Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ

እላይ [ባለፈው ሳምንት ጽሑፍ] የተጠቀሱት ዓለማዊና አካባቢያዊ የተሞክሮ ትምህርቶች፣ የለውጥ አካሄድንና የሕዝብ ግንዛቤን እንዳገዙ ሁሉ፣ ከልምድ ተምሮ የድሮ አቋማቸውን ማቃናት ሞት የሆነባቸውም ነበሩ፡፡ የመጋቢቱ ለውጥ ገና በለጋ ጉዞው ታፍነው ባደሩ ጥያቄዎችና በአዳዲስ ጥያቄዎች የመወትወት ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡ ጥያቄዎች እየተቅበጠበጡ/ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ጥቃትንና ጥፋትን እንደ ትግል መሣሪያ ይጠቀማሉ፡፡ ከልምድ ተምሮ ከድሮ አቋም መታረም ያልቻሉ ቡድኖች፣ የከሰሩ አቋሞች ላይ ተሟዘው ጣዕረኛ ትግል ማድረግን መርጠው ነበር፡፡ ዋነኞቹ መፈናቀልና ሞት አንጋሾችም የመጨረሻዎቹ (የአሮጌ ፖለቲካ መንገደኞች) ነበሩ፡፡ የፀጥታ አውታሯ ወደ አንድ ቡድን ይዞታነት የተቀየረባት ኢትዮጵያ በአግባቡ ሕግና ሥርዓት የማስከበር አቅም አልነበራትምና ከመቼውም ጊዜ በላይ ከባድ ፈተና ውስጥ የወደቀችው በዚህ የለውጥ ጊዜ ነበር፡፡

1) ከኦነጎች የመሰነጣጠቅ ጉዞ፣ ‹‹ኦሮሞ በአቢሲኒያውያን ቅኝ ተይዟል… መነጠል አለበት›› ከሚል አቋም ጋር ተጣብቆ የቀረው የኦነግ ዳውድ/ሸኔ ቡድን ከ1983ቱ ኦነግ (በሽግግር መንግሥት ውስጥ ቆይቼ ወደ ሪፈረንደም አመራለሁ ብሎ ከተሸወደው) ትምህርት ወስዶ የአሁኑን የለውጥና የሰላም አጋጣሚ ኢትዮጵያን ማሞኛ አድርጎ ሊጠቀምበት አቅዶ ሁለት ቢላ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ ከላይ በ‹ሰላም› ቢላ እየነገደ የተወሰነ የታጠቀ ቡድን አስመዝግቦ በሥልጠና ወደ አገሪቱ የፀጥታ ኃይል እንዲቀላቀልለት ይሠራል፡፡ ከሥር ድምፁን አጥፍቶ ይዞታዬ ነው በሚለው ሥፍራ ሁሉ የታጠቁ ኃይሎች እያራባ እዚያም እዚያም መተኮስ ይጀምራል፡፡ ቢተኩስም ኦሮሞና ኢትዮጵያውያን በአያሌው ተስፋቸውን በአንድነትና በለውጡ ላይ ከማድረግ ሌላ የሚወላውሉበት ነገር የላቸውም፡፡ በይፋ መነጠል ይበጃል ብሎ ሕዝብን አይቀሰቅስ ነገር በዓለምና በኢትዮጵያ ዙሪያ ያለው ተጨባጭ ልምድ አስፈራሪ ነው፡፡ እናም የቆረበበትን ግብ ለማሳካት ለውጡን ይደግፋሉ በተባሉም ሆነ ፖለቲካ ውስጥ በሌሉ ንፁኃን ላይ የትኛውንም ግፍና ጭካኔ እየፈጸሙ ትርምስና ምሬት ማባዛት፣ ሕዝብ ተከፋፍሎ ሊፋጅ የሚችልባቸውን ሃይማኖት ነክና ብሔረሰብ ነክ ጥቃቶችን ማድረስ የመጨረሻ መንፈራፈሪያ ሥልቶቹ አስከ ማድረግ ድረስ ጣዕረኛ ሆነ፡፡

ዓላማቸው የከሰረ ሆኖ (የሕዝብን ልብ መርቻ ፖለቲካ ሳይኖራቸው) እንደምን ግን ወጣቱን ከጊዜ ጊዜ መመልመላቸው መቀነሻ ሊያጣ ቻለ? በተለይ የሕወሓት ጦርነት ቆሞ እነሱ ላይ የመንግሥት ምቱ በጠነከረ ጊዜ አለቀላቸው ተብሎ ሲጠበቅ (አረመኔያዊ ግፋቸውም በቶሎ መጠናቀቃቸውን የሚያግዝ ሆኖ ሳለ)፣ የወጣት ምልመላቸውና ጭፍን ግፋቸው ያልተገመተ ዕድሜ እንደምን ሊያገኝ ቻለ? የእንቆቅልሹ መፍቻ ከሚከተሉት የተያያዙ ነገሮች ውጪ አይሆንም፡፡ ማለትም፡- ግፉ ኦሮሞን የሚቀረጥፍ ቢሆንም ‹‹የኦሮሞ ነፃ አውጪ›› የሚል ጭምብል ያለው መሆኑ፣ ትልልቅ ዲግሪ የተሸከሙ ፈረንጅ አገር ተቀምጠው የፕሮፓጋንዳና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች በዚሁ ጭምብል ውስጥ መኖራቸው፣ በማኅበራዊና በመደበኛ ሚዲያ ፅንፈኞች ከሚያደርጉት ውስወሳ በላይ በ‹‹ነፃ አውጪ›› ነኝ ባዩ ግፈኛ ዘረፋና ዕገታ የሚገኘው ሲሳይ ሥራ-አጡን ወጣት የሚያማልል መሆኑ፣ ያውም ዘርፎ በሌነቱንና ነፍሰ ገዳይነቱን ከህሊና ቅጣት አርቆ በታጋይነት ኩራት የሚሸነግል መሆኑ — ሳፊ ቀማኛነትና አራጅነት በነፃ አውጭነት ‹ሊብሬ› መቀሸራቸው፡፡

2) ሕወሓት ገና ከጅምሩ የትግራይን ሕዝብ ገዥነት የብቻ ርስቱ አድርጎ፣ ለትግራይ ሕዝብ እታገላለሁ የሚል ሌላ ድርጅትን መግደል እንደጀመረ ሁሉ (ከአማራ ገዥዎች ጋር የተፈራረቀና የተጎዳኘ የኢትዮጵያ ገዥነት ታሪክ ትግራዊ ገዥዎች ያልነበራቸው ይመስል)፣ የብሔር ጨቋኝነትን ለአማራ ሰጥቶ፣ ትግራዊ ብሔርን ከሌሎች ብሔሮች ጋር እኩል ተጨቋኝ አድርጎ ያሠለፈበትን አታላይነት ሕወሓት የጀመረውም ‹‹በኢትዮጵያ የብሔሮች ቅራኔ/ጥያቄ ዋናው ነው›› በሚል አቋሙ ነበር፡፡ ከሞላ ጎደል ኅብረ ብሔራዊነት የነበረውን የአገሪቱን የደኅንነትና የታጠቀ አውታር በትኖ በተጋዳላዮች ሲተካም አታላይነቱን አውታራዊ ማድረጉ (በሕወሓታዊ የበላይ ገዥነት ይዘት የትግራዊ ብሔር የበላይነት ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ አቅዶ መዘርጋቱ) ነበር እንጂ የብሔሮችን እኩልነት ማዋቀሩ አልነበረም፡፡ በተግባር እንደተረጋገጠውም በፌዴራላዊ መልክ ውስጥ የክልል አስተዳደሮች ፈጥሮ ባንዲራ መስቀል፣ በተወሰነ ደረጃ በአካባቢ ቋንቋዎች መሥራት መጀመር፣ በነጠላ ወይም በተቧደኑ የብሔር ፓርቲዎች አካባቢያዊ ገዥነትን መመሥረት ሁሉ የብሔር/ብሔረሰብ ‹‹የራስ አስተዳደርና እኩልነት›› አታላይ መልኮች ነበሩ፡፡ በዚህም፣ ሲወክሉት የነበረው ግንኙነት የሕወሓት ተቀጢላ ገዥነትን ነበር፡፡ ሁነኛው ገዥነትና መዝባሪነት ካፈጠጠ ፓርቲያዊ የኩባንያ አውታሮች ጋር የሕወሓት ነበር፣ ያውም ጠርናፊ የሆነ፡፡

በረዥሙ የታቀደበትና ‹‹የእኩልነትና የራስ አስተዳደር›› አጎዛ ያለው የአንድ ቡድን የጥርነፋ ገዥነት ግን ከአንድ ትውልድ በላይ መዝለል አልተቻለውም፡፡ ሕወሓትም እንደ ኦነግ ሸኔ ከጥፋቶቹና ከዓለም-ከአካባቢያችን ልምዶች ለመማርና ለመታረም አልፈቀደም፡፡ የሕዝብ የእርስ በርስ ጭፍጨፋ ለመለኮስና መንግሥትን ለማናወጫ እንዲሆን ታልሞ የተካሄደውን የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ፣ ማንም ያድርገው ማን፣ ግድያውን ተከትሎ ሰኔ 20ዎች ውስጥ (2012) የመጣው በቁጣ የተሞላ የጭፍጨፋና የአደባባያዊ ነውጥ ጅምር አዲስ አበባን ሲዖል ለማድረግ የተተመመበት ታላቅ የመንፈራፈር ክስተት ነበር፡፡ ነውጠኛው መንፈራፈር ከሽፎ የሚታሰረው ታስሮ ኦነግ ሸኔ ላይ የመንግሥት ዕርምጃ ሲበረታ፣ ለብቻ የመመታት አደጋ የሕወሓትንና የአጫፋሪዎቹን ደመ ነፍስ ተጣራ፡፡ በ1983 እስከ 1985 ዓ.ም. የኢትዮጵያን የፀጥታ አውታራት አከርካሪ ያነቀውን ሕወሓታዊ መዘዝ፣ ኢትዮጵያን ለሚያጠቃ ቡድናዊ ፍላጎታቸው የማሸፈትና የውስጥ አርበኛነትን እንዲያገለግል የሚቻላቸውን ሁሉ ደባ አቀባበሉ፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተከፈተው ወረራ በክልል ደረጃ ካደራጁት ግዙፍ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጋር በኢትዮጵያ ስም የደረጀ የመከላከያ ሀብትን አጣምሮ ኢትዮጵያን መልሶ የመምታት ዕርምጃ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ያስነከሳት ከባዱ የ1983 እስከ 1985 ዓ.ም. መዘዝ የተመዘዘውም በዋናነት ጦርነቱን ለመመከትና ለመቀልበስ በተካሄደ የተጋድሎ ሒደት ውስጥ ነበር፡፡ ኦነግ ሸኔ አለኝ ያለውን ጭካኔና በቀል በሕዝብና በልማት ላይ እንዳዋለው ሁሉ፣ ሕወሓትም በግዙፍ ጦርነቱ ውስጥ የግለሰቦች፣ የተቋማት፣ የማኅበረሰብ የሚል ልዩነት ሳያደርግ ንብረቶችን አውድሟል፣ ዘርፏል፡፡ በንፁኃን ላይ (ሕፃናት፣ አዛውንት፣ ሴት፣ ወንድ፣ ምእመናን፣ የሃይማኖት መሪዎች ሳይል) መልከ-ብዙ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ የወደቀ አሮጌ የትምክህት ስድብን ከታሪክ ቆሼ ላይ አንስቶ ማኅበረሰብ ለማበሻቀጥ እስከ መጠቀም ድረስ ጣዕረኛ ዝቅጠቱን አሳይቷል፡፡

3) የፋኖ ፉለላ ዘግይቶ የመጣ ክስተት ነው፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ገዥነት ትኩስና ያልተደላደለ በነበረበት ጊዜ የእነ አርባ ጉጉና የበደኖ የጎላ ጥቃት በተከሰተበት ጊዜ ነበር ከመአህድ ጋር የአማራ ብሔርተኝነት ብቅ ያለው፡፡ ያኔ ፋኖነት ዘራፍ አላለም፡፡ ከፕሮፌሰር አስራት የእስር እንግልት ጋር የመእህድ አባላትን እያደኑ ደብዛ ማጥፋት ሲካሄድ ፋኖነት ቡፍ አላለም፡፡ ጆሯችን ስለቄሮዎች በሰማ ጊዜ ግድም ስለ ወጣት ፋኖዎች ቢሰማም፣ የአማራ ብአዴንና የትግራይ ሕወሓት፣ ይዞታን የተመለከተ ውዝግብና ቅራኔ በጦዘበት ጊዜ፣ (‹በአገውና በቅማንት መብት ስም ጭፍራ ቡድኖች ሕወሓት አስታጥቆ አማራ ክልልን እያመሰ/እያበላ ነው› ይባል በነበረበት ጊዜ)፣ ከአማራ ክልል ውጪ ከተለያዩ ግጭቶችና ቁጣዎች ጋር ተያይዞ አማራ ናቸው የተባሉ ሰዎችን በጭፍን ማጥቃት 2011 ዓ.ም. እና 2012 ዓ.ም. (በተለይም 2012 ዓ.ም.) በናረ ጊዜ የፋኖ የብረት ትግል ተቀጣጥሎ አላየንም፡፡

2013 ዓ.ም. ጥቅምት ውስጥ ሕወሓት የከፈተው ግዙፍ ጦርነት ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ ያስከፈለ፣ አማራ ክልልም የተመነጠረበት እንደመሆኑ፣ በአጠቃላይ ርብርብ ወረራው ተቀልብሶ በድርድር መቋጨቱ ለኢትዮጵያም ለትግራይም ለአማራና ለአፋር ሕዝቦችም ትልቅ ዕፎይታ ነበር፡፡ ግዙፉ ጦርነት ከቆመ በኋላ ይከሰት የነበረው የእነ ሸኔ ጥቃት በሕወሓት ወረራዎች ማክተም የተገኘውን የአማራ ሕዝብ ዕፎይታና መልሶ የመቋቋም ጥማት የማደብዘዝ አቅም ፈፅሞ አልነበረውም፡፡ የኋለኛው የሸኔዎች ጥቃት በ2012 ዓ.ም. አካባቢ ከተፈጸሙት ጋር የሚወዳደር አልነበረም፡፡ ግዙፉ ጦርነት ባከተመበት ማግሥት የአማራን ሕዝብ የዕፎይታ ረሃብ ንቆ፣ የትጥቅ ትግል በአማራ ውስጥ መጀመርን ተገቢና ልክ ለማድረግ፣ የእነሸኔ ነገር ፈፅሞ የሚበቃ አልነበረም፡፡ ትልቁ ጦርነት ባከተመ ማግሥት ልዩ ኃይሎችና በአገር ጥሪው የተፈጠሩ ወዶ-ዘማቾች፣ ፍላጎትና መመዘኛዎች በተገናዘቡበት አኳኋን፣ ሕጋዊ የሙያ ሥምሪት ውስጥ እንዲገቡ በመንግሥት መወሰኑም፣ ሌላ ወረራ የመመከት አቅም ማሳጣትንና ትጥቅ ማስፈታትን የሚናገር አይደለም፡፡ ‹‹ሕወሓት ትጥቅ ሳይፈታማ…›› የሚል የፈለገ ሥጋት ቢኖር እንኳ፣ የምናልባቱ ሥጋት፣ ለአማራ ሕዝብ አንገብጋቢ ከነበረው ሰላም አጠገብ ለመቆም የሚበቃ አልነበረም፡፡

የታጠቁ ኃይሎችን ወደ ሕጋዊ መስመሮች የማስገባት የመንግሥት ውሳኔንና እንቅስቃሴ በመቃረን ወደ ጠመንጃ ትግል ያመራው ፋኖነት፣ እውነተኛ ምክንያቱ ለአማራ ደኅንነት መንገብገብ ነበር ወይ የሚለው ጥያቄ ቀላል መልስ የለውም፡፡ በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በተመራው አጠቃላዩ ተጋድሎ ውስጥ ፋኖዎችም ሆኑ ሌሎች የአማራ ታጣቂዎች ድንቅና ክቡር አስተዋፅኦ ማድረጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለሕወሓት ወረራ በመረጃ አቀባይነት፣ በሽብር ወሬ ነዥነት፣ በመንገድ መሪነትና በመሣሪያ ደባቂነት ያገለገሉ ወስላቶችም በጊዜው አልታጡም ነበር፡፡ ለሕወሓት ባያገለግሉም በጦርነቱ ጊዜም ሆነ ካበቃ በኋላ መሣሪያ እየያዙ ዘወር ያሉም እንደነበሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ከጦርነት ባረፍንበት ጊዜ፣ አጠቃላይ የታጠቁ ኃይሎችን መልክ የማስያዝ ተግባርን የሚያሳስብ ነበር፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ውስጥ ለሕገወጥ መሣሪያ ዝውውርና ግብይት የቀለለ ሁኔታ መፈጠሩ፣ በአገር ጥሪው ምክንያት መሣሪያ የያዘ/ሥልጠናና የውጊያ ልምድ የቀማመሰ መበርከቱ፣ ይኸው የባለ መሣሪያነት ብርካቴ፣ በድል መጀነኑና ፉከራው፣ ለሌላ ጀብድ የሚቅበጠበጥ ተኩስ መተኳኮሱ፣ በቁጥጥር ለማጨመት የማይቻል ነበር፡፡ ይህ የሻነነ ሁኔታ፣ ታጣቂዎችን ሕጋዊ ሥምሪቶች ውስጥ ከማስገባት የመንግሥት ውሳኔና እንቅስቃሴ ጋር ሲገናኝ፣ የመንግሥት ይህ ውሳኔም በጨለምተኞቹ የአማራ ብሔርተኞች በክፉ ሲተረጎም፣ የአማራ ተቆርቋሪ ነኝ ባዩ ጨለምተኛ ሁሉ ‹‹ውሳኔው በአማራ ላይ የተነጣጠረ ደባ ነው…፣ እንደገና አማራን ያለ ጠባቂ ለማስመታት የታቀደ ነው…፣ ወዘተ ወዘተ›› የሚለው ውስወሳ ሲጦፍ፣ በዚህ ላይ የሸኔዎችና የሌሎች ታጣቂዎች ማኅበረሰብ የለየ ጥቃት ሲታከል፣ ፋኗዊ ጀብደኝነት ጦዘ፤ በግብታዊነት ከአደባባይም ከካምፖችም ሰዎች እያሸፈተ በየአካባቢው በመንግሥት ላይ የሚተኩሱ ቡድኖችን ወለደ፡፡

ከእንግዲህ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጠሩ የታጠቁ ቡድኖች ሳይቀሩ የተንቀባረሩበትን ገዳይነት ፋኖም ሊንቀባረርበት ነው፡፡ በተለያየ ሥፍራ አማራ በማንነቱ ሲጠቃ ፋኖ ነኝ እያሉ ቡፍ ያለ ማለት የኃፍረት ጊዜ ከእንግዲህ ሊዘጋ ነው፡፡ በጀግንነትም በጀብዱ ሥራም ማናህሎን ባይ ትዕቢትና መንጠራራት ከጎሬው ወጣ፡፡ በተባራሪ ጥቃት መላሽነትና የአማራን ሥልጣን በመቆጣጠር ሳይወሰኑ፣ የትኛውም የታጠቀ ኃይል ያልሞከረውን (ለሕወሓት እንኳ የተሳነውን) አዲስ አበባን የማተራመስ ጀብዱ በመፈጸም ጥማት ልብ ተሞላ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሥልጣን መያዝ ቢሳካም ባይሳካም/ይህንን ማንም ያላደረገውን ገድል መፈጸም በራሱ አንደኛ ደረጃ ባለገድልነትን የሚያቀዳጅ ነው፡፡

ትርዒት ተጀመረ፡፡ ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረገው ዓይነት ጥቃት እንዳቅሚቲ፣ ‹‹እንዳትተኩሱ›› ተብለው በታዘዙ የመከላከያ ውስን ቡድኖች ላይ ተፈጸመ፡፡ መከላከያ ኃይልን የአንድ ግለሰብ ጦር፣ ፀረ ሕዝብና ፋሺስት አድርጎ መበከልና ‹‹ድል በድል ሆንን!፣ አጨድነው!!፣ መጣን/ደረስን!!›› የሚል ቱልቱላም ከሕወሓት ልምድ ተቀዳ፡፡ ሕወሓት ያቃተውን ጀብዱ አዲስ አበባ ውስጥ ሰርጎና ሚስጥራዊ ሰንሰለት ሠርቶ የዓብይን መንግሥት የሚያንቶሰቱስና ጀግኖቹ ‹‹ገዳዬ! ገዳዬ!.. እነሞት አይፈሬ!!..›› ብለው ለመዝፈን የሚበቁበት ፊልምም ተደረሰ፡፡ መንግሥትን በሽብር ማጣደፍም ሆነ መጣል የፊልም ሥራ አይደለምና ፊልም ሠሪዎቹ ገና በቅንብር ላይ እንዳሉ ዕይታ ውስጥ ገብተው ተለቀሙ፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ የነበራቸውም ፉለላ ክፉኛ እየተመታ፣ መማረክና እጅ በገፍ መስጠት በቱልቱላ የማይደበቅ እውነታ ሆነ፡፡

የፋኖዎች ትግል ላይ ከተቀመጠው ቀላል ሥዕል ምን ያህል የራቀ ነበር? ከዚህ የራቀና የኢትዮጵያን ውስብስብ የፖለቲካ መልክዓ ምድር የተረዳ አስተዋይነትና ብስለት ነበራቸው? የፕሮፈሰር ሽብሩ ተድላን የሕይወት ጉዞ መጽሐፍ የሚሰጠውን የተትረፈረፈ መረጃ ይዘን፣ በትግራይና በአማራ አካባቢዎች ምን ያህል የተከተሩ የአሮጌ ጦረኛነት አስተሳሰብና የባህል ቅሪቶች እንዳሉ ተረድተን የፋኖዎቹን አድራጎት ለመመዘን ከሞከርን ፋኖዎቹ ገና 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ሆነው እያሰቡ እንዳልሆኑ ደፍረን መናገር እንችላለን፡፡ ብሔርተኝነታቸው ዥንጉርጉሩን አማራ ማኅበረሰብ ያካተተ ንቃተ ህሊና ያለው እንኳ አይደለም፡፡ የአብዛኞቹ አስተውሎት ከኦርቶዶክስ ክርስትና ጋር የተጣበቀ ነው፡፡ የመንግሥት አርጩሜ መረር ሲል እነሱን ያልደገፉ ሙስሊሞችን እስከ መግደል ደነዝ ጥፋት ፈጽመዋል፡፡ የፖለቲካ ኦናነታቸውን የሚያጋልጥ ጥፋት መፈጸማቸውን ስለመረዳታቸውም እጠራጠራለሁ፡፡ በእነሱ ዓይን ‹‹ከጠላት›› ጋር ያበረን መቅጣት ተገቢ ሆኖ የታሰበም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ››፣ ሕዝባዊነት›› የሐሳብ ነፃነት›› የሚባል ነገር እነሱ ዘንድ ገና የደረሰ አይመስልም፡፡ ሕዝብን ጋሻ አድርጎ በከተማ ውስጥ መተኮስና በዚሁ ሥልት አማካይነት ‹‹መንግሥት ንፁኃንን ጨፈጨፈ›› የሚል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሞከርም የሕዝብን ደም የፖለቲካ መነገጃ የማድረግ ግፍ መሆኑም የገባቸው አይመስል፡፡

የሚሰጡት መረጃና ቅስቀሳም ጠያቂ አዕምሮ ያለውን የሚረታ ሳይሆን የሚያባርር ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አንዱ በጠመንጃ ትግሉ ሜዳ ውስጥ ያለ መሪ በሰጠው መግለጫ ውስጥ ‹‹የዓብይ መንግሥት በወለጋ በኩል ለኦነግ መሣሪያ እያስገባ እያስታጠቀ ይገኛል፤ አስተማማኝ መረጃ ነው…›› የሚል ነገር ረጭቶ ነበር፡፡ በምኞታዊ የበቀል ግርዶሽ ምክንያት እንዲህ ያለውን ውሸት ለማመን የፈቀደ፣ ከመፍቀድም የሚወድ በርካታ ደጋፊም አላቸው፡፡ ደጋፊዎቻቸው ‹‹ጀግኖች!!›› እያሉ የሚያሞግሱትና ከዛሬ ነገ አዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ከች ይላሉ ብለው የሚጠባበቁት፣ የፋኖዎችን ተጨባጭ አቅም እያስተዋሉ ሳይሆን፣ አዕምሯቸው ውስጥ የተሣለውን ተምኔታዊ የፋኖ አይበገሬነትና ትንግርት ሠሪነት እያስተዋሉ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ቅዠታም ደጋፊነት ውስጥ፣ ሁለት ሦስት ዲግሪ የጫኑ የህሊና ዕውራንም አሉባቸው፡፡ በህሊና መታወርና በስሜት በመወፈፍ ምክንያት፣ ከክህነት አልባሳታቸው ጋር የተጣሉና መጣላታቸው የማያሳፍራቸው የቀሳውስት ደጋፊም እስከ ጳጳስ ድረስ አነሰም በዛ አላቸው (ይህ ዓይነቱ የሃይማኖት መሪ ፖለቲካዊ ካድሬነት ከፋኖነት ጋር ብቻ ሳይሆን ከኦነግም ከሕወሓትም ጋር ተያይዞ የተከሰተ የጊዜያችን መንፈሳዊ ክስረት ነው)፡፡ እንደ እነዚህ ያሉት ቅዠታም ደጋፊዎችና ‹‹ታጋዮች›› ሕዝብ ያየውና እያየ ያለው መከራ አያንሰፈስፋቸውም፡፡ የሚያንሰፈስፋቸው ህሊናቸውን የተቆጣጠረው የፖለቲካ ግብ ነው፡፡ የህሊና ዕውራን ብዬ የገለጽኳቸውም ለዚህ ነው፡፡ ነባራዊ አስተዋይነት፣ ለሕዝብ ማሰብም ሆነ ለአገር ማሰብ ከህሊናቸው ተሠውሯል፤ ወይም አሳቢነታቸውን የጀብዱና የበቀል ጥማታቸው ደፍጥጦታል፡፡ ከዚህ አኳያ የፋኖዎች ‹‹በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ እናመጣለን›› ባይነት፣ ከቁም ቅዠት ያለፈ ዕርባና የለውም፡፡

አስተሳሰባቸውና ነገረ ሥራቸው እስከ ቋንቋ ድረስ የሰውን እኩል አክብሮትን አያንፀባርቅም፡፡ በጦር-አበጋዛዊ አዛዥ ናዛዥነት ተጀንኖ ንቀትንና ትዕቢትን ማግሳት፣ ለምላሳቸውና ለድርጊታቸው ቅርብ ነው፡፡ ‹‹ማንነታችንን እናሳያቸዋለን! አመዳም ሁላ…! እናሸናቸዋለን…!›› ከማለትም ያለፉና እዚህ ሊደረደሩ የማይችሉ ስድቦችንም ይደፍራሉ፡፡ በስድቡና በነውሩ ከሸኔና ከሕወሓት ጋር የሚተናነሱ አይደሉም፡፡ ሕዝብን የማነሳሳት ‹‹የነፃ አውጪ›› የድሮ ብልጠት፣ ለዛሬዎቹ ሸኔዎችም ለፋኖዎችም ባዕድ ነው፡፡ ‹‹አዲስ አበባ መጣን!›› የሚል ጉራቸው ከአፋቸው እየራቀ፣ ምንጠራው እየበረታ ሲሄድ፣ ለአማራ ሕዝብና ባለሀብት የተላለፈው የአንዱ ቡድን አዋጅ፣ የድጋፍ ገንዘብ እንዲያዋጡ ልጆቻቸውንም ለትግሉ እንዲሰጡ የሚያዝና በቅጣት የሚያስፈራራ ‹‹ኋላ አይቀጡ ቅጣት እንደይከተላችሁ!!›› ማለት የቀረው ‹አዋጅ› ነበረ፡፡ እናቶች በበረከቱበት አንድ ስብሰባ ላይ ተናጋሪ የነበረ ፋኖ ‹‹ከጠላት ያበረ›› አማራ እንደ አረም እንደሚነቀል፣ ከእንግዲህ ‹‹በሕግ አምላክ›› በማለት ፈንታ ‹‹በፋኖ አምላክ›› ማለት እንዳለባቸው ሲያሳውቅ ሰምተናል፡፡ ፋኖዎች በመሃላቸው የተከሰተውን መከፋፈል በማብራራት ረገድም ከግለሰቦች መሰሪነትና ከ‹666› የዘለለ ትንታኔ ሲሰጡት አላየንም፡፡ ልብስ አስወልቆ መግረፍን፣ የጠላት ቤት ንብረት እያሉ ማቃጠልና ማውደም እንደታየባቸው ከሆነም፣ ነገ እጅና እግር ቆረጣ ውስጥ አይገቡም ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ በአጭሩ እነሱ የተያያዙት መንገድ እነሸኔና ሕወሓት የገቡበት አዘቅት ዘንድ የሚያደርስ ነበር፡፡

ለ) ብሔርተኝነትና ትምክህት ምንና ምን?

የኢትዮጵያ የቅርብ አበሳችን ከብሔርተኝነትና ከማናህሎኝነት/ከትምክህተኝነት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ብሔርተኝነት ትምክህትን እታገላለሁ ሲል ዓይተናል፡፡ ትምክህትም ብሔርተኝነትን ሲንቅና ሲነቅፍ ተመልክተናል፡፡ ሁለቱ ተጣምደው ጠብ ሲያከሩም አስተውለናል፡፡ ብሔርተኝነት ከብሔርተኝነት ጋር ባልንጀራ እንደሚሆን ሁሉ ብሔርተኛነት ከብሔርተኛነት ጋር ሲናቆርና ሲዋጋ ዓይተናል፡፡ የማይዛመዱ (አንዳቸው ባሉበት ሌላው የማይገኝ) የሚመስሉት ብሔርተኝነትና ማናህሎኝነት፣ የአንድ እንቅስቃሴ አዝማቾች ሲሆኑም ታዝበናል፡፡ ሕወሓታዊው ጦርነት የብሔርተኛነት /የጎጠኝነትና የትምክህተኛነት ውጤት ነበር፡፡ የፋኖዎችም ጦረኝነት በብሔርተኝነትና በትምክህት የሾረ ነበረ፡፡ ብሔርተኛ ከብሔርተኛ ጋር ጓደኝነትም ጠላትነትም ሊይዝ እንደሚችል ሁሉ፣ ትምክህትና ብሔርተኝነትም ተጣምደው ሊናጩ ወይም የአንድ እንቅስቃሴ መንታ ገፆች ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡

የዚህ ሚስጥር ምንድነው? ሁለቱም አመለካከቶች ህሊናን የሚሸብብና ነገር ፈላጊ ባህርያት እንዳላቸው የኢትዮጵያ ልምዳችን ያስተምራል፡፡ ሁለቱም ገንታሮችና ጠባቦች ናቸው፡፡ ሁለቱም ጥበታቸውንና ገንታራነታቸውን የማይረዱና ለማሻሻል የሚቸገሩ/የማይጥሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም አንጓላዮች (ጨቋኞች) ናቸው፡፡ ሁለቱም ዘንድ የእኔን አላስነካም የሚል ስስትና ታሪክን አጣምሞም ሆነ ቆርጦ ቀጥሎ የሌላውን የእኔ ነው ባይ ተስፋፊነት ተዳብሏቸው ልናገኝ እንችላለን፡፡ አገራችን ውስጥ የታዩት ዋናዎቹ ግጭቶች እንዲያውም፣ በዓይን-አውጣ ሞጭላፋነት የተቆሰቆሱ ናቸው፡፡ የአካባቢዬ ሀብት የሌሎች መጠቀሚያ ሆነ/አንተ ጋር መሬት ቀረኝ የሚል ስስት በሌሎቹ ዘንድ ያለውን ሀብት ባለማወቅና የልዩ ልዩ አካባቢዎች ዥንጉርጉር ሀብት ከሰላም ጋር ተደምሮ ለጋራ መመንደጊያነት በመጥቀም ተወዳዳሪ-የለሽ መሆኑን ባለመረዳት ድንቁርና የተሞላ ነው፡፡ የትምክህት ማናህሎኝ ባይነትም የሌሎችን አስተዋፅኦ ባለማወቅ/ባለማክበር ድንቁርና የተሞላ ነው፡፡ ንቀትና ቁንንነቱም የዚህ ድንቁርና እንፋሎት ነው፡፡ የኤርትራ የነፃነት ትግል በቅኝነት ይዞ በደለኝ የሚለውን የኢትዮጵያን መንግሥት የሚንቅ ነበር፡፡ ሕወሓትም ሆነ ፋኖዎች ራሳቸውን አሳብጠው ገዥውን መንግሥት የሚንቁ ነበሩ፡፡ ገዥዎችን አግንኖ በማወደስና በገዥዎች ‹‹ገድል›› በመመካት ረገድ ብሔርተኞች ከትምክህተኞች ሩቅ አይደሉም፡፡ እነሱም በብሔራቸው ውስጥ የሚያገኟቸውን አግዝፈው ያሽሞነሙናሉ፡፡ ሁለቱም (ብሔርተኝነትም ትምክህተኝነትም) ለአስተሳሰባቸው የሚጥም ግነትን፣ ሐሰትን/ልብ ወለድን እውነተኛ ብሎ ለመያዝ የቀለሉ ግብዞች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ፣ ሁለቱም ዝንባሌዎች በሚዛናዊ ጠያቂና አንጣሪ የአዕምሮ ልምምድ የደኸዩ፣ ፍትሐዊ ህሊና የሚያጥራቸው፣ ዒአድሏዊ ፍርድ የሚቸግራቸው፣ ጭፍን ተቃዋሚነት/ኮናኝነትም ሆነ ጭፍን ደጋፊነት/አወዳሽነት የሚያጠቃቸው ናቸው፡፡

እናም እነዚህን የመሳሰሉት የጋራ ፀባዮች/ዕንከኖች አንድ ላይ ለመጋባት እንደሚያስችሏቸው ሁሉ፣ ባላጋራ ሆነው ሕዝብን ሰላም ለመንሳትም ያስችሏቸዋል፡፡ ሁለቱም በጭፍን-ጠባብ ውዳሴያቸውና በጭፍን ወገንተኛነታቸው ምክንያት ለተባበረ ጥንካሬ፣ ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ልምላሜ የማይበጁ (ለፍትሕ-አልባ አገዛዝና ለሙስና ኮርቻነትና አራማጅነት የተመቹ) ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር የንቁሪያ፣ የተከፋፈሉ ልቦችና የልሽቀት መፍለቂያ መሆናቸውን መናገራችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሁለቱ እየተማሰለች ምን ያላየችው መከራ አለ!

ሐ) ፍሬሕይወት የኢትዮጵያ ተምሳሌት

ፍሬሕይወት ‹‹ዩቲዩብ›› ውስጥ በአጋጣሚ የተዋወቅኳት አሳር ያሳለፈች ወጣት ጎልማሳ ነች፡፡ እሷ በቃለ መጠይቅ እንዳወሳችው፣ ለወላጆቿ አምስተኛ የሆነችው ሕፃን፣ ከወላጆቿ ትነጠላለች፡፡ ለሕፃኗ በሕይወት መኖር ሲባልም እናቲቱ መስዋዕት ትደረጋለች (ባለታሪኳ በአንደበቷ ፍርጥ አድርጋ ባትናገረውም ነገሩ ሁሉ ከባለ ውቃቢ የአምልኮ ጣጣ ጋር የተገናኘ ይመስላል)፡፡ ለተመላኪው ነገር መሰጠቷን ለማመልከት ‹የሱነሽ› የሚል ስም የነበራት ፍሬሕይወት፣ መጀመሪያ አጎቷ ዘንድ ከዚያ በኋላ ደግሞ አክስቷ ዘንድ ታድጋለች፡፡ በተለይ አክስቷ ዘንድ የነበረ ኑሮዋ በአድልኦ፣ በረሃብና በዱላ የተሞላ ነበር፡፡ መኝታዋም አመድና አዛባ ግድም ነበር፡፡ ከአክስቷ በኋላ ወደ አጎቷ አዲስ አበባ (ኳስ ሜዳ) ተወስዳ፣ የማታ ትምህርት ከመማር ዕድል ጋር ከባድ የአሽከርነት ሥራዋን ትቀጥላለች፡፡

በቀን አጋጣሚ የአባቷ ሁለተኛ ሚስት (ፍሬሕይወት ‹ሁለተኛዋ እናቴ› የምትላት) ያለችበት ቤት ትመጣለች፡፡ ባየቻትም ጊዜ በሩኅሩኅ ስሜት ታቀርባታለች፡፡ ፍሬሕይወት ደጉን አጋጣሚ፣ ስለማንነቷ ለመጠየቅ ትጠቀምበታለች፡፡ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ አባት፣ ወንድምና እህቶች እንዳሏት ስታውቅ ፍሬሕይወት ወደ እነሱ እንድትወስዳት ትማፀናለች፡፡ ሄዳ ግን የጠበቀችውን የአባት ፍቅር አላገኘችም፡፡ አባቷ ለዓይን እንኳን አላስጠጋትም፡፡ በቀን ትምህርት ቤት ትምህርቷን መቀጠል ብትችልም፣ ከሌሎቹ ልጆቹ ለይቶ ሰላም ይነሳታል፣ ‹‹ገፊ›› እያለ ይሰድባታል፣ ይተፋባታል፣ ይደበድባታል፡፡ የእንጀራ እናቷ ግን አቅርባ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበች ስለክርስትና እምነት ታስተምራት ነበር፡፡ የሁለቱ መግባባት በባልና ሚስቱ መሀል የማይበርድ ፀብና ጭቅጭቅ አስከተለ፣ ሚስት ተመርራ ወጣች፡፡

ከዚያ በኋላ አባት አምሽቶ በመጣበት አንድ ዕለት፣ አይፈጸም ነውር ፈጽሞባት በጨለማ ያባርራታል፡፡ ማባረሩ ሳያንስ ድብደባ እንዲደርስባት ‹‹ሌባ! ሌባ!›› የሚል ጩኸት ይለቅባታል፡፡ ፍሬሕይወት ባለ በሌለ አቅሟ ሮጣ የፍሳሽ ቱቦ ውስጥ በመደበቅ ነፍሷን አትርፋ በሁለተኛ እናቷ በኩል ወዳወቀቻት አንድ ሴት ዘንድ ትሄዳለች፡፡ መልካም አቀባበል ታገኛለች፡፡ ቀናዋ ሴት ከራሷ ጋር ልታኖራት ባትችልም፣ የቤት ሠራተኛነት ሥራ ፈልጋ ታስቀጥራታለች፡፡ የተቀጠረችበት የባልና ሚስት ቤት ለክፉ የማይሰጥ ቢሆንም፣ ሚስት ቅናት ውስጥ ስለገባች የፍሬሕይወት በዚያ ቤት መኖር ዕድሜ አላገኘችም፡፡ ሚስት ቅናቷ በናረ ቀን 250 ብር ሰጥታ ዝናብ ባለበት ጨለማ ትሸኛታለች፡፡ ፍሬሕይወት ከጎዳና አዳሪ ጥቃት ለማምለጥ በዶፍ ውስጥ እየሮጠች ሎዛ ማሪያም የምትባል ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ትደርስና በጥበቃ ሠራተኛው ፈቃድ ማሪያም ግቢ ውስጥ ሌሊቱን ለማሳለፍ በቃች፡፡

ከዚያች አዳር በኋላ፣ የፍሬሕይወት ብልህ የኑሮ መፍጨርጨር ምዕራፉን ትጀምራለች፡፡ ማደሪያዋን ቤተ ክርስቲያን ግቢ አድርጋ አካባቢውን ትቃኛለች፡፡ በሊስትሮነት ጫማ የሚጠርጉ ሽማግሌ ላይ ቀልቧ ያርፋል፡፡ ማሪያምን ዋሴ ብላ የሊስትሮ ሥራውን እየሠራች ገንዘብ ሳታጎድል ልታስረክብ፣ ሽማግሌው ከዚያ ላይ ትንሽ ሊሰጧት ታማክራቸዋለች፡፡ ሐሳቧ ተቀባይነት አግኝቶ ሥራ ትጀምራለች፡፡ አዳሯም ከሽማግሌው ዘንድ ይሆናል፡፡ የሊስትሮ ሥራዋ ‹‹ጥሩ›› ገቢ ካመጣ በኋላ ደግሞ ዓይኗ እንጀራ ጋግረው ወደሚሸጡ ሴቶች ይሳባል፡፡ አዛውንቱን ታማክራቸውና የሊስትሮ ሥራውን ለእሳቸው መልሳ፣ እንጀራ ጋግሮ የመቸርቸር ሥራ ውስጥ ትቀጠራለች፡፡ በዚህ ሁሉ የኑሮ ለውጥ ውስጥ ለትምህርቷም ጊዜ ነበራት፡፡

አንድ የእንጀራ ደንበኛዋ ቦሌ ሠፈር ውስጥ የቤት ሠራተኛ ስለመሆን ነገር ይፈነጥቅባታል፡፡ ፍሬሕይወት ቦሌን ከጀለች፡፡ ቦሌ የት አካባቢ እንደ ሆነ ፈልጋ ጠይቃ ካወቀች በኋላ፣ አንድ ቀን ጠዋት እግሯ ያደረሳት የቦሌ መንደር ውስጥ ከች ትላለች፡፡ ትልቅ በር ከፍቶ መኪና ካወጣ በኋላ በር እየዘጋ የነበረ ሰው ላይ ታተኩራለች፡፡ ሰውየው ወደ መኪናው ሲመለስ እግሩ ላይ ወድቃ ቤተሰብም ዋስም የሌላት ሥራ ፈላጊ መሆኗን በተማፅኖ ትናገራለች፡፡ ሰውየው ወደ ቤት አስገብቶ ከባለቤቱ ጋር ያስተዋውቃታል፡፡ ባለትዳሮቹ ደግ ሆነውላት በዚያው ዕለት የዘመድ ያህል የቀረበች ተመላላሽ የቤት ሠራተኛ ሆና ተቀጠረች፡፡

በዚሁ ሥራዋ ላይ እንዳለች፣ አንድ ዕለት አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ግንብ አጥር ጋር ብዙ ተመልካች የነበረውን ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ሞግዚትነት የወጣ ማስታወቂያ ታያለች፡፡ ውድድሩ የሚፈልገውን የትምህርት ደረጃ ታሟላ ነበርና ጉዳዩዋን ለቦሌ አሠሪዋ ትነግራታለች፡፡ አሠሪዋ ሞግዚትነት ምን እንደሆነ ጥሩ ግንዛቤ ትሰጣታለች፡፡ በዚያ ላይ የፍሬሕይወት ንቁነት ታክሎ የምልመላ ፈተናውን በስኬት ታልፋለች፡፡ ዕጣ ስታወጣም ሞግዚትነቷ ወደ ‹ልዩ ፍላጎት› የትምህርት መስክ ያመራል፡፡

በዚሁ መስክ መስማት ከተሳናቸውና የአዕምሮ ጉዳት ካለባቸው ሕፃናት ጋር ትገናኛለች፡፡ ሥራዋን ትወደዋለች፡፡ ሞግዚትነቷም በሥልጠና ዕገዛና በልምድ ይተባል፡፡ ብሎም የልዩ ፍላጎት ሞግዚትነቷ በ‹‹ኦቲስቲክ›› ሕፃናት ላይ ያተኮረ ይሆንና ልዩ ዕገዛ ፈላጊ ሕፃናትን የመግራት አቅሟም ተራምዶ፣ በግሏ መቶ ምናምን ገደማ ሠራተኞችን የማስተዳደር ስኬት ላይ ለመድረስ ቻለች፡፡ የፍሬሕይወት ይጨነቁን የግል ሕይወት ትረካ ጨምቄና አደብዝዤ ያቀረብኩት እሷን ያገኘ ስቃይ እኔን አግኝቶኝ ቢሆን ኖሮ ተሰባብሬ በአጭር መቅረቴ እየተሰማኝ፣ እሷ የሰው ብረት ሆና ስለገዘፈችብኝ ነው፡፡

ፍሬሕይወት ያለፈችበት ዓይነት አበሰኛ ኑሮ የመንፈስ ጉዳት አያደርስም የሚል ክርክር የለኝም፡፡ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ዕገዛ (የአንድ ለአንድም ሆነ የቡድን ዕገዛ) በኢትዮጵያ ያለው ታሪክ የቅርብ ከመሆኑ ባሻገር፣ የአገልግሎቱ አድማስ ዓባይን በጭልፋ ከመሞከር ያልራቀ በሆነበት ሁኔታ የሰቆቃ ሕይወት ብዙ ተመላልሶብናል፡፡ ከፍሬሕይወት የከፋ ሰቅጣጭ ልምድ ብዙ ሰዎች ላይ ስለመድረሱም ጥርጥር የለኝም፡፡ የ‹ቀይ/ነጭ ሽብር› ጊዜን በአዲስ አበባና በጎንደር ዓይቻለሁ፡፡ ያ ጊዜ እያንዳንዷ ደቂቃና ሰዓት መኖርና አለመኖር የማይታወቅበት ነበርና እናቶች 24 ሰዓት ሙሉ የምጥ ኑሮ ነበር የሚያሳልፉት፡፡ ልጅን መንገድ ላይ ተደፍቶ ማየት፣ ይሙት ይኑር ሳያውቁ መኖር፣ ለታሰረ ልጅ ስንቅ ሲያመላልሱና ከዛሬ ነገ ይፈታልኛል እያሉ ሲጓጉ ኖረው አንድ ቀን ‹‹ከእግዲህ እንዳይመጡ›› መባል… ስንቱ ሰቀቀን ይወራል! በመንግሥትና በቡድን ጥይት ከሚገደሉት ውጪ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያጠፉ ጥቂት አልነበሩም፡፡ መቀናደቡ ካለፈ በኋላ ከእስር የተፈታ ባልጀራዬ ራሱን አጥፍቷል፡፡ ጨርቃቸውን የጣሉ/መንገድ ለመንገድ የሚባዝኑ እናቶች ዓይቻለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ በተከሰቱ ግጭት/ጦርነት ነክ ጥቃቶች የተለያየ ዕድሜ ባላቸው ሰዎች ላይ የልቦና ጉዳቶች እንደሚያደርሱ መገመት አይከብድም፡፡ ግን፣ የጉዳቶችን ዓይነት በዓይን ዓይቶ መለየት እንደማይቻል ቢታወቅም፣ ኅብረተሰባችን ውስጥ እንደተከሰቱት ሰቆቃዎች መከታተልና መደራረብ፣ በርካታ የመንፈስ ስብራቶች ደርሰዋል ወይ? ፈረንጅ አመጣሹ የሥነ ልቦና ዕገዛው እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች የሰቆቃ ጉዳቶችን ተቋቁመው እንደምን መኖር ቻሉ? የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ሥነ ልቦና ከምዕራባውያን ምን ያህል እንደሚለይ፣ ኅብረተሰባችን እንዴት ያሉ ልቦናን የመንከባከቢያና የማበርቻና ቁስልን የማስረሻ/የማሻሪያ ብልኃቶች እንዳሉት ተጠንቷል ወይ? በቅርብ ሰቆቃዎች ውስጥ ያለፈና ታሪኩን የምተርክለት ሰው ባላውቅም፣ ከስቃይ ውስጥ ብርቱ ሆነው የሚወጡ ብዙ ፍሬሕይወቶች እንደሚኖሩ ግን አልጠራጠርም፡፡ በእነ ፍሬሕይወት ‹‹ብረትነት›› አማካይነትም የአገሬ ኢትዮጵያ ብረትነት ወለል ብሎ ይታየኛል፡፡

በደልና ክፋት የፍሬሕይወትን የመንፈስ ጥንካሬ፣ ብልህነት፣ ሩኅሩኅነትና ለሰዎች ያላትን ቸር ፍቅር አልነጠቃትም/አላደነዘባትም፡፡ ሰው የመርዳት ቅንነትና ትጋት የማያልቅባት፣ ተስፋ የማትቆርጥ፣ እክል የመወጣት ድፍረቷ የማይልፈሰፈስ፣ ሳቅና ዕንባዋ ቅርብ የሆኑ ችግሮችን አልፎ ሂያጅ ሆነች፡፡ ኢትዮጵያም፣ በጣም በቅርቡ የደረሰባትን ብናስተውል፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ በሰዎች ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይጠበቅ ነበር፡፡ ከሕፃን እስከ አዛውንት/መነኩሴ ድረስ ያዳረሰ ጭካኔና ነውር (መደፈር፣ መወገር፣ መታረድ፣ መዘንጠል፣ ቤት ውስጥ ተዘግቶ መቃጠል፣ መረሸን፣ ሬሳን ሳይቀር መበቀል…) ተካሄደ፡፡ የሃይማኖት አባቶች ጠመንጃ እስከ ማንገትና ‹‹አትማረው ግደለው…›› ብሎ እስከ መቀስቀስ ሲወፍፉ ታየ፡፡ ትምህርት ቤት መሄድ ወንጀል ሆኖ ሕፃናት በቦምብ ሲቀጡ ታየ፡፡ ኢትዮጵያ እንድትበተን ወጥመድ ተጠመደባት፡፡ ግን አልበተን አለች፡፡ እርስ በርስ ጭፍን መተጫጨድ ውስጥ እንድትገባ ተደጋግሞ ክብሪት ተጫረባት፤ አልተበገረችም፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ የተወራረሰበትን የዘመናት ጥሪቷን ይዛ፣ ዕለት በዕለት ኑሮ የምትተናፈሰውን መተሳሰብ/መቻቻል የሙጥኝ ይዛ፣ መባላት መጥፊያ መሆኑን በተረዳ ግብታዊ ዕውቀቷ ከግልፍታ የመቆጠብንና ‹‹ፈጣሪ ይህንን ቀን አሳልፎ ደጉን ቀን ያምጣልን›› የመባባል ሀብቷን አስተባብራ መከራዋን እያቀለለች አለፈች፤ መከራን ከማለፍ ጋርም የነገ መልካም ተስፋ ይዛ አዲስ ሕይወት ውስጥ ለመግባት ትርጉም ያለው መፍጨርጨር አካሄደች፡፡ ይህ ጥንካሬ ‹‹ብረቷ ኢትዮጵያ›› ለመባል አያንሳትም፡፡ ኢትዮጵያን ‹‹ብረቷ›› ስል የኢትዮጵያን ሕዝቦች ከመንግሥታዊ አመራራቸውና አውታራቸው ጋር ማለቴ ነው፡፡

የፍሬሕይወትን የሕይወት ጉዞ ለኢትዮጵያ ተምሳሌት አድርጎ ወደ ማየት የወሰደኝ ከፊት ለፊት የሚታይ ከመከራ ወደ ተሻለ ኑሮ የማለፍ ትግል ብቻ አይደለም፡፡ ከጀርባ ያለም የጭቆናና ያለ መሠልጠን ጣጣም ነው፡፡ በኅብረተሰብ ግንኙነት ረገድ በመደብ ደረጃ ገዥነትን ከተገዥነት ጋር አነፃፅሮ ማውራት፣ በግንዛቤ ላይ አሳሳችነት አይፈጥርም፡፡ ብዝበዛና ጭቆናን በገዥና በተገዥ መደብ ለመስፈር መሞከር ግን በጣም አሳሳች ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት ከኢትዮጵያ ርቆ መሄድ አያስፈልገንም፡፡ የምዝበራ አውታር ከላይ እስከ ታች (እስከ ጥበቃ ሠራተኛ) መዋቅሩን ዘርግቶ አገር ሲቆረጥም ብዙ ዓይተናል፡፡ ጭቆናም በመደብ አይቀነበብም፡፡ ከትናንትና ወደ ዛሬ ከጎን ወደ ጎን፣ ከላይ ወደ ታች፣ ከታችም ወደ ላይ እየተወራረሰ ኅብረተሰብን ያዳክራል፡፡ የጨቋኝነት መንሰራፋት (የራስ በራስ ጨቋኝነትን ጨምሮ) ያለ መሠልጠን አንዱ ሁነኛ መገለጫ ነው፡፡ ዛሬ ባለ የተራቀቀ ቴክኖሎጂና የቅንጦት ኑሮ ውስጥ የሚንፈላሰሱ በአስተሳሰብና በልቦና ለአሮጌ ዘመን ቅርብ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዓለም መኖራቸው ይታወቃል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንም 21ኛ ክፍለ ዘመን ውስጥ ብንሆንም፣ ስለሰው አክባሪነታችንና ስለእንግዳ ተቀባይነታችን ብዙ ብናወራም፣ በአሮጌ ዘመን የጭቆና ጭርንቁስ የተሞሉ (ከመወለድ/ከደም ጋር የማይገናኙ ነገሮችን ከመወለድ ጋር ያገናኙ፣ የማይመለኩ ነገሮችን የሚያስመልኩና በሰዎች ላይ ልዩ ልዩ በደሎችን የሚያደርሱ) የባህል ቅሪቶች በውስጣችን አሉ፡፡ በአጠቃላይ የተወራረሰ ኅብረተሰባዊ ገጽታችን ውስጥ የተከታተሩ ትናንሽ ማኅበራዊ ኩሬዎች ይገኛሉ፡፡ ስለማኅበራዊ ኩሬዎች ስንናገር ስለጠበቡ/ስለተከተሩ የኑሮ ትልሞች/ህልሞች፣ የንክኪ ንፋስ ስላልረበሻቸው የእምነት፣ የምግባር፣ የነውርና የኩራት መሥፈሪያዎች፣ ስለ አልተነቃነቁ የዙሪያ ዓለም ግንዛቤዎች መናገራችን ነው፡፡

የፍሬሕይወት ወላጆች የቡትቶ ባህል ሰለባ ናቸው፡፡ በእኔ የጉልምስና ዕድሜ ውስጥ ሙስሊምነትና ኦሮሞነት ተነጣጥሎ የማይታይበትን/ኦሮሚኛ ‹እስላምኛ› ተብሎ የሚጠራበትን/መሐመድ በሚል ስም እየተጠሩ ‹‹አማራ ነኝ/አማርኛ ብቻ ነው የምናገረው›› ብሎ ነገርን ህሊና ለመረዳት የሚቸገርበትን ማኅበራዊ ኩሬ ዓይቻለሁ፡፡ ሰዎች ምን ያህል በየአደግንበት ማኅበራዊ አካባቢ (ባህልና አስተሳሰብ) እንደምንቀረፅ፣ በየአካባቢያችን ምን ያህል አሮጌ ቡትቶ ሊኖር እንደሚችል ለመረዳት የፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላን ከጉሬዛም ማሪያም እስከ አዲስ አበባ እንድናነብ እጋብዛለሁ፡፡ ይህንን መጽሐፍ ያነበበ ሰው፣ ዛሬ ያመሰን ጦረኝነት የ30 ዓመት የብሔርተኛነት ሙሽት አመጣሽ ፖለቲካዊ ጣጣችን የብቻ ውጤት እንዳልሆነ፣ ከእኛው ጋር ሲንኳተት የኖረ የቡትቶ ባህል ውጤትም እንደሆነ በቀላሉ ይገነዘባል፡፡ እናም የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ቁሳቁሳዊ የኑሮ ሁኔታዎችን ከማሻሻል ባሻገር፣ ባህልና ህሊና ነክ የሥልጣኔ ዕርምጃዎችን ይዞ የሚመጣ (ክትርትር ማኅበራዊ ኩሬዎችን የሚያፋስስ፣ የጭቆና ቡትቶዎችንና ትብትቦችን የሚጠራርግ) አብዮት መሆኑ ወሳኝ ነው፡፡

በፅንፈኛ-ዕብሪተኛ ብሔርተኝነትና በኢትዮጵያ የትልቅ አገርነት ትርታ መሀል፣ ሲካሄድ የቆየውን የቅርብ ጊዜ መራር ግብግብ፣ የከሰረ አሮጌ ፖለቲካ በሞት ሞት ውስጥ ሆኖ – የትልቅ አገርነት ነፍሳችን ደግሞ (ከዓለማችን የትስስር ጉዞ ጋር ተዛምዶ) የተፋለሙበት ነበር ተብሎ ቢገለጽ፣ ብዙ ሰዎችን የሚያግባባ ቢሆንም ነገሮችን የተገላቢጦሽ የ‹ተረዳ›ም ግንዛቤ አለ፡፡ ይህ ግንዛቤ በየቦታው ተነስተው የነበሩትን ቡድናዊ ግጭቶችና ውጊያዎች፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን የተጋመድን ነን›› የሚለው ዕሳቤ የተሳሳተ መሆኑን ያሳዩና አካባቢዎች የተለያዩ ፍላጎቶች እንዳሏቸው የመሰከሩ ትርዒቶች አድርጎ ይተረጉማቸዋል፡፡ ‹‹አለመጋመዳችን ተገላልጦ ታየ›› ባዩ አስተሳሰብ ‹‹ዓለማችን ንጠታም ሆኗል/ሊገመት የማይችል እየሆነ ነው ወዘተ›› የሚሉ ምሁራዊ ቃጭሎች ከማንኳኳት በስተቀር፣ ኢአድሏዊ በሆነ ዓይን ድምዳሜውን ከሁሉም የእውነታችን ገጾች ጋር ለማገናዘብና ልክነቱን ለማረጋገጥ ግን አይደፍርም፡፡

የእውነታችንን ገጾች እኛ እናንሳለት፡፡ እዚያም እዚያም ለተነሱ ‹‹ነፃ አውጪ›› ነን ባይ ፅንፈኞች፣ ለምን በነፃ ፍላጎት ሕዝቦች አልተመሙም? የሰሜን ዕዝ ሠራዊት መልቲና ጨከኝ ጥቃት ሲፈጸምበት፣ አገሬ ተነካች ብለው ለምን ሕዝቦቻችን ቱግ አሉ? ያለ አካባቢ ልዩነት፣ ያለ ዕድሜና ያለ ፆታ ልዩነት ሚሊዮኖች ቅሬታዎቻቸውንና ጥያቄዎቻቸውን ወደ ጎን ብለው፣ ለምን ለኢትዮጵያ መቀጠል ሊሞቱ ያለ ጎትጓች ተነቃነቁ? ይህ ንቅናቄ እንደምን የኢትዮጵያ ምድር ግዙፉ እውነታ ሊሆን ቻለ? ሚሊዮኖች ከአራቱም ማዕዘን እየተገማሸሩ በተረባረቡበት ተጋድሏቸው ውስጥ የገነቡት ኅብረ ብሔራዊነት የተንጨፈጨፈበትና የአገር ፍቅር የተንበለበለበት ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ግንባታቸው አጠገብ ሊቆም የሚችል የትኛው ክስተት? ፅንፈኞቹ ቢደመሩ እንኳ ሊፎካከር የሚችል የሕዝብ ፍላጎት መገለጫ ለመሆን ይበቃሉ? ጠመንጃ ተኳሾቹ ቡድኖች በፊትም ሆነ በትልቁ ጦርነት ሒደትና በኋላ ለምን አውሬያዊና ነውረኛ ሥልት ውስጥ ዘቀጡ? የሕዝብ ፍቅር ለማግኘት ብለው ወይስ ከሕዝባዊነትና ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ሁለመናቸውና ዓላማቸው ተለያይቶ? (ተገትሮ የቀረ ፍላጎታቸውን በጥርስ ንክሻና በቡጭሪያ ሁሉ በማሳካት ጣዕረኛ መንፈራፈር ውስጥ ገብተው?) ‹‹አልተገማመድንም›› ባዩ ድምዳሜ በእነዚህ ጥያቄዎች ፊት ቆሞ የእውነተኛነት አቅሙን ለመፈተሽ አልደፈረም፡፡

ዓብይ አህመድና ብልፅግና ፓርቲ በወኔ ሕዝብን አሰከረ አይባል ነገር፣ የሆነው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ሕወሓቶች ሰሜን ዕዝን መንካታቸው ለዓብይ መንግሥት ወርቃማ ሽልማት አመጣለት፡፡ በተወሰነ ደረጃ ተጨራምቶ የነበረውን የሕዝብ ድጋፉን፣ ስለአገር ‹‹ሆ!›› ብሎ በተነሳ የሕዝቦች ማዕበል አደመቀለት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችንና የዓብይን መንግሥት ተራክቦ ያሠላው፣ ለኢትዮጵያ የመረባረብ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ ርብርብ መዋለልም መልፈስፈስም ያልታየበት፣ ሞት ያልተፈራበት፣ የትኛውም ጥቅም ከአገር በታች ውሎ የነበረበት ነበር፡፡ የትኞቹም ጦረኞች እየተረቱ፣ በብዙ የባሩድ እሳቶች ውስጥ የኢትዮጵያውያን አገራዊ ሠልፈኝነት እየጠነከረ ነው የሄደው፡፡ ይህ በብዙ እሳት የተፈተነ ሀቅ ነው — ብ ረ ት ነ ት፡፡ (ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...