች ገና ብዙ እንደሚቀራቸውም የአዋጁ መግለጫ ያትታል፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2016 መጨረሻ (በቅርቡ ወደ ባንክነት የተሸጋገሩ ስድስት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞችን ጨምሮ) በአጠቃላይ የባንክ ብድር አገልግሎት ደንበኞች ብዛት ከ3.1 ሚሊዮን ብዙም አይዘልም ይላል፡፡ ተደራሽነቱ ደግሞ በአዲስ አበባና በጥቂት ዋና ዋና ከተሞች ብቻ የተወሰነ ሆኗል ሲል ያክላል፡፡

በመግለጫ ሰነዱ ላይ የረቂቅ ሕጉ አስፈላጊነት በሚል ወደ ሦስት አንኳር ጉዳዮች ተቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም አዋጁ ባንኮች ሲቋቋሙ ሊያሟሉ ስለሚገባቸው መሥፈርት ለመወሰን መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረጉን ሒደት በሕግ ለመምራት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ባንኮች የፋይናንስ ቀውስ ሲገጥማቸው ዕልባት የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመወሰንም እንደሆነ ያክላል፡፡

አዋጁ የሚጠበቅ እንደሆነና የውጭ ባንኮች የመግባት ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የማይቀር መሆኑን የተናገሩት የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ፣ የብሔራዊ ባንክ የወቅቱ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ መሾም በራሱ የዚህን ለውጥ አይቀሬነት ቀድሞም ጠቋሚ ነበር ብለዋል፡፡

በዓለም ባንክ አማካይነት ከ21 ዓመታት በፊት ‹‹Foreign Bank Entry: Experience, Implications for Developing Economies., and Agenda for Further Research›› በሚል ርዕስ የቀረበን ቆየት ያለ የጥናት ወረቀት በማጣቀስ ማብራሪያ የሚሰጡት ተንታኙ፣ የውጭ ባንኮች የመግቢያ ጊዜው አሁን ነው/አይደለም የሚለው ሙግት እንደማይገባቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹በ1983 በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን በመለስ ዜናዊ መተካት ብቻ ነው እኛ ያስተዋልነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ወቅት በዓለማችን እጅግ ብዙ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ የበርሊን ግንብ ፈርሶ ጀርመን አንድ የሆነችው፣ በርካታ የዓለም አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ነፃ አድርገው ከመላው ዓለም ጋር ኢኮኖሚያቸውን ያስተሳሰሩት፣ እንዲሁም የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ተጠናቆ መላው ዓለም በኢኮኖሚ የተሳሰረው ያን ጊዜ ነበር፡፡ እኛ አገር የሥርዓት ለውጥ መጣ ተብሎ ኮሙዩኒዝም በካፒታልዝም ስለመተካቱ ቢለፈፍም፣ ነገር ግን በተጨባጭ በኢኮኖሚው ሥርዓት ላይ በተለይ በፋይናንሱ ዘርፍ የመጣ ሥር ነቀል ለውጥ አልነበረም፡፡ የላቲን አሜሪካና የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ብዙዎቹ ባንኮቻቸውን የከፈቱት የዚያን ጊዜ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች የባንክ ዘርፍን በመክፈትና ከዓለም ገበያ ጋር በመተሳሰር ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡ ህንድ ለምሳሌ ወደ 45 የውጭ ባንኮች አሉ፡፡ ለረዥም ጊዜ ገብተው የቆዩ ናቸው፡፡ እዚህ አጠገባችን ኬንያ 14 የውጭ ባንኮች አሉ፡፡ ወደ ናይጄሪያ ብትሄድ ወደ 21 የውጭ ባንኮች አሉ፡፡ ሌላውን ትተን ኮሙዩኒስት በምንላት ቻይና 1,031 የውጭ ባንኮች አሉ፡፡ እዚሁ ከጎናችን ሱዳን አምስት የሚሆኑ የውጭ ባንኮች አሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ 12 የውጭ ባንኮች አሉ፡፡ ጋና ከ27 አጠቃላይ ባንኮች 16 የሚሆኑት የውጭ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ታዲያ የውጭ ባንክ የሚገባው መቼ ነው?›› ሲሉ በጥያቄ ይናገራሉ፡፡

የውጭ ባንኮችን በነፃነት እንዲሠሩ መፍቀድ ያን ጊዜ የሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ካልተሞከረ ከ30 ዓመታት በኋላም ሊሞከር አይገባውም የሚል ሙግት ማንሳቱ ተገቢ አለመሆኑን ተንታኙ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በናይጄሪያ የባንኮች ብዛት ከ23 አይበልጥም፣ በኬንያ 32 አካባቢ ናቸው፡፡ በቻይናም ቢሆን ወደ 4,000 ዓይነት ባንኮች አሉ ይባላል፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ አንድ የውጭ ባንክ ገና ባይገባም በርካታ የአገር ውስጥ ባንኮች እየተቋቋሙ ይገኛሉ፡፡ ሥራ ላይ ያሉት ወደ 30 ደርሰዋል፡፡ ለማቋቋም አክሲዮን እየሸጡ ያሉት ደግሞ ወደ 30 ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ተቋማት ብድር ያገኙ ደንበኞች ከ300 ሺሕ ገና አይዘልም፡፡ ቁጠባ አሰባሰብ፣ የቅርንጫፍ ተደራሽነት በብዙ መንገዶች ውስንነት አለባቸው፡፡ ባንኮቻችን የሀብታም ባንኮች ናቸው ማስያዣ ካላቀረብክ እኮ የብድር ጥያቄን የሚሰሙ አይደሉም፤›› በማለትም አክለው ገልጸዋል፡፡ በእሳቸው እምነት ባንኮች ከበቂ በላይ ራሳቸውን የማጠናከሪያና ተወዳዳሪ የማድረጊያ ጊዜ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል አቅም ካልገነቡ፣ ‹‹ለዝንተ ዓለም›› ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ተዘግቶ ቢቆይም ተወዳዳሪ መሆን አይችሉም በማለትም ደምድመዋል፡፡

የባንክ ዘርፉን ለውጭ ስለመክፈት ጉዳይ ከኢሕአዴግ ዘመን በፊት በደርግም ሆነ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ተነስቶ ያውቅ እንደሆነ የተጠየቁ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቀድሞ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ፣ በደርግ ጊዜ ጨርሶ ዝግ እንደነበር አስታውሰው በስተኋላ ቅይጥ ኢኮኖሚ ተብሎ በቀረበው ሐሳብም ለውይይት አለመቅረቡን ገልጸዋል፡፡ በጃንሆይ ዘመን ግን ባንኮ ዲ ሮማ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

‹‹በአሁኑ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ በሬን ዘግቼ እኖራለሁ የሚባል ነገር አይቻልም፡፡ ለፉክክር በርን ክፍት ማድረግ የግድ ነው፡፡ ሁለተኛ ከፖለቲካ ሥርዓት ልምድ አንፃር ጉዳዩ ሲታይ ሞኖፖሊ (ውድደር የሌለበት ገበያ) ማንንም አገር አሳድጎ አያውቅም፡፡ ፉክክር ነው ዕድገት የሚያመጣው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

እኚሁ አስተያየት ሰጪ ሲቀጥሉ የንግድ ከለላ ሰጥቶ ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማሳደግ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ‹‹የንግድ ከለላ የሚሰጠው የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተፎካካሪ እስኪሆኑና አቅማቸውን እስኪያጎለብቱ በሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ከጨቅላነት ሳይወጡ ሳይጎለብቱ ሊቀሩም ይችላሉ፡፡ ለዚህ ነው የንግድ ከለላን ለኢንፋንት ኢንዱስትሪዎች የሚሠራ ብቻ እያሉ የሚጠሩት በማለት የውጭ ባንኮች አይግቡ የሚለው ከለላ ሊበቃው የሚገባው ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ባለው በውድድር በተሞላ የዓለም ኢኮኖሚ የሞተው ሞቶ በሕይወት መቆየት የቻለው ይደግ የሚል ነው፤›› ሲሉ የጠቀሱት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ ያም ቢሆን ግን ፖሊሲ በኢኮኖሚ ሳይንስ ስህተት/ትክክለኛ ሊባል እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ለአንዱ አገር የሠራ ለኢትዮጵያ ሊሠራ እንደማይችል ጠቅሰው፣ በሌላ በኩል በአንድ ወቅት ሥራ ላይ የዋለ የንግድ ከለላ ለዘለዓለም እየሠራ መቀጠል እንደማይችልም ጠቁመዋል፡፡

የባንክ ዘርፉ በኢትዮጵያ ያሉበትን ችግር ሲያስረዱም ‹‹በሙስና መጨማለቁ ከባድ ቀውስ ነው፡፡ ብድር ለማግኘት ሰዎች ይህን ያህል ፐርሰንት ጉቦ ክፈል ይባላሉ፡፡ አንድ ባንክ ውስጥ ሥራ ለመቀጠርም ብዙ ሺሕ ብር ጉቦ ክፈል ይባላል፡፡ የባንክ ዘርፉ በብሔርና በሃይማኖት ፖለቲካም የተተበተበ ነው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ በተለይ ሸገር ከተማ አስተዳደር አንድ ሰው ቅጣትም ሆነ ሌላ የመንግሥት ክፍያ በስንቄ ባንክ ብቻ ካልከፈልክ ይባላል፡፡ ባንኮቻችን በኢኮኖሚ ውድድር ላይ ብቻ ተመሥርተው የሚሠሩበት ሜዳ መፈጠር አለበት፡፡ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መደረጉ በቴክኖሎጂ፣ በአገልግሎት ወይ በተደራሽነት ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ የአስተዳደር ክፍተቶችን ሁሉ ለማከም የሚረዳ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ደምድመዋል፡፡

የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በበኩላቸው፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ ትክክለኛ ጊዜው አይደለም በሚል የሚነሳውን ሐሳብ አጣጥለውታል፡፡ ‹‹ስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ ጊዜው አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በጃንሆይ ጊዜ ስቶክ ማርኬት እንደነበር ማስታወስ ይገባቸዋል፡፡ ቴሌኮምን ለመክፈት ብዙ ተፈራ፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ተከፍቶ ሳፋሪኮም ገባ፡፡ ከጠበቅነው በላይ እንዲያውም የውጭ መግባቱ የእኛን ኢትዮ ቴሌኮም ታታሪ አደረገው፡፡ አሁንም ለባንኮች ጊዜው አይደለም ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ በኢኮኖሚክስ ጊዜው አይደለም የሚባል ነገር የለም፡፡ የውጭዎቹ መግባት ብዙ ትሩፋት ይዞ ሊመጣ ይችላል፤›› በማለት ነው የዘርፉን መከፈት በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት ያብራሩት፡፡

በቅርቡ ‹‹የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለውጭ ባንኮች መክፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?›› በሚል ጠያቂያዊ ርዕስ ለሪፖርተር ጽሑፍ ያበረከቱት አመሐ ኃይለ ማርያም የተባሉ በአሜሪካ ነዋሪ ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ፣ የውጭ ባንኮች መግባት ጉዳይ ለአገር ውስጥ ባንኮች ፈጽሞ ሥጋት ሊሆን እንደማይችል ሞግተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ባንኮች በውጭዎቹ መግባት ተወዳዳሪ ለመሆን የካፒታል ውስንነት፣ እንዲሁም የሠራተኞች ፍልሰትና ሌላም ተያያዥ ችግር እንደሚገጥማቸው እንደሚሠጋ ባለሙያው በመነሻቸው ይጠቃቅሳሉ፡፡ ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ወደኋላ ተመልሰው ከ1930 ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረውን የቢዝነስ ከባቢ አየር ይቃኛሉ፡፡

‹‹በ1930ዎቹ ኢትዮጵያ በአኅጉሩ መቶ በመቶ በጥቁር አፍሪካዊያን ባለቤትነት የተያዘ የመጀመሪያው ባንክ ባለቤት ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በ1950ዎቹ በአፍሪካ የአክሲዮን ገበያ ካላቸው ሁለት አገሮች አንዷ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የውጭ ባንኮችና 16 የውጭ ኢንሹራንሶች ነበሩ፡፡ ኢኮኖሚው ክፍት በመሆኑ በውጭ ካፒታል፣ አመራርና ቴክኖሎጂ በእጅጉ ተጠቃሚ ሆነናል፡፡ የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚውን በፊታውራሪነት ይመራ ነበር፡፡ በ1950ዎቹና 60ዎቹ የውጭ ኢንቨስትመንት በሁሉም ዘርፎች የተለመደ ነበር፡፡ የጣሊያን፣ የግሪክ፣ የህንድ፣ የየመንና የአርመን ኩባንያዎች በሰፊው ይገቡ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ተጠቅማ ማደግ የቻለች ሲሆን የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአንድ ሺሕ ዶላር በላይ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሬም በገበያ ዋጋ በቀላሉ ማግኘት ይቻል ነበር፤›› በማለት ኢትዮጵያ በቀደመው ዘመን ፋይናንስን ብቻ ሳይሆን፣ መላው ኢኮኖሚዋን ለውጭ ገበያ በመክፈቷ ብዙ እንደተጠቀመች በሰፊው ከትበውታል፡፡

ከዚህ ተነስተውም ‹‹ለአገር በቀል ባንኮች ከለላ ይደረግ ሲባል በትክክል ስለአክሲዮን ባለቤቶች፣ ስለደንበኞች ወይስ ስለባንኮች ነው አልያስ ስለኢኮኖሚው እየተወራ ያለው?›› በማለት ጥያቄ ያስከትላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ባለአክሲዮኖች በግምት ከ520 ሺሕ ሰዎች በላይ አለመሆኑን የጠቀሱት የባንክ ባለሙያው የውጭ ባንኮች እንዳይገቡ መደረጉ የግል ባንኮችን ይጠቅማል የሚለው ሙግት የማያስኬድ ሐሳብ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡ ከዚያ ይልቅ መንግሥት ለራሱ ጥቅም ሲል በሩን ከርችሞት መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -