Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ ሁኔታችን ከሆነ አያያዛችን  ያስፈራል፡፡  አያያዛችንን አስተካክለን መራመድ ከተሳነን ብዙ ችግር እንደሚገጥመን ነጋሪ አያሻንም፡፡ ይሁንና የደከመው መንፈሳችን ለጊዜውም ቢሆን ሕይወት ዘርቶ በአዲስ ወኔና ጉልበት ይጓዛል። እግር ውሎ ይግባ…›› እያለ ይራመዳል፡፡ የመንገዱና የመንገደኛው ፍራቻ እንደሆነ ለወሬ ማፋፋሚያ ውሏል። ‹‹ስንቱ ጎዳናው ላይ እያወራ ወሬ ጠፋ ትለኛለህ?›› ሲል የምሰማው ወያላውን ነው። የዛሬ ወያላችን ሾፌራችንን በዕድሜ ይበልጠዋል። ክንዱ ሳይበቃው ገጹ በፈርጣማ ክፍልፋይ ጡንቻው ተከፋፍሎ ወጣት ባይመስል፣ አንዴ አይደለም ሁለት ጊዜ ወልዶ ያደርሰዋል ይባልለታል። ወጣቱ ሾፌራችን የታላቁን ወያላ ስላቅ እያጣጣመ፣ ‹‹የወሬ እናት ሞተች አሉ፣ ለጊዜው ጎረቤቷ አንደኛ ተጠርጣሪ ተብላ ተይዛለች አሉ፡፡ ወሬን ተራራ ካላሳከልነው እኮ የሰማም አይደብቀውም …›› ይለዋል። ‹‹ተውእንጂ…›› ወያላው ያዳንቃል። ተሳፋሪዎች አንድ በአንድ ወደ ታክሲያችን እየገቡ መቀመጫቸውን እየያዙ ነው። የወያላውና የሾፌሩ ነገረ ሥራ ተሳፋሪዎችን በድራማ እያማለለ ልብ የሚሰቅል እንጂ፣ የግላቸውን ፍሬ ፈርስኪ የያዙ አያስመስልም። ዘመኑ እንዲህ ነው!

            ወያላው ቀጥሏል፣ ‹‹እና ‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች› ስለጉዳዩ ምን አሉ ተባለ?›› ያሽሟጥጣል ። ወጣቱ ተረበኛ ሾፌር ተቀብሎ፣ ‹‹ዌል እንግዲህ ብዙ ብለዋል፣ ለምሳሌ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠቀሰ የመዲናችን ነዋሪ በአንክሮ፣ የወሬን እናት ጎረቤቷን ‹መርደር› ማድረጓ በእውነቱ ‹ሪል› ከሆነ ለአገሪቱ ‹ፊውቸር› ጥቅሙ የጎላ ይሆናል ብሏል። ሌላዋ እንዲሁ ስሟም መልኳም እንዲጠቀስ ያልፈለገች ወጣት ደግሞ በእውነቱ ‹ፌር› አይመስለኝም። ማንም ገደለ ማንም ሞተ ወሬን ያህል ‹ሂውጅ የሶሳይቲ› ቤንዚን እንዲህ አቅሎ ማየት የኋላ የኋላ ‹ሂውጅ ኮስት› ያስከፍላል ብላለች…›› ሲል ገሚሱ ግራ ተጋብቶ ገሚሱ እየተዝናና ሲያዳምጠው ቆየ። ድንገት ወያላው፣ ‹‹ከሁሉ ከሁሉ እኔን የገረመኝ ቋንቋችን ራሱ ስደተኛ በሆነበት ዘመን ስደትን አውጋዡ ነው…›› ብሎ በሩን ከረቸመውና ወደ ተሳፋሪዎች መለስ ብሎ፣ ‹‹ሲሪየስሊ…›› አለ ሸራፋ ጥርሱን እያስቃኘ። አቤት የዘመኑ ወሬና አወራሩ። ማማሩ ወይስ መምረሩ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ጭቅጭቁም አብሮ ጀምሯል። መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየሙ ተሳፋሪዎች ናቸው። አንደኛው፣ ‹‹ምን ያጋፋሃል? ድንበርህን ብትጠብቅ ይሻልሃል…›› ማለት። ‹‹ማን ያሰመረው ድንበር ነው? ወንበር እኮ ነው…›› ብሎ ያ ማባባስ። ‹‹ምንድነው ሽብሩ?›› ብሎ ጎልማሳው ወያላ መገላገል ያዘ። ‹‹አታየውም እንዴ እግሩን እላዬ ላይ ሰቅሎ?›› ይደነፋል ከሳሽ። ‹‹ወንበሩ ሰፊ ነው፣ ደግሞ እግሩን አልጫነብህም…›› ብሎ ወያላው ዓይቶ ፈረደ። ‹‹ለምን ይታከከኛል?›› ከሳሽ ነገር ነገር አለው። ‹‹ታክሲ ውስጥ ነው እኮ ያለኸው ወንድም? የግልህ ሊሞዚን አደረግከው እንዴ›› ተከሳሽ እያባሰው ሄደ። ‹‹በቃ ወደ ግዛቴ አትምጣ ማለት አትምጣ ነው…›› ከሳሽ ደረቅ ቢጤ ይመስላል። ‹‹ፌዴራሊዝም ታክሲ ተሳፍሯል እንዴ?›› ትላለች ባለ ሻሿ። ወያላችን፣ ‹‹ተይው ሰዓቱ ደርሶ ነው እንዲህ የሚሆነው…›› እያለ ያዛጋል። ነገር እኮ እንዲህ ነው የሚጀመረው!

‹‹ነገር ሲከር ይበጠሳል ተስማሙ እስኪ…›› ብለው አንድ አዛውንት መሸምገል ያዙ። ‹ፈርስት› እሱ ሥርዓት ይያዝ…›› አለ ከሳሽ። አዛውንቱ ደግሞ፣ ‹‹‘ፈርስት’ የሚባል አማርኛ የለም። በቅድሚያ አትልም?›› ሲሉት፣ ‹‹አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ እስካልሆነ ድረስ ‹Idon’t care›…›› ብሎ ጮኸባቸው። እሳቸው እንዳቀረቀሩ ቀሩ። ሸዋ ዳቦ ስንደርስ፣ ‹‹ወራጅ…›› ሲል አዛውንቱ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው፣ ‹‹በላ ወንበርህን ይዘህ ውረድ…›› አሉት ድንበር ድንበር ሲል የቆየውን። ይኼኔ አመዱ ቡን። አዛውንቱም፣ ‹‹ጊዜና ታክሲ አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር፣ አንድ ቀን ፈልገን ሳይሆን ሳንፈልግ ከተሳፈርንበት የምቾት ኮርቻ ላይ ማስወረዳቸው ነው። ስንሞት ሁሉ ቀሪ ነው። ስንኖር ግን ከተጋራነው መሬቱ፣ ሳሩ፣ ቅጠሉ፣ እንስሳቱ ሁሉ ለእኛ ነው። እስኪ እንቻቻል፡፡ በድንበር፣ በክልል፣ በቀዬ ተቀያይመን ስለኖርን ባስከበርነው ይዞታ አፈር አንቀበር። መሬቱስ ችሎናል ምናለበት እኛ ብንስማማ?›› ሲሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ስቆባቸው ወረደ። አውቆ አበዱ ባሰን እኮ ዘንድሮ!

በአንድ ሁከተኛ የተነሳውን ግብግብ ለማስረሳት የተሳፋሪውን ቀልብ ለመሳብ ይመስላል፣ ሾፌሩ ሬዲዮ ከፍቶ የሰዓቱን ዜናዎች ያስደምጠናል። ‹‹አይ አንተ ፈጣሪ ሩሲያን ከተረሳችበት አስታውሰህ እንዲህ በየአርዕስተ ዜናው ስሟን ያስናኘኸህ አምላክ፣ እባክህ እኛንም አስታውሰን እባክህ?›› ይላል ጋቢና የተቀመጠ ጎልማሳ እጆቹን ዘርግቶ። ይኼን ጊዜ አጠገቡ የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹ደስ አይልም?›› ብሎ ፀሎቱን አቋረጠው። ‹‹ምኑ?›› ሲለው፣ ‹‹ለጉልቤም ጉልቤ ሲያዝበት ደስ አይልም?›› አለው። ጎልማሳው፣ ‹‹ደስ ይል ነበር። ግን ጉልቤ ሲበዛ ደግሞ ጥሩ አይደለም። አሜሪካ ብቸኛ ጉልቤ ነኝ እያለች ነው። ማን ለማን ነው የሚታዘዘው እስኪ?›› ብሎ መልሶ ሲጠይቀው፣ ‹‹ዋናው ጉዳይ እኮ ምሥራቅ ምዕራብን ማስበርገግ መጀመሩ ነው። አሜሪካ እንዲህ አድርጋ፣ አሜሪካ እንዲህ ቆንጥጣ፣ አሜሪካ እንዲህ ስቃ፣ አሜሪካን ትን ብሏት… ከሚል ዜና ዕድሜ ይስጣቸውና እነ ፑቲን ገላግለውናል። እ  ያለ ቀን ደግሞ እኛም…›› ብሎ ሳይጨርሰው፣ ‹‹በል! በል! ወንድም። እኛ ከዚህ በላይ ማዕቀብ የሚችል ትከሻ የለንም። እንኳን አዲስ ለሚጣል ማዕቀብ ኑሮንም አልቻልነው… እንኳን የእነሱን ውርጅብኝ የእኛንም የፍጅትና የመገለማመጥ አባዜ አልቻልነውም…›› ብሎ ጎልማሳው አቋረጠው። ወይ ፍራቻ!

‹‹እስኪ ስላቁን ተውትና አንዴ ዜና እንስማበት?›› ሲል ከኋላ መቀመጫ፣ ‹‹ሰው በዜና ብቻ አይኖርም በስላቅና ሽሙጥ ጭምር እንጂ ብለህ ጥቅስ ለጥፍ…›› ይላል ጎልማሳው። ‹‹አንዳንዶቻችሁ የምታስወነጭፉት ሚሳይል የት ላይ እንደሚያርፍ እያስተዋላችሁ…›› ብሎ ወያላው ማስጠንቀቂያ ቢጤ ሲወረውር፣ መጨረሻ ወንበር ያሉት ወጣቶች ተኮራኩረው የሳቁ እስኪመስል ድረስ በሳቅ ካውካኩ በኋላ አንደኛው፣ ‹‹ፀረ ሚሳይል መግዛት ነዋ፣ ደግሞ ለዚህም ተበደሩና ግማሹን ቆርጣችሁ ኑሯችሁን አደላድሉበት አሏችሁ። ግን ሰሞኑን እንዴት ነው? ከቁጥሩ ነው ከጆሯችን? የፕሮጀክቶቻችን የቢሊዮን ብዛትና ዕዳችን እየተመጣጠነላችሁ ነው?›› ትላለች። ‹‹ማንን ነው? ይኼ ጆሮዬ እኮ እንቢ አለ በቃ…›› ብለው አዛውንቱ ከጎናቸው ያለውን ቢጠይቁት፣ ‹‹እንኳን ቀረብዎ፣ እንኳንም አልሰሙ፡፡ የሰሞኑን ነገራችንን ቢሰሙት ኖሮ ያብዱ ነበር…›› ብሏቸው ሲያበቃ፣ ‹‹ምነው ጆሮ እንደሚያከራክር ሁሉ ሆድም የሚያንገራግር ሆኖ ቢፈጠር?›› አለን ወደ እኛ ዞሮ። ወይ ታክሲና አፍ!

‹‹ኧረ ተመሥገን ነው ይኼንንስ ማን አየብን?›› ብለው አንዲት አዛውንት ሲናገሩ፣  ‹‹ድሮስ ማን  ያይብናል  እማማ?  ነው  ወይስ  ጉዳይ  ለማስፈጸም  የሕይወት  ጉቦ  ስጡን  መባል  ተጀመረ?››  አላቸው።  ‹‹የምን  ሕይወት?  እኮ  ይኼ  እስትንፋሴን  ማለትህ  ነው?››  አዛውንቷ  የምራቸውን  ደነገጡ።  ‹‹እህ  ሌላ  ምን  አለ?››  አላቸው  ግራ  ገብቶት  ግራ  እያጋባቸው። ‹‹ሞልቶ እስትንፋስማ በየፈርጁ አለ…›› ሲሉ ፈገግ አስባሉን። ይኼን ጊዜ አንዱ ኮልታፋ፣ ‹‹አይ እማማ እሱማ  ድሮ  በደጉ  ጊዜ  ቀረ።  አሁን  ማን  ይሙት  ሕይወታችንን  እንደ ለመድነው  እንዳሻን  የምናዝበት  ቢሆን  ኖሮ  የገዛ  ወገናችን  እየበላን  ይጨርሰን  ነበር?››  ሲላቸው  ከት  ብለው  ሳቁ።  ‹‹ቆይ  ግን  የሰው  ሕይወት  በመብላት  ሰላም ይኖራል እንዴ? ግራ አጋባን እኮ ሰውዬው…›› ስትል ደግሞ አንዷ፣ ‹‹ግድያ በሁሉም ዓይነት ወረርሽኝ  መልክ  ተቀስቅሶ  እናንተ  ድምፅ  የሌለውን  ሞት  ታነሳላችሁ?››  አለ  ጎልማሳው።  ‹‹ይደንቃል  እንዴ  ይኼ?  ሲከፋንና  ሞት  ደጃችን  ላይ  ሲንጎማለል  አይደለም  ሕመም  ሌላ  ነገር  ጠቅልሎ  ቢውጠን  ይገርማል?››  ብላ  ወጣቷ  ስትንጣጣ  የመለሰላት  አልነበረም።  ወያላው  ‹‹መጨረሻ…››  ብሏል።  እኛም  በድንጋጤ  ግር  ብለን  እንደ  ተሳፈርነው  ግር  ብለን  ወርደናል፡፡  ‹‹ጎበዝ እናንተ ዝም ባላችሁ ታወራላችሁ እንጂ፣ አዳዲስ ልምዶች ከተለያዩ አገሮች እየተቀመሩልን ነው፡፡ ለምሳሌ ከሲንጋፖር ሰሞኑን የመጣ ልምድ ስላለ እባካችሁ ቅሰሙ…›› ሲል አንዱ፣ ‹‹አይ ልጄ ልምድማ ጥሩ ነገር ነው፣ ዋናው ነገር እንዴት ይቀሰማል የሚለው ነው…›› እያሉ እኚያ እናት ሲናገሩ፣ ‹‹ከልምድ ቀሰማ በተጨማሪ የልምድ ልውውጡ ላይ ቢተኮር…›› የሚል ሌላ ድምፅ እየሰማን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት