Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየስኬት ጎዳና

የስኬት ጎዳና

ቀን:

ኑሮውን ጎዳና ላይ ማድረግ የጀመረው በልጅነቱ ነበር፡፡ የጎርፍ መፍሰሻ ቱቦ መዋያና ማደሪያው ነበር፡፡ ቤንዚን ይስባል፣ ከትልልቅ ሆቴሎች እስከ ትንንሽ ምግብ ቤቶች የሚወጡ ትርፍራፊ ምግቦች የዘወትር ቀለብ ማግኛ መንገዶቹ ነበሩ፡፡ ስቃይ፣ መከራ፣ ረሃብና ጥማቱ፣ ብርዱና ፀሐዩ ዛሬ ላይ በነበረ ቀርቷል፡፡

የስኬት ጎዳና | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ወጣት ሳቦና ቡሎ

አዳፋ ልብሱን ዓይተው፣ መዋያና ማደሪያውን ተመልክተው፣ አብረውት ለመቆም ቀርቶ ለማየትና ለመንካት የተፀየፉት ሁሉ ዛሬ ላይ ሠርቶ የመለወጥ ሚስጥርን እንዲነግራቸው ይጠይቁታል፡፡

ለአራት ዓመታት በጉስቁልና ሕይወት ሲኖር የት ነህ፣ ምን ሆነህ ነው፣ ሐሳብህን ለማን እናድርስልህ ያላሉት የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና ሚዲያዎች፣ በአሁኑ ወቅት ከወደቅህበት እንዴት ተነሳህ? የጎዳና ላይ ውሎና አዳር እንዴት ነበር? በሚሉ ጥያቄዎች እንደሚያጣድፉት ባለታሪኩ ይናገራል፡፡

- Advertisement -

ወጣቱ ሳቦና ቡሎ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ከሻሸመኔ በቅርብ ርቀት በምትገኝ ኮፈሌ አካባቢ ነው፡፡ ገና በልጅነቱ ከነገሌ ቦረና እስከ ድሬዳዋ፣ ከሞያሌ እስከ ጂቡቲ ድረስ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እንደተዘዋወረ ይናገራል፡፡

‹‹በየደረስኩበት ከተማ ከወር በላይ አልቆይም ነበር፤›› የሚለው ወጣቱ፣ በአዳማ ሙሉ ሕይወቱን ለጎዳና ኑሮ አሳልፎ በመስጠት አራት የመከራ ዓመታትን ማሳለፉን ያስታውሳል፡፡

ከአራት ዓመታት ውስጥ የመጨረሻዋ አስቀያሚ ቀን ለሳቦና ከሁሉም የተሻለችና አሁን ለሚገኝበት የተሳካ ሕይወት በር የከፈተች፣ ሁሌም የሚያስታውሳትና የሚመርቃት ዕለት ነበረች፡፡

ሳቦና ሁሌም እንደሚያደርገው ቤንዚን በመሳብ ብቻ አልታለል ያለውን እንጀቱን ለማስታገስ ወደ አንዲት አነስተኛ ምግብ ቤት ያመራል፡፡ ደንበኞቿን በማስተናገድ የደከመችውን አስተናጋጅ ትርፍራፊ ካለ እያለ መወትወት ጀመረ፡፡

ልመናው ያሰለቻት አስተናጋጅ ትራፊ ቁራሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ‹‹ሠርተህ አትበላም!›› በማለት በቆሻሻ የተሞላ የባልዲ ውኃ በማንሳት መላ አካላቱን አለበሰችው፡፡

ይህ ከሆነ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ዛሬም ሁኔታው ከህሊናው እንደማይጠፋ የሚናገረው ባለ ታሪኩ፣ በወቅቱ አልቅሶና በእጀጉ ተማሮ ነበር ፡፡ ሁኔታውን ግን በለቅሶ ብቻ ለማለፍ አልሞከረም፡፡ ይልቁንስ ወደ ነበረበት ሕይወት ዳግመኛ ላይመለስ ከራሱ ጋር ተማምሎ ለፈጣሪውም ቃል ገብቶ ሳይውል ሳያድር አዳማ ውስጥ ይገኝ ወደ ነበረ የዕርዳታ ማከፋፈያ መጋዘን በማቅናት፣ እህል የማውረድና የመጫን ሥራን ተቀላቀለ፡፡

በረንዳ እያደረ ምግብ ሲያገኝ በልቶ፣ ሲያጣ እየፆመ፣ እህል ማውረድና መጫን ቀርቶ ቁሞ ለመራመድ አስቸጋሪ የነበረውን ጊዜ ማሳለፉን ያስታውሳል፡፡ ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ‹‹ሠርተህ አትበላም›› የምትለዋ ንግግርና ፊቱ ላይ የተደፋበት የእጅ እጣቢ ቆሻሻ ውኃ እየታወሰው፣ ዳግም ወደ ነበረበት ሕይወት መመለስን እንደ ሞት ፈራው፡፡ ‹‹ዳግመኛ ወደ ልመና ከምመለስ ብሞት ይሻለኛል›› የሚል መርህ እንደነበረው ባለታሪኩ ያስታውሳል፡፡

‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› እንደሚባለው፣ ሳቦና አዳማን በመሰናበት ወደ ድሬዳዋ ተጓዘ፡፡ ምንም እንኳን መዳረሻውን ባያውቅም ከድሬዳዋ ባገኘው ባቡር በመሳፈር ከአንዴም ሁለት ጊዜ ጂቡቲ ደርሶ በፖሊሶች እየተያዘ ተመልሷል፡፡

በወጣትነቱ የጎዳና ላይ ኑሮን፣ ልመናን፣ ከአገር የመውጣት ትንቅንቅን የቀመሰው ወጣቱ፣ ወደ ድሬዳዋ መጓዙ ዓይንና ጆሮውን፣ እጅና እግሩን፣ መላ አካላቱን ለሥራ አነሳሳው፡፡ የተገኘውን ሥራ ሌት ተቀን ለመሥራት ወሰነ፡፡ ድሬዳዋ 07 ቀበሌ ታይዋን እየተባለ በሚጠራው ሠፈር በወቅቱ ውኃ ይሽጥ ከነበረ ሰው ተጠግቶ የሚሸጠውን ውኃ በየሰው ቤቱ በመሸከም ማድረስ የዕለት ተዕለት ሥራው አደረገ፡፡ አንድ ጀሪካን ከ20 እስከ 25 ሌትር ውኃ ተሸክሞ ከ300 እስከ 400 ሜትር ተጉዞ ሃምሳ ሳንቲም ይከፈለው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታው ነው፡፡

ከሥራው መብዛት የተነሳም ‹‹ትከሻዬ ይጣመም ነበር፤›› ሲል የሥራውን ክብደት ያስታውሳል፡፡ ሳቦና ትከሻው እስኪጣመም ይሥራ እንጂ፣ የሚያገኘው ገንዘብ ወደ ኪስ የሚገባ አልነበረም፡፡ ከምግብ ዘሎ ለቤት ኪራይ ባለመብቃቱ ሲሠራ ውሎ ጎኑን የሚያሳርፈው ጎዳና ነበር፡፡

ውኃ ከመቅዳትና ከማከፋፈል ባለፈ በሚያገኘው ትርፍ ጊዜ በምግብ ቤት አስተናጋጅነት እንዲሁም ጫት በማሻሻጥ አብዛኛውን ጊዜውን በሥራ ተወጥሮ ማሳለፉ ሰዎች ‹‹ልታብድ ነው እንዴ›› እያሉ እንዲቀልዱበት አድርጓል፡፡

ወጣቱ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ገንዘብ ሳይሆን አንድ ትልቅ ነገር እንዳተረፈ ይናገራል፡፡ ‹‹ከተለያዩ ሰዎች ጋር መተዋወቅ ትልቁ ስኬቴ ነበር፤›› ብሏል፡፡

‹‹ከሠራህና ጥሩ ነገር ካገኘህ ሰዎች ሁሉ ይወዱሃል፤›› የሚለው ሳቦና ጠንክሮ በመሥራቱ በብዙ ሰዎች ዘንድ አድናቆትን ማግኘቱን ይገልጻል፡፡ ሥራ ወዳድነቱን የሰማ የአሜሪካ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ድሬዳዋ ላይ ምግብ ቤት በከፈተበት ወቅት ወጣቱን በአስተናጋጅነት ቀጠረው፡፡ ‹‹ከብዙ ዓመታት በኋላ እንደ ሰው ከቤት ማደር የጀመርኩበት ወቅት ነበር፤›› ሲል በወቅቱ የተሰማውን ደስታ ያስታውሳል፡፡

የነበረበት ውስብስብ የሕይወት ውጣ ውረድ ውሉ የተገኘለት የመሰለውም በዚህ ወቅት ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቀጣሪዎቹ የተሰማሩበት ሥራ ትርፋማ አልነበረም፡፡ በዚህም ምግብ ቤቱ ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ተዛውሮ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ተከፈተ፡፡ የሳቦናን ታታሪነት በተግባር የተመለከቱት አሠሪዎቹ፣ ድሬዳዋ ጥለውት ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ አልቻሉም፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ሰቦናና አዲስ አበባ የተዋወቁት፡፡

 ችግሩ ምኑ ላይ እንደሆነ ባይታወቅም ወደ አዲስ አበባ የተዛወረው ምግብ ቤት ከአንድ ዓመት ከ6 ወራት በላይ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ በድጋሚ ኪሳራን አስተናገደ፡፡ ባለቤቱ ዘግቶ ወደ ትውልድ ቦታው ሶማሌ ክልል ተመለሰ፡፡

አዲስ አበባን በደንብ ያላወቃት ወጣቱ ብቻውን ቀረ፡፡ የሚያውቀው ዘመድም ሆነ የሚጠጋበት ጓደኛ ባለመኖሩ በድጋሚ ችግር ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ነጋ ሲል እየጨለመ፣ አለቀ ሲል እየቀጠለ ችግር የሚደራረብበት ሳቦና፣ አሁንም ለችግር እጁን አልሰጠም፡፡ ‹‹ሠርተህ አትበላም›› የምትለዋን ቃል ነክሶ ይዟል፡፡ መሞከር ያልሰለቸው ወጣቱ፣ የድለላ ሥራን እንደ ዋዛ ይጀምራል፡፡ እንደዋዛ የጀመረው የድለላ ሥራ ግን ከሁሉም የተሻለ ገቢን አስገኘለት፡፡

መኖሪያ ቤቶችን በማከራየት ከሁለት ሺሕ እስከ አምስት ሺሕ ብር ማግኘት ጀመረ፡፡ መነሻ ገንዘብ ሲያገኝ፣ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ቆሻሻ መጣያ የነበረ ቦታን በማፅዳት ትንሽ የጀበና ቡና መሸጫ አቋቋመ፡፡ የጀበና ቡና ከሁሉም የተሻለ ገቢ ከማስገኘት ባሻገር የትዳር አጋሩ የሆነችውን ባለቤቱን ያገኘበት ጭምር ነበር፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሳቦና የስኬትን እርካብ ረግጦ ወደፊት መገስገስ ጀመረ የብርሃን ጭላንጭል የነበሩት የተስፋ ፍንጣቂዎች አሽተው ለመበላት ደረሱ፡፡ ሰቦና እንደማንኛውም ሰው ሠርቶ መብላት ጀመረ፡፡ ከዚህም ተሻግሮ ለሰዎች መትረፍ ቻለ፡፡ የአሸናፊነት እልህን ተላብሶ የጎዳና ሕይወትን አሸንፎ ከልመና ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ሁሉንም በአሸናፊነት አጠናቀቀ፡፡

ከባለቤቱ ጋር በመሆን ለቡና ጠጪዎች ቁርስ ማቅረብ ጀመሩ፣ ድለላውንም ጫት መሸጡንም ጎን ለጎን አጧጧፉት፡፡

ከሚያገኙት ገቢ ከቤት ኪራይ፣ ከቀለብና ከሌሎች ወጪዎች የተረፋቸውን ገንዘብ ለማጠራቀም በሚል ዕቁብ መጀመራቸውን የተናገረው ሳቦና፣ የዕቁብ ብር ሲጥሉ ቆይተው ወደ መጨረሻው ሲደርስ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ 17 ሺሕ ብር በወጣበት ቀረ፡፡ ዳግመኛ ኪሳራ ተከሰተ፡፡

በብዙ የተፈተነው ወጣቱ በዚህም ተስፋ አልቆረጠም ነበር፡፡ ዳግም ዕቁብ በመግባት የመጀመርያውን ዕጣ 25 ሺሕ ብር ተቀበሉ፡፡ በገንዘቡ ወግ ማዕረጋቸውን አዩበት፣ ተዳሩበት ስኬቱም ቀጠለ፡፡ የነበረውን ሁሉ የሚያስንቅ ሌላ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ቤት ከማከራየት ወደ ቤት ማሻሻጥ የተሻገረው ወጣቱ፣ ከአራት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ግማሽ ሚሊዮን ብር ወደ ካዝናቸው ገባ፡፡

ሳቦና ያገኘውን ገንዘብ ወደ ባንክ አላስቀመጠም፡፡ ድርሻውን ተቀብሎ ወደ አርሲ አካባቢ ሰፋፊ መሬቶችን በኮንትራት በማረስ ስንዴና ድንች በማምረት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመላክ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ማግኘት ጀመሩ፡፡ ድንች ከማምረት ባሻገር ከአርሶ አደሮች በመግዛት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሸጥ ገበያቸው ጨመረ፡፡ በአሁኑ ወቅት ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ተጨማሪ ምግብ ቤቶችንና ሁለት አትክልት ቤቶችን በመክፈት እየሠሩ እንደሚገኙ ይናገራል፡፡

ከችግሮቹ የተማረው ወጣቱ በዚህ አላቆመም፡፡ ፉሪ አካባቢ ከሁለት ሺሕ 500 በላይ ዶሮዎችን በማርባት ላይ እንደሚገኝ ተናግVል፡፡

‹‹የጎዳና ሕይወት ምን እንደሚመስል በደንብ አውቀዋለሁ፤›› የሚለው ባለታሪኩ፣ ጎዳና ያሉ ወጣቶችን ሲመለከት አንጀቱ እንደሚላወስ፣ ያለውን ከማካፈል እንደማይቦዝንና ከወደቁበት እንዲነሱ ለማድረግ እንደሚሠራ ያክላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከራሱ አልፎ 13 ሠራተኞችን በመቅጠር ሥራዎቹን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...