Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለግል ባለሀብቶች ከተሰጠው 2.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ እየለማ ያለው 41 በመቶ ብቻ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለግል ባለሀብቶች ከተላለፈው 2.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ድረስ እየለማ ያለው 41 በመቶ ብቻ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመሆን በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ያሉትን ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል፡፡

የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ግብርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ቢሆንም፣ አብዛኛውን አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ዘርፉን እያለሙት ነው፡፡

የግል ባለሀብቶች መሬት ከወሰዱ በኋላ በሙሉ አቅም መጠቀም ባለመቻላቸው ሰፋፊ የእርሻ መሬት ጾሙን እያደረ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

የግል ባለሀብቶች የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ስለሚገጥማቸው ይህ ነገር ሊከሰት ችሏል ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ በአሁኑ ወቅት 5,700 የሚሆኑ ባለሀብቶች መሬት የወሰዱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 98.6 በመቶ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 1.4 በመቶ ደግሞ የውጭ ባለሀብቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የግል ባለሀብቶች በዘርፉ ላይ ያላቸው የአፈጻጸም ሁኔታ ሲታይ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ከማልማት አንፃር ከሞላ ጎደል የውጭ ባለሀብቶች አፈጻጸም የተሻለ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በባለሀብቶች የተያዘውን ሔክታር መሬት በሙሉ አቅም ማልማት ቢቻል ምን ያህል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻል ነበር የሚለው ጥያቄ ውስጥ እንደሚከትና አሁንም ከለማው 41 በመቶ የእርሻ መሬት ውስጥ በቂ የሆነ ምርት እንዳልተገኘ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ 59 በመቶ በባለሀብቶች እጅ ሥር የሚገኝ የእርሻ መሬት መልማት አለመቻሉን ጠቅሰው፣ አብዛኛውን ክልሎች ለባለሀብቶች ሰፋፊ የእርሻ መሬት ቢሰጡም የበርካቶቹ ግን አፈጻጻሙ ዝቅተኛ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የግል ባለሀብቶች በተመለከተ ከዚህ በፊት የነበረው የመረጃ አያያዝ ሥርዓት የዘመነ ባለመሆኑና ባለሀብቶቹም በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ባለመግባታቸው የተነሳ ለግል ባለሀብቶች የተላለፈውን የእርሻ መሬት በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡

ለግብርና ዘርፍ ከተሰጠው አሥር ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ ግማሽ ያህሉ የተበላሸ መሆኑ፣ ባንኩ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ አያሌው ተናግረዋል፡፡

ባንኩ ብድር ሲሰጥ ከባለሀብቶች እንደ መያዣ ይዞታ ከነበረው መሬት 35 ሺሕ ሔክታሩንም ለክልሎች ማፅደቁን አክለው ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በ2016 ዓ.ም. በ11 ወራት ውስጥ 7.1 ቢሊዮን ብር ብድር ማፅደቁን፣ ከፀደቀውም ብድር ውስጥ 1.9 ቢሊዮን ብር ለሰፋፊ እርሻዎች የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ልማት ባንክ ባለፈው ዓመት ለግብርና ዘርፍ 3.4 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቶ እንደነበርና በአሁኑ ወቅትም ለግብርና ዘርፍ የሚሰጠው ብድር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን አክለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች