Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

ቀን:

በአብዱ ሻሎ

አንገት ማስገቢያ

እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን›› በሚል ጦሩን ወደ ዩክሬን ካዘመተ ከቀናት በኋላ በዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ አረዳዱ በጣም ከማደንቀው ወዳጄ ጋር ተገናኝተን ሁልጊዜ እንደምናደርገው በወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ የጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ የጦርነቱ መጀመር ለዓለም አቀፉ የሰላምና የደኅንነት ያለው አንድምታ፣ እንዲሁም በቀጣይ ሊሆኑ ስለሚችሉ አዝማሚያዎች ያደረግነው ውይይት በሰፊ የአመለካከትና አረዳድ ልዩነት መቋጨቱን አስታውሳለሁ፡፡ ጦርነቱ ሁለተኛ ዓመቱን ከያዘና ሌሎች አዳዲስ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁነቶች ተደምረው እየተወሳሰቡ ባሉበት በአሁኑ ወቅትም፣ ባደረግናቸው ተከታታይ ውይይቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለማስታረቅ በሚያስቸግሩ የሁኔታዎች ትንተና፣ አረዳድና ትንበያዎች የታጀቡ የሐሳብ መለዋዋጥ አድርገናል፡፡ በዚህ ሉላዊነት (Globalization) ዓለምን ባቀራረበበት፣ በአብዛኛው ዓለም አቀፍ የቀውስ መረጃዎችን የምናገኝባቸው ምንጮች ተቀራራቢ በሆኑበት ዘመን በሚታይና በሚጨበጥ ወቅታዊ ሁኔታዎች አረዳድ ላይ ስለምን እንዲህ የሰፋ ትንተና ወይም አረዳድ ሊኖረን ቻለ የሚለውን ጥያቄ ደጋግሜ ራሴን እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡

ይህ በወዳጄና በእኔ መካከል ያስተዋልኩት እየተፈጠሩ ያሉ እውነታዎች (Facts) ትርጉም የምንሰጥበትና የምንረዳበት ሁኔታ መለያየት በጂኦ ፖለቲካ ጥርሳቸውን ነቅለዋል በተባሉ ተንታኞች፣ ምሁራን፣ ፖሊሲ ቀራፂዎችና  የአገሮች መሪዎች (ውሳኔ ሰጪዎች) እየተፈጠሩና በመፈጠር ሒደት ላይ በሚገኙ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ የደኅንነት ሁኔታዎች ላይ በሚይዙት ፅንፍ የያዘ ወይም ለማቀራረብ እንኳ የሚያዳግት አቋም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ማስተዋሉ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በእርግጥ በተጨባጭ እያስተዋልናቸው ጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች (Geopolitical Realities) በተመሳሳይ ወይም ወጥ በሆነ አንድ ዓይነት መንገድ ትርጉም መስጠት ወይም መተንተን አለብን የሚል የተሳሳተ አመለካከት የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ለማስታረቅ አስቸጋሪ በሆኑ ፅንፎች መረዳት ወይም መተንተን በራሱ ችግር እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ለዚህ በተጨባጭ በሚስተዋሉ ጂኦፖለቲካዊ እውነታዎች አረዳድ ልዩነት የተለያዩ ምክንያቶች የሚሰነዘሩ ቢሆንም በዋነኝነት የማንፈልጋቸውን ውጤቶች ለመቀበል መቸገር (Difficulties in Accepting the outcomes)፣ ከግል አመለካከት ወይም ፍላጎት ነፃ በሆነ መልኩ እውነታዎቹን መተንተን አለመቻል (Biased Analysis)፣ በሚተነተነው ጉዳይ ላይ በቂ ያልሆነ ኢንፎርሜሽን/ ዕውቀት መኖር (Lack of Basic information/knowledge) ወይም በጨበጣ መተንተን እንዲሁም ወደምንፈልገው ድምዳሜ ብቻ የሚያደርሱ አጋዥ ኢንፎርሜሽኖችን እንደ ግብዓት መጠቀም (employing Narrowly selected information as an inputs) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አንድን እየተከሰተ ያለ ወይም የተከሰተ ፖለቲካዊና ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ቀደም ሲል በገለጽኳቸው አራት መሠረታዊ የትንተና ችግሮች (Analytical Pitfalls) ውስጥ ሆነን ትርጉም የምንሰጥ ወይም የምንተነትን ከሆነ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ መሄዳችን አይቀሬ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይህንን መሠረታዊ የትንተና አካሄድ በመከተል በወዳጄ ገና ታምሩና መሰል አስተያየት ሰጪዎች የሚቀነቀነውን ‹‹የምዕራባዊያኑ ኃያልነት አይገረሰስም›› የሚለውን አስተሳሰብ በማሳያዎች በማስደገፍ ለመሞገት (Challange)፣ ብሎም ለቀጣይ ግብረ መልስና ገንቢ አስተያየቶች በር ለመክፈት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ እገባለሁ፡፡

የዓለም ጂኦፖለቲካዊ ዋልታ ከባለ አንድ ወደ ባለብዙ ዋልታዎች የመቀየር ሒደት

እ.ኤ.አ በ1945 የጀርመንና አጋሮቿ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሶቭየት ኅብረት፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሣይ እንዲሁም አጋሮቻቸው መሸነፍ ማብቃቱን ተከትሎ በሊበራል ዴሞክራሲ ተከታዮቹ የምዕራብ አውሮፓ አገራዊና አሜሪካ በአንድ በኩል ሶቭየት ኅብረትና የሶሻሊዝም ተከታይ አገሮች በሌላ ጎራ ተሠልፈው ዓለም አቀፉን የጂኦፖለቲካ፣ ቀጣናዊ ብሎም ስትራቴጂክ የበላይነት ለመያዝ በሚፈልጓቸው አገሮች ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ሲሻኮቱ፣ አለፍ ብለውም በእጅ አዙርና ቀጥታ ሲዋጉ (ቬትናምና አፍጋኒስታን ጥሩ ማሳያዎች ናቸው)፣ እንዲሁም መሸናነፍ ሲያቅታቸው አገሮቹን በሁለቱ የተፅዕኖ አድማሶች ሲከፋፍሉ (ሰሜንና ደቡብ ኮሪያን ልብ ይሏል) ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በሁለቱ ኃያላን የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊዎችና ጀሌዎቻቸው ሲዘወር የነበረው የባለ ሁለት ዋልታ ዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ ሥርዓት በ1991 የሶቭየት ኅብረትን መፍረስ (በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች) ተከትሎ ማክተሙ ይታወሳል፡፡

በዚህም ሊበራል ዴሞክራሲን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ርዕዮት አንግቦ የተነሳው የምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ ጥምረት ያለ ምንም ኃያል አገር ተቀናቃኝነት ርዕዮታቸውን በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋት ሲንቀሳቀሱ እምብዛም ችግር ያላጋጠማቸው ሲሆን፣ ተግዳሮት የሆኑባቸውን አገሮች በቀጥታ የወታደራዊ ጣልቃገብነትና ወረራ አልያም ተቃዋሚ ታጣቂዎችን በማደራጀት ያዳከሟቸውና ያተራመሷቸውን አገሮች ብዘረዝር የሪፖርተርን ዕትም ግማሽ ገጽ እንደሚሸፍን ስገልጽ ያለማጋነን መሆኑ ይያዝልኝ፡፡ ታላቁ ፈላስፋና ኢኮኖሚስት ካርል ማርክስ ከጓደኛው ኤንግልስ ጋር ባረቀቀው የዲያሌክቲካዊ ቁስ አካላዊነት (Dialectical Materialism) ፍልስፍና እንደሚነግረን ይህ ጽሑፍ ከተተየበበት ኮምፒውተር ጀምሮ፣ ጽሑፉ የታተመበት ወረቀት ወይም የማይዳሰሱ የሰው ልጅ እሴቶች (ባህል፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች ኑባሬ በነበረበት የማይቀጥል ከመሆኑም በላይ በየዕለቱ በማይቋረጥ ለውጥ ውስጥ እያለፈ ይገኛል/ያልፋል፡፡ ይህንን የማርክስና ኤንግልስ ዲያሌክቲካዊ ለውጥ ዕሳቤ ይዘን በአሁኑ ወቅት በፍጥነት ከአሜሪካና አጋሮቿ ወደ ሌሎች ኃያላን እየተቀየረ ያለውን የዓለም ሥርዓት ለውጥ እንገምግም፡፡

የምዕራባዊያን መራሹ ዓለም ሥርዓት ማክተም ገፊና አፋጣኝ ሁነቶች

የኢኮኖሚ ክሽፈት

በምዕራባዊያኑ የተመሠረቱና የሚዘወሩ እንደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም እንዲሁም የዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ባወጧቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያና ክትትል መረጃ የምዕራባዊያኑ ክለብ ቡድን ሰባት (G7) አባል አገሮች ኢኮኖሚ ትንበያ እ.ኤ.አ. በ2023 የአሜሪካ አጠቃላይ አገራዊ የምርት ዕድገት መጠን በ2.5 እንደሚያድግ የተተነበየ ቢሆንም፣ በ2024 ከተጠበቀው በታች 2.1 ማስመዝገቡ፣ ጀርመን ከ0.3 በታች እንደሚያሽቆለቁል ተገምቶ ከተጠበቀው በታች በ0.5 መውረዱ፣ እንግሊዝ በ0.5 ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ ወደ 0.4 መውረዱ፣ እንዲሁም ፈረንሣይ በ0.8 ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ በ0.6 ብቻ ማደጉ የኢኮኖሚያቸው ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደማይገኝ ማሳያ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት የጀርመንና እንግሊዝ ኢኮኖሚ ግራፍ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል (Recession) ውስጥ መሆናቸውን በይፋ በመንግሥቶቻቸው በኩል ማመናቸው የሁኔታውን መባባስ ያሳያል፡፡ ከዚህ ባሻገር በቤልጅየም፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ እንዲሁም ሆላንድ ገበሬዎች ትራክተሮቻቸውን ይዘው በጎዳናዎች ላይ በመውጣት አውሮፓ ኅብረትና መንግሥቶቻቸው ለገበሬዎች ትኩረት እንዲሰጡና የምርት መቀነስን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች እንዲደግፉ ሲጠይቁ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ለአብዛኛው የአውሮፓ አገሮች የምርት መቀነስ፣ ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል እንዲሁም የመሠረታዊ ፍጆታዎች የዋጋ ንረት የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡ ቢሆንም፣ የመንግሥታቱ ሕዝቦችን ያላገናዘበ የኃይል ፖሊሲ (Energy Policy)፣ ቀደም ሲል በአገራቱ ቁጥጥር ሥር የነበሩ ዓለም አቀፍ ገበያዎች በሌሎች ተፎካካሪዎች እየተተካ መሄድና የዩክሬን ጦርነት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ የአውሮፓ አገሮች በሩሲያ ነዳጅና ምርቶች ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች ከሩሲያ ይልቅ ራሳቸው ላይ ጉዳቱ እየታየ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የአውሮፓ የኢኮኖሚ ማዕከል (ሞተር) ተደርጋ የምትወሰደው ጀርመን ያጋጠማት ሁኔታ ሲሆን፣ አገሪቱ በኖርድ ስትሪም የነዳጅ ማስተላለፊያ በኩል ከሩሲያ በምታገኘው የዝቅተኛ ዋጋ ነዳጅ ኢንዱስትሪዎቿን ስታበለፅግ የነበረ ቢሆንም ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መቀስቀስ በኋላ እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 2022 በኖርድስትሪም 1 እና 2 የነዳጅ ማስተላለፊያዎች ላይ በደረሰ ጥቃት የኃይል አቅርቦቱ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ በጥቃቱ ምዕራባዊያኑ ጣታቸውን ሩሲያ ላይ ለመቀሰር ጊዜ ያልወሰደባቸው ቢሆንም፣ አንድም ሩሲያ በምትሸጠውና የገቢዋ ከፍተኛውን ድርሻ በሚወስደው የምርት ማስተላለፊያዋ ላይ ጥቃት እንደማታደርስ ለማንም ግልጽ የነበረ ከመሆኑ በሻገር ጥቃቱን ተከትሎ ሲሞር ኸርሽ በተባለ አንጋፋ መርማሪ ጋዜጠኛና የፑሊዘር አዋርድ ተሸላሚ ‹‹How America Took out the Nord Stream Pipe Line’ በሚል ርዕስ በፌብሩዋሪ 2023 ባወጣው የምርመራ ሪፖርት ጥቃቱን አሜሪካ ስለመፈጸሟ በጠንካራ ማስረጃዎች ሞግቷል፡፡ የኋላ ኋላም ጉዳዩ ‹‹የውሾን ጉዳይ ያነሳ ውሾ ይሁን›› በሚል ምዕራባዊያኑ ለመሸፋፈንና ከሕዝቡ ለመሰወር ቢጥሩም የኢኮኖሚ ጉዳቱ ግን በሩሲያ ርካሽ የኃይል አቅርቦት ላይ የተንጠለጠሉት የጀርመንን ከፍተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲከስሩ፣ ከአሜሪካና እንግሊዝ ነዳጅ አቅራቢዎች ከሦስት እስከ አምስት ዕጥፍ እንዲገዙ አልያም ወደ ሌሎች አገሮች እንዲሰደዱ በማድረግ፣ አገሪቱን ኢንዱስትሪ አልባ ማድረጉ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡

የወታደራዊና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ (ተደማጭነት) የበላይነት እያከተመ መምጣት

ምዕራባዊያኑ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በፈጠሩት ወታደራዊ ጥምረት፣ የሚተኮስ ኢኮኖሚ እንዲሁም ባቋቋሟቸው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ ተቋማት አልንበረከክም ያሉትን አንድም በማዕቀብ ሽባ በማድረግ ወይም በቀጥታ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማንበርከክ የበላይነታቸውን ለማስቀጠል አስተማማኝ ሥልቶች አድርገው ሲወስዱ ኖረዋል፡፡ በምዕራባዊያኑ ወታደራዊ ጣልቃገብነትና ወረራ የኑሮ ደረጃቸው ከአውሮፓዊያኑ ጋር ይስተካከል የነበረው የሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ ዜጎች ምስክር ሲሆኑ እንደ ዚምባቡዌ፣ ቬንዙዌላና ኩባ ያሉ መመንደግ የሚችሉ አገሮች በተጣለባቸው ማዕቀብ አሁን ያሉበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ አንድም እየተቀየረ በሚገኘው የጦርነት ዓውደ ውጊያ ስልት፣ የኃይል አሠላለፍ ለውጥና የአዳዲስ አገሮች ወደፊት መምጣት ይህ ቀደም ሲል የምዕራባዊያኑ የበላይነት የሚንፀባረቅባቸው የወታደራዊና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ዘርፎች አዳዲስና የቀደመውን የዓለም ሥርዓት የሚቀናቀኑ ብሎም በአዲስ ለመተካት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ ለዚህ የምዕራባዊያኑን የወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት ለውጥ በታዳጊና መካከለኛ ልዕለ ኃያል አገራዊ ለሁለትና ሦስት አሥርት ዓመታት የዘለቁ ሥራዎች ሲሠሩ የነበረ ቢሆንም አሁንም ከዩክሬንና ጋዛ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ ባስተዋልናቸው ሁነቶች ማሳያ ላቅርብ፡፡

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት በቀሰቀሰች ማግስት እንግሊዝን ጨምሮ አሜሪካና አውሮፓ ኅብረት በዋናነት በነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ፣ በወርቅ ንግድ፣ በአላቂና ትላልቅ የኢንዱስትሪ ምርቶቿ ላይ ማዕቀብ ከመጣላቸው ባሻገር የዓለም አቀፉን ስዊፍት የገንዘብ ማስተላለፊያ እንዳትጠቀም ጭምር መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት የተሳሰርን አንዱ በሌላው ላይ የኢኮኖሚ፣ ንግድ እንዲሁም ቴክኖሎጂ ጥገኛ በሆነበት ዓለም የአሜሪካና ከአትላንቲክ ባሻገር የሚገኙት አጋሮቿ በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ የሚፈልጉትን ውጤት እንዲያመጣ ሌሎች አገሮች የግድ ማዕቀቡን መደገፍና መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን የአሜሪካና ምዕራባዊያኑ አጋር ተብለው የሚጠቀሱት እንደ ሳዑዲ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ህንድና ብራዚል በአንድ በኩል ከምዕራባዊያኑ ጋር በዓይነ ቁራኛ የሚተያዩት እንደ ቻይና፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያና አብዛኛው የምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪካ አገሮች ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት በማጠናከር ማዕቀቡ እንዳይሠራ ብቻ ሳይሆን ሩሲያዊያኑ ይበልጥ አትራፊ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የምዕራባዊያኑ ጥምረት ሩሲያ ላይ ጫና ለማድረግ ያቀረቧቸው የውሳኔ ሐሳቦች (ሪዞሊሽኖች) በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ያገኙትን የድጋፍና ተቃውሞ ድምፅ በማየት ምን ያህል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችላ እንዳላቸውና ያላቸው ተቀባይነት እያከተመ ስለመሄዱ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ በጣም ደካማና ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላም በድኅረ ቅኝ ግዛት ኢምፔሪያሊዝም (Neo-Colonial Imperialism) የፊጥኝ ታስረው በነበሩ የአፍሪካ አገሮች የተሰጡ ድምፆችን እንመልከት፡፡

ጦርነቱ በጀመረ በቀጣዩ የማርች 2/2022 ወር ‹‹Russian aggression against Ukraine›› በሚል የቀረበውን ሞሽን 28 አገሮች ሲደግፉት፣ 17 አገሮች ተዓቅቦ፣  ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት አገሮች በአዳራሹ አልተገኙም፣ ኤርትራ ብቻዋን ተቃውማለች፡፡ እ.ኤ.አ. አፕሪል 7 ቀን 2022 ሩሲያን ከኅብረቱ የሰብዓዊ መብት አባላነት ለማገድ በቀረበው ሪዞሊሽን አሥር አገሮች ውሳኔውን ሲደግፉ፣ 24 የአፍሪካ አገሮች ተዓቅቦ ሲመርጡ 11፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት አገሮች ተቃውመው፣ 11 በአዳራሹ አልተገኙም፡፡ አንድ የመጨረሻ ልጨምር፣ ፌብሩዋሪ 23 ቀን 2023 በተጠራው የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በተመድ መርሆች መሠረት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ለቀረበው ሪዞሊሺን 30 አገሮች ደግፈው፣ 15 በተዓቅቦ፣ ሁለት አገሮች ተቃወሞ፣ እንዲሁም ሰባት አገሮች በአዳራሹ አልተገኙም፡፡ እነዚህ በአጠቃላይ ለተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ከቀረቡ አራት ሪዞሊሽኖች ሦስቱ የሚያሳዩት አፍሪካዊያን ለምዕራባዊያኑ ፍላጎት ተገዢነት እንቢ ማለታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የምዕራባዊያኑን ተሰሚነት መውረድ መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዛን ጦርነት በተመለከተ በቀረቡ የፀጥታው ምክር ቤትና የጠቅላላ ጉባዔ ሪዞሊሽኖች በመጀመሪያ አሜሪካና አውሮፓዊያኑ፣ በመቀጠልም አሜሪካና እንግሊዝ በመጨረሻም አሜሪካ ብቻ ድምፅን በድምፅ እየሻረች ውሳኔውን ውድቅ ስታደርግ ለተመለከተ ምን ያህል ዓለም አቀፍ መገለል እንደደረሰባቸው ይረዳል፡፡

የወታደራዊ የበላይነት ማክተም

የአሜሪካ ጦር ከኔቶ አጋሮቹ ጋር ለ17 ዓመታት በከፍተኛ የወታደራዊ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች በአፍጋኒስታን ተራሮች ክላሽና ቀላል መሣሪያዎችን ከታጠቀው የታሊባን ኃይል ጋር ሲያደርግ የነበረው ጦርነት በድንገትና ባልታሰበበት ሁኔታ ከአገሪቱ በመውጣቱን ተከትሎ፣ ታሊባን አፍጋኒስታንን ሲቆጣጠር ዓለም በአግራሞት ያስተዋለበት የኦገስት 30 ቀን 2021 ክስተት ለዚህ ርዕስ እንደ መነሻ እጠቀመዋለሁ፡፡ በእርግጥ አሜሪካኖቹ እንዲህ ያለ ወታደራዊ ሽንፈት ሲገጥማቸው የመጀመሪያ አለመሆኑ እ.ኤ.አ. የማርች 1973 የቬትናም፣ እንዲሁም ለሁለት ቀናት ብቻ ተዋግተው የተሸነፉበት የ1993 ሞቃዲሾ ጦርነት (Black Hawk Down) ጥሩ ማሳያዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ የአሜሪካ ዓመታዊ የጦር በጀት 886 ቢሊዮን ዶላር በደረሰበት፣ በዓለም ላይ ከሚገኙ አሥር የመጀመሪያ ረድፍ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ አምራቾች ስድስት የሚሆኑት ባለቤት፣ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ ጦርነትና የባህር ኃይል ተገዳዳሪዎቻቸውን ለአሥርና ከዚያም በላይ ዓመታት ጥለው በሄዱበት በዚህ ዘመን፣ በኢራቅና በሶሪያ የሚገኙ ቤዞቻቸውንና በቀይ ባህር የሚያልፉ የንግድና ወታደራዊ መርከቦቻቸውን ከኢራን የእጅ አዙር ጥቃቶች መከላከል አለመቻላቸው ወታደራዊ ኃያልነታቸው ለማብቃቱ ጠንካራ ማሳያዎች ናቸው፡፡

የጋዛ ጦርነት በኦክቶበር 7 ቀን 2023 ከጀመረበት እስከ ፌብሩዋሪ 4 ቀን 2024 ባሉ አራት ወራት ብቻ በኢራቅ፣ ሶሪያና ጆርዳን በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ካምፖች 170 ጥቃቶችን ያስተናገዱ ሲሆን በአጠቃላይ 180 ወታደሮች መጎዳታቸውን (137 አካባቢ ለድህረ ጥቃት የአዕምሮ ጉዳት (Traumatic Brain Injury) መዳረጋቸው) የፔንታጎን ቃል አቀባይ ፌብሩዋሪ 13 ቀን 2014 በሰጠው መግለጫ አመላክቷል፡፡  ይባስ ብሎም የኢራቅ መንግሥት የአሜሪካ ጦር ከአገሪቱ እንዲወጣ በፓርላማው በኩል ውሳኔ ያሳለፈ ከመሆኑም በላይ እንደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኳታርና ሳዑዲ ያሉ ላለፉት 50 ዓመታት አካባቢ በአሜሪካኖቹ የደኅንነት ጥበቃ ሥር የቆዩ የገልፍ አገሮች በአገሮቻቸው ከሚገኙ የጦር ቤዞች በመነሳት በኢራን የኢራቅ፣ የሶሪያ እንዲሁም የየመን ኃይሎች ላይ ለሚደረግ ጥቃት ተባባሪ እንደማይሆኑ ለፔንታጎን ሹማምንት ማሳወቃቸውን ‹‹POLITICO›› ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ ባሻገር ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ በየመን የሚገኘው የሁቲ ኃይል በቀይ ባህር (በባብኤል መንደብ) በሚያልፉ የአሜሪካ፣ እስራኤል እንዲሁም የእንግሊዝ መርከቦች እንዳያልፉ በጣለው ማዕቀብ ከእነዚህ አገሮች ጋር ግንኙነት ባላቸው ወታደራዊ፣ የንግድና የሎጂስቲክስ 45 መርከቦች ላይ ጥቃት የሰነዘረ ሲሆን አንድ የእንግሊዝ መርከብ መስመጡ ይታወቃል፡፡ አሜሪካ ‹‹Operation Prosperity Guardian›› በሚል ደርዘን ከሚሆኑ አጋሮቿ ጋር በመጣመር የሁቲን ጥቃት ለመከላከልና መርከቦቹን ለማሳለፍ የጀመረችው ጥረት ውጤት ማምጣት አልቻለም፡፡ ይህ እንዲሆን ያደረገው በዓለም የባህር ላይ ጥቃቶች በሁቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የረዥም ርቀት ባለስቲክ ሚሳይልና የአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች (Kamakazi Drones) አቅም መሆኑ ይገለጻል፡፡ በአጠቃላይ የዛሬ አሥር ዓመት ለማሰብ እንኳን የሚያዳግቱ የአሜሪካና አጋሮቿን የወታደራዊ አቅም የሚፈታተኑ ብሎም አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁነቶች መስተዋላቸው የወታደራዊ የበላይነቱ ማክተሙ ማሳያ ናቸው፡፡

የሚዲያ የበላይነት እየተሸረሸረ መሄድ

“The one who controls the Narration controls everything” የአሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ አገሮች በከፍተኛ ሁኔታ ከሚመፃደቁበትና ሌላውን ከሚያንኳስሱባቸው ጉዳዮች አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ፈጥረናል የሚሉት የሚዲያ ነፃነትና ብዝኃነት ነው፡፡ በዚህም በማንኛውም ጉዳይ መንግሥትና አሠራሩን ያለ ምንም ፍርኃት በርብሮ ለሕዝቡ እውነታውን ያሳውቃል የሚሉት ሚዲያና የተቃኘበት አሠራር ለብዙዎቻችን እንደ መልካም ምሳሌ ብሎም መመዘኛ አድርገን ስንወስድ እንታያለን፡፡ ይሁን እንጂ የአደባባይ ምሁር፣ ፈላስፋ፣ እንዲሁም የቋንቋ ፕሮፌሰሩ ኖአም ቾምስኪ (Noam Chomsky) ከጓደኛው ‹‹Edward S.Herman›› ጋር በመሆን “Manufacturing Consent: The Political Economy of the Mass Media” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ ላነበበ የአሜሪካና ምዕራባዊያኑ ሚዲያ እነሱ እንደሚሉት የመንግሥትን ኃይል የሚቆጣጠሩበት ሦስተኛ ክንፍ (ከተወካዮች ምክር ቤትና ፍርድ ቤቶች ቀጥሎ መሆኑ ነው) ሳይሆን፣ ሕዝቡን በመንግሥት ፖሊሲና ፍላጎት የሚነዱበት ብሎም ለትልልቅ ኮርፖሬሽኖች ባርያ የሚያደርጉበት የሸፍጥ ተቋማት መሆናቸው በማያዳግም መንገድ አሳይቷል፡፡

እነዚህ ሚዲያዎች በጣም ፅንፍ የያዙና የተለያዩ የሚመስሉን የቀኝ ዘመሙ (Fox News) ወይም (CNN) እና (MSNBC) ታማኝነታቸው ለመንግሥትና ስፖንሰር ለሚሆኗቸው ከመድኃኒት እስከ ጦር መሣሪያ አምራች ኮርፖሬሽኖች እንጂ፣ እውነትን ለማወቅ ለሚዳክረው ሕዝብ አለመሆኑን ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠሩ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ለመረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች የኢራቁ ሳዳም ሁሴን ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ እንዳለው (አሜሪካኖቹ ከወረራው በኋላ እንደሌው አረጋግጠዋል)፣ አንድም ኢራቃዊ ባልተሳተፈበትና ኢራቅ እጇ በሌለበት የሴፕቴምበር 11 የሽብር ጥቃት ጋር በማያያዝ ሕዝቡን ለጦርነት ቀስቅሰዋል፣ ከዝርፊያና ወረራውም ተካፋይ ነበሩ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢንተርኔትና ስማርት የእጅ ስልኮች መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ ይህ በአሜሪካና በተቀረው ዓለም በመንግሥታት ወይም ኮርፖሬሽኖች ቁጥጥር ሥር የነበረው የመረጃና የሚዲያ የበላይነት እየፈራረሰ መጥቷል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ፣ በምዕራቡና በተቀረው ዓለም ከኮርፖሬት ሚዲያዎች ይልቅ በዩቲዩብ፣ ቲክቶ፣ የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ (X) ወይም ፌስቡክ የሐሳብ መንሸራሸሪያና የመረጃ ምንጮች ሆነዋል፡፡ ይህም ምዕራባዊያኑ እንደ ቀድሞው በማንኛውም ጉዳይ ላይ ሕዝቡ ማወቅ ያለበትን ሳይሆን፣ እነሱ የሚፈልጉትን ለመንገር አዳጋች እንደሆነባቸው እየተመለከትን ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ የቀድሞው የ‹‹Fox News›› ጋዜጠኛና የቀኝ አክራሪው ታከር ካርልሰን በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የምዕራባዊያኑ ሚዲያዎች ከሚግቱን ውጪ ያለውን የሩሲያ እውነት ከፕሬዚዳንቱ እንስማ በሚል ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ (በዩቲዩብና ኤክስ የተለቀቀ)፣ አሜሪካና ምዕራባዊያኑ በጦርነቱ መነሻ (ታሪካዊና ጂኦ ፖለቲካዊ) ብሎም አጠቃላይ ትርክት ላይ የነበራቸውን የበላይነት ሚዛን ማዛባቱ፣ ይህም በቀጣዩ ምርጫ አሁን በሥልጣን ላይ ላለው ፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር አደጋ ጥሎ ማለፉን ተመልክተናል፡፡ ሌላው የሚዲያ የበላይነታቸውን ያንኮታኮተው በአብዛኛው ወጣት ትውልድ ተወዳጅ እየሆነ የመጣው ቲክቶክ ነው፡፡  

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካና አውሮፓ የመምረጥ ዕድሜ ላይ የሚገኘው አዲሱ ትውልድ (Gen-Z) መካከለኛው 1990ዎቹ እስከ 2010 መጀመሪያዎቹ የተወለዱ) በአብዛኛው ከዲጂታል ዓለም ጋር የተቆራኘ ባህሪ ያላቸው በመሆኑ፣ (Traditional Media) ለሚባሉት ተቋማት ፕሮፓጋንዳ የሚመቹ አልሆኑም፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቦቻቸውን በኮርፖሬት ሚዲያዎቻቸው ለሚነዱት መንግሥታት በሥጋት ከመታየቱ ባሻገር፣ በቀጣይ ለሚደረጉ ምርጫዎች መቀስቀሻ ለሆኑ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ከባህላዊው ሚዲያ ሽፋን በመሻገር አገሮቻቸው በዓለም መድረክ የሚያደርጉትን ከሞራልና የዓለም አቀፍ ሕጎች ተፃራሪ ድርጊቶች በቀላሉ እንዲመለከቱ አስችሏል፡፡ በዚህም የአሜሪካ ከፍተኛ የሕግ አውጪ ምክር ቤት የሚመፃደቁበትን የነፃ ሚዲያ መርህ በሚፃረር ሁኔታ ቲክቶክን አንድም በአሜሪካ ኩባንያ እንዲገዛ፣ ወይም እንዲታገድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹if you can’t buy them, ban them›› እንዲሉ!

የፅንፈኛ ቀኝ አክራሪ ፖለቲካ ማቆጥቆጥ

የባለአንድ ዋልታው የዓለም ሥርዓት ዘሩን የተከለው በአውሮፓና አሜሪካዊያኑ ቁጥጥር ሥር የዋለው የቀኝ አክራሪ ዘረኛና ሕዝበኛ (populist) ሥርዓቶች የነበሩት እንደ የጀርመኑ ናዚና የጣሊያኑ ፋሽስት ሥርዓት በአውሮፓ፣ እንዲሁም የጃፓንን ኢምፔሪያሊዝም በምሥራቅ በማሸነፍ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሸናፊው የሊበራል ኢምፔሪያሊዝም አሁን ላለው ለአውሮፓዊያን የሠራተኛ መደብ የሚመች አልሆነም፡፡ በተለይም የአውሮፓ ኅብረት መፈጠር ‹‹ርካሽ የሰው ጉልበት›› (ለእኔ የሰውን ጉልበት ርካሽ ማለት ነውር ነው) እንዲትረፈረፍ ማድረጉ፣ የምርትና አገልግሎት ዝውውር በአንፃራዊነት ነፃ በሆኑ ከውጭ የሚመጡ ምርትና አገልግሎቶች በአውሮፓና አሜሪካ የገበያዎች ላይ የበላይነት እየያዙ መምጣታቸው (በቅርቡ የአሜሪካ ካዝና ቁልፍ ያዥ ጃኔት ያለን በሚያስቅ ሁኔታ ቻይናን ከመጠን በላይ በማምረት መክሰሷ ጥሩ ማሳያ ነው) እንዲሁም ሉላዊነት (Globalization) ወለድ የባህል ተፅዕኖ (Traditionalist) የሆነውን የአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ሕዝብ ቀስ በቀስ እንዲማረር ብሎም ‹‹በገዛ አገራችን በሌሎች እየተዋጥን ነው›› የሚል ዕሳቤ እያደገ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎ በምዕራቡ ዓለም የቀኝ አቅራሪ ሕዝበኛና ዘረኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያቆጠቆጡ እንዲመጡና አሁን አሁን ደግሞ ሥልጣን እንዲይዙ (በኔዘርላንድ፣ ሃንጋሪ፣ ጣሊያን) ከማስቻሉ ባሻገር በጀርመን የቀኝ አክራሪና አፍቃሪ ናዚ የሆነው (Alternative For Germany – AFD)፣ በፈረንሣይ በማሪን ላፔን የሚመራው ‹‹National Rally Group›› እንዲሁም የስፔኑ ‹‹VOX›› ሕዝባዊ ቅቡልነታቸው ከፍ እያለ መምጣቱ ታይቷል፡፡ በተመሳሳይ በአሜሪካ ባለፉት ሦስት ወራት እየተደረጉ ባሉ የቅድመ ምርጫ አስተያየቶችl የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ በሚባሉ ስቴቶች ቀዳሚነቱን እያሳየ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በጁን 2024 በሚካሄደው የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ብዙ ወንበር ሊይዙ እንደሚችሉ በስፋት እየተተነበየ ይገኛል፡፡ ይህ ለምዕራባዊያኑ ኢምፔሪያሊስት የፖለቲካና ኢኮኖሚ የበላይነት የሬሳ ሳጥን ላይ የመጨረሻውን ሚስማር የሚመታና የሚበታትን ነው የሚል አረዳድ አለኝ፡፡

ይህንን ካልኩ ዘንዳ ይህንን ሐሳብ መሞገት ለሚፈልግ (ወዳጄን ጨምሮ) ወገን በዚህ ጋዜጣ ላይ መልሱን እንዲያቀርብ እየጋበዝኩ፣ ይህንን ለሚያነቡ ፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪ አካላት በቀጣይ እየተፈጠረ ለሚገኘው አዲስ ዓለም አቀፋዊ የኃይል አሠላለፍ ሁኔታ ኢትዮጵያ ምን ያህል ዝግጁ ናት? በሚል አጭር ነገር ግን ሰፊ መልስ የሚሻ ጥያቄ ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...