Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

 የኤሌክትሪክ አገልግሎትና የቴሌኮም ኩባንያዎች ቫት እንዳይጣልባቸው ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የእምነት ተቋማት ቫት እንዲከፍሉ ይደረጋል ተብሏል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የቴሌኮም ኩባንያዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እንዳይጣልባቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ጥያቄው የቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው የውይይት መድረክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ሳፋሪ ኮምና የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ወክለው በተገኙ ተሳታፊዎች ነው፡፡ 

ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የፀደቀውና ከዚህ ቀደም ሁለቴ ማሻሻያ የተደረገበት የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን በአዲስ ለመተካት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተወያየበት የሚገኘው የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣል ይደነግጋል፡፡ 

‹‹በድረ ገጽ፣ በኢንተርኔት፣ በፖርታል፣ በጌትዌይ፣ በመደብር (ስቶር)፣ በገበያ ቦታ ወይም በሌላ ማንኛውም አቅራቢ ከሩቅ ሆኖ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወይም በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚታዘዙ ዕቃዎችን፣ በሌላ ሰው አማካይነት ለሦስተኛ ሰው ግብይት ሲያከናውን የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበሰብ፤›› ይላል ረቂቁ፡፡

የአዋጁን ድንጋጌ አስመልክቶም የኢትዮ ቴሌኮም የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ታረቀኝ፣ ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰጣቸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ ታክስ ለመጣል መታቀዱ አገሪቱ በጀመረችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ወደ ዲጂታል አገልግሎት ለመግባት ለሚደረገው ሥራ፣ ‹‹አንዳንድ አገልግሎቶችን ያለ ክፍያ ጭምር እየሰጠን ባለንበት ሁኔታ ታክሱ መጣሉ ተገቢ ነው ወይ?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ታክሱን መጣል ካስፈለገም ኅብረተሰቡ አገልግሎቶችን መጠቀም ከተለማመደ በኋላ ሊሆን ሲገባ አሁን በአዋጅ መደንገጉ ምክንያታዊ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

አክለውም የኢትዮጵያን ሲም ካርድ በውጭ አገር መጠቀም የሚያስችለው አገልግሎት የሚሰጠው በኦፕሬተሮች መካከል በሚኖር ስምምነት መሆኑን በመግለጽ፣ አገልግሎቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጥ ስለሆነ ታክስ እንዲከፈልበት መደንገጉ በምን አግባብ እንደሆነ ጠይቀዋል። ‹‹ውጭ አገር ሄዶ ሲጠቀም የምንከፍለው በውጭ ምንዛሪ ነው። ስለዚህ በዶላር እየከፈልን ባለበት ሁኔታ ተጨማሪ ታክስ መቁረጡ ተደራራቢ ይሆናል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል። 

ሌላው ኢትዮ ቴሌኮምን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ ለማ ተሰማ በበኩላቸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር የሚሰጣቸው የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን የሚያመላክቱ የአዋጁ ድንጋጌዎች መኖራቸውን በመግለጽ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ 

የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን የገለጹት የሳፋሪኮም ተወካይ፣ በዚህ ሁኔታ በእነዚህ አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉ ዘርፉን እንዳያድግ ያደርገዋል በማለት የሌሎችን አገሮች ተሞክሮ ጠቅሰዋል፡፡ 

ሁሉንም ግብይቶች ከታክስ ነፃ እናድርግ ማለት አይቻልም ያሉት የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ፣ በቴሌ ብር የሚሰጠው አገልግሎት የፋይናንስ እንጂ የቴሌኮሙዩኒኬሽን እንዳልሆነ ገልጸዋል። ‹‹በቴሌ ብርም ሆነ በሌላ ማንኛውም የዲጂታል አገልግሎት ገንዘብ ማስተላለፍ ከታክስ ነፃ ተደርጓል፤›› ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ የማመቻቸት ሥራውን የሚያከናውኑ እንደ ኢትስዊች ያሉ ተቋማት ግን የክፍያ ሥርዓት አገልግሎት ተብለው የሚታወቁ በመሆናቸው ከታክስ ነፃ መሆን እንደሌለባቸው አስረድተዋል። 

አክለውም መንግሥት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ቢሆንም፣ ይህንን ሊያስኬድበት የሚያስችል ገንዘብ ከታክስ መሰብሰብ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሲም ካርድ አውጥቶ በውጭ አገሮች ሲጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ታክስ ሊከፈል እንደሚገባ በሚደነግገው አንቀጽ ላይ ምላሻቸውን ሲሰጡም፣ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመመልከት የተደረሰበት ውሳኔ እንደሆነ አብራርተዋል። 

‹‹የኢትዮ ቴሌኮም ወይም የሳፋሪኮም ሲም ካርድ በመያዝ በውጭ አገሮች አገልግሎት የሚያገኝ ሰው ታክሱን መክፈል ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ከሌላ አገር ሲም ካርድ ይዞ በመምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት የሚያገኝ ሰውም በተመሳሳይ ካርዱን ባወጣበት አገር ይከፍላል፤›› ብለዋል። 

ከቤተ እምነቶች የሚከራይዩቸውን ቤቶች አስመልክቶ የኢትዮ ቴሌኮም የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሮቤል፣ ቤተ እምነቶቹ የንግድ ፈቃድ ስለሌላቸው ሥርዓቱን ተከትሎ ለመሥራት መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው ለቤተ እምነቶቹ የሚከፍለው ቀላል የሚባል ባለመሆኑ ሕጋዊ አሠራር እንዲከተሉ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ቤተ እምነቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ አለመደረጋቸውን የገለጹት በገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች መምርያ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ተወዳጅ መሐመድ፣ ከታክሱ ነፃ የሚደረጉት ከእምነት አገልግሎቱ ጋር በቀጥታ የሚገናኙት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሕንፃ ገንብተው ሱቅ የሚያከራዩ ቤተ እምነቶች ከታክሱ ነፃ እንደማይሆኑ፣ የታክስ ምዝገባ መሥፈርቶችን አሟልተው ያልተመዘገቡ ቤተ እምነቶች ካሉም እንደሚታይ ጠቁመዋል፡፡ 

አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጪ ለመቀነስ በማሰብ ከታክሱ ነፃ ተደርገው የነበሩ የኤሌክትሪክና የውኃ ፍጆታ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ ከሚወሰን በታች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚጣልባቸው በረቂቁ ተመልክቷል።

የረቂቁን ድንጋጌ አስመልክቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በመወከል የተገኙት አቶ አበበ ተስፋ፣ ዘርፉ ገና በማደግ ላይ ያለና ተደራሽነቱም ዝቅተኛ መሆኑን፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ስለሆነ ጫና እንደሚፈጠርበት ገልጸዋል፡፡ አክለውም በዝቅተኛ የማምረቻ መስክ የተሠማሩ አምራቾችም ይጎዳሉ ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በውኃና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የተጣለው ታክስ መሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ የተጣለ በመሆኑ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሊደረጉ እንደሚገባ አቶ ሮቤል አሳስበዋል፡፡

በዚህ የረቂቁ ክፍል ላይ ማብራሪያቸውን የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በኤሌኬትሪክና በውኃ ላይ የሚጣለው ታክስ ሁሉንም የሚመለከት አለመሆኑን ገልጸው፣ ሚኒስቴሩ ወደፊት በሚያወጣው መመርያ ከሚወሰነው ዝቅተኛ ኪሎ ዋት በላይ የሚጠቀሙት ላይ እንደሚጣል ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አገሪቱ የምትሰበስበው ታክስ ለጠቅላላ ምርቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ መንግሥት በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት ይህን ለማስተካከል እንደሚሠራ ገልጸዋል። ሆኖም ይህንን ለማሳካት የታክስ ፖሊሲዎችን ማስተካከል፣ አዳዲስ የታክስ ፖሊሲዎችን መቅረፅ፣ እንዲሁም የታክስ አስተዳደሩን ማዘመን እንደሚገባና ለዚህም ረቂቅ አዋጁ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

‹‹በጥናት ያገኘነው የተጨማሪ እሴት ታክስ የክፍያ ምጣኔውን መጨመር ነበር፤›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ ‹‹ነገር ግን አላስፈላጊ በሆነ ምክንያት ከታክስ ነፃ የሆኑት ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ወስነናል፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች