Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመሬት ማገገም አንድምታ

የመሬት ማገገም አንድምታ

ቀን:

ከመሬት ማገገም ጋር የማይነጣጠለው የመሬት መጎዳት በአብዛኛው ከሰዎች እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪንና ሌሎች አገራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን ለማሳካት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መሬትን የሚጎዱ በመሆናቸው መሬትን ማገገም ዋና ጉዳይ ነው፡፡ የመሬት መጎሳቆልን ተከትሎ የሚከሰተው በረሃማነትም ሆነ ድርቅ መሬትን በአግባቡ ካለመያዝ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው፣ የመሬት ማገገም ሥራ ቀጣይነት ባለውና በተቀናጀ መልኩ መከወን የዜጎችን ህይወት ከማዳን ተነጥሎ የማይታይ ነው፡፡

ዓለምን እያሰጨነቀ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች፣ በመካከለኛም ይሁን ባደጉና በበለጸጉትም ጫናውን ማሳረፍ ከጀመረ አሠርታት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለመፍትሄው የተሰጠው ትኩረት ግን እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ፣ ከዓለም ህዝቦች ከ 3 ቢሊዮን በላይ ያህሉ በተጎሳቆሉ አካባቢዎች እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥና እርስ በርሳቸውም ተነጣጥለው ሊታዩ የማይችሉ ሐሳቦችን በማቀናጀት ሰሞኑን እየተከበረ ያለው የዓለም አካባቢ ቀንም፣ ዋና ጭብጡን ‹‹የመሬት ማገገም፣ በረሃማነትና ድርቅን መቋቋም›› በማድረግ በአለማቀፍ ደረጃ ተከብሯል፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያም ይህንኑ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ደን ልማት ባለሥልጣን በጋራ በመሆን የፓናል ውይይትን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶችን በመከወን፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጡን ተፅዕኖ እንድትቋቋም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ገልጸዋል፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደ የፓናል ውይይት የመሬት ማገገም፣ በረሃማነትንና ድርቅን የመቋቋም አስፈላጊነትንና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የፖሊሲና ሕግ አማካሪ አየለ ሄገና (ዶ/ር) እንዳሉት፣ መሬት ወሳኝ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት አለበት፡፡

ውኃ፣ ብዝኃ ሕይወት፣ የሰዎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች፣ አጠቃላይ የተፈጥሮ ሀብቶች ሁሉ ከመሬት ጋር የተያያዙ በመሆቸው፣ በመሬት ማገገም፣ በረሃማነትና ድርቅን መቋቋም ላይ መሥራት የግሪን ሀውስ ጋዝ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመቀነስ ወሳኝ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ የብዝኃ ሕይወት መቀነስ/መጥፋት፣ የድርቅና በረሃማነት መከሰት በአብዛኛው የሚያያዘው ከመሬት መጎዳት ጋር ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ለመኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውን መሬት ከጉዳት ቀድሞ በማዳን አልያም የተጎዳውን መልሶ ማገገም ላይ በችግሩ ስፋትና አሳሳቢነት ልክ ባለመሰራቱ ዓለም ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡

እንደ አየለ (ዶ/ር) ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለት ቢሊዮን ሔክታር መሬት በጣም የተጎሳቆለና የተጎዳ ነው፡፡ በተጎዱና በተመናወኑ አካባቢዎች ደግሞ 3.2 ቢሊዮን ሕዝብ ይኖራል፡፡ የከፋ ጉዳት የሚደርስባቸው ደግሞ በድኅነት ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡

በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ውስጥ የመፍትሄ እርምጃዎች ካልተወሰዱና በነበረው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ፣ 95 በመቶ የመሬት ሀብት ይመናመናል፡፡ ስለሆነም የዓለም አገሮች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የአኗኗር ልምድ በመቀየር ችግሩን ለመፍታት መሥራት አለባቸው፡፡

አጠቃላይ ዓለም ውስጥ ካሉት የመሬት ሀብቶች ሲሶው ለበረሃማነት ተጋላጭ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበረሃማነት መጠኑ ከ30 እስከ 35 ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ይህም በረሃማነት በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ያሳያል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም በመሬት መመናመንና መቆራቆዝ ምርታማነትን ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ በብክለት፣ በደን መመናመን፣ በተፈጥሮ ሀብት መጎዳት ጭምር ጉዳቶች እየደረሱ ነው፡፡ በመሆኑም ከችግሩ ለመውጣት የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የሕግና ሌሎች ማዕቀፎችን ወደ ትግበራ ማሸጋገር፣ የመሬት ማገገምና መሬት ከመጎዳቱ በፊት ቅድመ መከላከል ላይ መሥራት ወሳኝ እንደሆነም አየለ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡

መሬት አስቀድሞ እንዳይጎዳ የሚሠሩ ሥራዎች መሠረታዊ ናቸው ያሉት አየለ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የሕግና የፖሊሲ ዕይታዎች በዚህ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ኢንሽየቲቮች መካከል እንደ አገር እየተሠራበት ያለው የግሪን ሌጋሲ ኢንሽየቲቭ የገጠርና ከተማ አካባቢዎችን ታሳቢ አድርጎ የሚተገበር መሆኑ፣ በከተማና በገጠር ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲጠበቁ ከማስቻሉም ጎን ለጎን የተጎዱ የውኃ አካላትን፣ በረሃማ አካባቢዎችንና ሌሎች ክፍተቶችን አይቶ ለመሙላት የሚያስችል መሆኑን አክለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ፖሊሲዎች፣የደን ፖሊሲዎች፣ ከኢኮኖሚው ጋር የተያያዙ ሥራዎች መሬትን በማይጎዳ ወይም በከፋ መልኩ በማይጎዳ እንዲተገብሩ የተቀረጸ ስትራቴጂ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ኢንሽየቲቭ፣ የብክለት ቁጥጥር ፍሬምወርክና ሌሎችም በርካታ ሕጎችና ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚደርስን ጉዳት ቀድሞ ለመከላከልና ለማገገም የሚያስችሉ መሆናቸውን ስታውሰዋል፡፡

ድርቅን በተመለከተም፣ በዓለም ያለው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰው መብዛትና የአካባቢ ዕድገት የውኃ ሀብት ለከፋ ችግር መጋለጡን እንደሚያመላክት፣ የኢትዮጵያ ሲታይ በ2050 የከፋ የውኃ እጥረት ከሚያጋጥማቸው አገሮች ተርታ መሆኗን የዓለም የምግብ ድርጅት ዳሰሳ እንደሚያሳይ በመጠቆም፣ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ እሳቤዎች እንዲተገበሩ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውኃ ሀብት እንዳላት አድርገን ብናስብም መረጃዎች የሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያ በ2050 መጨናነቅ፣ እጥረት ውስጥ እንደምትገባ ነው፣ ያለው የውኃ ሀብትም ካለው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር እያጠረና እያነሰ የሚሄድ ይሆናል፣ ስለሆነም ይህንን የሚቋቋም ዕሳቤ ያለው አሠራር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ በዙሪያዋ ያለውን ሁኔታ ሲታይ ወደ ውሃ እጥረትና መጨናነቅ መገባቱ እንደማይቀር፣ የከፋ የውኃ እጥረት የሚያጋጥም ከሆነ እንዴት ነው የምንቋቋመው? ፖሊሲዎቻችን በቂ ውኃ አለን የሚል ዕሳቤ ይዘው ነው የተነሱት? ወይስ የውኃ እጥረት አገርና ከተሞችን ያጋጥማል ብለው? የሚለውን ወደኋላ ሄዶ መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለበረሃማነትና ለድርቅ ባላት ተጋላጭነት፣ ፈተናና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ዳሰሳ ያቀረቡት በኢትዮጵያ ደን ባለሥልጣን የደን ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ሃላፊ ክብሩይስፋ ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የሰሃራ በረሃ ኢትዮጵያን ወደ በረሃ ሊቀይራት ይችላል የሚለው፣ በአፋር ክልል ከጎረቤት የምትጋራው የደናከል በረሃና የደቡብ ምሥራቅ ክፍል ወደ በረሃማነት እየተቀየሩ መሆኑ፣ ድርቅና በረሃማነት የአገሪቱ ሥጋቶች መሆናቸውን ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ክፍል በደረቅ አግሮኢኮሎጂ እንደሚካተት፣ ይህ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር ወደ በረሃማነትና ተደጋጋሚ ድርቅን የሚያስከትል መሆኑ ዋናው ሥጋት ነውና መላ ሊበጅለት ይገባልም ብለዋል፡፡

70 በመቶ ያህል የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖርበት ደጋው ክፍል ከፍተኛ ወጣ ገባ ያለበትና በአግባቡ ካልተያዘ ለከፍተኛ የአፈርና ውኃ እጥበት ሚጋለጥ መሆኑ፣ በሥፍራው የሚከወነው ግብርና የተበጣጠሰ መሆኑ የመሬት መታጠብን የሚያባብስ መሆኑ ኢትዮጵያ ካሉባት ሥጋቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ያሏት የተፈጥሮ ሀብቶች በርካቶች ቢሆኑም፣ እነሱንም ጠብቆ ማቆየት ካልተቻለ ሥጋት ውስጥ ይከታል፡፡

እንደ ክብሩይስፋ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት እ.ኤ.አ. በ2018 ባደረገው ጥናት፣ የኢትዮጵያ ግማሽ ክፍል መልሶ ማገገም እንደሚያስፈልገው አሳይጽል፡፡ ወደ 50 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ዛፍ ላይ የተመሠረተ የመሬት ማገገም ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ ከመሬቱ 11 ሚሊዮን ሔክታሩ ቶሎ ማገገም የሚፈልግ ሲሆን፣ ይህ ካልተሠራ መሬቱ ወደ በረሃማነት ይቀየራል፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖውን እያሳረፈ የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥም ተግዳሮቷ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ከበረሃማነትና ከድርቅ ተከላክሎ መሬቱን አገግሞ እንዴት መቀጠል ይቻላል? የሚለውን ለመመለስ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው፣ ኢትዮጵያ ከመሬት መጎሳቆል፣ ከበረሃማነትና ከድርቅ ጋር የተያያዙ ችግሮቿን ለመፍታት በርካታ ዛፎች እየተከለች መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የደን ምንጣሮን በመቀነስ፣ የደን ሽፋንን በመጨመር የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን፣ የተፈጥሮ ደኖች ጥበቃ በአካባቢው በሚኖር ማኅበረሰብና መንግሥት በጋራ እንዲተዳደር ማድረግን ጨምሮ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ በሦስት ፕሮጀክቶች በተሠሩ ሥራዎች በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሰው ሠራሽ ደን በ82 ሺሕ ሔክታር በአርሶ አደርና በግል መሬት ላይ መልማቱን ፣ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከከብትና እንስሳት ንክኪ በማራቅ መልሶ እንዲያገግም መደረጉን፣ ተጨማሪ አገር በቀል ዛፎች ተከላ መከናወናቸው ችግሮቹን ለመቅረፍ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡

ይህን ይበልጥ ለማጠናከር ደግሞ የኢትዮጵያ ደን ባለሥልጣንና የገንዘብ ሚኒስቴር በመተባበር ግሪን ሌጋሲ ኤንድ ሪስቶሬሽን ፈንድ በማቋቋም ላይ መሆናቸውን፣ ረቂቁ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መላኩን፣ ይህ ሲጸድቅ መሬት ከማገገም፣ ከበረሃማነትና ድርቅን ከመቋቋም ጋር ያሉ ችግሩን ለማቃለል እንደሚያግዝ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...