Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበቅዱስ ያሬድ ስም ሊገነባ የታሰበው ሁለገብ የልህቀት ማዕከል

በቅዱስ ያሬድ ስም ሊገነባ የታሰበው ሁለገብ የልህቀት ማዕከል

ቀን:

‹‹ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ራስ

ከቤቶቨን ናላ ከሞዛርት መንፈስ

ከሾፐን ትካዜ ከያሬድ ልቦና

መዓዛ የሞላብሽ ብስጭት ቃና

ረቂቋ ድምፅ ሆይ ውቢቷ ሙዚቃ

ውብ እንደ ፀሓይ ንፅህት እንደ ጨረቃ…››

ብለው ለሙዚቃ የተቀኙላት ከበደ ሚካኤል ናቸው፡፡ የቅኔ አዝመራ በተሰኘው የግጥም መድበላቸው የሙዚቃ ፈጣሪዎችን አወድሰዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድን ከትልልቆቹ የሙዚቃ ሰዎች ሠፈር አውለውታል፡፡ ስሙንም ከፍ አድርገው አውስተውታል፡፡

በቅዱስ ያሬድ ስም ሊገነባ የታሰበው ሁለገብ የልህቀት ማዕከል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ቅዱስ ያሬድ በሠዓሊው ምናብ

ቅዱስ ያሬድ ዓለም ያጨበጨበላቸው እነ ቤትሆቨን፣ ሞዛርትና ሌሎችም ከመፈጠራቸው ሺሕ ዓመት ቀድሞ በ6ኛው ክፍለ ዘመን ረቂቋን ዜማ ከነፍስ ያዋሃደ የሙዚቃ ኖታን ለመንፈስ ስንቅ ያበቀለ ነው፡፡ መንፈስን በሐሴት እያጠመቁ፣ ሩህን ከአጥናፍ ወዲያ እያመጠቁ ባሳብ ደም ሥር እየዘለቁ ሕይወት ከሚዘሩና ዕድሜ ከሚቀጥሉ ዜማዎች ውስጥ ቅዱስ ያሬድ አለ፡፡

ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ የሥነ ዜማ ታሪክ ውስጥ በጥንታዊነቱና በቀዳሚነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሊቅ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም.  በአክሱም ነበር የተወለደው፡፡

በዓለም በረቀቀ ሥነ ዜማ ድርሰት ታሪክ ውስጥ ድምፅን በኖታ በመጻፍ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንድትሆን ከማድረግ ባሻገር የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ወጥ ድርሰቶችን በመጻፍ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ፋና ወጊ ነው፡፡

ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ መዋስዕት ዝማሬ ምዕራፍ፣ አንቀጸ ብርሃን በቅዱስ ያሬድ የተደረሱ/የተጻፉ የዜማ መጽሐፍት ናቸው፡፡ እነዚህንም ታላላቅ ድርሰቶቹን በሦስት የዜማ ሥልቶች ማለትም በግዕዝ፣ በዕዝልና በእራራይ ቀምሯቸዋል፡፡

‹‹የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ›› በሚል ጽሑፋቸው ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌሰር) እንደጠቀሱት፣ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ በድርሰቶቹ የሚታዩት የቃላት አመራረጥ፣ የዓረፍተ ነገር አወቃቀር፣ የሚስጥርና የዘይቤ አገላለጥ ቅዱስ ያሬድ ከፍተኛ የሥነ ጽሑፍ ተሰጥኦ እንደነበረው ያሳያል፡፡ ‹‹ቅዱስ ያሬድን ብቸኛ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ መሥራች አድርጎ ለማየት በቂ ምክንያት አለ፡፡ እንዲያውም የኢትጵያ ሥነ ጽሑፍ መሥራች ልንለው ይገባል፤›› በማለት ያሰምሩበታል፡፡

በቅዱስ ያሬድ ስም ሊገነባ የታሰበው ሁለገብ የልህቀት ማዕከል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የምሥራቅ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ድሜጥሮስ

የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ

ይህን ታላቅ ሊቅ የሚያስታውሱ ልዩ ልዩ መታሰቢያዎች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በመንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም በግል ድርጅቶች መሰየማቸው፣ መንገድም በስሙ እንዳለ ይታወቃል፡፡

ከነዚህም መካከል በሰሜን ጎንደር፣ በበየዳ ወረዳ በሳብራ ቀበሌ የሚገኘው የደብረ ሐዊ የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ተጠቃሽ ነው፡፡ ገዳሙ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የልህቀት ማዕከል የሚሆን የአብነት ትምህርት ቤትና ሙዚየም ለመገንባት ፕሮጀክት ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

ጥንታዊው የአብነት ትምህርት ቤት፣ ሁሉንም መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የያዘና ከሁለት ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ ዘመናዊ ሆኖ የሚታነፅ ነው፡፡ እንደ አገርም ለመንፈሳዊ ትምህርት የልህቀት ማዕከል ይሆን ዘንድም ታቅዷል፡፡

በተጨማሪም የቅዱስ ያሬድን ሥራዎች የሚይዝ ዘመናዊ ሙዚየምና ቤተ ክርስቲያን በማነፅ፣ ታሪኩን ጠብቆ ከመላው ዓለምና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚመጡ ጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ ዓላማን ያነገበ ነው፡፡ ሥፍራውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ተወጥኗል፡፡

የምሥራቅ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ እንደተናገሩት፣ ‹‹ኢትዮጵያ እግዚአብሔር የባረካትና በእግዚአብሔር አምልኮ ውስጥ የምትጓዝ አገር ናት፡፡ ቅዱስ ያሬድም የዚህ ምልክት ነው፡፡››

‹‹ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ ቁልፍ መንፈሳዊ አባት ነው፡፡ የሊቁንና የቅዱሱን ዜማ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ዓለም ሰምተው የሚጠግቡት አይደለም፡፡

ቅዱስ ያሬድ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ ‹‹ነገር ግን እንደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ እንደ አገር ካልተዘመረላቸው፣ ካልተነገረላቸውና የሚገባቸውን ልክ ያህል ክብር ካላገኙ መካከል አንዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ምስክር የሚሆነው በአብያተ ክርስቲያን ደረጃ እንኳ በስሙ የታነፁ ጥቂት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከአገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ብርቅ ከሆኑና በዘመናት መካከል የማይደበዝዝ ሥራ ከሠሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ቅዱስ ያሬድ ከፍ ያለ ቦታ የሚይዝ እንደሆነ ያወሱት ሊቀ ጳጳሱ፣ ‹‹በጥዑመ ዜማ እግዚአብሔርን እያመሰገነና ሕዝቡንም የእግዚአብሔር እንዲሆን ያደረገው አባት ዕውቅና እንዲያገኝ፣ ሥራው እንዲናኝና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን በስሙ የተጀመሩና የሚታነፁ ፕሮጀክቶችን ለፍጻሜ መብቃት ይኖርባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡  

ቅዱስ ያሬድን ከመዘከር ባለፈ እንደ አገር ትልቅ ትርጉም ያለውን ፕሮጀክት ወደ ከፍታ በማውጣት በታሪክና በትውልድ እንዲታወስ በማድረግ በኩል ሁሉም አሻራውን  ሊያኖር እንደሚገባ አክለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረችና የመጀመሪያ ፈር ቀዳጅ ሕዝብ ያለባት ናት ያሉት የቱሪዝም ባለሙያው አቶ ጌትነት ይግዛው ናቸው፡፡

‹‹እነ ቤትሆቨን፣ ሞዛርትና መሰል የሙዚቃ ሰዎች ከመፈጠራቸው ቀድሞ ቅዱስ ያሬድ ዜማ የደረሰና የሙዚቃ ኖታ የጻፈ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የሌላ አገር ሰው ሆኖ ቢሆን ኖሮ ዝናው በናኘ ነበር፡፡ እኛ እሱን በሚመጥን መልኩ ስላላጎላነውና ስሙን ከፍ ስላላደረግነው ታሪኩና ሥራው ተዳፍኖ ቆይቷል፡፡

‹‹አንዳንድ ሰዎች ታሪክ ምን ዋጋ አለው፣ ዳቦ አይሆን ሲሉ ይደመጣል›› ያሉት ባለሙያው፣ ታሪክ ከዳቦም በላይ ቅርስ ሆኖ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገርና የገቢ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል አስምረውበታል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ከባህር ወለል ከ3000 ሜትር በላይ ከሆኑት 25 ተራሮች አንዱ የሆነው የስሜን ተራሮችን የሚጎበኝ ቱሪስት የቅዱስ ያሬድን ገዳም ጎብኝቶ እንዲሄድ ከትራንስፖርት አማራጮች ጀምሮ ልዩ ልዩ ፋሲሊቲዎች መሟላት ይኖርባቸዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የተያዙና ገዳሙን ከስሜን ተራሮች ጋር የሚያስተሳስር ሥራ መሥራት ከተቻለ፣ በየዓመቱ ስሜን ተራራን የሚጎበኝ 50 ሺሕ ቱሪስት ገዳሙን በቀላሉ መጎብኘት እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ጌትነት፣ የቅዱስ ያሬድን ታሪክ በማስተዋወቅና በስሙ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን እንዲጠናቀቁ ማድረግ የትውልዱ ኃላፊነት ነው፡፡

በደብረ ሐዊ የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክት አስተባባሪ ኮሚቴ የሚዲያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ የአንድነት ገዳሙ በአራት ቢሊዮን ብር ሊተገብራቸው ላሰባቸው ተግባራት ከሐምሌ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሚቴ አዋቅሮ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይቷል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችና ገበሬዎች በነፃ በሰጡት 67 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ይህ ፕሮጀክት የመላ  ኢትዮጵያውያንን ትብብር ይጠይቃል፡፡

እንደ አቶ ታደሰ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ በመሆን፣ በታሪካዊው ፕሮጀክት ላይ በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በሚችሉት ሁሉ መደገፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለማስተዋወቅና ምዕመናኑን የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ ለማድረግ ያስችላል የተባለ የድረ ገጽ መተግበሪያ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ተደርጓል፡፡ መተግበሪያው ኅብረተሰቡ ፕሮጀክቱን በቀጥታ ለመርዳት እንዲችል ሆኖ መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...