Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥ ባንኮች ውህደትንና የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ሁኔታን ለመወሰን የተረቀቀው አዋጅ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባንክ ባለፈው ዓርብ ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበው የባንክ ሥራ አዋጅ አዲስ ድንጋጌዎች ይዟል፡፡ በዚህ አዋጅ ማሻሻያ ውስጥ እንደ አዲስ የተካተቱ በርካታ አንቀጾች ቢኖሩም፣ የባንኮች ውህደትንና የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅዱት ድንጋጌዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 

በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ከተካተቱት ዋና ዋና ድንጋጌዎች መካከልም፣ ባንኮች ሊዋሃዱ እንደሚችሉበትን መንገድ የሚዘረዝረው ይገኝበታል። አንድ ባንክ ከብሔራዊ ባንክ የጽሑፍ ይሁንታ ሳያገኝ በውዴታ ወደ ውህደት መግባት የሌለበት መሆኑን በመጥቀስ የሚጀምረው ድንጋጌ የውህደት ሕግ ያስፈለገበትንም ምክንያት በዝርዝር አመላክቷል፡፡ 

ችግር ያለበትን ባንክ ለመታደግ ወይም የበለጠ አዋጭና ጠንካራ ባንክ ለመፍጠር በብሔራዊ ባንክ በሕግ የተደነገገ ውህደት ሊፈቅድ እንደሚችል እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓት መረጋጋትን ለማረጋገጥ አንድ የአገር ውስጥ ባንክ በተለየ ሁኔታ በውጭ ባንክ ወይም በሌላ የአገር ውስጥ ባንክ እንዲገዛ ማፅደቅ የሚችል መሆኑን አስፍሯል፡፡ 

በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ የሚፈጸም የባንክ ውህደትም ሆነ ግዥ የባንኩን ጤናማነት፣ የፋይናንስ ሥርዓት መረጋጋትን፣ የፋይናንስ አገልግሎትና የሸማቾች መብትና ፍላጎትን፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ውድድርና ቅልጥፍናን መሠረት በማድረግ እንዲሁም የአክሲዮን ድርሻ ገደብና አግባብነት ያለው የብሔራዊ ባንክ መመርያን በማክበር እንደሚሆንም ይገልጻል፡፡

የባንኮች ውህደትንና በግዥ የሚተላለፉበትን መንገድ በሚገልጸው ረቂቅ አዋጁ፣ ‹‹ማንኛውም የውህደት ወይም የግዥ ፕሮፖዛል የሚወሰነው በባንኮች ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ነው›› ይላል፡፡ የዚህ ድንጋጌ አተገባበርና ዝርዝር ጉዳዮችም በብሔራዊ ባንክ መመርያ እንደሚወሰን አመላክቷል። ማንኛውም ውህደት ወይም ግዥ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም አግባብነት ያላቸው የመንግሥት አካላት ከብሔራዊ ባንክና ከሚመለከታቸው ባንኮች ጋር የመተባበር ኃላፊነትን እንዳለባቸውም ጠቅሷል፡፡ 

የውህደትና ግዥ ግብይቶች ዝቅተኛ ሁኔታዎችና መሥፈርቶች በብሔራዊ ባንክ በሚወጣ መመርያ እንደሚወሰኑ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉልህ የሆነ የባለቤትነት ድርሻ ማስተላለፍ፣ በባንክ ውስጥ ጉልህ የሆነ የባለቤትነት መብት የሚያመጣ ማንኛውም የአክሲዮን ዝውውር ወይም ግዥ በአክሲዮን መዝገብ ከመመዝገቡ በፊት በብሔራዊ ባንክ የሚፀድቅ ስለመሆኑም በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ተካቷል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ ጉልህ የሆነ የባለቤትነት ለውጥ ለማድረግ የቀረበውን ማንኛውንም ሐሳብ ውድቅ የማድረግ ወይም በእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ላይ የመምረጥ መብትን ከመጠቀም የመከልከል ሥልጣን እንዳለውም ጠቅሷል፡፡ 

በሐሰተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ የባለቤትነት ዝውውር ዋጋ እንደማይኖረው፣ እንዲሁም ጉልህ የሆነ የባለቤትነት መብትን ለማስተላለፍ ዝቅተኛ ሁኔታዎችና መሥፈርቶች ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣቸው መመርያዎች እንደሚወሰኑ ይገልጻል።

የንብረትና የዕዳዎች ማስተላለፍን በተመለከተም ባንኮች ንብረቶችንና ዕዳዎችን ለሌላ ባንክ ማስተላለፍ እንደማይችሉ እንዲሁም በተለመደው የሥራ ሒደት ካልሆነ በቀር የብሔራዊ ባንክ የጽሑፍ ፈቃድ ሳይኖር የንግድ ሥራውን ለመሸጥም ሆነ ለማስወገድ ማንኛውንም ስምምነት ማድረግ እንደማይችሉም ተጠቅሷል፡፡ 

‹‹በብሔራዊ ባንክ በዝውውሩ ውስጥ የተሳተፉትን የግል ባንኮች ጤናማነት፣ የፋይናንስ አገልግሎት ደህንነትን፣ የሸማቾች ጥቅምና የፋይናንስ ሥርዓት መረጋጋትን ይጎዳል ተብሎ ከታመነ የንብረትና የዕዳ ማስተላለፍን አይፈቀድም፤›› የሚል ድንጋጌም በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡ 

ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነትን የሚገልጸው ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባንኮች ወደ ውህደት መግባት ይኖርባቸዋል የሚለውን ጠንከር ያለ አመለካከት ወደ ተግባር ለመቀየር ጠቃሚ መሆኑን ያመለክታል። በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ ከውጭ ባንኮች ጋር ሊኖር ስለሚገባው ጥምረትና ውህደት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ይገልጻል። በተለይ የውጭ ባንኮች መግባት ጋር በተያያዘ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነው ለመወጣት የአገር ውስጥ ባንኮች ተዋህደው መሥራት እንዳለባቸው ሲነገር የቆየ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ባንክም የባንክ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል ባዘጋጀው አዲስ ረቂቅ ውህደትን የተመለከተው አንቀጽ እንዲካተት የተፈለገበት አንዱ ምክንያት በግዴታም ቢሆን አንዳንድ ባንኮች ካልተዋሀዱ በቀር ተወዳዳሪ ይሆናሉ ተብሎ ስለማይታመን እንደሆነ የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ 

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡን የፋይናንስ ባለሙያ ጨምረው እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ አሁን ባለው ሕግ ባንክ ለማቋቋም አምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መያዝ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ አሁን ካለው የገንዘብ የመግዛት አቅምና ወደፊት ከሚጠበቀው ውድድር አንፃር ሲታይ ይህንን የባንክ መመሥረቻ ካፒታል መጠን ሊያሳድደግ ይችላል የሚል ግምት ስላለም ብዙዎቹ ባንኮች ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ለማሟላት የሚቸገሩ ስለሚሆን አሁን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ውህደት እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ካልሆነም ወደፊት አስገዳጅ ሊያደርገው እንደሚችል እምነት እንዳላቸው ያክላሉ፡፡ 

በብሔራዊ ባንክ በባንክ ሥራ የማሻሻያ አዋጅ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ሌላው አዲስ ድንጋጌ የውጭ ባንኮች አግባብን የተመለከተ ድንጋጌ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚፈልጉ የውጭ ባንኮች መልካም ስምና የገንዘብ አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ሊገቡ የሚችሉትም በከፊል ወይም በሙሉ በባለቤትነት የተያዘ የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ ወይም ተወካይ ቢሮ በመክፈት እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ ከዚህም ሌላ የአገር ውስጥ ባንኮችን አክሲዮን ገዝተው መሥራት እንደሚችሉ ይፈቅዳል፡፡ 

ከውጭ ባንኮችና በውጭ አገር ከሚገኙ የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች በተጨማሪ፣ የውጭ አገር ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ ባንክ ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ሊይዙ እንደሚችሉ ይጠቅሳል፡፡ 

ስትራቴጂካዊ ተብለው የተጠቀሱ ባለሀብቶች በነባር ወይም በአዲስ የአገር ውስጥ ባንክ ውስጥ የሚኖራቸው የአክሲዮን ድርሻ ከተመዘገቡት የባንኩ አጠቃላይ አክሲዮኖች ውስጥ ሰላሳ በመቶ የሚደርስ ይሆናል። ስትራቴጂክ ያልሆኑ የውጭ አገር ባለሀብቶችና የውጭ ሕጋዊ አካላት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ ባንክ ውስጥ ሊይዙ የሚችሉት የአክሲዮን ድርሻ እንደቅደም ተከተላቸው አምስት በመቶና አሥር በመቶ ብቻ እንደሚሆን ረቂቁ ያመለክታል፡፡ 

ሆኖም የውጭ አገር ዜጎችና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለቤት የሆኑባቸው ድርጅቶች ከባንኩ ጠቅላላ አክሲዮኖች ውስጥ እስከ 40 በመቶ ድርሻ ሊይዙ እንደሚችሉ አመላክቷል። 

እንዲህ ያለ የኢንቨስትመንት ገደብ ቢኖርም ለኢኮኖሚው ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ወይም በችግር ውስጥ ያለን ባንክ ችግር ለመፍታትና የፋይናንስ መረጋጋትን ለማስጠበቅ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በልዩ ሁኔታ ሊያስተናግድ የሚችልበትን አሠራር ሊከተል እንደሚችል ቃቂቁ ያመለክታል፡፡ እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጡት መሥፈርቶች ባሻገር የሚገቡት የውጭ ባንኮች አቅምና ጥንካሬ እንዲሁም መልካም ስምና በገንዘብ ረገድ ያላቸው አቅም ታይቶ የአገር ውስጥ ባንኮችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መግዛት የሚችሉበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ረቂቁ አዋጁ ይገልጻል።

የውጭ አገር ዜጎችና በውጭ አገር የተመሠረቱ የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በውጭ ዜጎች የተያዙ ባንኮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት በውጭ ምንዛሪ እንደሚሆን ረቂቁ ደንጋጌው ያመለክታል።

ይህ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ በውጭ አገር ዜጎች በከፊል ባለቤትነት የተያዙና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለቤት የሆኑባቸው ድርጅቶች በአጠቃላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት የአክሲዮን ድርሻ መጠንን በውጭ ምንዛሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመጠቀም ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ። 

ሆኖም የውጭ አገር ዜጎችና፣ የውጭ አገር ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች በየበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚገኙትን የትርፍ ድርሻ በኢትዮጵያ ብር እንደገና ኢንቨስት ሊደረጉ እንደሚችሉ የሚገልጽ ድንጋጌ በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡ 

በውጭ አገር ዜጎች በባንክ ኢንቨስትመንት የሚያገኙት የትርፍ ድርሻና የውጭ አገር ሠራተኞች ደመወዝና ከአክሲዮን ሽያጮች ወይም ከባንክ ክፍያ የሚገኘው ገቢ በብሔራዊ ባንክ መመርያና ሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕጎች የሚወሰን ስለመሆኑ ረቂቁ ያመለክታል፡፡ 

በውጭ አገር ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ባለቤትነት የተያዙ የውጭ አገር ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ማንኛውንም ገቢ በመጀመሪያ በውጭ ምንዛሪ የተከፈለውን የአክሲዮን ድርሻ ወደ አገር ቤት መመለስ እንደሚችልም ይፈቅዳል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ የውጭ ባንክ ወኪል ወይም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ ለባንክ ሥራ ዓላማው ንብረት ሊኖረው እንደሚችል፣ የተያዙ ንብረቶችን ጨምሮ የሌሎች ንብረቶች ባለቤትነትም አግባብ ባለው የአገሪቱ ሕግ መሠረት እንደሚወሰን ይገልጻል። 

ረቂቅ አዋጁ አክሎም፣ የውጭ አገር ዜጎች ወይም የውጭ አገር ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች በባንክ ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ከማፍሰሳቸው በፊት የማጣራት ተግባር እንደሚከናወን፣ በተጨማሪም ፈቃድ የሚሰጣቸው የውጭ ባንኮች ቅርንጫፎችና ቅርንጫፎች ቁጥር ገደብና የጠቅላላ የባንክ ሥርዓት የውጭ ባንኮች ንብረት መቶኛ ገደብ እንደሚኖረው ይጠቅሳል፡፡ 

ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር በተያያዘ ሌላው በረቂቁ የተመለከተው ጉዳይ የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ ለመመሥረት የሚያስፈልገው ዝቅተኛው የመነሻ ካፒታል በብሔራዊ ባንክ የሚወስን መሆኑ ነው።

አንድ ባንክ በውጭ አገር ዜጎችም ሆኑ በአገር ውስጥ ነዋሪ ካልሆኑ ኢትዮጵያውያን የተውጣጡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊኖራቸው እንደሚችል፣ ለዚህም አፈጻጸም ብሔራዊ ባንክ ተስማሚና ትክክለኛ መመዘኛዎችን ዝርዝር የያዘ መመርያ እንደሚያወጣ ይጠቅሳል።

ረቂቅ አዋጁ የውጭ አገር ዜጎች በባንኮች ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የተመለከቱ ድንጋጌዎችንም ያካተተ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የውጭ ዜጎች ለዋና ሥራ አስፈጻሚና ለከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ የሥራ መደቦችና ልዩ ዕውቀት ወይም ዕውቀት ለሚፈልጉ የሥራ መደቦች በቅጥር ወይም በሠራተኛ ዝውውር በኮንትራት ቢበዛ ለአምስት ዓመት እንዲቸሩ ሊፈቀድላቸው ይችላል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በባንክ ውስጥ የሚኖራቸው ከፍተኛው ቁጥር በመቶኛ በብሔራዊ ባንክ በመመርያ እንደሚወሰን ይገልጻል።

አንድ የውጭ አገር ዜጋ ሊቀጥርም ሆነ ሊመደብ የሚችለው ብሔራዊ ባንክ የባንኩን የቅጥር ሒደቶች በማጣራትና በሚፈለገው የሥራ መደብ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ብቻ ነው።  የውጭ አገር ሠራተኛ የተመደበበት የአምስት ዓመት ገደብ ካለቀ በኋላ ግን የሥራ መደቡ በኢትዮጵያ ባለሙያ ተተክቶ ሊሠራ እንደሚገባም ደንግጓል፡፡ 

ለውጭ አገር ዜጋው ተተኪ ካልተገኘ ግን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ሊራዘም ይችላል። ለእንደዚህ ዓይነት የሥራ መደቦች ብቃት፣ ልምድ፣ ዕውቀት ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ባንክ የተረጋገጠ ነው። 

አንድ የውጭ አገር ዜጋ ወይም የውጭ አገር ዳይሬክተር በብሔራዊ ባንክ የተደነገገውን ብቃትና ትክክለኛ ፈተና ማለፍ ያልቻለ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነና ወይም በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ባንክ ወዲያውኑ ከሥልጣኑ የሚያስወግደው መሆኑም ተገልጿል፡፡  

በኢትዮጵያውያን ዜጎች መሙላት አስቸጋሪ መሆኑ ከተረጋገጠ ብሔራዊ ባንክ የአገልግሎት ጊዜውን ቢበዛ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በልዩ ሁኔታ ማፅደቅ ይችላል። በዚሁ ጉዳይ ሌሎች ተያያዥ አንቀጾች ተካተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባንክ ሥራ ጋር በተያያዘ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ አምስት ዓበይት ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ አደረጃጀትን ይለውጣል የተባለ አዲስ አዋጅም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ 

በዚህ ሳምንት ማሻሻያ የተደረገባቸው ናቸው የተባሉት መመርያዎች በዋናነት ባንኮች ከሚሰጧቸው ብድሮች ጋር በተያያዘ መከተል የሚገባቸውን አሠራር ቁጥጥር የሚያመለክት ጠንከር ያሉ ድንጋጌዎችን የያዙ ናቸው፡፡

እነዚህን ማሻሻያዎች በተመለከተ ባንኩ ባወጣው መግለጫ ማሻሻዎቹ የተደረጉት የባንክ ሥራን መቆጣጠር ለማስቻል ነው፡፡ መመርያዎቹን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም በሥራ ላይ ያለውን የባንክ ዘርፍ የቁጥጥር ሥርዓት ከዓለም አቀፍ መርሆዎችና ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲሁም የባንክ ዘርፍ ከደረሰበት ዕድገት ጋር የተጣጣመ በማድረግ ዘርፉ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሆን ለማስቻል መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

ማሻሻያ የተደረገባቸው አምስቱ መመርያዎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የሚመደቡ ሲሆን፣ ‹‹የብድር ተጋላጭነት ጣሪያ ስለመወሰን፣ ከባንኩ ጋር ዝምድና (ግንኙነት) ባላቸው ወገኖች አማካይነት ስለሚኖር የብድር ተጋላጭነት›› እንዲሁም ‹‹ስለንብረት ምደባና ለተዛማጅ ሥጋቶች ስለሚያዝ የመጠባበቂያ ፕሮቪዥን›› በተመለከተ የወጡ መመርያዎች ናቸው። ዓላማቸውም የባንኮችን የአደጋ ተጋላጭነት መቀነስና የሥጋት አስተዳደር ማዕቀፋቸውን በማጠናከር የበለጠ ጤናማና አስተማማኝ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብሏል።

ሁለተኛው ደግሞ በባንክ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አካላት ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ መሥፈርቶችና የኩባንያ አስተዳደርን የሚመለከቱ ናቸው። በተሻሻለው መመርያ መሠረት ማንኛውም ባንክ ለአንድ ወይም ተያያዥነት ላላቸው ደንበኞች የሚኖረው አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከሃያ አምስት በመቶ (25%) እንዳይበልጥ ገድቧል፡፡ ‹‹ይህ መመርያ ተያያዥነት ያላቸው አካላት እንደ አንድ የባንክ ተበዳሪ ሆነው እንዲቆጠሩ ይደነግጋል፤›› በሚል ገልጾታል።

ሌሎች ማሻሻያ የተደረገባቸው ጉዳዮችን በተመለከተም በመግለጫው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት በማንኛውም ጊዜ የሚኖረው አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከ15 በመቶ እንደማይኖርበት አስቀምጧል፡፡

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት በሙሉ በማንኛውም ጊዜ የሚኖር አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንክ ጠቅላላ ካፒታል ከ35 በመቶ እንዳይበልጥ፣ አንድ ባንክ ተዛማጅ ከሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ከማናቸውም ተዛማጅ ካልሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ተግባራዊ በሚደረግ ሁኔታዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልክ እንዲሆንና ከዚህ በተለየ ሁኔታ እንዳይፈጸም የሚደነግግ ነው፡፡

ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት ጉዳይ ደግሞ ካፒታል ከአምስት በመቶ (5%) በላይ የሆኑትንና የውል ማሻሻያ የተደረገባቸውን ብድሮች አጠቃላይ መረጃ በየጊዜው ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንዲደረግ የሚያስገድድ ነው፡፡

በባዝል መርህ መሠረት አንድ ወቅቱን ጠብቆ መከፈል ያልቻለና ለተበላሸ ብድር የተቀመጠውን መሥፈርት ያሟላ ብድር ለብድሩ መያዣነት የቀረበው ዋስትና ምንም ይሁን ምን እንደ ተበላሸ ብድር ተወስዶ ወለድ የማይከፈልበት ምድብ ውስጥ መካተት እንደሚኖርበትም መግለጫው አመልክቷል፡፡ 

አንድ ተበዳሪ ከአንድ ባንክ የተለያዩ ብድሮችን የወሰደ ከሆነና ከብድሮቹ አንዱ የተበላሸ ከሆነ ይህ የተበላሸው ብድር ባንኩ ለደንበኛው ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ወይም ተጋላጭነት 20 በመቶና ከዚያ በላይ ከሆነ ሁሉም ብድሮች ወዲያውኑ በተበላሸ ብድር መደብ ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውንም መግለጫው ያመለክታል፡፡

አንድ ብድር ምንም እንኳን የመክፈያ ጊዜው ያልደረሰ ቢሆንም፣ በተለያዩ ክስተቶችና ሁኔታዎች ሳቢያ ብድሩን በቀጣይ ለመክፈል የሚያስችል ዕድል የጠበበና የተመናመነ እንደሆነ አመላካች ሁኔታ ካለ ብድሩ እንደ ተበላሸ ብድር ተቆጥሮ ቢያንስ ‹‹አጠራጣሪ ብድሮች›› የሚል መደብ ላይ መካተት እንደሚኖርበት ስለመሆኑ  መግለጫው ያሳያል፡፡

ብድርን ሁልጊዜ ጤናማ አስመስሎ ማቅረብን ለመከላከል ለባንክ በሚፈቀደው ከፍተኛ የብድር ውል የማሻሻል ድግግሞሽ መጠን ላይ ገደብ ስለመጣሉ የሚጠቅሰው ይሄው መግለጫ፣ በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል ለአጭርና ለመካከለኛ ጊዜ ብድሮች አምስት ጊዜ ይፈቀድ የነበረውን የማሻሻል ድግግሞሽ ከሦስት ጊዜ እንዳይበልጥ እንዲሁም ለረዥም ጊዜ ብድር እስከ ስድስት ጊዜ ይፈቀድ የነበረው ድግግሞሽ ከአራት ጊዜ እንዳይበልጥ መደንገጉን ያመለክታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች