Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊጶስ ይናም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥ ዓመታት አገልግለዋል፡ ከአምስተርዳም ዩቨርቲ በ መንግትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማበር ራ አስጻሚ አባልና በአዲስ አበባ ዩቨርቲ ከሰብዓዊ መብት፣ ከ ምግባር ከፍርድ አሰጣጥና ንብረት ግ ጋር የተገናኙ ልጠናዎችን ይሰጣሉ፡፡ ሰሞኑንዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ባለውና በርካቶች ጥያቄ እያነሱበት በሚገኘው የንብረት ማስመለስ ረቅቂ አዋጅ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የግ አወጣጥን በተመለከ ሲሳይ ሳህሉ ከአቶ ፊሊጶስ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ንብረት ማስመለስ ረቅቂ አዋጅ ከመግባታን በፊት፣ ሕጎች ሲረ ምን ዓይነት መንገድ መከተል አለባቸው የሚለውን እስኪ በትንሹ ይግለጹልን?

አቶ ጶስ፡- እንግዲህ  ሰሞኑን እንዳየኸውና እንደሰማኸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ የንብረት ማስመለስ አዋጅ መነሻ በማድረግ አንድ የሕግ ረቂቅ ሲወጣ መሥፈርቱ ምንድነው? ሒደቱ ምን መምሰል አለበት? የሚለውን ጉዳይ እንመልከት፡፡ የተለያዩ ዓይነት ሕጎች አሉ፡፡ ሕገ መንግሥት፣አዋጅ፣ ደንብና መመርያ እያልን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ከዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ሕጎች መነሻቸው ሕገ መንግሥትን መሠረት አድርገው ነው የሚወጡት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ መርሆችን ባማከለ መንገድ ሊከተሏቸው የሚገቡ የዴሞክራሲያዊ የሕግ አወጣጥ ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንድ ሕግ ስለወጣ ብቻ ፍትሐዊ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ፍትሕ የሚጀምረው ከሕግ አወጣጥ ነው፡፡ የሕግ ማውጣት ዋና ዓላማው  ለዜጎች ፍትሕ ለመስጠት ነው፡፡ ሕግ ሲወጣ ዓላማ ሊኖረው ይገባል፡፡ የሕግ ዓላማ መግለጫ በየትኛውም የሕግ መጀመርያ ማብራሪያ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሒደት አንድ ሕግ ሁለት ጠቅላላ ዓላማዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የዜጎችን መብት ማክበርና ማስከበር፣ እንዲሁም በተፈጥሮ የተሰጡ የዜጎችንና የሰው ልጆችን መብት እንዲጠበቁ ማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው የሕግ ዓላማ በዜጎችና በተወካዮቻቸው፣ በመንግሥት አካላትና በተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት በሥርዓት መምራት ነው፡፡ በዚህ መነሻ ተንተርሶ ነው እንግዲህ አንድ ሕግ የሚተቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ‹‹የንብረት ማስመለስ›› የሚለውን አዋጅ ስንመለከት፣ ማስመለስ ብለህ ስትነሳ መጀመሪያ የተወሰደ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አዋጅ የሚገመገመው ከዓላማው ግልጽነት፣ ከሕገ መንግሥታዊነቱ፣ ከሥልጣን ክፍፍልና ከሕግ የበላይነት ጋር አሳታፊነቱ በቂ ውይይት የተካሄደበት እንደሆነ በማየት መሆን አለበት፡፡

በሌላ በኩል አንድ ሕግ ሲወጣ ከዓለም አቀፍ መብቶችና ድንጋጌዎች፣ ከሰብዓዊ መብቶች አከባበር ጋር ሊጋጭ አይችልም ወይ? ሕጉ የዜጎች ፍላጎት አለበት ወይ? የዜጎችን መብት ይፃረራል ወይ? የወጣው ሕግ ጥናት ተደርጎበት ነው ወይ? ከሚሉና ወቅታዊነት አኳያ በሚገባ መታየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ በሰሞኑ ረቂቅ ሕግ ላይ የተገለጸው አሥር ዓመት ወደኋላ ሄዶ ጉዳይን ይመለከታል በሚል የተቀመጠው ድንጋጌ ከሕግ አወጣጥ መርህ ውጪ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሕግ ተፈጻሚነቱ በነጋሪት ጋዜጣ ከታተመበት ጀምሮ ጊዜ ነው፡፡ ለምን ሲባል ሕጉ የተወለደው እዚህ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በሕግ አወጣጥ መርህ ሕግ በሌለበት ጊዜ ወደኋላ ሄዶ (Retroactively) ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

ምክንያቱም ሕግ ሲወጣ ዋነኛ ዓላማው ዜጎች እንዲቀጡበት ማስገደድ ብቻ ሳይሆን እንዲታወቅ፣ እንዲማሩበትና እንዲከበር መደረግ አለበት፡፡ አንድ ሕግ አለመግባባት ተፈጥሮ ዳኝነት ለመስጠት ብቻ ሳይሆን እንዲከበር መደረግ አለበት፡፡ ሕግ ተደራሽ መሆን መቻል አለበት፡፡ የአንድ ሕግ ግዴታና ውል ተፈጻሚነቱ ተዋዋዮች በተለየ ሁኔታ ወደኋላ ሄደው ለመዋዋል በልዩ ሁኔታ ካልፈለጉ በስተቀር፣ በሕዝብ ላይ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ ዛሬ የወጣው ነወ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው ሕግ ተፈጻሚነት የሚኖረው ሥልጣን ካገኘበት ቀን ጀምሮ ነው እንጂ፣ ሥልጣን ላይ ባልነበረበት ጊዜ ተፈጻሚ እንዲሆን መወሰን አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ መረት ይህ አዋጅ እንዴት ይታያል?

አቶ ጶስ፡- የአዋጁን ተፈጻሚነት ከመግቢያው ጀምሮ ስትመለከት ወደኋላ አሥር ዓመታት ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል ይላል፡፡ በሌላ በኩል የረቂቅ አዋጁን ሙሉ ዝርዝር ይዘት ስትመለከት የኢኮኖሚ ወንጀል በአገሪቱ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን፣ በወንጀል የተገኘን ንብረት ማጥናት፣ መለየት፣ ማስመለስና ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን መመለስ የሚሉትና አስቀድሞ በነበሩ ሕጎች ላይ ሽፋን ያላቸውን ጉዳዮች ይጠቅሳል፡፡ ምክንያቱም ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ከፀረ ሙስና ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ማስመለስን በተመለከተ ያፀደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በተግባር ለማስፈጸምና በወንጀል ድርጊት የሚገኝ ሀብትን ማስመለስ እያለ ያብራራል፡፡ ነገር ግን በሌላ የይዘት ክፍሉ ደግሞ ወንጀል ያልፈጸመ ሰውን የሚመለከት ይመስላል፡፡ ስለዚህ ይህ ረቂቅ ግልጽነት ይጎለዋል፡፡ ለምን ያህል እንደሆነ በረቂቁ ከትርጉም እስከ ዓላማው ያሉት ዝርዝር ጉዳዮች የወንጀል ሕግን መሠረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ እንዳይሠራ የሚከለክለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ስላለው፣ አሥር ዓመት ወደኋላ ተመልሶ የመተግበር ትልም መያዝ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህም ተገቢነት ያለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ  ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ያሉ ድንጋጌዎች የተፈጻሚነት ወሰን እንዴት ይታያል?

አቶ ፊልጶስ፡-  የአንድ ሕግ ተፈጻሚነት ወሰን ሲታይ ሕግ ወደኋላ ተመልሶ አይሠራም የሚለው ጉዳይ፣ አስቀድሞ በግሪክና በሮማን ሕግ አወጣጥና አተረጓጎም ሁሉ ተቀባይነት ያለው የሕግ ሳይንስ ነው፡፡ በረቂቁ እንደተብራራው ሕጉ ወጥቶ አሥር ዓመት ይመለስና ይተግበር ቢባል ተፈጻሚነቱ ከባድ ነው፡፡ መንግሥትስ ምን ያህል ያስፈጽመዋል? ብዙ ሕጎች እኮ እየወጡ የተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ብቻ ተፈጽመው ቀሪ የሚሆኑ አሉ፡፡ ይህ ማለት ሕጉ በከፊል ይፈጸማል በከፊል አይፈጸምም፡፡ ይህ ደግሞ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 25 ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው የሚለውን ድንጋጌ ይጥሳል፡፡ አድሏዊነትን ያመጣል፣ የሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ የደኅንነት ተቋማት ሕጉን ያለ አግባብ እንዲጥሱት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሕግ ተርጓሚው አካልም ወደኋላ ሄዶ ማስረጃ ለመፈለግ ገደብ አለው፡፡ ለዚህም ነው ይርጋ የሚባለው አሠራር የመጣው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ማስረጃ ለማቅረብ ባይችልስ? የአሥር ዓመት ማስረጃ ባያገኝስ ምን ሊሆን ነው? ስለዚህ ነው አንድ ሕግ ሲወጣ ተፈጻሚነቱን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡ አለበለዚያ ሕግ በወረቀት ላይ ይኖራል፣ በተግባር አይኖርም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሕግ የበላይነትን ይጎዳል፣ መብቶችን ይጥሳል፣ የሕግን መርህን ይጥሳል፡፡ ምክንያቱም ሕግ ተፈጻሚ ካልሆነ ተጽፎ መቀመጡ ምን ዋጋ አለው?

ሪፖርተር፡- በዚህ ረቂቅ አዋጅ ያሉ ድንጋጌዎች እንዳሉ ወደ ራ ቢገቡ ምን ችግር ሊያመይችላ?

አቶ ፊልጶስ፡- ዜጎች ኮሚሽን ለማግኘት እርስ በርስ እንዲጠቋቆሙና ጠላትነት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ሰላማዊ ኑሮን የሚያናጋ ነው፡፡ አስፈጻሚው አካልም ይህን ሕግ ያለ አግባብ እንዲጠቀመው ሊያደርግ ይችላል፡፡ በረቂቁ ዓቃቤ ሕግ ይከሳል ይላል፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ ሲከስ ማስረጃ የሚያቀርበው ተከሳሽ መሆኑን ያብራራል፡፡ ይህ በትልቁ የሥነ ሥርዓት ማስረጃ መርህን የሚጥስ ነው፡፡ ከማስረጃ ዋነኛ መርሆች ውስጥ፣ ማስረጃ የማቅረብ ኃላፊነት ግዴታ የከሳሽ ነው፡፡ በጣም በተለየ ልዩ ሁኔታ ከዚህ በፊት እንደነበረው ዓይነት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም በተለየ (Exceptional) ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፣ እንዲህ ዓይነት አዋጅ እኔ እከሳለሁ አንተ አስረዳ ሊባል አይችልም፡፡ ከሳሽ ያውም ትልቅ መዋቅር፣ የማስረጃ፣ የደኅንነትና የፖሊስ ተቋም ያለው ነው፡፡ አንድ ልጇ ዶላር ከውጭ ልካላት ቤት ከሠራች ደሃ እናት ወይም አባት አዛውንት ጋር፣ ወይም ለጉብኝት የመጣ ልጅ ገንዘቡን በአገር ውስጥ በሚገኝ ጥቁር ገበያ መንዝሮ ንብረት ካፈራ አንድ ተራ ግለሰብ ጋር ነው የሚካሰሰው፡፡ ይህ ደግሞ አሁን  እየታየ ካለው ሁኔታ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ ባለሥልጣናት፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ግለሰቦች ውጭ አገር ሄደው ሲመጡ እስኪ ስንቶቹ ናቸው በባንክ የሚመነዝሩት? በእርግጥ በባንክ የሚመነዝሩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በጥቁር ገበያ  ነው የሚመነዝሩት፡፡

የአዋጁ ዓላማ ደግሞ ያን ጥቁር ገበያ ለማስቀረት ከሆነ ጥቁር ገበያውን የሚያስተካክል ሌላ ጠበቅ ያለ ሕግ ማውጣት ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ጥቁር ገበያን ከባንክ ጋር እኩል ሕጋዊ አድርገው የሚሠሩ አገሮች አሉ፡፡ እዚህ አገርም እንዲተገበር ወይም የሁለቱ ምንዛሪ ተቀራራቢ እንዲሆን ውሳኔ መወሰንና መፍትሔ ማምጣት እንጂ፣ ለአንድ ችግር ሌላ ችግር የሚያስከትል አዋጅ መፍጠር የለብንም፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ሀብት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ፣ ኢንቨስትመንት ወደ አገር ቤት እንዳይሳብ፣ ዳያስፖራዎችና የውጭ አገር ዜጎች በራሳቸውና በዘመዶቻቸው ስም ብዙ ሀብት በዓይነትና በገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዳያስገቡ ይገድባል፡፡ ይህ ሀብት አገር ውስጥ በገባ በአንድም በሌላ መንገድ አገርን የሚጠቅም ነው፡፡ አዋጁ በባህርና በበረሃ አቋርጠው ሰው አገር ሄደው የሠሩበትን ገንዘብ ለመውረስ በሚመስል ሁኔታ ልክ የመንግሥትን ሀብት እንደወሰዱ ተደርጎ ንብረት ለማስመለስ ተብሎ መቅረቡ፣ ከርዕሱ ጀምሮ ጥልቅ ምርመራና ጥናት ያስፈልገዋል፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ረቂቁ ያለ በቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የቸኮለ ሕግ ውጤቱ አያምርም፡፡ ሕግ ከወጣ ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ሕጉን ወደኋላ አሥር ዓመታት ተመልሰህ ለመተግበር ብትሞክር፣ የዛሬ አሥር ዓመት አምስት ሚሊዮን ብር የነበረ ንብረት ዛሬ ግምቱ ስንት ነው? የዛሬ አሥር ዓመት ሁለት ሚሊዮን ብር የነበረው እኮ ዛሬ ሃያ ሚሊዮን ብር ገብቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ባለው ንብረት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ነው የሚያብራራው፡፡ ንብረቱ እንዴት ነው የሚገመተው? ገማቹስ ማን ነው? ይህ በአዋጁ አልተቀመጠም፡፡ በኢትዮጵያ ገለልተኛ የሆነና ፈቃድ ያለው ባለሙያ ገማች የለም፡፡

ስለዚህ ገማቹ የመንግሥት ባለሥልጣን ነው? ወይስ ራሱ የመንግሥት ባለሙያ ነው? ማን በገመተው? መቼ በተገመተ አሠራር ነው? በተጨማሪ ከሌላ ሀብት ጋር የሚቀላቀለው ሀብት ምን ሊሆን ነው? አንድ ደመወዝተኛ  ከደመወዙ ጋር ቀላቅሎ በሠራው ቤት፣ በሊዝ በያዘው መሬት፣ በማኅበር በተመራው ቤት፣ ዘመድ ረድቶት በሠራው ቤት፣ በውርስ በሠራው ቦታ የሆነ ገንዘብ ጨምሮ ሊሠራ ይችላል፡፡ ይህ እንዴት ነው የሚገመተው፡፡ በመሠረቱ ብዙ የሚወጡ ሕጎች የይዞታና የባለቤትነት መብትን ባለየ ሁኔታ የይዞታ መብትን የሚያሳጡና የሚጥሱ ናቸው፡፡ አንቀጽ 40 ላይ የተቀመጠውና የተደነገገው ሕገ መንግሥታዊ መብት ንብረት የማፍራት መብት ነው፡፡ ይህ የንብረት ባለቤትና የይዞታ መብት ነው፡፡ ይህ አዋጅ ሁለቱን ለይቶ ያልያዘ ነው፡፡ ለማስፈጸም እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ በእጅጉ ግልጽነት የሚጎድለውና ለማስፈጸም የሚያስቸግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ም አቀፍ ልምዱስ?

አቶ ጶስ፡-  ዓለም አቀፍ ልምዱ ሲታይ የሶሻሊስት መንግሥታት የሚከተሉት መንገድ ነው፡፡ በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሬትም ሆነ ሌላ ይዞታ ትርፍ ከሆነ በሶሻሊስት ሥርዓት አማካይነት ተወርሷል፡፡ በዚህ ጊዜ ለመውረስ ሲታሰብ ዋነኛ ማረጋገጫው ትርፍ መሆኑ ብቻ ነው የሚታየው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው በቂ መኖሪያ ቤት ካለው ሌላው ግን ትርፍ ነው፡፡ ይኼኛው ረቂቅ ግን ንብረት የማፍራት መብት ለዜጎች የሰጠውን ሕገ መንግሥት በግልጽ ይጥሳል፡፡ በተመሳሳይ አንድ ሰው በተለያዩ መንገዶች ማኅበረሰቡ ካለው ተደጋጋፊነት አኳያ ከቤተሰብና ከወዳጅ ከሚገኝ ሀብት ጋር ቀላቅሎ ሌላ ሀብትና ንብረት ያፈራል፡፡ በዚህ ውስጥ ዓቃቤ ሕግ አንድን ግለሰብ በመክሰስ ማስረጃ አምጣ ብሎ ማስገደዱ የሚያስኬድ ነገር አይደለም፡፡ ዜጋው ላለፉት አሥር ዓመታት መረጃ ባያስቀምጥስ? ሰነድ ከሌለውስ? በዚህ ውስጥ ሕግ ተርጓሚው እኮ ሕግን ብቻ የሚተረጉም በመሆኑ የቀረለበትን ተርጉሞ ውሳኔ ሊወስንለት ነው ማለት ነው? ሌላው የሕግ መርህ ተመጣጣኝነቱ (Balanced) ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሕጉ አጠቃላይ አስፈላጊነትስ?

አቶ ጶስ፡- የሕጉ አስፈላጊነትም ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ሕጉን ለማውጣት አስፈላጊ ነው ተብሎ ከታመነ በቅድሚያ በቂ ውይይት ተደርጎ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ ፀድቆ ወደ አፈጻጸም ሲገባ ንብረቱን ለመውረስ ከውጭ የተላከውን? ወይስ ሰውየው ከውጭ መጥቶ በጥቁር ገበያ የመነዘረው ገንዘብ ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ በመቅጣት ነው የሚለው መጀመሪያ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ የአንድ የባልና ሚስት ንብረት ክፍፍል እንኳ ሲደረግ የጋራ ንብረታቸው በአንድ በተወሰነ ሰው ገቢ ብቻ የሚፈራ አይደለም፡፡ ብዙ ነገር አለ፡፡ ጊዜ፣ ጉልበትና ዕውቀት የሚለው ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ላፈራው ሀብት ደረሰኝ ያላቀረበ ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው ሀብቱ ሊወርስ እንደሚችል ተብራርቷል፡፡ ለሁሉም ብት ደሰኝ ማምጣት ይቻላል?

አቶ ጶስ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ሕጋዊ ደረሰኝ ማን ነው የሚያጠራቅመው? በአንዳንድ ሃዋላ የሚላክ ገንዘብ እኮ ደረሰኝ ሊሰጠውም፣ ላይሰጠውም ይችላል፡፡ ደረሰኝ አለ ቢባል እንኳ አይደለም አሥር ዓመት ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ገንዘብ ከየት እንዳወጣን እናስታውሳለን ወይ? ይሁን ቢባልስ ከውጭ መጥቶ በጥቁር ገበያ የተመነዘረው ገንዘብ ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ በመቅጣት? ወይስ ሙሉውን ገንዘብ በመውረስ? የሚለው ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ በ1952 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ እኮ የሕግ መሠረቱን ሲያብራራ፣ አንድ ሰው ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ የሕግ መብት አለው ይላል፡፡ አንድ ሰው ንብረት የማፍራት፣ ባለይዞታ የመሆን፣ ባለሀብት የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ዓቃቤ ሕግ መጥቶ አንድን ግለሰብ ሕጋዊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ሕገወጥ አለመሆንህን አስረዳኝ ሊል እንደሚችል ነው እየነገረን ያለው፡፡ ይህን የማስረዳትና ግለሰቡ ሕገወጥ መሆኑን ሊያብራራ የሚገባው ግን ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ የንብረት መብት ትልቅ መብት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሕግ ሲወጣ የንብረት ሕግ ባለሙያዎች ሊነጋገሩበትና ሊመክሩበት ይገባል፡፡ አንድ ሰው ቤቱ ተወርሶ ጎዳና ላይ እንዲወድቅ ማድረግ ከመንግሥት ኃላፊነት ተቀራኒ የሆነ አሠራር ነው፡፡ ተቋማዊ ቢሆን የሒሳብ መዝገብ ይኖራል፡፡ ምን ያህል ገንዘብ ተላከ? ምን ላይ ዋለ? የሚለው ዝርዝር መረጃ ይኖራል፡፡ የግለሰብ የሒሳብ ዝርዝርን በተመለከተ ግን ግለሰቡ ይህ ሁሉ የሒሳብ መዝገብ ሊኖረው አይችልም፡፡

አንድ ሕግ ሲዘጋጅና ሲተረጎም ለአፈጻጸም አመቺ እንዲሆን የዜጎችና ተቋማት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት በሥርዓት የሚመራ ደንብ ያስፈልገዋል፡፡ ሕግ ሲወጣ የሕዝብን ጥቅም መሠረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም ሕግ ሲወጣ ለሕዝብ ጥቅም ይባላል፣ ነገር ግን ‹‹ለመሆኑ የሕዝብ ጥቅም ምንድነው?›› የሚለው በራሱ ሌላ አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ የሕዝብ ጥቅምን የሚገዛ ሕግ የለም፡፡ በአንዳንድ አዋጆች ላይ አስፈጻሚ አካሉ የሕዝብ ጥቅም ነው ብሎ ከወሰነው  የሕዝብ ጥቅም ተደርጎ ይወሰዳል ይላል፡፡ ይህ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅም በአስፈጻሚ አካል ብቻ ነው ወይ የሚወሰነው? ሕግ አውጭው አይወስነውም ወይ? ፖሊሲ ሊወጣለት አይገባም ወይ? በሕዝብ ጥቅም ስም ሥልጣን አይበዘበዝም ወይ? ለሕዝብ ተወረሰ ተብሎ ዜጎችን ማስለቀስና መጠቀሚያ ሊሆን አይችልም ወይ? የሚለው መመለስ አለበት፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚውን አምኖ የይዞታ ማረጋገጫ በውልና ማስረጃ ወስዶ የገዛውን ቤት ወይም መኪና መውረስ የማይቻል ነገር ነው፡፡ ከተቻለም በጉልበት ነው እንጂ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ሰው ጥፋተኛ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ከውጭ በተላከለት ገንዘብ ሀብት ስላፈራ ብቻ፣ አንድ ሕግ ተጠቅሶ  እንደ ወንጀለኛና ጥፋተኛ ሊታይ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ ሕግ ማለት እኮ የዜጎች ስምምነት ነው፡፡ ስለዚህ ለሕዝብ ጥቅም የወጣ ሕግ ለስንት ሰው ጥቅም ነው የሚለው በግልጽ መታየት አለበት፡፡

በሌላ በኩል ሀብት ወደ ውጭ እንዳይሸሽ መከላከል ነው? ወይስ አገር ውስጥ ያለው እንዲሸሽ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው? ይህ እንግዲህ እዚህ ያሉት እየሸጡ እንዲወጡ፣ ውጭ ያሉት ዳያስፖራዎችና ሪል ስቴት አልሚ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋይ እንዳያፈሱ ፍራቻ ይለቅባቸዋል፡፡ በማልማት ከመሳተፍ ይቆጠባሉ፣ ሥጋት ያድርባቸዋል፡፡ እዚህ አገር ሕገወጥ የሚባለው የውጭ ምንዛሪን በጥቁር ገበያ መቀየር እኮ ሌላ አገር ሕጋዊ ሥራ ነው፡፡ እዚህ ሥርዓት እንዲይዝ ለማድረግ ለምን አይቻልም? በእዚህ አገር እኮ ስንት የተፋለሰ አሠራር ነው ያለው፡፡ አይደለም በግለሰብ ተቋማትን ጠርተህ ከአሥር ዓመት በፊት ገንዘብ በባንክ የመጣበትን ደረሰኝ አምጡ ማለት በዚህ ወቅት የማይቻል ነው፡፡ ከጅምሩ ግዴታ ለምን አልተቀመጠም? ግለሰቦች ከውጭ የመጣ ገንዘብ የተቀበሉትን ደረሰኝ እንዲያስቀምጡ የሚያስገድድ ሕግ ለምን አልወጣም? ሰነድ ከሌለህ ወይም ካልያዝክ በዚያ ገንዘብ ያፈራኸው ሀብት ይወረሳል ተብሎ ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን ወደፊት ሊወጣ ይችላል እንጂ ላለፈ ጊዜ እንዴት ሰነድ አምጡ ይባላል? አስገዳጅ ሕግ ባልነበረበት ሰነድ የመያዝ ግዴታ ነበረብህ ብሎ አሁን እንደ አዲስ እያስገደደ እኮ ነው፡፡

በረቂቁ አንቀጽ 30 ላይ በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት መውረስን በተመለከተ ያብራራል፡፡ ይህ ማለት እኮ ሰው ገድለህ የማታውቅ መሆንህን አስረዳ፣ ሰርቀህ የማታውቅ መሆንህን አስረዳ፣ ገንዘብ በጥቁር ገበያ መንዝረህ የማታውቅ መሆንህን አስረዳ፣ እኔ ግን እጠረጥርሃለሁ ማለት ነው፡፡ ይህ የሚሆን አይደለም፡፡ በፍትሕ ሥርዓት ሦስት ዋነኛ ነገሮች አሉ፡፡ ሕግ፣ ፍሬ ነገርና ማስረጃ አለ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ፍሬ ነገርን መሠረት አድርጎ ክስ ሲያቀርብ ማስረጃም አብሮ ማቅረብ አለበት፡፡ ይህ ማስረጃ የቪዲዮ፣ የሰነድና የሰው ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሳሽ ይህን ሲያቀርብ ተከሳሽ በፍርድ ቤት እንዲከላከል ይጠየቃል፡፡ ይህ ለፍርድ ቤትም የሚቸግር ውሳኔ ነው፣ ዳኛ እያዘነ እንዲወስን የሚያደርገው ሕግ ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል አለመሆናቸውን የምታይበት አሠራር ሲኖር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ዓቃቤ ሕግ ያለ ማስረጃ ክስ ያቀርባል፣ ተከሳሽ በግድ ማስረጃ አቅርብ ሊባል ነው፡፡ እንዴት ሆኖ?

ንብረት ማስመለስ ሲባል በዓለም አቀፍ ሕግጋትም ቢሆን በሙስና የተወሰደ ንብረትን ማስመለስ ይቻላል፡፡ ወይም ነጋዴ ሆኖ ከገቢው በላይ ላጠራቀመው ሀብት ማስረጃ ከሌለው እንዲያስረዳ ይጠየቃል፡፡ ካላስረዳ ልትወርሰው የምትችልበት አሠራር ልትዘረጋ ትችላለህ፡፡  ነገር ግን የግለሰቦች የሀብት አፈራር በአብዛኛው በመረጃ ያልተደገፈና ባህላዊ መንገድን የሚከተል ነው፡፡ ማስረጃ የሌለው ሒሳብ ተመዝግቦ የማይቀመጥበት የሀብት ምንጭ የተደበላለቀ  በመሆኑ፣ ማስረጃ አምጡ ብሎ ግለሰቦችን ለማስገደድና ለመወሰን መሞከር ከሕግ ዓላማ፣ ከማኅበራዊ እሴትም ሆነ ከሞራል ሕግጋት አንፃር ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ እንዲሁም ዜጎች በሕግ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው፣ ሕግ ማስከበሪያ መሆኑ ቀርቶ መቀጣጫ ነው ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው።

በሌላ በኩል አንድ ሕግ በፍርድ ቤትም ሆነ በዜጎች ዕውቅና የሚኖረው በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሲወጣ በመሆኑ፣ ወደኋላ አሥር ዓመታት ተመልሶ ይሠራል ብሎ መደንገግ አግባብነት የለውም፡፡ በአጠቃላይ አዋጁ ከንብረቱ መብት አንፃር እጅግ አደገኛ ነው፡፡ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጁን ሕዝብን ለመጥቀም በሚመስል መንገድ ማቅረብ  ትክክል አይመስለኝም፡፡ በመጨረሻም ማስተላለፍ የምፈልገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ቋሚ ኮሚቴው  በተለይም ከሕግ ባለሙያዎችና ከባለሙያዎች ማኅበር፣ ከጠበቆችና ከጠበቆች ማኅበር፣ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ከሕግና ምርምር ተቋም፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሕጉ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ምክክር ሊያደርጉበት ይገባል፡፡ አስፈጻሚ አካላትም የሚፈልጉትን ሕግ አርቅቀው ማምጣታቸው  መቆም አለበት፡፡ አንድ ሕግ ሲወጣ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ማለፍ አለበት።

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...