Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የመኖሪያ ቤት ኪራይን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የወጣው አዋጅ በጥንቃቄ ይተግበር!

ቅጥ ያጣውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ በገበያ ዋጋ ሥርዓት ለማስያዝ ያስችላል የተባለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ወደ ትግበራ የማስገባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡  

ለዚህ አዋጅ መተግበር እንደ መሠረታዊ ጉዳይ የሚወሰደው የአከራይና የተከራዮች ሕጋዊ ውል ስምምነት ምዝገባ ከትናንት በስቲያ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር ጀምሯል፡፡ አዋጁን ለመተግበር በተወሰነው መሠረት ተከራይና አከራይ ሕጋዊ ውላቸውን በጽሑፍ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአከራይና ተከራይ መካከል ሕጋዊ የሆነ ስምምነት ኖሮ በአዋጁ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ለማስከበር ውል የማስመዝገብ ሥራው ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡  

ለዘመናት ሕግና ሥርዓት ያልነበረው የአከራይና ተከራይ ‹‹የመንደር›› ስምምነት ሕጋዊ መስመር እንዲይዝ በዚህ አንድ ወር ውስጥ የሚሰበሰበው መረጃ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚሰበሰበው መረጃ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ግድ ይላል፡፡ በጥንቃቄ ሊሠራ የሚገባውም ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ ወር የሚሰበሰበው መረጃ ወይም የውል ምዝገባ ግድፈት የሚኖርበት ከሆነ በቀጣይ አሠራሮች ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡  

ለዚህም በምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው አንድ ጉዳይ የአከራይና ተከራይ ስምምነት መረጃ መሰብሰብ እንደሚጀምር ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ የቤት አከራዮች ዋጋ ለመጨመር እየጣሩ ስለመሆናቸው መታዘባችን ነው፡፡ አንዳንድ አከራዮችም በተከራዮች ላይ ጫና እያሳደሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ የመረጃ አሰባሰቡ ትክክለኛነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳረፉም በላይ ተከራዮች ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ሰለባ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ የመረጃ አሰባሰቡ እንዲህ ያለውን ያልተገባ ተግባር መፈጸም አለመፈጸሙን ለማረጋገጥ ተዋዋዮች ከሚያቀርቡት መረጃ ፈቀቅ ያለ የማጣራት ሥራን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በዘፈቀደ በሚደረግ የአከራይና ተከራይ ስምምነት ጥቂት የማይባሉት ከቤት ኪራዮች ከቤት ኪራይ ገቢ መክፈል የሚገባቸውን ግብር ለመቀነስ ወይም ለመሰወር ለወረዳና ሕጋዊ ሥልጣን ላለው መሥሪያ ቤት የሚቀርቡ የአከራይ ተከራይ ‹‹ውሎች›› ተከራዩ በተጨባጭ ከሚከፍለው ዋጋ ያነሰ አኃዝ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ አከራዩ ከተከራዩ በወር 10 ሺሕ ብር እየተቀበለ ለወረዳና መሰል ተቋማት የሚገባው ውል ግን ቤታችንን ያከራየነው አምስት ሺሕ ብር ነው በሚል ነው፡፡ አሁንም እንዲህ ያሉት ውንብድናዎች መፈጸም አለመፈጸማቸውን በአግባቡ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተከራዮች ሁለት የተለያዩ ውሎች ላይ ይፈርሙ የነበረው በአማራጭ ዕጦት ስለነበር ይህንን ስህተት ላለመድገም የተከራዮች ከፍተኛ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ የሚከፍሉትን ትክክለኛ ዋጋ በማስቀመጥ መዋዋል ግድ ይላል፡፡ 

ይህ አዋጅ በአከራይና ተከራይ መካከል ሕጋዊ ስምምነት ኖሮ በዚህ ስምምነት መሠረት ተገዥ እንዲሆኑ ከማስቻሉ በላይ በቤት አከራይ የሚገኝ ገቢን በሕጋዊ መንገድ እንዲሰበሰብ ያስችላል ተብሎ ይታመናልና ትክክለኛ መረጃ መቅረቡን ማረጋገጥ መንግሥትን ይጠቅማል፡፡ 

አከራይና ተከራይም ለዚህ አዋጅ መተግበር የየራሳቸው ኃላፊነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እንደ ቀድሞ ሁለት ውል ላይ ፈርሞ መንቀሳቀስ ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚችልም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ 

እንዲህ ያሉ ድንጋጌዎች ሲተገበሩ መጀመሪያ አካባቢ ግርታ ሊፈጥሩ የሚችሉ ቢሆንም ይህ እንዳይሆን ቀድሞ በቂ መረጃዎችን መስጠት ደግሞ የውል ምዘገባውን እንዲያካሂድ ሥልጣን የተሰጠው አካል ኃላፊነት ነው፡፡ በአዋጁ ውስጥም በግልጽ እንደተቀመጠው መረጃዎችን በአግባቡ መሰጠት እንዳለት ይደነግጋልና አሁንም ያልረፈደ በመሆኑ በአዋጁ በተጠቀሰው መሠረት በዌብሳይቶች ስለ አተገባበሩ በቂ መረጃ መሰጠቱ ሥራውን ያቀላጥፋል፡፡ 

ከዚህ ባሻገር የአከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ ጋር በተያያዘ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አንድ ጉዳይ ግን ማስታወስ ይገባል፡፡ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን የተከራዮችን በእጅጉ የሚፈትኑ ድርጊቶች በመሆናቸው ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ 

ይህም ብዙ ጊዜ አከራይና ተከራዮች አንድ ላይ በሚኖሩባቸው ግቢ ውስጥ የሚከሰት ነው፡፡ በአንድ ግቢ ውስጥ አንድ አከራይ ለራሱ ከሚኖርበት ቤት ሌላ ሦስትና አራት ክፍሎችን ወይም ቤቶችን የሚያከራዩም አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ አከራይና ተከራዮችም በአዋጁ መሠረት ተገቢውን ስምምነት አድርገው መረጃውን የሚያቀርቡ ቢሆም በዚህ ውል ውስጥ ግን በጋራ ስለሚጠቀሙባቸው እንደ ውኃና መብራት ያሉ አገልግሎቶች ብዙ ጊዜ ያጋጫሉ፡፡

እነዚህ አገልግሎቶች አከራይም ተከራይም በጋራ የሚጠቀሙባቸው በመሆኑ ለእነዚህ አገልግሎቶች በየወሩ የሚከፈለውን ክፍያ እንዴት ይከፋፍሉታል? የሚለው ጉዳይ ለግጭት መንስዔ ሲሆን ይታያል፡፡ አንድ አከራይ እንደ ልቡ ተጠቅሞ ተገቢን ክፍያ ለመክፈል ዕድል አያገኝም፡፡ ብዙ ጊዜ በአንድ ግቢ ውስጥ ከአንድ የበለጠ የኤሌክትሪክ ሆነ ውኃ መስመር ባለመኖሩ አንድ ተከራይ ለእነዚህ አገልግሎቶች የሚጠይቀው ክፍያ በአከራይ ፈቃድና ውሳኔ  ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

እንደውም አከራይ ‹‹ልብስ ማጠብ የምትችሉት በዚህ ሰዓት ነው፣ ካውያ መጠቀም አትችሉም ይላሉ፤›› የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን የምትጠቀሙ ከሆነ ደግሞ ይህንን ያህል ትከፍላላችሁ ሁሉ ይላሉ፡፡ የሚጠየቀው ዋጋ ደግሞ የአካባቢ ሰው ሁሉ ተጠቅሞ በወር ሊከፍል የሚችለው በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ የጋራ መፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ላይ  የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የተከራይን መብቶች ይጋፋሉ፡፡ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ ማምሸት አይችልም የሚሉና እንደ አከራዩ ፀባይ የሚደረደሩ ‹‹የአከራይ ሕጎች›› የብዙ ተከራዮች ራስ ምታት ነው፡፡

አንድ አከራይ እንጀራ ለመጋገር የአከራዩን ይሁንታ ማግኘት ግድ የሚልበት ጊዜ ሁሉ ስላለ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች በአከራይና ተከራዮች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ?  ለሚለው ጥያቄ መልስ ያስፈልጋል፡፡ ቤት የምንከራየው እነዚህን አገልግሎቶች ጭምር ለማግኘት ከመሆኑ አንፃር የአከራይና ተከራይ የውል አካል ካልሆነ ላለመግባት ምንጭ በመሆን በመልካም የምንጠቅሰውን የአከራይ ተከራይ አስተዳደር አዋጅ ሊበርዝ ይችላል፡፡

ለማንኛውም የአከራይና ተከራይን ስምምነት በዋናነት ለማረጋገጥና የሁሉንም ወገኖች መብት ከማስጠበቅ አንፃር ይህ ሕግ ብዙ ለውጥ እንደሚያመጣ እርግጠኛ ብንሆንም አዋጁን ለመተግበር የሚሠሩ ሥራዎች ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡ በሥራው ሒደት የሚታዩ ክፍተቶች ካሉም በቶሎ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰውም ተከራዮች ከአከራዮች ጋር ሊኖራቸው የሚገባው ስምምነት የሚጠቀሙባቸው አገልግሎቶችም የሚመለከት ቢሆን በአከራይና ተከራይ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት የበለጠ ጤነኛና ሕጋዊ ያደርገዋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት