Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊውዳሴና ክብር በመቄዶንያ ገበታ

ውዳሴና ክብር በመቄዶንያ ገበታ

ቀን:

ሕይወትን በዥዋዥዌ የሚመስሏት አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከፍታ በሌላ ወቅት ደግሞ ዝቅታን ታስተናግዳለች፣ መንገራገጮች ይበዙባታል ይላሉ፡፡ መውጣትና መውረድ፣ መውደቅና መነሳት የሕይወት አንጓዎች ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነገር የተደመጠና የታየ ሀቅ ቢሆንም፣ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ መርጃ ማዕከል ተጠልለው እንደሚገኙ ወገኖች ምስክር ሊሆነን የሚችል ማግኘት ግን ያዳግታል፡፡

በማዕከሉ የሚገኙ ወገኖች ትናንት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትነትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙ፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አገራቸውን ያገለገሉና ታላቅ ውለታን ለሕዝብ የዋሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ሕይወት ፊቷን አዙራባቸው ያገለገሏት አገርም ውለታቸውን ዘንግታ፣ የእኔ ነው የሚሉት ጧሪና ደጋፊ ቢያጡ ከጎዳና ላይ ወድቀው የተነሱ ናቸው፡፡

ውዳሴና ክብር በመቄዶንያ ገበታ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ መርጃ ማዕከል ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙ አረጋውያን ውስጥ ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር አባላት ይገኙበታል፡፡ ‹‹የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ፋውንዴሽን››ም እነዚህን ጀግኖችና የአገር ባለውለታዎች ለማመሥገን ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በማዕከሉ በመገኘት የምሳ ግብዣ አድርጓል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ካፒቴን ከበደ ወልደ ፃድቅ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያዊው የአየር አብራሪ ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ የኢትዮጵያ ወደር የሌለው ጀግና ሜዳይ የሁለት ጊዜ ተሸላሚ ነው፡፡ ለገሠ በሙያው የተካነ፣ ቆራጥ፣ ሞትን የማይፈራና ለሁላችንም ዓርማና ምሳሌ የነበረ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት፣ የሶማሊያን ሚግ 23 እና ሚግ 21 የተባሉ አምስት የጦር ጄቶችን በመምታትና በመጣል ታላቅ ጀብዱ ፈጽሟል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ የአየር ክልል በጠላት እንዳይደፈር አድርጓል፡፡ በተሳሳተ መረጃም ተማርኮ በሶማሊያ እስር ቤት 11 ዓመታትን አሳልፏል፡፡

ጄኔራል ተፈራ ለኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ የከፈለ ቢሆንም ታሪኩ ብዙ ያልተነገረ፣ ያልተዘመረለትና ያልተወራለት ጀግና ነው፡፡ ከዘመኑ በፊት የተፈጠረና ለእናት አገሩ በጦር ሜዳ ውሎ ታላቅ ጀብድ የፈጸመ ነው ብለዋል፡፡  

ውዳሴና ክብር በመቄዶንያ ገበታ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ኢትዮጵያዊው የአየር አብራሪ ብርጋዲየር ጄኔራል
ለገሠ ተፈራ የኢትዮጵያ ወደር የሌለው ጀግና ሜዳይ
የሁለት ጊዜ ተሸላሚ ነው

ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ የራሳቸውን ኑሮ ትተው ሜዳ የወደቁና የተቸገሩ የጦር አባላትን ለመደገፍ በእህቱ አማካይነት በስሙ ፋውንዴሽን መመሥረቱም የሚመሠገን ነው ያሉት ካፒቴን ከበደ፣ ‹‹ለገሠ ለአገር ፍቅርና ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ከከፈለው መስዋዕትነት አንፃር በስሙ ተቋም ሊሰየምለትና ሐውልት ሊታነፅለት የሚገባ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ስለጄኔራል መኰንኑ ምስክርነት የሰጡት ኮሎኔል ዘውዴ ዘሪሁን በበኩላቸው፣ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ለገሠ ከጀግንነቱ ባሻገር ትሁት፣ ደግ፣ ቅንና ሁለገብ ሰው እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹ኢትዮጵያ በየዘመኑ ብዙ ጀግኖች ቢኖራትም ጀግኖችን ማክበር ባለመቻላችን በርካታ ለኢትዮጵያ የቆሰሉ፣ የደሙና ታላቅ ውለታ የዋሉ ባለውለታዎች አስታዋሽ አጥተው ሜዳ ላይ ወድቀው ሊቀሩ ችለዋል፤›› ብለዋል፡፡ በመቄዶንያ ድጋፍ ከጎዳና የተነሱትና ከማዕከሉ የተገኙት ወገኖችም ‹‹ኢትዮጵያ የቆመችው በእናንተ መስዋዕትነት በመሆኑ ልትኮሩ ይገባችኋል፤›› በማለት አወድሰዋቸዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ በማዕከሉ በመገኘት የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር አባላትን አስታውሶ የምሳ ግብዣ ፕሮግራም በማድረጉም ሊመሠገን ይገባል ሲሉ አክለዋል፡፡

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ ዓለሙ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በመቄዶንያ ድርጅት ድጋፍ ከሚደረግላቸው ወገኖች አብዛኛዎቹ መለዮ ለባሾች ናቸው ሲባል አዘንኩኝ፤ ይህ ለእናንተ አይገባም ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ግን እናንተን ከወደቃችሁበት ላነሳና እየደገፈ ለሚጦራችሁ መቄዶንያ ከፍ ያለ ክብር ይገባዋል ብለዋል፡፡

‹‹ከጀግናም ጀግና ከአካልም አካል አለ›› እንደሚባለው፣ ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ወደር የሌለው ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ መሆን የቻለ ነው፡፡

‹‹ለገሠ ከጀግንነቱ ባሻገር ለአገሩ የነበረው ፍቅር ወደር አልነበረውም፡፡ ከ11 ዓመታት በኋላ የእስረኞች ልውውጥ ተደርጎ ከሶማሊያ እስር ቤት ሲፈታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለስና ወደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ እንዲሻገር የተለያዩ ጫናዎች ቢደረጉበትም፣ እሱ ግን አይሆንም በማለት ኢትዮጵያን በማስቀደም ወደ አገሩ የተመለሰ ነው፡፡ ይህም ትልቅነቱን፣ የጀግንነት ምልክቱንና የኢትዮጵያዊነት ጠርዙን ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹አገራችን በየጊዜውና በየዘመናቱ ጀግኖችን አምጣ ትወልዳለች፣ ጀግና አይነጥፍባትም፡፡ ይህንን ጀግና ለመዘከርና ስሙ እንዲታወስ ፋውንዴሽን መቋቋሙ ታላቅ ተግባር ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ኢትዮጵያን ያቆሙ የጦር ጀግኖችን ከወደቁበት የሚያነሳና ድጋፍ የሚያደርግ እንደሚሆንም እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ አያየዘውም፣ ‹‹እናንተ ደምታችሁ፣ ቆስላችሁና ሞታችሁ ይህችን አገር ባታቆሟት፣ እኛም በሕይወት አንኖርም ነበር፤›› በማለትም አክብረዋቸዋል፡፡

የመቄዶንያ አረጋውያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፣ ፋውንዴሽኑ በማዕከሉ በመገኘት የምሳ ግብዣ በማድረጉ አመሥግነው፣ በየዓመቱም በዚህ ሥፍራ በመገኘት ተመሳሳይ ፕሮግራም ለማድረግ የጄኔራል ለገሠ እህትና የፋውንዴሽኑ መሥራች ወ/ሮ ሙሉ ብርሃን ተፈራ ቃል መግባቷንም ገልጸዋል፡፡፡

በመቄዶንያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ተገልጋዮች በጦር ሜዳ ያለፉ ናቸው፡፡ ከተራ ወታደር እስከ ኮሎኔል ማዕረግ የደረሱ ይገኛሉ፡፡ ለአገር ህልውና መስዋዕትነት የከፈሉ  ናቸው ምስጋና የሚገባቸው ናቸው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ትውልዱ ‹‹እኔስ ለአገሬ ምን አስተዋጽኦ አበረከትኩ?›› በማለት ራሱን መፈተሽ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...