Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሩሲያን ያላሳተፈው የስዊዙ የዩክሬን ሰላም ጉባዔ

ሩሲያን ያላሳተፈው የስዊዙ የዩክሬን ሰላም ጉባዔ

ቀን:

በሩሲያና በዩክሬን መካከል ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት በስምምነት ለመቋጨት ያስችላል የተባለ የሰላም ጉባዔ፣ በስዊዘርላንድ የተደረገው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ነበር፡፡

ከአገሮችና ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት የተውጣጡ 100 ያህል ተሳታፊዎች የተገኙበት የዩክሬን የሰላም ጉባዔ፣ ዋናዋን የጉዳዩ ባለቤት ሩሲያን ያገለለ ነበር፡፡

ሩሲያን ያላሳተፈው የስዊዙ የዩክሬን ሰላም ጉባዔ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ከ80 በላይ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በዩክሬን የሰላም ጉባዔ ተሳትፈዋል
(አናዶሉ ኤጀንሲ)

በሩሲያና ዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ለማክተም ያስችላል የተባለ የሰላም መንገድ ለመቀየስ የተቀመጠው ጉባዔ፣ ሩሲያን አለማሳተፉ ብቻ ሳይሆን፣ የሩሲያ ቀኝ እጅ የሆነችው ቻይናም ያልታደመችበት ነው፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ዲፕሎማሲያዊ ጉባዔ፣ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ እንዲሁም የእንግሊዝ፣ የካናዳ፣ የፈረንሣይ፣ የጀርመን፣ የጃፓን መሪዎችን ጨምሮ መቶ የሚጠጉ አገሮች ዲፕሎማቶችና አለማቀፍ ተቋማት የታደሙበት ነው፡፡

በዚህ ጉባዔ ማብቂያ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስቆም ያስችላል የተባለ ሐሳብ ቀርቦ፣ በሐሳቡ የተስማሙ አገሮች የመግባቢያ ሰነድ ፈርመዋል፡፡

የስዊዙ የዩክሬን የሰላም የመግባቢያ ሰነድ ምን ይላል?

አልጀዚራ እንደዘገበው፣ በጉባዔው ከተሳተፉ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት አብዛኞቹ በፊርማቸው መስማማታቸውን የገለጹበት መግባቢያ ሰነድ፣ በተለይ በሦስት ዋና ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ሲጀመር አንስቶ የዓለም ሥጋት የሆነው የዛፖሪሂዣ የኑክሌር ጣቢያ በዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሕገ ደንብ መሠረት ደኅንነቱ ተጠብቆ በኤጀንሲው ቁጥጥር ሥር መቆየት አለበት የሚለው አንዱ ነው፡፡

በአውሮፓ ትልቁ ነው የሚባለው የዛፖሪሂዣ የኑክሌር ጣቢያ፣ በጦርነቱ ምክንያት የኑክሌር አደጋ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት መጫሩ ይታወቃል፡፡

የዩክሬን የግብርና ምርቶች በነፃነት ወደውጭ የሚላኩበት ሁኔታ መፈቀድ አለበት የሚለውም ሌላው አገሮች የፈረሙበት አጀንዳ ነው፡፡

የዓለም የምግብ ዋስትና ያልተረባበሸ የምግብ አቅርቦትና ምርት ላይ የተመረኮዘ ነው ያለው ሰነዱ፣ በጥቁር ባህርና በአዞቭ ባህር በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦችና በግለሰብ በሚተዳደሩ የወደብ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸምም ጠቁሟል፡፡

በሁለቱም ወገን የእስረኞች ልውውጥ መደረግና ከዩክሬን የተፈናቀሉ ሰላማዊ ነዋሪዎች ወደቀዬአቸው መመለስ ሌላው አጀንዳ ነው፡፡ በተለይ አላግባብ ተጠርዘዋል ወይም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል የተባሉ ከ20 ሺሕ በላይ ልጆች ወደመኖሪያቸው መመለስ እንዳለባቸው በሰነዱ ተቀምጧል፡፡

የጋራ መግባቢያ ሰነዱን ማን ፈረመ?

 የስዊዘርላንድ ፕሬዚዳንት ቪኦላ አምኸርድ፣ የጉባዔውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ 82 የጉባዔው ተሳታፊዎች/ተወካዮች ሰነዱን ፈርመዋል፡፡

አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ካናዳ፣ ቺሊ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ ኳታር፣ ኮሶቮ፣ ሰርቪያ ከፈረሙ አገሮች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ የአውሮፓ ካውንስልና የአውሮፓ ፓርላማም ፈርመዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ወይም በልዑክ የተወከሉት ህንድ፣ ሜክሲኮ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታይላንድ፣ ኢንዶኔዥያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በመግባቢያ ሰነዱ ላይ ያልፈረሙ አገሮች ሲሆኑ፣ የጉባዔው ታዛቢ ብራዚል ሰነዱን አልደገፈችም፡፡

ህንድ እንዳስታወቀችው፣ የመግባቢያ ሰነዱን ያልፈረመችበት ዋና ምክንያት የጉዳዩ ባለቤት የሆነችው ሩሲያ በጉባዔው እንድትሳተፍ ባለመጋበዟ ነው፡፡

‹‹በዩክሬን ሰላም ለማምጣት ሁለቱን ወገኖች በአንድ መድረክ ማወያየት ያስፈልጋል›› የምትለው ህንድ፣ ሁሉም አካላትና ሁለቱም ወገኖች ለተግባራዊነቱ የሚሳተፉበት መንገድ እንደሚያስፈልግ ገልጻለች፡፡

በጉባዔው ንግግር ያደረጉት የሳዑዲ ዓረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሃን አል ሳዑዲ በበኩላቸው፣ ማንኛውም ተዓማኒነት ያለው የሰላም ስምምነት ሩሲያን ያሳተፈ መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ የመግባቢያ ሰነዱን ያልፈረመችበት ምክንያት እስራኤል በጉባዔው መሳተፏ ትክክል አይደለም በሚል ነው፡፡ እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በሚል በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የከሰሰችው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሲድኒ ሙፋማዲ፣‹‹በዚህ ጉባዔ እስራኤል መኖሯና መሳተፏ የሚያስገርም ነው›› ብለዋል፡፡ የመግባቢያ ሰነዱን ሕጋዊነትም ጠይቀዋል፡፡

በጉባዔው ያልተሳተፈችው ሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ዩክሬን በሩሲያ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ከፈጸመች ተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን የዘገበው ኤንቢሲ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2022 ወደሩሲያ ከተቀላቀሉ አራት ቀጣናዎች ዩክሬን ወታደሮቿን ሙሉ ለሙሉ የምታስወጣ ከሆነና የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ለመቀላቀል ያላትን ዕቅድ ከቀለበሰች፣ ሩሲያ ተኩስ አቁም ስምምነት አድርጋ ከዩክሬን ጋር ድርድር ታደርጋለች ሲሉም ፕሬዚዳንት ፑቲን አስታውቀዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው፣ ሩሲያ ከወረረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ከወጣች ‹‹ነገውኑ ድርድር እንጀምራለን›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...