Saturday, June 22, 2024

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራና ውጤቱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአማራ ክልል እንደ አስፈላጊነቱ በመላው ኢትዮጵያ ለአሥር ወራት የተተገበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በስተመጨረሻ የጊዜ ገደቡ አብቅቷል፡፡ አዋጁ በእነዚህ ወራት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ማስከበር የማይቻሉ የሕግ ጥሰቶችን ሥርዓት ለማስያዝ ያስቻለ ነበር ወይ? የሚለው አሁን የውይይት አጀንዳ የሆነ ይመስላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው የአማራ ክልልን ሰላምና ፀጥታ ወደ ቀደመ ሁኔታ ለመመለስ ተብሎ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ ውይይት ስለማድረጉ የተነገረው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ተብሎ የቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ላይ ነበር ውይይቱ፡፡ በአማራ ክልል የሚታየው የትጥቅ እንቅስቃሴ የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወከ በመሆኑ፣ እንዲሁም በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ ስለሆነ የአዋጁ መፅደቅ አስፈላጊ መሆኑን ምክር ቤቱ በዚህ ሰብሰባው ስለመወሰኑ በወቅቱ በወጣው መግለጫ ይፋ ሆነ፡፡

በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተብራራው ከሆነ የአማራ ክልል መንግሥት አዋጁ እንዲታወጅለት ጥያቄ ማቅረቡ ተነግሯል፡፡ በክልሉ ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲደነግግና ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስድ በማለት ክልሉ ስለመጠየቁ ተዘርዝሯል፡፡ ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ጠቅሶ የፌደራል መንግሥቱ እንዲረዳው ስለመጠየቁ በዚህ መግለጫ ተቀምጧል፡፡

ይህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ በወጣ በማግሥቱ ደግሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መገናኛ ብዙኃንን ጠርተው መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት ተጠርጣሪ ሰዎችን ማሰር ስለመጀመሩ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ዘራፊ ቡድን›› ሲሉ የጠሩትና በክልሉ በትጥቅ በታገዘ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ቡድን መንገድ በመዝጋት፣ ካምፖችን በመክበብና በመተኮስ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ስም በማጥፋትና በዘረፋ ላይ ተሰማርቷል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ክልሉን እያወከ ያለውን ኃይል ለመቆጣጠርና የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ መንግሥታቸው እየሠራ ስለመሆኑም ተናግረው ነበር፡፡

መንግሥት አከታትሎ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015ን ዝርዝር ድንጋጌ የያዘ ባለ አምስት ገጽ ሰነድ ይፋ አደረገ፡፡ ወደ 11 አንቀጾች የያዘው ሰነዱ ሰላምን የሚያውኩና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ለቅጣት እንደሚዳርግ ከመደንገግ ጀምሮ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምርያ ዕዙን እንቅስቃሴ የሚያውክ እንቅስቃሴ እንደማይፈቀድ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የጦር መሣሪያና ስለት መያዝ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ጠቅላይ መምርያ ዕዙ እንደ አስፈላጊነቱ የሰዓት እላፊ፣ የመንገድ መዝጋት፣ የአገልግሎት መስጫዎችን የመዝጋት፣ እንቅስቃሴን የሚገድብ ዕርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችልም ይዘረዝራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተመጣጣኝ ኃይል የመጠቀም ሥልጣን እንዳለው በአዋጁ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

በተለያዩ ከተሞች ‹‹ዘራፊ›› ብለው የጠሩትን የታጠቀ ኃይል ስለማፅዳታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት አከታትለው መግለጽ ጀመሩ፡፡ አንዳንድ ከተሞችን ማስለቀቃቸውንና መልሰው መቆጣጠራቸውን ይፋ ማድረግም ጀመሩ፡፡ በተቃራኒው የተሠለፉት የፋኖ ኃይሎች በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ኦፕሬሽን ስለመሥራታቸው፣ ከተሞችን ስለመቆጣጠራቸው፣ እንዲሁም የጦር ካምፕ ስለማጥቃታቸውና እስረኞችን ስለማስለቀቃቸው ይናገሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መከላከያ፣ የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ታጣቂ ኃይሎቹ ስለመደምሰሳቸው ደጋግመው መግለጫ ይሰጡ ነበር፡፡

በአማራ ክልል ከአሥር ወራት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የተለያዩ ክልሎች መንግሥታት ለአዋጁ ድጋፍ አቅርበዋል፡፡ ሁሉም የክልል መንግሥታት አከታትለው ባወጡት መግለጫ አዋጁን በመደገፍ፣ የሕግ ማስከበር ዕርምጃውን እንዲጠናከር ብርታት በመስጠት ‹‹ጃዊሳና ዘራፊ›› የሚሏቸውን ኃይሎች ሲያወግዙ ተደምጠዋል፡፡

በዚህ መንገድ ልዩ የሚዲያ ትኩረትና የድጋፍ ድምፆችን አሰባስቦ ወደ ሥራ የገባው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግን በሒደት ያሳስበናል የሚሉ የሥጋት መግለጫዎች ሲስተጋባበት ነው የታየው፡፡ በጥቅምት ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአማራ ክልል ሁኔታ እንዳሳሰበው መግለጽ ጀመረ፡፡ የድሮን ጥቃትን ጨምሮ መንግሥት በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጦርነት መክፈቱ ዜጎችን ለሰብዓዊ ቀውስ የሚዳርግ ስለመሆኑ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ቆየ፡፡

የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚቴ በኢትዮጵያ የተባለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አጣሪ ቡድን ሪፖርትን አጣቅሶ፣ ተመድ በወቅቱ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በክልሉ በቀጠለው ግጭት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ተመላክቷል፡፡ በአማራ ክልል በ11 ከተሞች አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የፆታዊ ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ተመድ በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ያለ ፈቃድና ከሕግ ውጪ እስራት፣ ብርበራ፣ ግድያን ጨምሮ ሌሎች መደበኛ እንቅስቃሴን የሚያውኩ ዕርምጃዎች ጭምር በፀጥታ አካላት እየተወሰዱ ነው ሲል የተመዱ ሪፖርት አሳስቦ ነበር፡፡ በዚሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ነበር በመርአዊ ከተማ የሰዎች ግድያ ሪፖርት መውጣት ጀመረ፡፡

በአማራ ክልል ባለፉት አሥር ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥር ብዙ ዓይነት ኦፕሬሽኖች መካሄዳቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተፋላሚ ኃይሎች በየጊዜው ገደልን፣ ማረክን፣ ደመሰስን፣ ተቆጣጠርን ወይም አፀዳን ከሚሉ የዘመቻ ድል ዜናዎች ጋር በሚነፃፀር ሁኔታ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ሲረጋጋ አለመታየቱ ግን በተደጋጋሚ ይነገራል የክልሉ ፀጥታና ሰላም ዕጦት ከዚያ ይልቅ ባለፉት አሥር ወራት እንደታየው ከሆነ ወደ እምነት ተቋማት ጭምር የተዛመተ ነበር፡፡ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት ከለላ ሊያገኙ ይገባል የሚባሉ የሚባሉ ገዳማትን ጨምሮ ቤተ ክርስቲያናትና መስጊዶች በክልሉ በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡

የአስተዳደር አካላትም የግጭቱ ሰለባ ሲሆኑ ታይቷል፡፡ መደበኛ አገልግሎት መስጫዎች የትምህርት፣ የጤና፣ የማኅበራዊ መገልገያዎችና ሌሎች ተቋማት ሲዘጉና የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ነበር፡፡ መንገዶች መቼ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዳላቸው ስለማይታወቅ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሲስተጓጎል የታየበት አጋጣሚ በርካታ ነበር፡፡ የአማራ ክልል ቀውስን ባለፈው አሥር ወራት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አረጋግቶታል ወይ የሚለው ጉዳይ ብዙ እንዳጠያየቀ ነው ያለፈው፡፡

አዋጁ ሲታወጅ መንግሥት በአጭር ጊዜ የታጠቁ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠርና ክልሉን ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሁኔታው እንደሚመልስ በብዙዎች ዘንድ ታምኖበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ይህ አለመሆኑና የክልሉ ሕዝብ ከሥጋት መላቀቅ አለመቻሉን ነው የክልሉ ነዋሪዎች የሚናገሩት፡፡

በላሊበላ ከተማ የቱሪስት ማስጎብኘት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሙጫው ደርበው፣ የአካባቢው ወሳኝ የደም ሥር የሆነው የቱሪስት እንቅስቃሴ እንደሞተ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በአካባቢያችን ቱሪስት በማስጎብኘት ሥራ ላይ የተሰማራን በርካታ ሰዎች ነን፡፡ ለምሳሌ የእኛ ማኅበር ብቻውን 200 ሰዎችን ያሰባሰበ ነው፡፡ ባለፉት ወራት ሥራው ሙሉ ለሙሉ በመቆሙ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ አባሎቻችን ወይ ወደ ግብርና ገብተዋል፣ ወይ ወደ ሌላ ቦታ አምርተዋል፡፡ ሥራው በመጥፋቱ የብዙዎች ህልውና ከእነ ቤተሰቦቻቸወ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅረን አባሎቻችን ችግሩ እስኪፈታ ሕይወታቸውን የሚያቆዩበት መጠነኛ መዋጮ ለማሰባሰብ የተለያዩ ደጋፊ አካላትን እየጠየቅን እንገኛለን፤›› በማለት ነው ስለአካባቢያቸው ሁኔታ የተናገሩት፡፡

የደብረ ማርቆስ ነዋሪ አቶ አንተነህ አሰፋ በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅትና የጊዜ ገደቡ ከተገባደደ በኋላ ያለው ሁኔታ ምንም ልዩነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የአካባቢያቸው የፀጥታ ሁኔታ የማይገመት በመሆኑ መቼ ግጭት እንደሚፈጠርና ሰላም እንደሚሆን መናገር እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ መደበኛውን የአካባቢያቸውን እንቅስቃሴ በአንፃራዊነት የተረጋጋ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በማርቆስ አካባቢ ትራንስፖርትም፣ ሥራም ሆነ ንግድ አለ፡፡ ባጃጆችም ሲንቀሳቀሱ አይቻለሁ፡፡ እኔም ለመዘዋወር አልተቸገርኩም፤›› በማለት ነው አካባቢያቸው ያለበትን ሁኔታ ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ለሪፖርተር በስልክ የተናገሩት፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ ባለው ሁኔታ ‹‹አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ ድባቴ ውስጥ ነው የምንገኘው፤›› በማለት የገለጹት የጎንደር ነዋሪና የሕግ ባለሙያው አቶ ደመወዝ ካሴ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀነ ገደብ ማብቃቱንና አለማብቃቱን እንኳን በቅጡ የሚገነዘብና ልዩነቱን ማጣጣም የሚችል ሰው ማግኘት እንደሚቸገሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹አንድ ሁለት ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለቀ እኮ የሚል ወሬ ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ሰው ከሥጋትና ከድባቴ አልተላቀቀም፡፡ ጦርነትንና ግጭትን ተለማምደነዋል፡፡ አሁንም ከጎንደር ከተማ ወደ ባህር ዳርና ወደ ሌሎች የአካባቢው ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች ዝግ ናቸው፡፡ ሰሞኑን እንቅስቅሴ ዝግ መሆኑን የፋኖ ኃይሎች አስታውቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ቀዝቃዛና የግጭት ሥጋት ያጠላበት ከባቢ አየር ነው በአካባቢያችን ያለው፡፡ መንገድ ላይ አዳዲስ የመከላከያ ምልምል ወታደሮችን የጫኑ መኪኖች ሲዘዋወሩ ይታያል፡፡ ምሽት የሰዓት ገደቡ እንዳለ ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅትም ቢሆን በከተማው ያለው የተለመደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኢንተርኔት የለም፣ መብራት በተደጋጋሚ ይጠፋል፣ ጎንደር ከጦርነቱ በፊትም እንደ ነበረው የውኃ ዕጦት ችግር እንደቀጠለ ነው፡፡ ቱሪዝሙና ጎብኚዎች በከተማችን ቆሟል፡፡ በገበያው ከፍተኛ ውድነት ይታያል፤›› በማለት የአካባቢውን ውስብስብ ችግር ዘርዝረዋል፡፡

በጎንደርና በዙሪያዋ አሁንም ቢሆን የተኩስ ድምፅ መስማትና የግጭት ዜና ማድመጥ እንደተለመደ የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ ‹‹መጀመሪያም ቢሆን ችግሩ የፖለቲካ መፍትሔ ነበር የሚፈልገው፡፡ በአጭር ጊዝ በአንድ ሳምንት እንፈታዋለን የተባለው ጉዳይ በአሥር ወራትም አልተቻለም፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ደመወዝ አሁንም ቢሆን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ተናግረዋል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ሠራዊቱ ግማሽ አቅሙን እንኳን በአማራ ክልል ዘመቻ እንዳልተጠቀመ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፡፡ ራሳቸው እንደተናገሩትም ድሮን ጭምር በመጠቀም የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ለአማራ ክልል ቀውስ መፍትሔ ሆኗል ወይ የሚለው ጉዳይ ግን ዛሬ ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የስድስት ወራት የጊዜ ምዕራፉን ባገባደደ ወቅት የአሜሪካ መንግሥት፣ ተመድ፣ የአውሮፓ ኅብረትና በኢትዮጵያ ያሉ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ጭምር በአማራ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ በክልሉ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መቀጠሉ ቀውሱን ከማባባስ በዘለለ የሚያመጣው መፍትሔ እንደሌለ ሲወተውቱም ነበር፡፡

በመጀመሪያው ዙር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምዕራፍ በሁለት ወይም በሦስት አጋጣሚዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ተብሎ የተቋቋመው አካል አፈጻጸሙን የተመለከተ መግለጫዎች ሲሰጥ ነበር፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ጠቅላይ ዕዙም ቢሆን ውስን በሚባሉ አጋጣሚዎች 23 ሰዎችን አስሮ ክስ ስለመመሥረቱና ስለሌሎች ዕርምጃዎቹ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የተለያዩ የመብት ድርጅቶች ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ወደ ክልሉ ገብቶ የሚመረምር ነፃና ገለልተኛ ቡድን እንዲፈቀድለት የተደረገው ውትወታና ግፊት ሰሚ ጆሮ አጥቷል ይላሉ፡፡ መንግሥት የተለያዩ ወገኖችን ውትወታ ወደ ጎን ብሎ ከስድስት ወራት በኋላ ለአራት ወራት እንዲቀጥል ያራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያመጣው አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ በቅጡ ሳይገመገም ነበር አሥር ወራት የተገባደዱት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -