Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዓመታዊ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ለሚያደርጉ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ሊሰጥ ነው

ዓመታዊ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ለሚያደርጉ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ሊሰጥ ነው

ቀን:

ለተስማሚነት ምዘና ተቋማት የላቀ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት (አክሬዲቴሽን) የሚሰጠው የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት፣ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የተሽከርካሪ ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ለሚያደርጉ ተቋማት የአክሬዲቴሽን ሰርተፊኬት ለመስጠት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ማረጋገጫ የሚሰጡ ተቋማትን የሚመራው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ አክሬዲቴሽኑን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

አቶ ወንድወሰን ከሚኒስቴሩ ጋር የተደረጉ ውይይቶችን ወደፊት የማስኬድ ክፍተቶች ቢኖሩም፣ ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ ለማስቀጠልና ተግባራዊ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡

የተስማሚነት ምዘና የሚሠሩ ተቋማት ራሳቸው ምዘናውን ለመሥራት ብቁ ናቸው ወይ? የሚለውን በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ አካሄድ ለመፈተሽ አገልግሎቱ እንደ ሦስተኛ ወገን ሆኖ እንደሚሠራ፣ በሥራ ሒደትም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ፈቃድ ለማደስ መሟላት አለባቸው ብሎ ካስቀመጣቸው መሥፈርቶች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች እንደሚካተቱ ገልጸዋል፡፡

የተሽከርካሪ ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ የሚሰጡ ተቋማት ፈቃድ ሲያድሱ ተቆጣጣሪው አካል እንደ ሁኔታዎች አቻችሎ ሊያልፋቸው የሚችሉ መሥፈርቶች እንደሚኖሩ፣ መሥፈርቶችን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ በማስታወስም፣ በተቋማቸው በኩል የሚሰጠው የአክሬዲቴሽን ሰርተፊኬት አገልግሎት ምንም አቻችሎ የሚያልፈው ነጥብ እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡

በመሥሪያ ቤታቸው በኩል አክሬዲቴሽን የተሰጠው ተቋም በማንኛውም ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በገምጋሚዎች ሊፈተሽ እንደሚችል፣ በ2017 ዓ.ም. ከሚኒስቴሩ ጋር የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ የሚሰጡ ተቋማት እንዲዘጋጁ እንደሚደረግና በአክሬዲቴሽን ሰርተፊኬት አግባብነት ላይ ግንዛቤ እንደሚሰጥም አክለዋል፡፡

ሰዎች ስለጥራት ያላቸው ግንዛቤ እየጨመረ ሲመጣ በሚያገኟቸው አገልግሎቶች ይበልጥ መተማመን ሲፈልጉ አክሬዲቴሽን ሰርተፊኬት መጠየቅ እንደሚጀምሩ በማስታወስም፣ በአሁኑ ጊዜ ኤምባሲዎች የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ለማድረግ ‹የአክሬዲቴሽን ሰርተፊኬት ያለው› የሚል መሥፈርት ማስቀመጥ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ብዙ ተለፍቶባቸው የተማሩ፣ ለአገርና ለቤተሰብ የሚጠቅሙ ወገኖችን በየዕለቱ በትራፊክ አደጋ እያጣን ነው ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ አክሬዲቴሽን በያዙ ተቋማት ተሽከርካሪን ማስመርመር አደጋውን ሙሉ ለሙሉ ባይቀርፈውም፣ ችግሩን ሊያቃልል እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተሽከርካሪ አገልግሎት ዘርፉን ወደ አክሬዲቴሽን ሥርዓት ለማምጣት ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ፣ አገልግሎቱ በፈቃደኝነት ላይ የተሠረተ የላቦራቶሪ ፍተሻ፣ የኢንስፔክሽን፣ የሰርተፍኬሽንና የካሊብሬሽን ሥራዎች በትክክል ስለመተግበራቸው የቴክኒክ ብቃት ማስረጃ የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡

አገልግሎቱ ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ የአክሬዲቴሽን ቀን አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክም፣ የኢትዮጵያ ሚቲሪዮሎጂ ኢንስቲትዩት ሐዋሳ ቅርንጫፍ፣ የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል፣ የበለስ አግሪፉድ ላቦራቶሪ ፒኤልሲን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ አምስት ተቋማት ለተለያዩ አገልግሎቶቻቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የአክሬዲቴሽን ሰርተፊኬት፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተቀብለዋል፡፡

በአፍሪካ የአክሬዲቴሽን ትብብርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሕክምና ላቦራቶሪ፣ በፍተሻ ላቦራቶሪ፣ በምርት ሰርተፊኬሽንና በኢንስፔክሽን ወሰኖች የኢትዮጵያ አየር መንገድና የህንድ ሰርተፊኬሽን ተቋምን ጨምሮ ለበርካታ ድርጅቶች የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ተደራሽ ማድረጉ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...