Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች ከንቲቦች በ2030 ያላቸውን ፍትሐዊ የልቀት መጠን በግማሽ ለመቀነስ፣ ዓለም አቀፋዊ የአየር ሙቀት መጨመርን ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዲገደብ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ ለመገንባት ሁሉን አቀፍ፣ ሳይንስን መሠረት ያደረገ የትብብር አካሄድን ለመጠቀምም ቃል ገብተዋል፡፡ ከተመሠረተ ሁለት አሠርታት ግድም ያስቆጠረው ቡድኑ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ተጠሪ አለው፡፡ የቡድኑ የምሥራቅ አፍሪካ የጥራትና ቴክኒካዊ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው እየሠሩ የሚገኙት አቶ ጥበበ አሰፋ ናቸው፡፡ ስለተቋሙ እንቅስቃሴ  አማካሪውን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአርባ ከተሞች የተሰየመው ‹‹ሲ40›› የአየር ንብረት አመራር ቡድን ተግባሩ ምንድነው?

አቶ ጥበቡ፡- ስለግሩፑ ከመግለጼ በፊት አንድ መታወቅ ያለበትን ጉዳይ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ጉዳዩም የአንዳንድ አገሮች መሪዎች እ.ኤ.አ. በ2015 በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ለመነጋገር በፓሪስ ከተማ ጉባዔ ተቀምጠው ነበር፡፡ በጉባዔያቸውም መጨረሻ ላይ አንድ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ስምምነቱም አገሮች ሁሉ እስከ 2050 ድረስ የካርቦን ልቀታቸውን ዜሮ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያቸውንም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እንዲያደርጉ የሚል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም ስምምነት ‹‹የፓሪስ ስምምነት›› ይባላል፡፡ ስምምነቱንም በየከተሞቹ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የሚያመቻችና የሚያስተባብር አካል በማስፈለጉ፣ ይህንኑ ያስፈጽማል ተብሎ የታመነበት የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት (ዩናይትድ ኔሽንስ ፍሬም ወርክ ኮንቬንሽን ኦን ክላይሜት ቼንጅ) የአርባ ከተሞች የአየር ንብረት አመራር ቡድን (ሲ-40 ሲቲስ ክላይሜት ሊደርሺፕ ግሩፕ) ተቋቋመ፡፡ ግሩፑንም ያቋቋሙት የትልልቅ/ሜጋ ከተሞች ከንቲባዎች ሲሆኑ፣ ያቋቋሙትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የሚከናወነውን የመሪነት ሚና ለመጫወት እንዲያስችላቸው ነው፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱ የሚገኘው ኒውዮርክ ሲሆን፣ በየአኅጉራቱ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ የአፍሪካ ቅርንጫፍ የሚገኘው ጆሀንስበርግ (ደቡብ አፍሪካ) ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስምምነቱ ተግባራዊ የሚደረገው በስንት ከተሞች ውስጥ ነው? ለተግባራዊነቱስ ምን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል?

አቶ ጥበቡ፡- ስምምነቱ ተግባራዊ የሚደረገው አዲስ አበባን ጨምሮ የግሩፑ አባል በሆኑ 100 ከተሞች ነው፡፡ ከተሞቹም ለተግባራዊነቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን በርካታ ተግባራት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሚጠበቅባቸውም ተግባራት መካከል እምቅ ጋዝን ወይም ግሪን ሐውስ ጋዞች ወይም የካርበን ልቀትን ገደብ እንዲበጅለት ማድረግ ይገኙበታል፡፡ ከዚህም ሌላ የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን በኢንዱስትሪያል አብዮት ዘመን ከነበረው 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ እንዳይሆን ለማድረግ ለሚከናወነው ሥራ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ከሚጠበቅባቸው ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሙቀቱ መጠን ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው ገደብ በላይ እንዳይሆን የማድረግ ጥረት ቢኖርም ሙቀቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሙቀቱ መጠን የሚያስከትለው ችግር ምን ይመስላል? ከተሞችስ እንዴት መከላከል ይችላሉ?

አቶ ጥበቡ፡- ሙቀቱ በእርግጥ ከፍ ብሏል፡፡ በዚያው ልክም የሚያስከትለው ችግር ብዙ ነው፡፡ ድርቅ፣ ጎርፍና ኃይለኛ ሙቀት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በፊት ደጋ የነበሩ አካባቢዎች ወደ ቆላማ አካባቢ ይቀየራሉ፡፡ በዚህም ልዩ ልዩ የጤና ቀውሶች ይከሰታሉ፣ የውቅያኖስ ከፍታ ይጨምራል፡፡ ከተሞች በውቅያኖስ መስጠም ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥጋት የገጠማቸውም ደሴቶች ይገኛሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመቋቋም ከረዥም ጊዜ አኳያ የካርቦን ልቀትን ወደ ዜሮ ማድረግ፣ ከአጭር ጊዜ አኳያ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ የሚከናወኑትም ሥራዎች ካርቦን የማይለቁ ኢነርጂዎችን መጠቀም፣ ከሰል ከመጠቀም ይልቅ ወደ ታዳሽ ኃይል ሶላር ሲስተም መሻገር፣ ጋዞሊንና ዲዝል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ኃይል በሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪዎች መቀየር፣ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን ወደ ኮምፖስት ወይም ሪ-ሳይክል መለወጥ ይገኝበታል፡፡ ከዚህም ሌላ ኢኮኖሚው የአየር ንብረት ለውጥን ያማከለ ማድረግ፣ ጎርፍን ታሳቢ ያደረገ የፈሳሽ ቦዮችን መሥራት፣ ችግኝ መትከልንና ከድርቅ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች ከተጠቀሱት ተግባራት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች ከተሠሩ የካርቦን ልቀት መጠንና የሙቀት መጨመር ሁኔታ እየተገደበ ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የዘረዘሩትን ተግባራት በማከናወን ረገድ የሲ-40 ቡድን ሚና ምንድነው?

አቶ ጥበቡ፡- ከተሞች ለሚያከናውኑት ተግባራት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በየከተሞቹ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያበረታታል፡፡ ሥልጠናው፣ የልምድ ልውውጡ የሚካሄደው አንድም በበይነ መረብ አለበለዚያም በአካል በመገናኘት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተሞች የሲ-40 የአየር ንብረት አመራር ቡድን አባል ለመሆን ማሟላት የሚገባቸው ምንድን ነው?

አቶ ጥበቡ፡- አንደኛ ከተሞቹ ትልልቅ መሆን አለባቸው፣ አንድ ከተማ ቢያንስ ሦስት ሚሊዮን ነዋሪዎችን ያቀፈ መሆን አለበት፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለመሥራት ቁርጠኛ የሆኑ ወይም ቃል የገቡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህም በየሁለት ዓመቱ የእማቂ ጋዝ ልኬት ማድረግና የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የካርቦን ልቀትን የመቀነስ ሥራ ማከናወንና ለሌሎች ከተሞች ልምዳቸውን የማካፈል ፍላጎት ሊያድርባቸው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2050 የካርቦን ልቀትን ወደ ዜሮ ለማውረድ የተያዘው ግብ በጣም ሩቅ ስለሆነ ከተሞች የየራሳቸው የሆነ የመሸጋገሪያ ወይም የአጭር ጊዜ ግብ አላስቀመጡም?

አቶ ጥበቡ፡- በእርግጥ ወደ ዜሮ ለማውረድ የተያዘው ዓመት ሩቅ ነው፡፡ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ አበባን ጨምሮ ሁሉም ከተሞች አንድ ዓይነት የሆነ የአጭር ጊዜ ግብ አስቀምጠዋል፡፡ ግቡም 2030 ነው፡፡ በተለይ አዲስ አበባ የእማቂ ጋዝ ቅነሳን በ2030 ወደ 68 በመቶ ለማድረስ የሚያስችል ግቧን አስቀምጣለች፡፡ ይህንንም ለግሩፑ አስታውቃለች፡፡ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው መጠን መቀነስ ከተቻለ የቀረውን 32 በመቶ ለመሸፈን ብዙም ችግር አያስከትልም፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ በ2030 ለመፈጸም የተያዘውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ጥበቡ፡- ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ካርቦን የሚለቁ አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በማገድ በምትኩ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ ቀላል ባቡርን  መጠቀም፣  የሕዝብ ትራንስፖርትን ማስፋፋት፣ በእግር መሄድና በብስክሌት መዘዋወርን ማበረታታት፣ መንገድን ለሰው በሚል መርህ መሠረት አልፎ አልፎ መንገዶች ከተሽከርካሪዎች ነፃ ማድረግ ወዘተ ይገኝበታል፡፡ ለጥላ የሚያገለግሉ ችግኞችን መትከል፣ የአየር ንብረት መቆጣጠሪያ ማሽኖችን በተለያዩ ቦታዎች ማስቀመጥ እየተፈጸሙ ያሉ ተግባራት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአየር ብክለት ወይም ጥራት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ተግዳሮቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያን የአየር ጥራት እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ጥበቡ፡- ለአየር ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠለት መጠን አምስት ሚክሮ ግራም ፐር ሜትር ነው፡፡ በኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ የተያዘው ደግሞ 15 ሚክሮ ግራም ፐር ሜትር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ የአየር ጥራት በአገር አቀፍ ከተያዘው በሁለትና በሦስት እጥፍ ያደገ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ አካባቢ ከ30 እስከ 40 ሚክሮ ግራም ፐር ሜትር የሚደርስበት ጊዜ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ የአየር ብክለት ደረጃ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው መጠን ከሆነ በሰው ጤንነት ላይ የሚያደርሰው እክል እንዴት ይገለጻል?

አቶ ጥበቡ፡- ሲ-40 ባካሄደው ጥናት መሠረት አዲስ አበባ ውስጥ አየር ብክለት በሰው የመተንፈሻ ሥርዓትና በልብ ላይ በሚያደርሰው የጤና እክል ምክንያት በዓመት 935 ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት ይደርጋል፡፡ የዓለም ባንክ ጥናት ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር 1600 አድርሶታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...