Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው  

የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ ባለፀጋ ልጆች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ እነኚህ ልጆች አባታቸው በድንገተኛ ሞት ያልፍና ንብረት ክፍፍል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ቤቱን፣ ገንዘቡን፣ እርሻውን፣ ከብቱን… ተከፋፍለው ያባክኑና አንድ ላም ብቻ ቀረቻቸው፡፡ 

‹‹እንግዲህ ሁሉም ንብረት አልቋል ይቺን ላም እንከፋፈል ይሉና ካለሌላ አደራዳሪ በራሳቸው ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ይሄውም ላሟን ከወገብ በላይና በታች እንከፋፈል የሚል ሆነ፡፡

   ‹‹ክፍፍልም ተደረገ፡፡ የላሟን አካል ከወገብ በታች የደረሰው ሰው ላሚቱ አርግዛ በመውለዷ ምክንያት ወተት እያለበ መጠቀም ጀመረ፡፡ ከወገብ በላይ የደረሰው ደግሞ እኔንም እስኪ ወተት አካፍለኝ በጋራም እንጠቀም ሲል ጠየቀ፡፡

‹‹ይሁንና ባለ ወተቱ ሊሰማው አልቻለም፡፡ ድርሻችንን እንካፈል ብለህ ዕድልህ ባለመስመሩ ምክንያት ከወገብ በላይ የደረሰ በመሆኑ እንጂ የማካፍልህ ነገር የለም ሲል ደረቀ፡፡ ወንድም ያውም እባክህ አሬራ እንኳን ለልጆቼ ላቅምስ ቢለው ሰሚ ሊያገኝ አልቻለም፡፡

‹‹ተበዳይ ግን ሳይናገር ዕርምጃ ከመውሰድ ብሎ፣ ተው ምንጩን እንዳታደርቀው በማለት አሳሰበ፡፡ በተቃራኒው ወገን ግን የሚቀየር ሐሳብ ጠፋ፡፡ በመጨረሻ በነገሩ በጣም ያዘነው ላሟን ከወገብ ከላይ የሚያስተዳዳረው፣ እንግዲያው እኔም ልጆቼ ሥጋ አምሯቸዋል ላሟን አርዳለሁ ብሎ ቢላውን ሳለ፡፡

‹‹በተናገረው መሠረትም አንገቷን በእምነቱ ባርኮ ላሟ ወደ መቃረጥ ገባች፡፡ የተገኘውን ቀሪ ንብረት በፍትሐዊነት መካፈል የተሳነውና አባዝቶ መጠቅም የተሳነው ራስ ወዳዱ የወገብ በታች ሰው ወተቱን ቀርቶ አሬራዋን እንኳን ማካፈል ባለመቻሉ፣ ከእነ አካቴው ላሟን ከእነ ቄንሳዋ አጣትና አረፈ፡፡ ወተት የለ፣ ጥጃ መደርደር ሁሉም ነገር ቀረና አረፈ ይባላል››፡፡

የምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ የሽማግሌውን ተረት እየመሰለ መምጣቱን ሁሉም በአርምሞ የሚከታተለው ይመስለኛል፡፡ ገና ከድህነት ለመውጣት በምትፍገመገም አገር ውስጥ የምንገኝ ሕዝቦች ሆነን፣ ቁጥራችን ከመቶ ሃያ ሚሊዮን የበረከተና ማንነታችንና ባህላችን እጅግ የተሰባጠረ ቢሆንም፣ በታሪክ አጋጣሚ በአንድ ሉዓላዊት ግዛት ተጋምደን የኖርን መሆናችን እየተወናበደ መጥቷል፡፡

ታሪካችን፣ አብሮነታችንም ሆነ ህልውናችን የማይነጣጣልና ዕጣ ፈንታችን የተሰናሰለ መሆኑ ቢታወቅም፣ ብልህና ሆደ ሰፊነት የተላበሰ የፖለቲካ መስተጋብር ጠፍቶ፣ ካልበላሁት ጭሬ ልበትነው ወይም አገርን ላተራምሰው ማለት በርክቶ እየታየ ነው (ከጥንት እስካሁን የአገዛዝ ጥፋትም ሆነ መልካም ተግባር በሕዝብ እየተሳበበ ሲያናቁርም ይታያል)፡፡

በእርግጥም አገራችን የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ‹‹በፈተና የተሞላ›› የሚባል ብቻ ሳይሆን፣ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋና መተላለቅ እያረበበት መሆኑ አባባሉን ያረጋግጣል፡፡ በአንድ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ዋስትና ማጣት፣ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ ሥርዓት አልበኝነቶችና የተለያዩ የንፁኃን መከራና ሥቃዮች እየታዩበት ነው፡፡ በሌላ በኩል የተሳለጠ አገራዊ ምክክርና የሰላም ጥሪ ተደርጎ ሁሉም ወደ መነጋገር ባለመምጣቱ አገራችን የነበራት ተስፋና ዕድል ጭጋግ እየለበሰ ይገኛል፡፡

 አሁን ያለው ደመና በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አገራዊ ለውጥ ከመጣ ወዲህ ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን ከአምስት አሠርት ዓመታት ላላነሰ ወቅት እየተደማማረ የመጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማኅበረ ባህላዊ ለውጥ እንደሚንፀባረቅበት የታሰበው አዲስ ምዕራፍ ሲመጣ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ‹‹ይህ ዓይነት ደመና ይፈጠራል፣ ቢፈጠረም እየተባባሰ ይቀጥላል›› የሚል እምነት ያለ አይመስልም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ለውጥ ሲመጣ ተከትሎ የሚመጣ ፈተናና የፖለቲካ ጥቅም ግጭት መኖሩ አይቀሬ ቢሆንም፣ የጋራ ምክክርና ስምምነት እንዲኖር ከመሥራት ውጪ የኖረውን ውስብስብ ችግር የሚቀርፈው መፍትሔ እንደሌለ ምሁራን ሲናገሩ መቆየታቸውም አይረሳም፡፡

ለውጡ ኢትዮጵያን ወደ ሦስት አሠርት ዓመታት ገደማ ያስተዳደረው ኢሕአዴግ በተሃድሶው ባካሄደው የአመራር መቀያየር ብቻ አልነበረም የመጣው፡፡ ይልቁንም ብዙኃኑ ሕዝብ፣ የተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ሚዲያዎች ጭምር የለውጥ መሻቱን በማቀጣጠላቸውና ዕውን እንዲሆን በመታገላቸውም የተገኘ ነበር፡፡ ያም ሆኖ በሒደቱ መመልከት እንደተቻለው በለውጡ አስፈላጊነት ላይ የተሰባሰቡ ኃይሎች ሁሉ በቀጣዩ ሒደት ላይ ስምምነት ሊኖራቸው አልቻለም፡፡ እንዲያውም በመካረር ውስጥ የሚብሰከሰክ የጥቅም ግጭትና አለመደማመጥ ነው እያረበበ የመጣው ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን ዝንባሌ ለመቀየር ደግሞ አንድ ወገን የለውጡን መንፈስ ነጥቆ ከመታገል አሳታፊና የወል የፖለቲካ መስተጋብርን ለመፍጠር ቢሠራ ለመፍትሔው መቅርብ በተቻለም ነበር፣ ደግሞም ይቻላል፡፡

ቀደም ሲል በአገር ደረጃ የነበሩ የኢኮኖሚውም ሆነ የማኅበራዊ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ለውጡ እንዲመጣ በቀዳሚነት በሕዝብ የተፈለገው የፍትሕና የፖለቲካ ጥያቄዎችን እንዲፈታ ነበር፡፡ በተለይም ሁሉም በሀብቱ እንዲጠቀም፣  የዴሞክራሲ ምኅዳሩና የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ የወደቀው ጫና እንዲነሳ፣ ጠንካራ አገረ መንግሥትና የሕዝቦች አንድነትን እንዲመለስ ሕዝቡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በአመለካከትም ሆነ በዕድሜ ያሉትን ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን እንዲያጠብ የሚረዱ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱም የብዙዎች ምኞት ነበር፡፡

ገና የታለመው የለውጥ መንፈስ በተሟላ ፈለግ መሬት ሳይነካ አለመግባባትና መካረር ተቀሰቀሰ፡፡ ይህም የድሃዋን አገር ከፍተኛ ሀብት ወደ ጦርነትና ዘመቻ ሰደድ እሳት መማገዱ ብቻ ሳይሆን፣ ከታሪክም ባለመማር በየአካባቢው የአንድ አገር ልጆች ጎራ ለይተው ለመፋለምና ለመገዳደል አስገደደ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ለሞትና የአካል መጉደል ተዳረጉ፡፡ የሰው ልጅ በሚሰቀጥጥ አኳኃን ተገድሎ ማየት፣ በጅምላ መቀበር፣ ሕፃናትና ሴቶች ሳይቀሩ ቀላል ለማይባል መከራ እየተዳረጉ፣ ስደቱ፣ መፈናቀሉና ለችግር መዳረጉም ከሚባለው በላይ እየተባባሰ ይገኛል፡፡ መሀሉ ዳር ከመሆኑ ባሻገር፣ አንፃራዊ ሰላም ያለባቸው አዲስ አበባን የመሰሉ ከተሞች በተፈናቃይና በተቸገረ ኢትዮጵያዊ እየተጨናነቁ ይገኛሉ፡፡

 በአገር ደረጃ የተጀመሩ የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በፍትሐዊ ሥርጭት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም እንደ ኢፍትሐዊነት፣ አድሏዊነት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ብልሽቶች እንዲታረሙ የተነሳሳው የሕዝብ ፍላጎት እየሟሸሸ ሄደ፡፡ ለዚህም በሒደት በሕዝብ ቅቡልነት ያለው፣ አካታች፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ መንግሥታዊ ሥርዓት መፍጠርን ሕዝብ በጉጉት ቢጠብቅም ቅድሚያ ለሰላምና አገር መረጋጋት መብሰልሰል ሆነ ውሎ አዳሩ፡፡

 በለውጡ ጅማሮ ሰሞን በአጭር ጊዜ ውስጥ የለውጡ ኃይል በአመለካከት ልዩነት ሰበብ የታሰሩ ዜጎችን መፈታቱ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበራዊ አንቂዎች የሐሳብ ነፃነት እንዲያገኙ፣ የተጋጩና ጫፍና ጫፍ የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገራቸው እንዲገቡና እንዲቀራረቡ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ጉዳያቸው እየመከሩ፣ በልዩነታቸውም በነፃነት እየተንቀሳቀሱ በአገራቸው ጉዳይ ያገባኛል የሚሉበት ጊዜ እንዲመጣ፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር አገርን የዘረፉ እንዲጠየቁና የሕዝብ ሀብትም እንዲመለስ ያሳያቸው ተራማጅ ሙከራዎችም ተደነቃቀፉ፡፡ እንዲያውም አለመግባባቱን የፖለቲካ ቅራኔው ተባብሶ እስሩ፣ መተኳኮሱም ሆነ መወነጃጀሉ በርትቶ የአገር ገጽታ ወደ መጠልሸት ገባ፡፡ ቢያንስ አሁን እስከ መቼ ብሎ መጠየቅ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

ሌላው ቀርቶ ከኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ጋር የነበረውን ፍጥጫ በማስወገድ መቀራረብ መጀመሩ፣ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋርም በሰጥቶ መቀበል መርህና በመስማማት በጋራ ተጠቃሚ ለመሆን የተጀመሩ አዳዲስ ዕርምጃዎች ጥላ አጥልቶባቸው ነው ያሉት፡፡ ከዚያም አልፎ የለውጡ አመራር አኅጉራዊ ሕልሙን በማንፀባረቅ ብቻ ሳይወሰን ለመላው ዓለም ዜጋ ተኮርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ እንደሚከተል አቋሙን ማንፀባረቁ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን፣ ሌላው ዓለምም አጋርነትና ዕውቅና እንዲሰጠው የተነሳሳውን ያህል መቀጠል አለመቻሉ ሁሉንም የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት ማስቆጨት ነበረበት፡፡

በቅርቦቹ ዓመታት እንኳን በአስከፊዎቹ ጦርነትና ግጭቶች የውጭ አገር ሰዎች ሳይቀሩ ሺዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተንገላተዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቃይና ተረጂ ሆነዋል፡፡ የግለሰቦችና ለመረጃ ቅርብ ባልሆኑ ገጠራማ አካባቢዎች የወደመው ሳይቆጠር በግርድፍ ግምት 1.5 ትሪሊዮን ብር የሚገመት የአገር ሀብት ወድሟል፣ ባክኗል፡፡ ያንኑ ያህል ለጦር መሣሪያና ለጦርነት ሎጂስቲክስ የወጣ ወጪ መኖሩም አይቀሬ ነው፡፡ ይህም ለስንት ድህነት መቀነሻ ተግባርና የተጀመሩ ልማቶች በእጥፍ እጥፍ ለማስቀጠል መዋል ሲገባው ተደፋፍቷል፡፡ ይህ አስከፊ ሁኔታ ደግሞ መንግሥትና ተፋላሚዎቹን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ፖለቲከኛና ሕዝቡን ካላስቆጨ ማንን ሊያሳምም ይችላል፡፡ ዝምታውስ አገር እንደ ላሟ እስክትታረድ ነው? ወይስ…? አያስብልም፡፡

በፖለቲካው መቃወስ ምክንያት ብዙዎች እንደሚናገሩት በርከት ባሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰላምም ሆነ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ዋስትናም ጠፍቷል፡፡ እንደ ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት (ዓለም አቀፍ ሁኔታውም የራሱ ጫና እንዳሳደረ ሳይካድ)፣ ተረጂነትና ተፈናቃይነት ተባብሰዋል፡፡ ከሁሉ በላይ የሕዝቦች አብሮ የመኖር ባህል ተሟጦና ተሸርሽሮ ጫፍ ላይ የደረሰው ቀደም ባሉት ዓመታት በተነዙት ትርክቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በተሳከሩ ፖለቲከኞች ሴራና በባዕዳን ተንኮልና ጫና ነው፡፡ ይህንን መሰነካከልና የአገር ግንባታ እንቅፋት የሆነ አካሄድ ከዕርቅና መነጋጋር ብሎም ብሔራዊ የሰላም ጥሪ ውጭ አስተማማኝ በሆነ መንገድ መፍታትስ እንዴት ይቻላል ነው ጥያቄው፡፡

በመሠረቱ ያረበበውን አስቸጋሪና አስከፊ ሁኔታ በማስወገድ አገር በተረጋጋና ዋስትና ባለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንድትቀጥል የለውጥ ኃይሉም ሆነ መንግሥት ብቻ አልነበረም ኃላፊነት ያለበት፡፡ እንደ ሕዝብም ከዛገውና የተጋነነው አስተሳሰብ ተላቆ፣ በሕግና ሥርዓት እየተመሩ መኖር በተገባ ነበር፡፡

ፖለቲከኞቻችንና የማኅበራዊ አንቂዎች የዘውግ ትርክትና የብሔር ፉክክርን፣ በተለይም ከመጠራጠርና ከማጋጋል ይልቅ አብሮነትን፣ የግልጽነትና ተጠያቂነትን ብሎም የፍትሐዊነት አጀንዳን ማራመድ መጀመር አለባቸው፡፡ የሰላም ጥሪና ሀቀኛ የፖለቲካ ድርድር የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የትናንቱንና የነገውን ሃልዮታችንን እንደሚያቃና አምነው ከአንጀት መታገልና ጫና ማሳደርም አለባቸው፡፡

ከሁሉ በላይ ሁሉም የራሱን ጥያቄና ጥቅም ብቻ በማቀንቀን፣ በሌላው ጫማ ውስጥ ሳይቆም ለራስ ጥቅም ብቻ ከመስገብገብ መላቀቅ ይኖርበታል፡፡ ከተወናበደና የተንሻፈፈ ትርክት በመውጣት አብሮ ሊያኖር የሚችል የወል ሕግና ሥርዓት፣ አስተሳሰብና የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር መፍጠሩም ነው ከአረንቋው የሚያወጣው፡፡ በመግባባት መንፈስ ኢመደበኛ ኃይሎችና በሁሉም አካባቢ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ሁሉ የጠላትነት ፍረጃቸውን አንስተውም/ተነስቶላቸውም ለሕዝብ ደኅንነትና የአገር ሉዓላዊነት መረጋገጥ ከልብ እንዲነሱ ሚዲያዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ሁሉ መስዋዕት ከፍለውም ቢሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡም ግድ ይላል፡፡ ዓለም እንዳሁኑ ብንተላለቅም ቆሞ ከማየት ውጪ የሚያደርገው ያለ አይመስልም፡፡

እንደ አገር የመጣንበትን አስቸጋሪና ፈታኝ ጊዜ ለመሻገር መንግሥትም ፈራ ተባ ሳይባል ለአገር ሰላምና ደኅንነት፣ ለፖለቲከኞች መነጋገርና መግባባት፣ ለሕዝቦች አብሮነት፣ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ብሎም ፍቅርና አንድነት አቅሙን አሟጦ ከመነሳትና መትጋት ውጪ አማራጭ ሊኖረው አይገባም፡፡

 ጦርነትና የኃይል ዕርምጃ ከጥንት እስካሁን እንደ አገር ብለነው፣ ብለነው ጥቁር ጠባሳና ቂም እያዋለደ፣ የሰው ኃይልና ሀብትን እያወደመ ከማለፍ ውጪ ያስገኘልን አንዳች ፋይዳ የለም ባዮች መበርከት አለባቸው፡፡ እናም አሁን እንኳን በቃ ብሎ፣ በይቅርታና ሆደ ሰፊነት መፍትሔ መፈለጉ ይበጃል የሚሉ ሰዎች ቢደመጡ ክፋት የለውም፣ ብልህነትም ነው፡፡

አገራችን ደሃም ብትሆን ሰፊና ባለፀጋ ነች፡፡ ገና ተሠርቶባቸው አይደለም ተጠንተውና ተገንብተው ያላለቁ ዕምቅ አቅሞች ባለቤትነቷም ተደጋግሞ የተነገረ ነው፡፡ የሕዝቡ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ንቃተ ህሊናም ዝቅተኛ የሚባል አይመስለኝም፡፡ ፖለቲከኞቻችንም ቢሆኑ አገር ከመምራት አንስቶ፣ በሰላማዊ ትግል፣ በጫካና ድባቴ ወይም ሽሽትና ፍርኃት ውስጥ እስካሉት ድረስ ዕልፍ አዕላፍ ናቸው፡፡

ዋናው መሰናክላችን ግን የተወናበደ ትርክትና የጥላቻው እሽክርክሪት አለመቋረጡ ነው፡፡ እናም የመቃቃርና ተቀራርቦ ያለመነጋገር ሰንኮፍን በቁርጠኝነት ነቅሎ፣ ከስግብግብነት ወጥቶ መፍትሔ መፈለግ ይበጃል፡፡ በመጃጃል የአባታቸውን ውርስና ርስት አወዳድመው ወላድ ላማቸውን አርደው እንደበሉትና ለፍፁም ድህነት እንደተዳረጉት ወንድማማቾች እንዳንሆንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ወሳኝ የሆኑ አገር የማቆም መሠረቶች (በተለይ ዕርቅ፣ ሰላምና ደኅንነት) ቀድመው ዕውን እንዲሆን ፖለቲከኞችና በሕዝብ የተሠለፉ ሁሉም ኃይሎች ከፍ ያለ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ ሕዝቡም በወግና ሥርዓት ያውም በነፃነት የሚደመጥበትና የሚወሰንበት መንገድ ሊመቻችለት ግድ ይላል፡፡ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩን ፅንፈኞች፣ ገታራ የዩቲዩብ ፖለቲካ ነጋዴዎች፣ አክራሪ የብሔርና የሃይማኖት ፍላፃዎች፣ አድር ባዮችና እንደ እስስት ተለዋዋጭ ልሂቃን፣ አፍራሽ ኃይሎች ብሎም ሆደ ሰፊ ያልሆኑ የመንግሥት ኃይሎች እያደፈረሱት እንዳይቀጠሉም ብርቱ ትግል መደረግ አለበት፡፡ 

የፖለቲካ ችግሮችን ሁሉ በፀጥታ ኃይልና በመሣሪያ ብቻ ለመፍታት መሞከርም ተደጋግሞ እንደታየው፣ ኪሳራው ከባድና ውስብስብ ነው፡፡ እንኳንስ ፖለቲከኞች በአንድ አገር ላይ ያሉ ሕዝቦች ተደማምጠውና ከመንግሥትም ጋር ተነጋግረው በሰላምና በሥርዓት መዋል ማደር ካልቻሉ ፍፃሜው ውንብድናና ጥፋት ነው፡፡ ስለሆነም የትኛውንም የውስጥ ፖለቲካዊና የደኅንነት ችግር ለመፍታት የሚያስፈልገው  ውጫዊ  ሰበብ መደርደር፣ ውዥንብር ወይም የፖለቲካ ሽኩቻ ሳይሆን ተደማምጦና ተግባብቶ በጋራ ሕግና ሥርዓት ማደር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዕርቅና የሰላም ጥሪ ቢጀመር ይበጃል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዘግይቶ ወይም በድሮ በሬ ለማረስ በመሞከር አገረ መንግሥቱ ተዳክሞ ችግር በችግር ላይ እየተከመረ ከቀጠለ ሕዝብ እንዲንገሸገሽና እንዲቆጣ ይገፋል፡፡ የአገርንም ጥቅምና ህልውና ለአደጋ ማጋለጥ ያስከትላል፡፡ በተለይ  በአለመግባባቱ የሚፈጠረውን ትርምስ ተከትለን፣ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አደፍርሰን፣ የዓረቡን ዓለም ቀደምት አገሮች የማንኮታኮት አብዮት (ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ልብ ይሏል) ወይም የአንዳንድ አፍሪካውያንን ቀውስ (ሱዳንና የምዕራብ አፍሪካዎቹ እንኩቶዎች ዓይነት) በኢትዮጵያ ዕውን እናደርጋለን››  የሚሉ ተስፈኞች አገራችንን እንዲንቦጫረቁባት ያደርጋል፡፡ ውርደት ይሏል ይህ ነውና ሁሉም ይጠንቀቅ፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...