Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ብዛት ያላቸው የኦዲት ክፍተት ግኝቶችን ለፓርላማ አቀረበ

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ብዛት ያላቸው የኦዲት ክፍተት ግኝቶችን ለፓርላማ አቀረበ

ቀን:

  • ሪፖርቱ ሲቀርብ የመንግሥት ባለሥልጣናት አለመገኘታቸው ጥያቄ አስነስቷል
  • ለኦዲተሮች የሚመደብላቸው 300 ብር የቀን አበል እንዲሻሻል ተጠይቋል

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በባለበጀት የመንግሥት ተቋማት ላይ ባካሄደው የ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲትና የክዋኔ ኦዲት፣ ብዛት ያላቸው የአሠራር ክፍተቶችንና የፋይናንስ ጉድለቶችን የሚያመላክት የኦዲት ሪፖርት አቀረበ፡፡

በየዓመቱ መጨረሻ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኦዲት ሪፖርት፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. አቅርበዋል፡፡

ባለ 60 ገጽ ጥራዝ ሪፖርቱን ያቀረቡት ወ/ሮ መሠረት፣ ለምክር ቤቱ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በኦዲት ሪፖርት ስብሰባው ላይ መገኘት ከነበረባቸው 22 ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከአራት ያልበለጡ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙና ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በሚያቀርቡበት ወቅት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በስተቀር ሁሉም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በስብሰባው መገኘት እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡

ከአባላቱ መካከል በኦዲት ሪፖርቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አለመገኘታቸውን ለምን አልተገኙም ሲሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ በርጢማ ፈቃዱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አቶ በርጢማ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶቹ የት አሉ? ለማን ነው ይህ ሪፖርት የቀረበው? ምክር ቤቱ የሚያቀርበውን አስተያየት ተከታትለው ምላሽ ካልሰጡ በምን ዓይነት መንገድ ነው ችግሩ የሚፈታው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከ173 የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በ162 መሥሪያ ቤቶችና በ58 ቅርንጫፎች በዋና ኦዲተር አማካይነት፣ በሒሳብ ምርመራ ኮርፖሬሽን አማካይነት ደግሞ በ11 ተቋማት ላይ ኦዲት ለማድረግ ዕቅድ እንደነበረው አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ መሥሪያ ቤት ለኦዲት ሥራ ቢሮ ባለመስጠት፣ አሥር መሥሪያ ቤቶችና አራት ቅርንጫፎች በፀጥታ ምክንያት ኦዲት አለመደረጋቸው ተገልጿል፡፡

በኦዲቱ እንደተብራራው በ2014 በጀት ዓመትና ከዚያ በፊት በተከናወኑ የኦዲት ሪፖርቶች መሠረት ዕርምጃ የተወሰደ መሆኑን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት፣ በ92 መሥሪያ ቤቶች  ተመላሽ እንዲደረግ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊዮን ብር እና 23 ሺሕ ዶላር ተመላሽ የተደረገው 48 ሚሊዮን ብር ወይም 11 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል፡፡

የዋና ኦዲተር ኦዲተሮችን በገንዘብ ለመደለል የሞከሩ የአንድ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባላት ጉዳይ ለትምህርት ሚኒስቴር ቀርቦ፣ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በ124 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በወቅቱ መሰብሰብ የነበረበትና ከአሥር ዓመታትና ከዚያ በላይ ቆይታ ያለው 14 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡ  ተገልጿል፡፡ በ15 መሥሪያ ቤቶች በወቅቱ ያልተወራረደ 514.5 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ማስረጃ ባለመቅረቡ የሒሳቡን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ 363 ሚሊዮን ብር በኦዲቱ መገኘቱን ወ/ሮ መሠረት አስረድተዋል፡፡

በግብር፣ በቀረጥና በሌሎች ገቢ ለመሰብሰብ በሚደነግጉ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች መሠረት በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን ሥር ባሉ ሃያ ቅርንጫፎች 6.4 ቢሊዮን ብር ያልተሰበሰበ መኖሩ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር በሚገኙ ዘጠኝ ቅርንጫፎችና በጉምሩክ ኮሚሽን ሥር በሚገኙ 11 ቅርንጫፎች በተለያየ ደረጃ እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብሳቢ ውዝፍ ገቢ ሒሳብ እንደሚገኝ በ2014 በጀት ዓመት በሪፖርት የተመላከተ ቢሆንም፣ በወቅቱ በተሰጠው ማሰባሰቢያ መሠረት ዕርምጃ አለመወሰዱን የቀረበው ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲና የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ 16 ሚሊዮን ብር ከደንብና ከመመርያ ውጪ ክፍያ መፈጸማቸውን ዋና ኦዲተሯ ተናግረዋል፡፡

የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመርያ ያልተከተሉ ግዥዎች በፈጸሙ ተቋማት 2.1 ቢሊዮን ብር በኦዲት መገኘቱን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ከተቋማቱ መካከል የገቢዎች ሚኒስቴር 1.4 ቢሊዮን ብር፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 91 ሚሊዮን ብር፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 65.5 ሚሊዮን ብር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 63 ሚሊዮን ብር፣ ኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 87 ሚሊዮን ብርና ሌሎችም በሪፖርቱ ተዘርዝረዋል፡፡

በ14 መሥሪያ ቤቶች 1.7 ቢሊዮን ብር በተከፋይ ተመዝግቦ የተያዘ መሆኑን፣ ነገር ግን ለማን እንደሚከፈል ተለይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ወ/ሮ መሠረት ያቀረቡት የኦዲት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ከተደለደለላቸው በጀት በላይ 1.3 ቢሊዮን ብር ከተጠቀሙ መሥሪያ ቤቶች መካከል ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 322 ሚሊዮን ብር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 268 ሚሊዮን ብር፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 173 ሚሊዮን ብር፣ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት 109.5 ሚሊዮን ብር እና ሌሎች ተቋማትም ይገኙበታል፡፡

መሥሪያ ቤቶች በፋይናንስ አስተዳደር አዋጁ መሠረት የተመደበውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ማዋል የሚጠበቅባቸው ቢሆንም የገንዘብ ሚኒስቴር ስምንት ቢሊዮን ብር፣ የጤና ሚኒስቴር ሁለት ቢሊዮን ብር፣ ግብርና ሚኒስቴር 1.2 ቢሊዮን ብር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 818.4 ሚሊዮን ብር፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ 727.8 ሚሊዮን ብር፣ የትምህርት ሚኒስቴር 724.2 ሚሊዮን ብር እና የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴሩ 613.6 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት የሞዴል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል (የሳይንስ ካፌ) ፕሮጀክቶች አማካይነት ወጣቶች የሳይንስ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲያዳብሩ እንዲሁም የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸው የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ለመስጠት ቢቋቋሙም፣ ሚኒስቴሩ ያቋቋማቸውን አምስት የሳይንስ ካፌ ማዕከላት ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ ማለትም ካፊቴሪያ፣ ፑል ማጫወቻ፣ ፕሌይ ስቴሽንና ስፖርት ማዘውተሪያ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ከተቋቋመ 50 ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ ኦዲቱ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ የማዕድን ሀብትና ልማትን የሚመለከት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ አለመደረጉ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ከ2010 እስከ 2016 ዓ.ም. ሩብ ዓመት 4.2 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የሰበሰበው 1.2 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 28 በመቶ ብቻ መሆኑ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብዓቶችንና የማዕድን ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የድንጋይ ከሰል ለማምረትና ያመረቱትን ፕሮሰስ ለማድረግ ፈቃድ የተሰጣቸው ዘጠኝ ኩባንያዎች ወደ ተግባር አለመግባታቸውን፣ ወ/ሮ መሠረት በሪፖርታቸው አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ማዕድናት ለምርመራ ናሙናዎች ወደ ውጭ አገር ለፍተሻ ከተላኩ በኋላ፣ ኢኮኖሚክ ጥቅም የላቸውም እየተባለ የማይመለሱ መሆናቸው በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በፌዴራል መንግሥት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን የያዙ ሥራ ተቋራጮች የያዙትን ፕሮጀክት ሳያጠናቅቁ ወይም አፈጻጸማቸው ሳይገመገም በሌላ ጨረታ እንዳይወዳደሩ የሚከለክል አሠራር ባለመዘርጋቱና ቁጥጥር ባለመደረጉ፣ ዋጋቸው 10.7 ቢሊዮን ብር የሆኑ 12 ፕሮጀክቶች በሁለት ሥራ ተቋራጮች መያዛቸው ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቶች መቋረጥ እየፈጠረ ያለውን ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ሊቀንስ የሚችል ሥራ አስቀድሞ ባለመሠራቱ በናሙና ከታዩ 41 የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ውስጥ በመጀመሪያ ውላቸው ሳይጠናቀቅ፣ ለሁለተኛ ጊዜ በወጣ ሌላ ጨረታ ወደ ግንባታ የገቡ 13 ፕሮጀክቶች በመንግሥት ላይ 16.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸው ተመላክቷል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለፓስፖርት አሰጣጥ የፀደቀ መመርያ ስታንዳርድ የሌለው መሆኑ፣ ከድንበርና ከጎረቤት አገሮች የመጡ መሆናቸው አጠራጣሪ የሆኑ ተገልጋዮች ሲያጋጥሙ ዜግነታቸው የሚጣራበት መሣሪያ ስለሌለው፣ ዜግነት የማጣራት ሥራ በልምድ የሚከናወንና ውሳኔው ዜግነትን በሚያጣራው ግለሰብ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተና ወጥ ያልሆነ አሠራርን እንደሚከተል ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ሥር ተጠሪ የሆኑ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እስከ እ.ኤ.አ. መስከረም 30 ቀን 2023፣ በአጠቃላይ በብድር መክፈያ መርሐ ግብራቸው መሠረት ያልከፈሉት 50.8 ቢሊዮን ብር መኖሩ ተገልጿል፡፡

ከልማት ድርጅቶች ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም. ሳይሰበሰብ የቀረው በገንዘብ 12 ቢሊዮን ብር፣ ወይም 36.8 በመቶ የትርፍ ድርሻ ዕዳ ያለባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን በ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስ ዕቅድ አፈጻጸሙ  ለተለያዩ የውጭ አበዳሪ አካላት 1.8 ቢሊዮን ብር መክፈል የሚገባውን ባለመክፈሉ፣ ከአጠቃላይ ሀብቱ ዕዳው 126 በመቶ መድረሱንና በፋይናንስ አቅሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት 482 የኦዲት ባለሙያዎች እንዳሉትና በተቋሙ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት በመኖሩ አዲስ ሠራተኛ ማግኘት አለመቻሉን የገለጹት ወ/ሮ መሠረት፣ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ለሥራ አመቺ ባልሆኑ አካባቢዎች ጭምር በመስክ የሚሠራ በመሆኑ የቀን አበል ማነስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩን በመቋቋም ሥራዎችን በታቀደው መሠረት ጥሩ በሚባል ደረጃ ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የሠራተኛ የውሎ አበልን በተመለከተ ሠራተኛው ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ጭምር በመሥራት በ300 ብር የቀን አበል ብር ቁርስ፣ ምሳ፣ እራትና አልጋ ሸፍናችሁ ሥሩ ማለት አሉታዊ ስሜት እየፈጠረ በመሆኑ ምክር ቤቱ ጉዳዩን በትኩረት ዓይቶ ምላሽ እንዲሰጥበት ዋና ኦዲተሯ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...