Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ የሚከፍሉትን የገንዘብ የሚመጥን አገልግሎት ያለማግኘት ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ተገልጋይ መብታቸው የሆነን አገልግሎት ለማግኘት ይጉላላሉ፡፡ እንዲህ ያለው ችግር በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሆነ በግል ዘርፉ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ደንበኞችን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶችን የመስጠት ችግር በርክቷል፡፡ 

በተለይ ለአንድ አገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያ ልክ የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የሚሰጠውን አገልግሎት አይመጥንም። ብዙዎቹ የሚጠይቁት ክፍያ አገልግሎታቸውን የሚመጥን መሆን አለመሆኑን በትክክል አሥልተው ዋጋ የሚያወጡ አይደሉም፡፡ 

ደንበኞች ምን ይፈልጋሉ? ምን ያህሉ የኅብረተሰብ ክፍል በአገልግሎት ላይ የሚጣሉ ክፍያዎችን ለመክፈል አቅሙ ይፈቅዳል? የአገልግሎት አሰጣጡ በትክክል ደንበኞችን እያረካ ነው ወይ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ሊመልስ በሚችል መልኩ እየሠሩ ነው ተብሎ ቢጠየቅ ማጣፊያው ያጥራል፡፡ ለዚህም ነው ተገልጋዮች ሁሌም የሚማረሩት፡፡ 

እንዲህ ያሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊመልስ በሚችል መልኩ ራሳቸውን አዘጋጅተው ወደ ሥራ የሚገቡት የአገራችን ተቋማት ስንቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማወቅ እንቸገራለን፡፡ 

አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ለመድረስ ተብለው የተቋቋሙ የተለያዩ የቢዝነስ ተቋማትን ነጥለን ብንወስድ እንኳ የመጀመርያ ግባቸው በምንም መልኩ ‹‹ጠቀም ያለ›› ትርፍ እንደሚያገኙ የሚያሠሉ እንጂ፣ ለደንበኞች ዕርካታ የሚጨነቁ አይደሉም፡፡ እርግጥ ነው ማንኛውም የቢዝነስ ተቋም መሠረታዊ ግቡ ማትረፍ ነው፡፡ ነገር ግን የሚሰጡትን አገልግሎት የማይመጥን ክፍያ የሚጠየቅባቸው ከሆኑና ያልተገባ ትርፍ ማግኘትን ካስቀደሙ አገልግሎት ይታጎላል፡፡ 

ቢዝነስ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ተብሎ ዘው ተብሎ የማይገባበትና ከትርፍ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል ሞራልና ጨዋነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ዛሬ መሠረታዊ ለሚባሉ እንደ ሕክምና፣ ትምህርትና መሰል አገልግሎቶች የሚጠይቁ ክፍያዎች እንዲህ አስደንጋጭ የሚሆኑት ከትርፍ ባሻገር ማኅበረሰቡን በአግባቡ ለማገልገልና የተመጠነ ትርፍ አግኝቶ የማደግ አመለካከት በመጥፋቱ ነው፡፡ 

የአብዛኛውን ተገልጋይ አቅም ያገናዘበ አገልግሎት መስጠትን ከማሰብ ይልቅ፣ በአጭር ጊዜ ከብሮ ለመውጣት የሚደረጉ መፍጨርጨሮች መልካም የአገልግሎት አሰጣጥን ተጭነዋል፡፡ 

ለማንኛውም በመንግሥት ተቋማትም ውስጥ ለአንድ አገልግሎት ከሚጠየቀው ሕጋዊ ክፍያ አንፃር በጎንዮሽ የሚጠየቁ ደረሰኝ የሌላቸው ክፍያዎች የመንሰራፋታቸው የአገልግሎት ትርጉምን አዛብቷል፡፡ ተገልጋዮን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጋ ለአገልግሎት መነሳት በራሱ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ 

ተገልጋዮች ያለ ምንም ተጨማሪ ውጪ በሕግ የተፈቀደላቸውን መብት ተጠቅመው አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩ የምናይበቱ ሌላው ምክንያት፣ በሙስና የተጨማለቁ ሠራተኞችን ለማረም አለመቻሉ ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም በግልጽ ጉቦ የሚጠይቁ ሠራተኞች ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ ያለመኖሩ፣ አንድ ጉዳይ በእጅ ሳይባል ማስፈጸም ዘበት እንዲሆን እያደረገው ነው፡፡

ይህ ሥር የሰደደ ብልሽት አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ አገር ተረካቢዎች ይቀረፅባቸዋል በተባሉ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ጭምር መንሰራፋቱ ነው፡፡ የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ የማይጠቀሙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስማቸው ነጋ ጠባ ሲነሳ መስማት ያማል፡፡ እነዚህ ተቋማት የተቋቋሙለትን ዓላማ ስተው ባልተገባ ክፍያና ያልተገባ ግዥ የሚፈጸምባቸው ናቸው ተብለው መከሰሳቸው በራሱ ያሳፍራል፡፡

ያላግባብ አበል የሚበላባቸው፣ ደረጃውን ያልጠበቀ ምግብ የሚያቀርቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሠራተኞች ካሉ ትልቅ ችግር ውስጥ ገብተናል ማለት ነው፡፡ ከሆነ እነዚህ የትምህርት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሽት እንዲህ ከተገለጠ አስተምረው የማይወጧቸው ልጆች ወደ ሥራው ዓለም ሲገቡ በተመሳሳይ ድርጊት ቢሠማሩ ይፈረድባቸዋል፡፡ ስለዚህ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚታዩ ችግሮች አንዱ መንስዔም የትምህርት ተቋሞቻችን እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ተማሪዎችን መቅረፅ ባለመቻላቸው ጭምር ነው ማለት ይቻላል፡፡

የቢዝነስ ተቋማቶቻችንም ሆኑ ሌሎች ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ የተቋቋሙ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት አጠቃላይ አሠራር መስተካከል ካልቻለ፣ አደጋው የከፋ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ቀደም ተብለው የተጠቀሱት የጤና፣ የትምህርትና መሰል አገልግሎቶች አካባቢ ያለው ከሥነ ምግባር ያፈነገጡ ተግባራት ዝም ብለው እንዲቀጥሉ መፈቀድ የለበትም? አንድ ታማሚ ለአንድ ሳምንት ሕክምና ሚሊዮን ብር የሚጠየቀው በየትኛው አግባብ ስለመሆኑ ልንገምት ይገባል፡፡ አገልግሎታቸውን በተጋነነ ክፍያ ለመግለጽ የሚፈልጉ ተቋማትን መስመር ማስያዝ እስካልተቻለ ድረስ ችግሩ ይቀጥላል፡፡

በትክክል የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ክፍያ የሚጠየቅባቸው የከተማችን ትምህርት ቤቶችን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በትክክል የሚሰጡት ትምህርት ለአንድ ተማሪ በዓመት በመቶ ሺሕ ብሮች የሚጠየቅበት ምክንያትስ የተለየ ያደረገው ምን እንደሆነ በግልጽ ማሳመን የማይችሉ አንዳንድ የትምህርት ተቋማት በክፍያ መጠናቸው ራሳቸው ሲገልጹ እየታዩ ለምን ዝም ይባላሉ? 

ዋናውን ዓላማ ስተው ግባቸውን ዓለም ላይ የሌለ የትርፍ ህዳግ ይዘው እየሠሩ ስለመሆኑ ሳይታወቅ ቀርቶ ነው?  

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች የ2017 ዓ.ም. የተማሪዎች ምዝገባ እያካሄዱ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ትምህርት ቤቶች በአግባቡ በሕግ የተቀመጠውን አሠራር ባለመከተላቸው እንደሆነ ሰምተናል፡፡ እንደ ተገልጋይ ግን መሆን የነበረበት እነዚህ የትምህርት ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት በሕግ የተቀመጡ አሠራሮችን በመጋፋታቸው ብቻ ሳይሆን፣ አገልግሎታቸውን ያገናዘበ ክፍያ ስለሚጠይቁ ጭምር ነው ቢባል የተሻለ ነበር፡፡

የትምህርት ቢሮ ከሰጠው ምክንያት በላይ ይህ ትርጉም አለው፡፡ አገልግሎታቸውን በማይመጥን ክፍያ ከሚጠየቅባቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት ቤቶች ዋነኞቹ ከመሆናቸው አንፃር ተቋማቱ አገልግሎቱን የሚመጥን ክፍያ እየጠየቁ መሆን አለመሆናቸው ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል። አልግሎት ሰጪ ተቋማት ትኩረትና ትጋት በቅድሚያ የተሰማሩበትን ዓላማ ለማሳካት እንጂ፣ የተጋነነ ትርፍ ለማትረፍ መሆን የለበትም።

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት