Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመብት ተሟጋቾች በመንግሥት ጫና ምክንያት የሲቪል ምኅዳሩ እየጠበበ ነው ሲሉ ወቀሳ አቀረቡ

የመብት ተሟጋቾች በመንግሥት ጫና ምክንያት የሲቪል ምኅዳሩ እየጠበበ ነው ሲሉ ወቀሳ አቀረቡ

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 12 የሲቪክ ማኅብረሰብ ድርጅቶች የበረታ የመንግሥት ጫና የሰቪክ ምኅዳሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠበበው ነው ሲሉ ወቀሳ አቀረቡ፡፡

በሰብዓዊ መብቶች ላይ አተኩረው የሚሠሩና አገር በቀል የሰብዓዊ መብቶች በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እንዲሻሻል የበኩላቸውን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰው፣ አሁንም አስተዋጽኦ ለማድረግ ቢሞክሩም መንግሥትና የፀጥታ ኃይሉ በሚያሳድሩት ጫና ለመሥራት ተቸግረናል ሲሉ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

መግለጫውን በጋራ ያወጡት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት፣ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ ሴታዊት፣ ትምራን፣ ሚዛን ወጣት የሕግ ባለሙያዎች ማዕከል፣ ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል ይሰኛሉ፡፡

ከመንግሥት በኩል ተደጋጋሚ ጥቃትና ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ስለመሆኑ የጠቆሙት ድርጅቶች አንዳንድ ጊዜም ጫናዎች በሚወጡ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና አሠራሮች ላይ ጭምር ጎልተው እንደሚታዩ አስታውቀው፣ በእነዚህ ጥቃቶችና ከፍተኛ ጫናዎች ምክንያት የሲቪል ምኅዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጠበበ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመንግሥት በኩል እየተፈጸሙ ያሉት ክልከላዎች፣ ጫናዎችና ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ ከመምጣት ይልቅ እየጨመሩ መሆናቸው በመስኩ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች እጅግ አሳሳቢ እየሆኑ ስለመምጣታቸው፣ የጫናዎቹ ዓይነትና ባህሪ መጠናቸውን በመቀያየር ተስፋ ታይቶበት የነበረው የሲቪክ ምኅዳር ዳግም ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ  ስለመመለሱ አመላካች ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቶቹ በጋራ መግለጫቸው በሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ላይ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት እየደረሰ ነው ያሉትን ሁሉን ዓይነት ጥቃትና ጫና ሲያብራሩ፣ በአንዳንድ የድርጅቶቻችን የሥራ ኃላፊዎች፣ በቦርድ አመራሮችና በሠራተኞች ላይ ከፍተኛ የሆኑ ማስፈራሪያዎች፣ ዛቻዎችና ጫናዎች መፈጸማቸውናና አሁንም እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችና ተቋማት ውስጥ በሚሠሩ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ በተደጋጋሚ ሕገወጥና የዘፈቀደ እስራት መፈጸሙን፣ ለዚህም የኢሰመጉ የምርመራ ሠራተኞች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት መድረሱን እንደ አንድ ተጠቃሽ ምሰሌ ስለመሆኑ በመግለጫው አስቀምጠዋል፡፡ ለአብነት የድርጅቱ አራት የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ባለሙያዎች ላይ ታኅሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ተፈጸመ ያሉትን ‹‹ሕገወጥ እስር›› ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በሚዲያ ተቋማትም ጭምር ንብረቶችን የመውሰድ ድርጊት አሳሳቢ ክስተት መሆኑን፣ በተደጋጋሚ የሚፈጸሙት የቢሮ ሰበራዎችና ንብረቶችን የመውሰድ ድርጊት እንደ ተራ ወንጀል መቆጠሩን፣ እንዲህ ያሉትን የጥቃት ዕርምጃዎችና የክስተቶቹ መደጋገም ሆን ተብሎ በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ላይ የተፈጸመ ድርጊት አድርገው እንደሚውሰዱት ተገልጿል፡፡

የድርጅቶቹ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ከዝርፊያዎቹ ጋር በተያያዘ አጥፊዎች አለመታወቃቸውና የተወሰዱትም ንብረቶች አለመመለሳቸው፣ መንግሥት በሴክተሩ ላይ ላሉ ተቋማት በቂ ጥበቃ እያደረገ አለመሆኑን አመላካች ስለመሆኑ በመግለጫው ተገልጿል፡፡

የጋራ መግለጫ ላይ የተካተቱትን የተወሰኑ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ በሥራቸው ምክንያት ከአገር ውጪ በሚያደርጓቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የሥራ ጉዞዎች፣ ስብሰባዎችና ሥልጠናዎች በሚሄዱበትና በሚመለሱበት ወቅት በመንግሥት የፀጥታ አካላት የሚደርስባቸው ከፍተኛ የሆነ ማንገላታት፣ ጥብቅ ፍተሻ፣ ዛቻና ማስፈራራት አሳሳቢ እየሆነ ስለመምጣቱ በመግጫው ተጠቁሟል፡፡ የፀጥታ አካላት የሚወስዷቸው ያልተገቡ ዕርምጃዎች፣  የሰላም ጥሪ የፈረሙ ሲቪል ማኅበራት ላይ የተፈጸመ ግልጽ የሆነ ዛቻ፣ ማስፈራሪያዎችና ጫናዎች የሲቪክ ምኅዳሩን ክፉኛ እየጎዱት መጥተዋል ይላል መግለጫው፡፡

ድርጅቶቻችን በሚጠሯቸው ስብሰባዎችና ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩት ከዕገዳ ጀምሮ የተለያዩ ማስተጓጎሎች፣ ሥራን በነፃነት ለማከናወን እንቅፋቶች ስለመሆናቸው በመግለጫው አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቶቹ በጋራ መግለጫቸው ሁሉም የመንግሥት አካላት የተጠቀሱትን ሕገወጥ ድርጊቶች የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ለሲቪል ማኅበራት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግና የሕግ የበላይነትን እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት፣ በነፃነት ከሥጋት ውጭ ሆነው ሥራቸውን መሥራት እንዲችሉ ምቹ የሆኑ የሕግና የፖሊስ ማዕቀፎችን በመዘርጋት፣ የሲቪል ምኅዳሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያስቆም አክለው ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...