Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዕድሜ ጠገብ የሚባሉ የአገሪቱ ማኅበራት መካከል አንዱ ነው፡፡ 

የተለያየ ስያሜዎችን በመያዝ ወደ 80 ዓመታት የተጠጋ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባለፉት ሃያ ዓመታት ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ ንግድ ምክር ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም ከሃያ ዓመታት በፊት የወጣው አዋጅ አጠቃላይ የንግድ ምክር ቤቱን የቀደመ የአሠራር ሥርዓት የለወጠ መሆኑ በሥራው ላይ ጫና እንዳሳደረ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ አዋጁ ከረቂቅ ዝግጅቱ ጀምሮ ሲያጨቃጭቅ እንደነበር የሚታወስም ነው፡፡ አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላም ፈጠራቸው የተባሉ ችግሮች በአደባባይ ቢገለጽም አዋጁ ሳይሻሻል አሁን ድረስ ቆይቷል፡፡ አዋጁ መሻሻል እንዳለበት ታምኖ የማሻሻያ ሥራው ከተጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ የወሰደ ቢሆንም እስካሁን መቋጫ አላገኘም፡፡ በቅርቡ ግን ንግዱንና ኢንዱስትሪውን በመለያየት የየራሳቸው አደረጃጀት እንዲኖራቸው ተወስኖ ረቂቅ አዋጆቹ ለማፅደቅ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ተደርሷል፡፡ 

እስካሁን ሥራ ላይ የቆየው ይህ አዋጅ ግን በንግድ ምክር ቤቶች አጠቃላይ አሠራር ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

አገር አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአባልነት ያቀፋቸው 18ቱ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ቀድሞ በነበራቸው ጥንካሬና አቋም ልክ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው አላሠራ አለ የተባለው አዋጅ ይጠቀስ እንጂ ከሃያ ዓመታት ወዲህ በተለይ ከምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ንግድ ምክር ቤቶች ሽኩቻዎች የማያጣቸው ሆነው ዘልቀዋል፡፡  

ንግድ ምክር ቤቶችን ለመምራት በሚካሄዱ ምርጫዎች የሚፈጠሩ ችግሮች የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ብዙ ሲተችበትም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም በየሁለት ዓመቱ በተደረጉ ተከታታይ የምርጫ ዘመኖች ተመሳሳይ ሽኩቻዎች የተስተናገዱበት ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ደግሞ አዋጁ ብቻ ሳይሆን ወደ አመራር ቦታዎች ለመምጣት የሚደረጉ መጠላለፎች ንግድ ምክር ቤቱን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዳይወጣ አድርጎታል የሚል አመለካከት ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ 

ከሰባት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለየት ባለ መልኩ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ከመተዳደሪያ ደንባቸው ውጭ በየዓመቱ ሊጠሩ የሚገባቸውን ጠቅላላ ጉባዔ ሊያካሂዱ አልቻሉም፡፡ በየሁለት ዓመቱ አዳዲስ አመራሮችን ማስመረጥ ቢኖርባቸውም ይህንን ሊያደርጉ አለመቻላው የአብዛኛዎቹ ንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች ከስድስት ዓመታት በላይ ባሉበት መቆየታቸው ሕገወጥ ነው እስከመባል ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አሁን ያለው አመራር ከሰባት ዓመታት በላይ በኃላፊነት ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ስድስት ጠቅላላ ጉባዔዎችን ማካሄድ ነበረበት፡፡ በየሁለት ዓመታቱ ምርጫ በማድረግ አዳዲስ አመራሮችን መሰየም የሚገባው ቢሆንም ሦስት የምርጫ ዘመኖችን አሳልፏል፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ቦርድ ኃላፊነቱን ከተረከበበት ጀምሮ ምክር ቤቱ ባልተለመደ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባዔውንም ሆነ መካሄድ የነበረበትን ምርጫ ሊያካሂድ ያልቻለበት ምክንያት በብዙዎች ዘንድ አሳማኝ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ ለጠቅላላ ጉባዔዎች አለመጠራትና ወቅቱን ጠብቆ የቦርድ አባላት ምርጫ ላካሄደው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ስለመሆኑን ቢገልጽም ንግድ ምክር ቤቱን በቅርብ የሚያውቁ ወገኖ የሚቀርቡትን ምክንያቶችን አይፈልጉም፡፡ 

በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔም ሆነ ምርጫ ላለማድረጉ እንደ ምክንያት ሲጠቀሱ ከነበሩት ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት፣ የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀስ በቀዳሚነት የሚቀመጡ ናቸው፡፡ ከዚያም በኋላ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሚሻሻል በመሆኑ በሚሻሻለው አዋጅ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔንና ምርጫውን ማካሄድ የተሻለ መሆኑ ስለታመነበት ነው የሚል ምክንያት ቀርቦ ነበር፡፡

ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ አባል ምክር ቤቶች በጠቅላላ ጉባዔ ለመሳተፍ ማሟላት የሚገባቸው መሥፈርቶችን ለሚያሟሉ ባለመቻላቸው ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ እንዳልተቻለ የተገለጸበትም ጊዜ አለ፡፡ ከወራት በፊት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአስገዳጅነት ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያካሂዱ ባሳሰበው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ከዚህ ቀደም በየምርጫ ዘመኑ እንደሚካሄደው በጠቅላላ ጉባዔው ለመወከል አባል ምክር ቤቶች እንደሚገቡ በቅድሚያ የተጠየቀበትን የተለያዩ መሥፈርቶች ልናሟላ አንችልም በማለታቸው ጠቅላላ ጉባዔው ሊሰረዝ መቻሉ እንደ ምሳሌ የሚጠቀስ ነው፡፡ አንዳንድ አባል ምክር ቤቶችም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን በተጣበበ ጊዜ በመሆኑ በዚያ ወቅት የተጠቀሱትን መሥፈርቶች ልናሟላ አንችልም ማለታቸውም ኅዳር 2016 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው ጉባዔ ተሰርዟል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔን ለመጥራት በየምርጫ ዘመኑ ከሚቀርቡ አስገዳጅ መሥፈርቶች መካከል አንዱ ንግድ ምክር ቤቶቹ በበጀት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ ይኖርባቸዋል የሚል ነው፡፡ በዚህ ጉባዔ ወቅት ያሉዋቸውን አባላት ቁጥር ማስተዋወቅና በአባላቱ ቁጥር ልክ ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ዓመታዊ መዋጮዋቸውን ማስገባት የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ ቢያንስ እነዚህን ማሟላት ካልቻሉ በጠቅላላ ጉባዔው የማይወከሉና ምርጫም ካለ ዕጩ ማቅረብ የማይችሉበት ድንጋጌ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ይህንን ማሟላት እንዳልተቻለ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን በተመለከተ ራሱ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ያለማካሄድ  ከሰሞኑ ግን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወጣ አዲስ ማሳሰቢያ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ንግድ ምክር ቤቱ በአስገዳጅነት ሲያስቀምጣቸው የነበሩ መሥፈርቶችን ትተው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን እንዲያካሂዱ የመጨረሻ ነው የተባለ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ 

በዚሁ ማሳሰቢያ መሠረት እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫውን እንዲያካሂዱ በደብዳቤ በሰጠው ማሳሰቢያ ጉባዔው መካሄድ የሚኖርበትን መንገድ ሁሉ ገልጿል፡፡  

በዚህም ማሳሰቢያው ጉባዔው እንዲጠራ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ በተጠየቀው መሠረት የተሰጠውን ውሳኔ በገለጹበት ደብዳቤው ንግድ ምክር ቤቱ ማድረግ የነበረበትን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና የአመራር ቦርድ ምርጫ በተለያየ አሳማኝ ምክንያት ሳይደረግ የቆየ ቢሆንም መራዘሙ የተለያዩ ቅሬታዎች ሲያስነሳ ቆይቷል ብሏል፡፡ አያይዞም የአባል ምክር ቤቶች ነባራዊ ሁኔታን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተወሰኑ መሥፈርቶች ላይ ለውጥ በማድረግ ጠቀላላ ጉባዔው እንደደረግ ውሳኔ ላይ መድረሱንም ጠቅሷል፡፡ 

በዚህም መሠረት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማድረግ የሚጠየቁ መሥፈርቶች መደረግ ይኖርባቸዋል ያላቸውን ማሻሻያዎች በዝርዝር አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት የአባል ምክር ቤት በጠቅላላ ጉባዔው የሚወከሉበትን የአባላት ቁጥርን በተመለከተ የሁሉም ነጋዴዎች በንግድ ምዝገባቸው ላይ በተገለጸው አድራሻ መሠረት ትክክለኛ ቁጥራቸው ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመውሰድ ጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ዓመታዊ መዋጮ ኦዲት ሪፖርትና የሥራ ሪፖርት በቀጣይ በአዲስ መልክ ሲራጁ የሚያሟሉ መሆኑ ታሳቢ ተርጎ በጉባዔው እንዲሳተፉም ወስኗል፡፡ ከዚህም ሌላ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሕዝብ ውሳኔ አዲስ የተፈጠሩ የሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችን የምሥረታ ጉባዔ አባል አድርጎ የአመራር ቦርድ ያስመረጡ መሆናቸው ተጣርቶ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ እንዲደረግ ስለመወሰኑ ተጠቅሷል፡፡ ሁሉም አባል ቤቶች ሊጠቅማቸው የሚችል በጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባዔና የአመራር ቦርድ ምክር ቤት እንዲቀርቡ በማድረግ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ጠቅላላ ጉባዔ እንድታደርጉ እናሳስባለን የሚል ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ 

ያሻሻላቸውን መሥፈርቶች ዳግም ‹‹የአባል ምክር ቤት በጠቅላላ ጉባዔው የሚወከሉበትን የአባላት ቁጥርን በተመለከተ የሁሉም ነጋዴዎች በንግድ ምዝገባቸው ላይ በተገለጸው አድራሻ መሠረት ትክክለኛ ቁጥራቸው ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመውሰድ ጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ በአሁኑ ሰዓት የሆነ ንግድ ሥራ ፍቃድ ናቸው፤›› በማለት ጠቅላላው ለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲካሄድ አሳሰበ፡፡

በሚኒስቴሩ ትዕዛዝ መሠረትም የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ምርጫውን በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ በጽሕፈት ቤቱ በኩል ጠቅላላ ጉባዔው ለሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዲጠራ አድርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ መሥፈርቶች መነሳታቸውንም በሚመለከት በዕለቱ ምርጫ የሚደረግ መሆኑን አስታውቆ አባል ምክር ቤቶች ዕጩዎችን እንዲያሳውቁ አሳስቧል፡፡ ተመራጮች ምን ማለት እንዳለባቸውና እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው የሚያመላክት መረጃም ተሠራጭቷል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ለተመራጮች አዘጋጅቶ ካሠራጨው መሥፈርት መረዳት እንደተቻለው ለኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት መመዘኛ የወጣ መሥፈርት በሚል በተጠቀሰው ሥር ለፕሬዚዳንትነት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት በዕጩነት የሚጠቆሙ ወይም የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችን በተሰማራበት ወይም በተሰማራችበት የሥራ ዘርፍ በስሙ ወይም በስሟ የንግድ ፈቃድ በማውጣት ወይም የተቋቋመ ኩባንያ ባለቤት በመሆን ወይም በዋና ሥራ አስኪያጅነት በመምራት ከሁለት ዓመት በላይ የሥራ አመራር ልምድ ያለው ወይም ያላት መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ የፕሬዚዳንቱ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የሥራ አገልግሎት ዘመን ሁለት ዓመት እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ 

ሌላው ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እንደገና ሊመረጡ እንደሚችል ሆኖም ከሁለት ተከታታይ ጊዜያት በላይ ሊመረጡ አይችሉም የሚልም መሥፈርት ተቀምጧል፡፡ 

እንዲህ ያሉ ወደ ሰባት የተዘረዘሩ መሥፈርቶች መካከል ‹‹በተቀመጡበት የሥራ ኃላፊነት ቦታ ለሁለት ተከታታይ የምርጫ ዘመን ያገለገለ አንድ የሥራ አመራር ቦርድ አባል በቂ የሥራ ልምድና ክህሎት እንደሚያዳብር ስለሚታመን ወደሚቀጥለው የኃላፊነት የዕርከን ደረጃ ማለትም ለፕሬዚዳንትነት ወይም ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ዕጩ ሆኖ መቅረብ ይችላል፤›› የሚልም ይገኝበታል፡፡ 

ቀደም ሲል አገራዊ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ወይም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ወይም በሥራ አመራር ቦርድ አባልነት ተመርጦ ያገለገለና የአገልግሎት ዘመኑ ካበቃ በኋላ በቀጣይ የምርጫ ዘመን አገልግሎት በሰጠበት የሥራ ኃላፊነት ዳግም ለመመረጥ አይችልም እንደማይችልም ተገልጿል፡፡ 

‹‹የተጣለባቸውን አደራና ኃላፊነት በብቃት በመወጣት በክብር የተሰናበቱ የአገራዊ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትነት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትነትና የሥራ አመራር ቦርድ አባልነት በጠቅላላ ጉባዔው ዕውቅና እንዲሰጣቸው፣ አገራዊ ምክር ቤቱ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች በሚያደርጋቸው ጉብኝቶች፣ ሥልጠናዎችና አጠቃላይ እንዲሳተፉ፣ እንዳስፈላጊነቱ ያላቸውን ልምድና ክህሎት የንግድ ቤቱ ጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያካፍሉ ያደርጋል፤›› የሚል ጭምር ያካተተው የተመራጮች መሥፈርት እንደ አዲስ ቀርቧል፡፡ 

በተመራጮች መሥፈርትም ሆነ አጠቃላይ በጉባዔው አጠራር ላይ ግን ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ አንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች ቀድሞ የነበረውን መሥፈርት ማስቀረት የለበትም እያሉ ነው፡፡ እንደ ቀድሞ በኮታ መወከል አለብን እንጂ በጅምላ የሚደረግ ጥሪ ብዙ አባላት ያላቸውን ድምፅ ይቀንሳል የሚል መከራከሪያ እያላላው ይገኛል፡፡ 

እያስነሳ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅብራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው የሚካሄድበትን መንገድ ተውሏል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ለንግድ ሚኒስቴር የአገራዊ ምክር ቤቱ ግን አጥጋቢ ያልሆነ ምክንያቶችን በመደርደር በየጊዜው የምርጫ ጊዜ ቀጠሮውን በማራዘም ተጨማሪ ጊዜ በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡ ዳሩ ግን ይህ የአገልግሎት ዘመኑን ያጠናቀቀ አገራዊ ምክር ቤት ቦርድ ለክልሎች አመራር ለመስጠት ምንም ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች የሥልጣን ሽግግር የሚደረገው በምርጫ ብቻ መሆኑ እየታወቀ ይህ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይካሄድ ማድረግ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑ መታወቅ ይገባዋል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የንግዱ ኅብረተሰብ አንደኛ የንግዱ ኅብረተሰብ በምርጫ በሚወክለው አመራር ድምፁን ማሰማትም ሆነ ለመብቱና ጥቅሙን ልሚያስከብርለት የሚገባውን ሕጋዊ ውክልና ያለው ቦርድ ማግኘት አልቻለም፡፡ ከቦርድ አመራሩ ቆይታ የተነሳ መሰላቸት በመምጣቱ የንግዱን ኅብረተሰብ ችግሮች ከመፍታትም አንፃር ለውጥ እየታየ አይደለም፡፡

አዋጅ 341/95 እንዲለወጥ በተመሳሳይ መልኩ በተደጋጋሚ ጥያቄዎች የቀረቡና አስተያየቶችም የተሰጡ ቢሆንም እስካሁንም ተጨባጭ ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡ ይህ አገራዊ ምክር ቤት በአዋጁ መሠረት የፈረሰና ሕጋዊ ቅቡልነት የሌለው በመሆኑ አባል ምክር ቤቶችን ማደራጀትና መመራት እያዳገተ መጥቷል፡፡

ለአባል ምክር ቤቶች መስጠት የሚገባውን አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ እንዲሁም ምክር ቤቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻውን መወጣት አላስቻለውም፡፡

ጉባዔው በወቅቱ አለመጠራትና የቦርዱ ምርጫ በወቅቱ አለመፈጸም የነበረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ወደ ኋላ የሚጓተት በመሆኑ በአጠቃላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ከማኅበሩ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቀጥታ የሚመለከተው ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ የአገራዊ ምክር ቤቱን ምርጫ በማከናወንና መልሶ በመደራጀት ወደ ሕጋዊ ህልውናው እንዲመለስ እንዲደረግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ የሚል ደብዳቤ እስከመጻፍ ደርሷል፡፡

ከዚህም ሌላ አንዳንዶች በመቧደን ኃላፊነት ቦታውን ለመውሰድ ውስጥ ለውስጥ እየሠሩ ሲሆን፣ ይህን እንደ ቀድሞ የምርጫ ሽኩቻውን ያስነሳል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን በሚኒስቴሩ የተሰጠው ቀነ ገደብ መታለፍ የለበትም በመባሉ በፉክቻ ውስጥም ቢሆን አዲስ ምርጫ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ አንዳንዶች ግን አሁንም ምርጫው ላይካሄድ ይችላል የሚል እምነት አላቸው። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች