Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በፌደራል በሁሉም ደረጃ ፍርድ ቤቶች በጥብቅና ሲሠሩ የቆዩ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ በሕፃናት ላይ የአካልና የአዕምሮ ዕድገት እክል እያስከተለ ያለውን በየዓመቱ አሥር ሺሕ ሕፃናትን የሚጎዳውን የነርቭና የኅብረሰረሰር ችግር ለመቅረፍ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ማያ በጎ አድራጎት ድርጅት የተባለ ተቋም መሥርተው በዋና ሥራ አስኪያጅነት ይመራሉ፡፡ ከሁሉ በላይ ሰፊ ልምድ ባካበቱበት የሕግ ሙያ ዕውቀት በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ በራዲዮ ከሚያቀርቡት ፕሮግራም በተጨማሪ፣ ‹‹ወንጀልና ፍትሕ›› የተባለ የፍትሕ ሥርዓቱን የተመለከተ መጽሐፍ በቅርቡ አዘጋጅተው ለአንባብያን አቅርበዋል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ካነሷቸው የሕግ ጉዳዮች በመነሳት ስለፍትሕ ሥርዓቱ ያላቸውን ምልከታ በሰፊው ያጋሩበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ሰፊ ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- መጽሐፉ በርካታ የሕግ ትንተናዎችን በዝርዝር የቀረቡበት ቢሆንም፣ የሕግ ጉዳዮችን በተጨባጭ የሚያሳዩ ኬዞች በሰፊው ለምን አልቀረቡበትም?

አቶ አበባው፡- የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ከበቂ ጥርጣሬ በላይ ማስረጃዎች ተደራጅተው የሚቀርቡበት ነው፡፡ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ተጠርጣሪ ወንጀልን ተጠያቂ ለማድረግ ከተቋቋመ ተቋም ጋር ክርክር የሚያደርጉበት ነው፡፡ በቂ የሕግ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ካሉት በመዋቅርም ከተደራጀ ዓቃቤ ሕግ ጋር ነው ተጠርጣሪዎች ሙግት የሚያደርጉት፡፡ ብዙ ጊዜ ግለሰብ ተጠርጣሪዎች የሕግ ዕውቀት ስለሌላቸው በቀላሉ ሊረቱና ሊወጡበት ይችል የነበረ ጉዳይን ይሸነፋሉ፡፡ ነፃ የሚሆኑበት ዕድል እያለ ነገር ግን እንደ ፍትሕ ሚኒስቴርና ዓቃቤ ሕግ ካለ ተቋም ጋር ተሟግተው መርታት ሳይችሉ ይቀራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሕግ ዕውቀት ክፍተት የመጣ ነው፡፡ ለዘጠኝ ዓመታት ሕጉ ምን ይላል የሚለውን ፕሮግራም ሠርቼበታለሁ፡፡ በዚህ ሒደት ብዙ የሕግ ዕውቀት ክፍተቶችን አይ ስለነበር ከተጠርጣሪነት ጀምሮ፣ በተከሳሽነት ሒደት፣ በችሎት፣ በማረሚያ ቤት ጭምር ያሉ ሕጎችን ጨምቆ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ይህን መጽሐፍ ያዘጋጀሁት፡፡ ዜጎች አንብበው መብታቸውን እንዲጠይቁ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በተበታተኑ የሕግ ሰነዶች ውስጥ ያሉ ሕጎችን አሰባሰቦ በአንድ ገበታ ማቅረቡ የፍትሕ ሥርዓቱን ያግዛል በሚል መንፈስ ጭምር ነው ያቀረብኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ኬዞችን በተለይ በአገር ውስጥ የተፈጠሩ የፍርድ ሒደቶችን ማሳያ አድርጎ ለምን ማቅረብ አልተቻለም?

አቶ አበባው፡- ይህ የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ መጽሐፉ ከ500 በላይ ገጾች ነበሩት፡፡ በሒደት ወደ ሁለት ምዕራፎችን ማውጣት ነበረብን፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች በእያንዳንዱ ያነሳናቸው የሕግ ጉዳዮች ሥር ሊገቡ የሚችሉ ጭብጦች ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚያን ሁሉ አሰባስበን እናስገባ ብንል የመጽሐፉ ስፋት ይጨምራል፡፡ እርግጥ ነው ጥቂት ኬዞችን ጨማምረናል፡፡ ለምሳሌ የ1997 ዓ.ም. የቅንጅትን ኬዝ ብናይ የዋስትና መብትን አተረጓጎምና ወሰኑን ለማየት ሞክረናል፡፡ የውጭ አገሮች ተሞክሮዎችንም ጨማምረናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ በቂ ነው አልልም፡፡ ‹‹ጠጅ በብርሌ ነገር በምሳሌ›› እንደሚባለው፣ ይህ የመጀመሪያ ዕትም እንደመሆኑ ወደፊት እያዳበርነው እንሄዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- በገጽ 185 እና 186 ኢሰብዓዊ አያያዝን በተመለከተ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንኳን ሕገ መንግሥቱ ኢሰብዓዊ አያያዝንም ሆነ ሰብዓዊ ክብር በጎደለው መንገድ የሚደረግ አያያዝን እንደሚከለክል ይገልጻል፡፡ ይህ አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እንዴት ሊገለጽ ይችላል? በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ኢሰብዓዊ አያያዞችን መታዘብ አይቻልም?

አቶ አበባው፡- በግልጽ ማሳየት የፈለግኩት ሕጉ የሚለውን ለዜጎች ማሳወቅ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ከፍትሕ አንፃር እንመዝነው ከተባለ በዜሮ የሚጣፋ ነው የሚሆነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ተብለው በሕገ መንግሥታችን ከአንቀጽ 14 እስከ 28 የተዘረዘሩ አሉ፡፡ እነዚያ የተዘረዘሩ ድንጋጌዎች የማይጣሱና የማይገሰሱ ናቸው፡፡ አንድ ሰው የመኖር መብቱ የሚገደብበት ሁኔታ እንኳን ካለ በሕግ ያውም በፍርድ ቤት ሲወሰን ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲህ ያለውን መብት ጥሰት ሊያስከትል እንደሚችል ቀድሞ ይታሰባል፡፡ ያም ቢሆን ግን ሰብዓዊ መብቶች ተብለው ከአንቀጽ 14 እስከ 28 የተደነገጉ ድንጋጌዎች በምንም ሁኔታ በአዋጁም ቢሆን ሊጣሱ እንደማይችሉ ነው ታሳቢ መደረግ ያለበት፡፡ በግልጽ እንነጋገር ከተባለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ አይደለም በየቀኑ እኮ ብዙ ሰዎች የሚሞቱበት አገር ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ በፊት ነውር አድርገንና አጋነን የምናወራው ነገር ዛሬ የዜና ርዕስ እንኳ አይሆንም፡፡ አንድ ሰው ሞተ ተብሎ በታላቅ ድንጋጤና ገረሜታ የሚወራበት ጊዜ ቀርቶ አሁን እየሰፋ መጥቶ የቁጥር ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ሊጣሱ አይገባም፡፡ ሰብዓዊ መብቶች መከበር ያለባቸውም ሰብዓዊ ክብርን በጠበቀ መንገድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከገጽ 213 ጀምሮ ስለተከላካይ ጠበቃ አቋቋም ጉዳይ መጽሐፉ ይዘረዝራል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ተከላካይ ጠበቃ የማቆም አሠራርም በተነፃፃሪነት ያስቀምጣል፡፡ ምንድነው የሚለያቸው?

አቶ አበባው፡– ተከላካይ ጠበቃ ከባድ ለሆኑ ወንጀሎች ብቻ የሚቆም ነው፡፡ ሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 19 ላይ ፍትሕ የሚጓደል መስሎ ከታየ ተከላካይ ጠበቃ ለተጠርጣሪዎች መንግሥት ራሱ እንደሚያቆም ተቀምጧል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ግን አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ ለሚያስፈርዱ ወንጀሎች ብቻ ነው ጠበቃ የሚቆመው፡፡ በሌላ አገር ግን አንድ ሰው ወንጀል ሠርቶም እንኳ ቢሆን አጠራጣሪ ነገር እያለ እንዲቀጣ ከማድረግ ይልቅ ነፃ ቢወጣ ይሻላል የሚል የሕግ መርህ ነው ያለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ስለሰብዓዊ መብቶች ክብር ነው የሚናገረው፡፡ ለምሳሌ የተከላካይ ጠበቃን ሲተነትን ዜጎችን ከፍትሕ ጋር ሊያግባባና ሊያስታርቅ የሚችል፣ እንዲሁም የሕግ መብቶቻቸውን ሊያስከብር የሚችል ግለሰብ ወይም ተቋም እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከዚህ አንፃር የተያዙ ሰዎች በከባድ ወንጀል የሚጠረጠሩ ከሆነ፣ ተከላካይ ጠበቃ እንደሚቆምላቸው ተደንግጓል፡፡ የተከላካይ ጠበቃ ቢሮዎች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተደራጅተዋል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተደራጁ ብቻ ሳይሆኑ ጠበቆችም ሥሩ ይባላሉ፡፡ በፊት በሰዓታት ነበር የሚለካው፣ አሁን ግን በዓመት ሁለትም ሦስትም ጉዳዮች ያዙ ይባላል፡፡ በፍትሐ ብሔርም ሆነ በወንጀል ከባድ ቅጣት ለሚያስጥሉ የወንጀል ድርጊቶች ብቻ ቁሙ ነው የሚባለው፡፡ ይህ የሕግ ድንጋጌ ግን ክፍተት ያለውና መሻሻልም አለበት ነው የሚባለው፡፡ አንድ ሰው በሕግ የሚቀጣው ወይም የሚታሰረው እኮ እንዲታረም ነው፡፡ ሳያጠፋ ሰውን የምታስረው ከሆነ በቀለኛ ነው የሚሆነው፡፡ የተከላካይ ጠበቃ አሰያየምም ሆነ አቋቋም ከዚህ አንፃር መሻሻል አለበት፡፡ በኦሮሚያ ክልል በዚህ በኩል የተሻለ አሠራር አለ፡፡ ሆኖም እዚያም ቢሆን ከተማ ቀመስ አካባቢዎች እንጂ ወደ ወረዳዎች ያለው ተደራሽነት አጠያያቂ ነው፡፡ አስበህ ሊሆን ይችላል ወይም ሳታስብ፣ ራስን ለመከላከል ወይም የማኅበረሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ሊሆን ይችላል፣ የግል ወይ የቤተሰብ ጥቅም ለማስጠበቅ ብሎ ሊያጠፋና በወንጀል ድርጊቶች ሊሳተፍ ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ በሕጉ ራሱን የቻለ አተረጓጎም ያለው ነው፡፡ ተከላካይ ጠበቃ ሲቆም እነዚህን ነገሮች ታሳቢ ያደረገ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ግን ክፍተት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- በሦስቱም ክልሎች የቅጣቱ መጠን መርዘም ማጠሩ ብቻ ነው የተከላካይ ጠበቃ የማቆም ያለ ማቆም ጉዳይን የሚወስነው?

አቶ አበባው፡- ሕገ መንግሥቱ ፍትሕ የሚጓደልበት ዕድል መኖሩ ከታመነ የተከላካይ ጠበቃ ሊቆም እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ ፍትሕ የሚጓደልበት ሁኔታ በተግባር ሲተረጎም በከባድ ወንጀል ለተጠረጠረ ሰው ነው የሚል ነው፡፡ አሥር ቀን የሚያስቀጣ ጥፋትስ ቢሆን ተከላካይ ጠበቃ ለምን ሊቆም አይገባም የሚል ጥያቄ ነው የሚነሳው፡፡ በተግሳፅ የሚታለፍ ጉዳይ ሆነ፣ በሦስት ወር፣ በስድስት ወር ሆነ በዓመት የሚያስቀጣ ጉዳይ ቢሆን መቆም የለበትም፡፡ እኛ አገር እኮ መከላከያ አለህ ሲባል ኧረ ጌታዬ መከላከያ ዘመድ የለኝም ብለው የሚመልሱ ስለሕግ መሠረታዊ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች እኮ ናቸው ፍርድ ቤት የሚቀርቡት፡፡ ዳኛው ከቀረበለት አቤቱታ ውጪ ወጥቶ አንተን አይመራህም፡፡ የመጀመሪያ መቃወሚያህን ወይም አቤቱታህን የምታቀርብበት ሁኔታ የፍርድ ሒደቱን በእጅጉ ይወስነዋል፡፡ አንተ ካላነሳህ ዳኛ አያነሳልህም፡፡ እሱ ያንተ መብት ነው፣ መጠቀም አለብህ፡፡

ሪፖርተር፡- የቅጣት ሁኔታን የሚወስነው የፍርድ ሒደቱ አይደለም ወይ? ከፍርድ ሒደቱ በፊት ጉዳዩ አምስት ዓመት ሆነ አሥር ዓመት የሚያስቀጣ ነው ብሎ እንዴት መወሰንስ ይቻላል? ይህ ባልታወቀበት ሁኔታ የተከላካይ ጠበቃ የመቆም ያለመቆም ጉዳይ በምን አግባብ ይወሰናል?

አቶ አበባው፡- አዎ ትክክል ነው፡፡ ይህ ሰውዬ እኮ አምስት አሥር ዓመት አይደለም ነፃ ሊወጣም ይችላል፡፡ ቅጣት ማቅለያ ቅጣት ማክበጃ ሒደቶች ሁሉ በፍርድ ሒደቱ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ታልፈው ነው የፍርድ ውሳኔ የሚሰጠው፡፡ መቃወሚያ አለህ ወይ ሲባል ኧረ ጌታዬ እኔ በፍፁም መንግሥትን ተቃውሜ አላውቅም የሚል አንድ ሰው፣ የተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምለትም ሆነ ቅጣት ማቅለያ እንዲደረግለት መጠየቅ እንዴት ይችላል የሚለው መታየት አለበት፡፡ ተቃውሞ አለህ ወይ ስትለው አንድም ቀን ተቃውሜ አላውቅም የሚል በጣም የሚያሳዝን የሕግ ግንዛቤ ክፍተት ያለበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ማስቀጣት ነው ዓላማው፡፡ እኛ አገር ማስቀጣት የፍትሕ ሥርዓቱ ስኬት ተብሎ በቁጥር ሪፖርት ይደረጋል፡፡ ይህን ያህል ሰው በስድስት ወር በዓመት አስቀጣን ተብሎ ይቀርባል፡፡ ነገር ግን በትክክለኛው ከሄድን የዓቃቤ ሕግ ዓላማው ፍትሕን ማስፈን፣ ወንጀልና ወንጀለኞችን ከፖሊስ ጋር ሆኖ በመከላከል ሕግን ማረጋገጥ፣ በወንጀል ጥርጣሬ ነፃ የሆኑ ሰዎችን መብት ማረጋገጥም ሌላው ኃላፊነቱ ነው፡፡ ይህን ሰው ጠርጥረን ይዘነው ነበር፣ ነገር ግን ባደረግነው ማጣራት ነፃ በመሆኑ ሕጋዊ መብቶቹ ይከበሩለት ብሎ የሰዎችን ንፅህና የሚያረጋግጥ መሆንም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡-የመጽሐፉ ገጽ 223 ስለማስረጃ ሕግ ይተነትናል፡፡ በኢትዮጵያ ትኩረት የተሰጠው ማስረጃ ከመቅረቡ በፊት ላለው ሒደት ሳይሆን ከቀረበ በኋላ ላለው ሁኔታ ነው በማለት ይገልጻል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?

አቶ አበባው፡- በዓለም ላይ ሁለት አይነት የሕግ ሥርዓት አሉ፡፡ እነሱም ‹‹ኮመን ሎው›› እና ‹‹ሲቪል ሎው›› ይባላሉ፡፡ ኮመን ሎው እንደ አሜሪካ ዓይነት አገሮች የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ በዝርዝር ያልተጻፉ ሕጎች ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡ ሙግቱ ‹‹በላ ልበልሃ›› ዓይነት ነው የአሜሪካ ሕግን ስታይ፡፡ የዳኞች አሿሿም ሒደቱ ብዙ ጥናትና ምርመራ የሚደረግበት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በአካዴሚው፣ በልምድ ብቻ ሳይሆን በገንዘብና በሀብትም የበቁ በመሆናቸው ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ሲያከራክሩ የፍትሕና ርትዕ ጥያቄ ብዙም አይነሳባቸውም፡፡ እኛ ግን የሲቪል ሎው የሕግ ሥርዓት የምንከተል ነን፡፡ የእኛ በአብዛኛው እንደ ፈረንሣይ ዓይነት አገሮች የሚከተሉት የተጻፈ ሕግ ያለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኔን ጨምሮ ብዙዎች ኢትዮጵያ ሲቪል ሎውን አትከተልም ብለን እንከራከራለን፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ የማስረጃ ሕግ የላትም፡፡ የተጻፈና የተደራጀ የማስረጃ ሕግ የለም፡፡ በወንጀል ሕጉም ቢሆን የፍርድ ሒደቱ ቅደም ተከተል አካል ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በፍትሐ ብሔሩም ቢሆን ቅደም ተከተል ሆኖ ተንጠባጥቧል እንጂ ራሱን ችሎ የተደራጀ የማስረጃ ሕግ የለንም፡፡ ያኔ በ90ዎቹ ተማሪ እያለሁ ጀምሮ የማስረጃ ሕግ እንደተረቀቀ አውቃለሁ፡፡ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ይፀድቃል ሲባል የነበረ፣ ነገር ግን እስካሁንም ያልፀደቀ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ስለማስረጃ ሕግ ጽፈዋል፡፡ ማስረጃ በወንጀል ሕግ አንድን ጉዳይ ከበቂ ጥርጣሬ በላይ (Beyond Reasonable Doubts) መሆኑ የሚመዘንበት እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ የሰው፣ የሰነድ፣ የገላጭ ማስረጃ (ኤግዚቢት) ማስረጃዎች አሉ፡፡ አንድን ሰው ማስረጃ እስካሟላ አይለቀቅ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ይባላል፡፡ ሰውዬውን የሚያስከስሱ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲቻል ነው ይህ የሚደረገው፡፡ ማስረጃ ለማሟላት ሁለት ጊዜ ያክል የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አስፈላጊና እየተመረመረ ያለ ጉዳይ አለኝ በሚል ነው የሚጠየቀው፡፡ ይህኛው ቀነ ቀጠሮ አጠያየቅ ደግሞ ስንት ጊዜ ድረስ ይቻላል ለሚለው የጊዜ ገደብ የለውም፡፡ ለዘመናት ሰውዬውን ልታቆየው ትችላለህ፡፡ የተቀመጡም ሰዎች አሉ፡፡

የማስረጃ ሚዛኖቻችንን ቀድመን ለመሰብሰብ ትኩረት እንደምንሰጠው ሁሉ ሰብስበን ካመጣን በኋላ ደግሞ በምን መንገድ አደራጅተን የምንጠቀምበት አግባብ ሕጉን በተከተለ መንገድ አይደለም፡፡ ማስረጃ የሚመዘነው እንደየ ዳኛው ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ማስረጃ አቀራረባችንና እንደ ማስረጃዎቻችን አስረጂነት ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ስልክህን ወስዶ ማስረጃ ለማግኘት ይመረምረዋል፡፡ እኔ በግሌ የትግራይ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት የገጠመኝን አንድ ኬዝ ላንሳ፡፡ ሰውዬው አሰብ አካባቢ የኖሩ ከኤርትራ የመጡ በጣም ሀብታም የሚባሉ ናቸው፡፡ በፊት በነበረው ታሪክ ደግሞ አሰብና አፋር አንድ ግዛት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተፈጥሮ ጋዝ አግኝተናል ብለው የተናገሩትን ንግግር ሰምተው ወደ ኢትዮጵያ ነዳጅ አወጣለሁ ብለው ነው ሰውዬው የመጡት፡፡ በኮሮና ወቅት ድርቅ በአፋርና በአሰብ አካባቢ ጉዳት ባደረሰ ጊዜ ቢያንስ እንስሳትን ከሞት ለማትረፍ በሚል፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው የነቀዘ በቆሎና ስንዴ በማስመጣት ለከብቶች ማትረፊያ መኖ እንዲሆን አከፋፍለው ነበር፡፡ ይህ ካለፈ በኋላ ሰውዬው ነዳጅ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ደግሞ አሰብ አብሯቸው የሚሠራ ሰው አስከትለው ነበር የመጡት፡፡ ይህ ሰው ግን የተበደረውን ገንዘብ ባለመክፈሉ የተቀየሙ የአፋር ተወላጆች አሳሰሩት፡፡ ሰውዬውን ለማስፈታት አፋር ሄደን ስንመለስ ደግሞ ጦርነቱ በፈጠረው ውስብስብ ችግር የተነሳ፣ እዚህ ዋናው ሰውዬ በአሸባሪነት ተወንጅለው ታሰሩ፡፡ ስልካቸው ይመርመር ተብሎ ተመረመረ፡፡ ምንም ባይገኝበትም ነገር ግን ስለጦር መሣሪያ ያደረጉት ንግግር ማስረጃ ተብሎ ቀረበ፡፡

በ2009 ዓ.ም. መሣሪያ ከኢራን በመርከብ ጭነው ወደ ደቡብ ሱዳን ወስደዋል የሚል ውንጀላ ቀረበባቸው፡፡ እሺ ይህ ማስረጃ ቀረበ፡፡ ነገር ግን ሰውዬው ለተከሰሱበት ዓላማ አስፈላጊ ማስረጃ ነው ወይ የሚለው መታየት አለበት፡፡ የመጣው ማስረጃ ምንጩ ቅቡልነት አለው ወይ? ማስረጃው ተዓማኒ ነው ወይ? ማስረጃው ለዳኝነቱ ሚዛን የሚደፋ ነው ወይ? የሚለው መታየት አለበት፡፡ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ማስረጃ ብለህ ያመጣኸው ነገር አንዳንዴ ተመዝኖ ዋጋ ሳይኖረው በ42 ሊዘጋ ይችላል ወይም በክርክር ሒደት ሊዘጋ ይችላል፡፡ ስለዚህ የማስረጃ ዓላማ ምንድን ነው የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በዚያ ላይ ፖሊስ ማስረጃ የሚሰበስበው ፖሊሳዊ ጥበቡን ተጠቅሞ ነው? ወይስ በግርድፉ አልያል ዝም ብሎ ሰዎችን እየረገጠና እየጠፈጠፈ ነው የሚያሳምነው የሚለው ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ለምሳሌ አስገድደህና ደብድበህ የምትቀበለው ማስረጃ ተቀባይነት የለውም ይባላል፡፡ ነገር ግን ዛሬም ድረስ ያውም በየአደባባዩ ሰዎች እየተቀጠቀጡ እኮ ነው ይህን ሰርቀሀል፣ ያንን ወስደሀል እየተባሉ እንዲያምኑ የሚገደዱት፡፡ ይህ የሚደረገው ከክስ በፊት ማስረጃ ለማደራጀት ነው፡፡ ማስረጃውን ለማሰባሰብ የሄድክበት ርቀት ግን ምን ያህል ሕገወጥ እንደሆነ ሕግ አስከባሪ ነኝ ባይ ሁሉ ብዙም አያውቀውም፡፡ ‹‹ሩል ኦፍ ሎው›› ወይም ‹‹ሩል ባይ ሎው›› የሚለው ብይን ላይ ነው ይህ ጉዳይ የሚወድቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ቅጣትን በሚመለከት በመጽሐፉ ገጽ 224 ላይ እስር፣ መቀጮ (ገንዘብ)፣ የግዴታ ሥራ፣ የሞት ብይን፣ ማስጠንቀቂያና ተግሳፅ ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ማኅበራዊ ግልጋሎት እንደ መቅጫ እንደማይታይ በግል ይናገራሉ፡፡ የዚህን ጉዳይ አስፈላጊነት ቢያብራሩ?

አቶ አበባው፡- በክልልም ሆነ በፌደራል ፍርድ ቤቶች በአብዛኛው የተለመደው ቅጣት እስራት ነው፡፡ ለወንጀሉም፣ ለፍትሐ ብሔሩም፣ ለግድያውም፣ ለደፈራውም ሆነ ለሌላውም ጥፋት እስራት ነው የሚታዘዘው፡፡ ሰውን ስታስር ግን የሚባክነው የመንግሥት በጀት ነው፡፡ የመንግሥት በጀት ደግሞ ከራሱ ከማኅበረሰቡ የሚሰበሰብ የአገር ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ ከምታስር በማኅበረሰብ አገልግሎት ቅጣት ሰዎችን ማስተማር ለምንድን ነው የማይቻለው? ለምሳሌ ክሪስ ብራውን የተባለ አንድ ታዋቂ የአሜሪካ ሙዚቀኛ ሪሀና የተባለች ታዋቂ ሙዚቀኛ ዕጮኛውን በአንድ ወቅት በመደብደቡ የተጣለበት የማኅበረሰብ አገልግሎት ቅጣት ነበር፡፡ ዘፋኙ እጅግ ታዋቂ፣ ሀብታምና አይነኬ ነው ተብለው ከሚታመኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ሰውዬው ሰክሮ ይሁን በሌላ የማይታወቅ የአዕምሮ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የምወደውን መኪናዬን ነካሽብኝ በማለት ነው ሪሀናን የደበደባት፡፡ ገንዘብ ልቅጣው ብትል በቀላሉ ከፍሎ ነፃ ይወጣል፡፡ ልሰርህ ብትለውም ተገቢውን ቅጣት ይቀበላል ተብሎ አይታመንም፡፡ እስር ቤትም ቢገባ እንቅስቃሴው በአንድ ቦታ ከመገደቡ በስተቀር፣ ታዋቂ ሰው በመሆኑ በሌሎች እስረኞች እንክብካቤ መሬት አይንካህ ተብሎና ተከብሮ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የሟቹ ራፐር ቱፓክ ሻኩር ፕሮዲዩሰርና የዴዝ ሮው ሬከርድስ ባለቤት ሹጌ ናይት በእስር ቤት ልዩ እንክብካቤ ነበረው፡፡ የኮሎምቢያው ሀሺሽ ነጋዴ ፓብሎ ኤስኮባር ራሱ መንግሥትን በመርዳት ባሠራው የኮኮብ ሆቴል ደረጃ ባለው እስር ቤት ነበር የታሰረው፡፡ ብዙ ጊዜ እስር ቤት ኃይለኞች የሚታረሙበት ቦታ አይደለም፡፡ እንኳን ክሪስ ብራውን ቀርቶ በእኛም አገር እኮ ገንዘቡ ካለህ በምትፈልገው የጥራትና የእንክብካቤ ደረጃ እንደምትታሰር ይነገራል፡፡ ማታ 12 ሰዓት ተቆጥረው ወጥተው ጠዋት 12 ሰዓት ተቆጥረው የሚገቡ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ሌሎችም ያልተፈቀዱ ብዙ ነገሮች የሚደረጉላቸው ታሳሪዎች መኖራቸው ይሰማል፡፡ ይህን መሰል ሸፍጥ ባለበት ዓለም ማስተማርን ግብ ያደረገው የቅጣት ዓላማ ሊሳካ አይችልም፡፡ ስለዚህ ዳኛው ይህን አገናዝበው ክሪስ ብራውን የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሠራ ፈረዱበት፡፡ በአካባቢው የመንገድ ላይ ቆሻሻ እየጠረገ እንዲደፋ ተፈረደበት፡፡ ለዚህ በጣም ታዋቂ ለሆነ ሰው ጠዋት እየተነሱ መንገድ ከሚያፀዱ ሰዎች ጋር ቱታ ለብሶ ቆሻሻ መጥረጉ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ፓፓራዚዎች ሲገባ ሲወጣ እየተከተሉት ኃፍረቱን ለመሸፈን ፊቱን ተከናንቦ ጭምር ሲያፀዳ መታየቱና የዓለም መገናኛ ብዙኃን ትኩረት በመሆኑ ተገቢውን ቅጣት አግኝቷል፡፡ ለሌሎችም ከሕግ በላይ አድርገው ራሳቸውን ለሚያስቡ ሰዎች ትምህርት የሚሰጥ፣ አይነኬ የሚባል ሰው እንደሌለ የሚያሳይ ማረጋገጫ የሆነ ኬዝ ነው፡፡ ወደ እኛ አገር ስትመጣ ግን ገበሬውን፣ ሥራ ፈቱን፣ ባለሀብቱንና ሌላውን ከምታስር ማኅበራዊ አገልግሎት መስጠትን ማስተማሪያ አድርጎ መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተማ ልማት በሰፊው እየተካሄደ ነው፡፡ ለምንድነው በእነዚህ ሥራዎች የማይሳተፉት፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ማረሚያ ቤቶች እርሻ ልማቶችን ጨምሮ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን መሥሪያና ሙያ መቅሰሚያ የሆኑ ወርክሾፖች ነበሯቸው፡፡ ታራሚዎች የሚያመርቱት ምርትም ከማረሚያ ቤት ቀለብነትና አገልግሎት መስጫነት አልፎ ለሕዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርብ ነበር፡፡ አሁን አሁን ይህ ነገር ቀርቷል?

አቶ አበባው፡- የሚገርመው በ1949 ነው የወንጀል ሕጉ የወጣው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህን መሰል የቅጣት ዓይነት በኢትዮጵያ አለ ማለት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን ግን ቅጣትን የተረጎሙበት መንገድ እስራት ላይ ያተኮረ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ማረሚያ ቤቶች ከመንግሥት ሳይጠብቁ በራሳቸው በጀት የሚተዳደሩበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ የሚታረስ ቦታ አላት፡፡ ኢትዮጵያ መንገድ ለማሠራት ብዙ ቢሊዮን ብሮችን ለጉልበት ሠራተኞች ታወጣለች፡፡ እዚህ ላይ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራውን እንደ ቅጣት ሲሠሩ በነፃ ይሥሩ ተብሎ አይደለም የሚታሰበው፡፡ የሚገባቸውን ዋጋ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡ ልፋትና ድካማቸው ከገንዘብ ማስገኛነት ባለፈ በቅጣት ማቅለያነትም ሊታይ ይገባል፡፡ ሲወጡ ታርመው ብቻ ሳይሆን ዳግም ሕይወትን ለመቀጠል የሚያስችል ጥሪት ይዘውና ሙያ ቀስመው እንዲወጡ ማድረጉ ደግሞ፣ እንደ አገር በዘላቂነት ማኅበራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚረዳ ውጤት ይኖረዋል፡፡ የአንድ ሰው ሕይወት የአገር ሀብትና የሉዓላዊነት ህልውና ነው፡፡ እኛ አገር እኮ ብዙ ሚሊዮኖች በረሃብ የሚረግፉ ቢሆንም፣ በተቃራኒው ደግሞ ሰብል አሽቶና አዝመራው ደርሶ ነገር ግን የሚሰበስበው የሰው ኃይል አጥቶ ዝናብና ውርጭ አበላሽቶት ባክኖ ይቀራል፡፡ ቁጭ ብሎ መንግሥት እየቀለበው የሚያሳልፍ ታራሚ ግን በአብዛኛው ሲወጣ ተመልሶ ከነበረበት ቦታ ነው የሚጀምረው፡፡ ወንጀልም ሊደጋገም ይችላል፡፡ ቀላል እስራት የሚባሉ በማኅበረሰብ አገልግሎት ቅጣት ቢታለፉ ውጤታማ ነው፡፡ ሰዎች ገንዘብም፣ ሙያና የሥራ ልምድ ይዘው ይወጣሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ተደጋጋሚ የወንጀል ድርጊቶች የሚፈጽሙ በተለይም ዘረፋና ሌብነት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ጉዳይ ዋስትና ሲጠየቅ የቀደመ ሪከርዳቸው አይታይም፡፡ ጥፋታቸው ዋስትና የማያስከለክል ነው በሚል ብቻ በተደጋጋሚ ወንጀል ላይ መሳተፋቸው ግምት ውስጥ ሳይገባ በዋስ እንዲለቀቁ ይደረጋል፡፡ ይህ ምን ችግር አምጥቷል?

አቶ አበባው፡- እኛ አገር ወንጀሎች ዋስትና የሚያሰጡና ዋስትና የማያሰጡ ተብለው በሁለት ተለይተዋል፡፡ ዋስትና የሚያስከለክሉ ወንጀሎች ከአምስት ዓመት በላይ የሚያስቀጡ ከባድ ጥፋቶች ናቸው፡፡ ዳኞች ሁሌም ቢሆን ዋስትና ያሰጣል አያሰጥም የሚለውን ነው የሚመዝኑት፡፡ ይሁን እንጂ የወንጀል ተደጋጋሚነትና ተደራራቢነት የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በክረምት የውጪውን ብርድና ቁር ፍራቻ ሆን ብለው ወንጀል እየሠሩ የሚታሠሩ ሰዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግሥት እንደሚያበላቸው፣ እንደሚያጠጣቸውና ብርድ እንደማይመታቸው እርግጠኛ መሆናቸውን አስልተው ነው የሚታሰሩት፡፡ የቅጣት ዓላማ ማስተማር እንደ መሆኑ መጠን የምናስተምረው ደግሞ በትክክል ቀጥተን መሆን አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለአመክሮ ብለው ብዙ ውሸት ሰዎች ይዋሻሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተከሰስኩት ይላሉ፡፡ የወንጀል ደጋጋሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ ማከማቻና ማስታወሻ ዳታ ቤዝ (ቋት) የለም፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚያን ሰዎች ፖሊስ እያወቃቸውና ቢለቀቁም ወንጀል በመደጋገም እንደሚያስቸግሩ አቤቱታ እያቀረበ ፍርድ ቤቱ ለምን ይለቃል? የፖሊስ የወንጀል ደጋጋሚነት ማስረጃ ለምን ተቀባይነት የለውም?

አቶ አበባው፡- ሕጉ ዋስትና አያስከለክልም ካለ ፍርድ ቤቱ የሚያየው እሱን ነውና ሰውዬው ዋስትና ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም ወንጀል የሚደጋግሙ ሰዎችን አስራት የማያስተምራቸው ከሆነ በምን እንቅጣቸው ብሎ ሌሎች አማራጮችን ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሠራ ቢደረግ ሊማር ይችላል፡፡ ትናንት ችግኝ ተከላ ወይ መንገድ ጠረጋ ሠርቶ ከሆነና ሳይታረም ጥፋተኛ ሆኖ ከመጣ በምትኩ ድልድይ ግንባታ ላይ መመደብም ይቻላል፡፡ እስኪማርና ከወንጀለኝነት እስኪርቅ ድረስ ቅጣትን በማለዋወጥ መሞከሩ የተሻለ አሠራር ነው፡፡ የወንጀል ተደጋጋሚነት ብቻ ሳይሆን፣ ተደራራቢነት የሚባል ጉዳይም አለ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ለስርቆት ብሎ አንድ ቤት ውስጥ ሲገባ ባልተፈቀደ ቦታ ተገኝቷል ወይም የሌሎችን ነፃነት ተዳፍሯል፡፡ ሲገባ ጥበቃውን ታግሎና ጎድቶ ነው የገባው፡፡ ከገባ በኋላ ደግሞ ያገኘውን የቤቱን አባወራ ገደለው፡፡ ሦስት ወንጀል መፈጸሙ ሳያንስ በቤቱ ውስጥ ያገኘውን ዕቃ ይዞ በመሰወር አራተኛ ወንጀል ፈጸመ፡፡ ብዙ ጊዜ አንዱን ከባድ የወንጀል ጉዳይ በማንሳት ብቻ ነው ወንጀለኞች ተጠያቂ የሚሆኑት እግረ መንገዳቸውን ያደረሱት ወንጀል ይዘለላል፡፡

ሪፖርተር፡- በውጭው ዓለም እያንዳንዱ ጥፋት በተናጠል ተጠቅሶ 100 እና 200 ዓመታት እስር ሲፈረድ ይታያል እኮ?

አቶ አበባው፡ በትክክል፡፡ በእኛ አገር የፍትሕ ሥርዓት ግን ከ25 ዓመታት በላይ የእስር ቅጣት አይሰጥም፡፡ ለምሳሌ እኔ የማውቀው አንድ የወንጀል ጉዳይን ልንገርህ፡፡ ሁለት ሰዎች በኤሌክትሪክ አጥር የታጠረና ዘበኛ የሚቆምለት የአንድ ሀብታም ቤትን ለመዝረፍ ይሰማራሉ፡፡ የመኖሪያ ቤቱ ባለቤቶች ሙስሊሞች እንደሆኑ በማጥናት የሙስሊም ልብስ ለብሰው ነው በር ላይ ቆመው ያንኳኩት፡፡ ዘበኛው አጮልቆ ሲያይ በመኪና መምጣታቸውና ልብሳቸው ዘመድ የመጣ እንዲመስለው የሚያደርግ ነበር፡፡ የሰው መግቢያ በሩን ገርበብ አድርጎ ከፍቶ ሊያናግራቸው ሲሞክር ግን ጎተቱት፡፡ መሣሪያ ይዞ ስለነበርም ሲታገላቸው አናቱን በብረት መትተው ጣሉት፡፡ ከዚያም ወደ ቤቱ ዘለቁ፡፡ ሲገቡ የቤቱ ባለቤት ሚስት ከሴት ልጇ ጋር ሳሎን ተቀምጠው አገኟቸው፡፡ ዓላማቸው መስረቅ የነበረ ቢሆንም እየተፈራረቁ እናትና ልጅን ወደ መድፈር ይገባሉ፡፡ በሌላ የቤቱ ክፍል የነበረ ወንድ ልጅ በድንገት ወደ ቦታው ሲደርስ እሱን በያዙት ስለት ወግተው ይገድሉታል፡፡ ይሁን ሁሉ አድርገው ዘርፈው ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሰው ቅጥር ግቢ ጥሰው ከመግባት ጀምሮ፣ ዘበኛው ላይ ለከባድ አደጋ የሚዳርግ አካላዊ ጉዳት አድርሰው፣ ሁለት ሴቶችን አስገድደው ደፍረው፣ አንድ ልጅ ገድለው፣ እንዲሁም የሰው ንብረት ዘርፈው ነበር የሄዱት፡፡ ይህ ሁሉ አምስትና ከዚያ በላይ የሚሆን የተደራረበ የወንጀል ድርጊት ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ሰው ገድለው ዘረፉ የሚለውን እንጂ ሌላውን ብዙም አትሰማውም፡፡ አስገድዶ መድፈር በራሱ በድብቅ የሚፈጸም ነው አይነገርም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚከሰሱት ከባድ የሆነውን የወንጀል ድርጊት መርጠው ነው፡፡ ገድለው የሚለው እንጂ አካላዊ ጉዳት አድርሰውና ዘርፈው ስለመሄዳቸው ክሱ ላይ ላይተኮር ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ደጋጋሚነትና ደራራቢነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ከበድ ያለ ቅጣት መበየን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ጣሪያውን ነው የምትሰጠው፡፡ የሚታሰሩ ሰዎች በደንብ ወንጀልን የማጥናት ዕድል ያገኛሉ፡፡ አንዱ አንዲት ደረሰኝ አልቆረጠም ተብሎ ይታሰራል፡፡ ሌላው ደግሞ የሐሰት ደረሰኝ እየቆረጡጠ መሸጥን ዋናው የገቢ ምንጩ አድርጎ በመቶ ሚሊየኖች ሲያጭበረብር ኖሮ የታሰረ ይሆናል፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ የታሰሩ ከሆነ በአንዲት ደረሰኝ የታሰረው ሰው ከሁለተኛው ሰው ብዙ የወንጀል ልምድ ቀስሞ ነው ከእስር የሚወጣው፡፡ የቅጣት ዓላማ እዚህ ላይ ፉርሽ ሆነ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዋስትና ጉዳይን ስናይ በፍርድ ቤት ዋስ የተፈቀደላቸው ታሳሪዎችን ፖሊስ አልለቅም ሲል በተደጋጋሚ ይታያል፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል?

አቶ አበባው፡- ፖሊስ ሥልጣኑ ወንጀልን መከላከልና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ማስፈጸም ነው፡፡ ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ማስረጃ አደራጅቶ ተጠርጣሪውን ለፍርድ ቤት በማቅረብ፣ የተፈረደበትን ጥፋተኛ ደግሞ ማረሚያ ቤት ወስዶ ቅጣቱን እንዲቀበል ማድረግ ነው የፖሊስ ዋና ሥራ፡፡ ለምንድነው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማይከበረው? የአንድ ወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔን ላለመፈጸም ሌላ ወረዳ ፍርድ ቤት መውሰድ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ይህ በፍፁም የሕጉም ሆነ የፖሊስ ዓላማ አይደለም፡፡ ፖሊስ ማለት እኮ በዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ማዕቀፍ ሥር የሚመራ ዓለም አቀፍ ስምና ክብር ያለው ትልቅ ሙያ ነው፡፡ የዲሲፕሊን መርሆዎችን ልታወጣ ትችላለህ እንጂ፣ ፖሊስ እንደ መደበኛው ሥራ በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ የማይተዳደር ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የተከተለ ሥርዓት ያለው ተቋም ነው፡፡ ሕግ አንዳንዴ የአንዱ ውሽማ የሌላው ደግሞ ጣውንት ትሆናለች፡፡ ፖሊስ ገለልተኝነቱን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ ሲሆን ብዙም አይታይም፡፡ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ሳይፈቱ የሚቀሩ ሰዎች በሚያስገምት ደረጃ የአንድ የፖለቲካ ወገን አባል ናችሁ የተባሉ ሰዎች፣ ለፖለቲካው አደጋ ናችሁ የተባሉ ሰዎችና ከፖለቲካ ጋር የተገናኙ ሰዎች ናቸው፡፡ በአንድ የፖሊስ ጣቢያ አዛዥ የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው እየተሻረ ያለው፡፡ አንድ ሰው በዋስትና ይፈታ ከተባለ ልቀቀው፣ በሌላ ወንጀል ጥርጣሬ የምትፈልገው ከሆነም ከለቀቅከው በኋላ ነው ከፍርድ ቤት መጥሪያ አምጥተህ የምትሰጠው፡፡ ፍርድ ቤቱ በዋስ ይውጣ ሲል በር ላይ ጠብቀህ ሌላ መጥሪያ የምትሰጠው ከሆነ ግን አግባብ አይደለም፡፡ ይህ ነው ወይ የፖሊስ ፋይዳውና ዓላማው? ፍርድ ቤት እኮ ከእግዚአብሔር በታች እውነትን የሚያረጋግጥልህ ተቋም ነው፡፡ መብት አለኝ ብለህ ቆመህ የምትሄደው ፍርድ ቤት ስላለ ነው፡፡ ሰው ደብድበሃል ተብለህ የዋስትና መብት ትከለከላለህ፡፡ ነገር ግን ሰው ሲደበድብ ዓይን የሚያጠፋ የፖሊስ አባል የለም እንዴ? በአደባባይ እየደበደቡ የአካል ጉዳት የሚያደርሱ ፖሊሶች ምን ያህል ተጠያቂ እየተደረጉ ነው የሚለው መጤን አለበት፡፡ አገራዊ ኃላፊነት፣ የሕግ ተገዢነት፣ ፖሊሳዊ ሥነ ምግባርና የሕግ የበላይነት የሚለው ሁሉ ከፖሊስ ሥራ ጋር ተያይዞ ይነሳል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የፍትሕ ሚኒስቴር ባቀረበው አንድ ጥናት ማስረጃና ምስክሮችን ማቅረብ ባለመቻል ብዙ ተጠርጣሪዎች ያለተጠያቂነት ይለቀቃሉ የሚል ድምዳሜ ይፋ ሆኗል፡፡ ይህን ሐሳብ ይጋሩታል?

አቶ አበባው፡- ወንጀል አለ ከተባለ ወንጀል መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሐሰት ማስረጃ አስመስክረህ፣ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽሟል ብለህ ተገደለ የተባለ ሰው ግን በሕይወት አለ ሲባል ምንድነው የሚሰማህ? ከዚህ በላይ ምን ሞት አለ? ማኅበረሰቡ ነፍሰ ገዳይ ብሎህ፣ ሥራህ፣ ቤተሰብህ፣ ቤት ንብረትህ ሁሉ ተበታትኖ ያ ነፍሰ ገዳይ እየተባልክ፣ የሟች ቤተሰቦች የዕድር ገንዘብ በልተው እርማቸውን አውጥተው ጨርሰው ነገር ግን የሞተው ሰው በሕይወት ተገኘ ሲባል ምን ይባላል? እኔ የማውቀው አንድ ዓለማየሁ የሚባል ልጅ ሐና ማሪያም አካባቢ ባላቸው ሰፊ ግቢ መኪና ማጠቢያን ጨምሮ ሞባይል መሸጫዎችንና ሱቆችን አከራይተው ከቤተሰቡ ጋር ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን በሆኑ ችግሮች ከዚያ አካባቢ ፖሊሶች ጋር አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ደግሞ ሰው ተገደለ ተብሎ እሱና አምስት ሰዎች ይታሰራሉ፡፡ ከአምስቱ ሁለቱ ይፈታሉ፡፡ እሱን ጨምሮ ሦስቱ ግን ቃሊቲ ተዛውረው ታሰሩ፡፡ በየሦስት ወሩና በሆነ ጊዜ አንዴ ፍርድ ቤት እየሄዱ ክሳቸውን ይሰማሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እየተራዘመ ለሦስት ዓመት ከ11 ወራት ታሰሩ፡፡ ‹‹ጀስቲስ ዲሌይ ጀስቲስ ዲናይድ›› እንደሚባለው አስታዋሽ አጥተው በእስር በሰበሱ፡፡ በዚህ መካከል የዓለማየሁ ሚስትና ልጅ ወደ ውጭ አገር ሄደዋል፡፡ በተጨማሪ ወላጅ እናቱ ሕመምና ብስጭት ተደራርቦባቸው አርፈዋል፡፡ ይህ ሰው ፍርደኛ ባለመሆኑ መንግሥት አይቀልበውም፣ ከቤት ነው ምግብም ውኃም የሚመላለስለት፡፡ መጠጥ ቤትና የሚያከራየው ንግድ ቤቶች ስለነበሩት እንጂ የእስር ወጪውን መቋቋም ከባድ ነበር፡፡ ወደ አራት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሲታሰር የነበረው ሀብትና ንብረትም በአብዛኛው ጠፍቷል፡፡

በመጨረሻ ግን ተገደለ የተባለው ሰው ደሴ ከተማ አካባቢ ተገኘ፡፡ በብዙ ጥረት ሰውዬው መጥቶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ከዚያ በኋላ በአንዲት ደረሰኝ ነበር ነፃ የወጣው፡፡ ከተከሰሱበት ወንጀል ነፃ ስለተባሉ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተለቀዋል የምትል ብጣሽ ደረሰኝ ስትጻፍለት ግን ዕድሉን እያመሠገነ እሰይ እያለ ነው የወጣው፡፡ የእኛ የፍትሕ ሥርዓት እንዲህ ያለ ነው እንግዲህ፡፡ ይህ ሰውዬ የፍትሕ በደለኛ አይደለም ወይ? በሦስት ዓመት ከ11 ወራት ያለ ፍርድ ታስሮ ቢለቀቅ በሌላ አገር ምን ሊባል ነው? በሐሰት ለተወነጀለ ሰው ካሳ አለን ወይ? አንድ ሰው በዚህ ደረጃ የፍትሕ በደለኛ ሆኖ ፖሊስም፣ ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፍርድ ቤትም አይጠየቅም፡፡ የሰውዬው መጠርጠር እኮ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ አስረህ ስታበቃ ነፃ ብለህ ስትለቅ የገንዘብና የሞራል ካሳው ቀርቶ በወጉ ይቅርታ ማለትን እንኳ ልትነፍግ ይገባል ወይ? እሱንም፣ ቤተሰቡንም፣ የሚኖርበትን አካባቢንም በወጉ ተሳስተን ነበር ብለህ ይቅርታ መጠየቅና ጥፋትን ለማረም መሞከር የለብህም ወይ? ሰዎች በዚህ ደረጃ የፍትሕ በደለኛ ከሆኑ ከማኅበረሰቡ ጋር ቀርቶ ከአገራቸው ጋር ጭምር የሚቃረኑ አይሆንም ወይ? ፍትሕና ሕግን ከአፈር በታች አውርደው ሊመለከቱት አይችሉም ወይ የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ኢንቨስትመንት ሲገባ የአንድን አገር ሕግ ያጠናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ ለውጭ ኢንቨስተሮች ከለላና ዋስትና የሚሰጥ ነው ወይ? በዚህ ረገድ ያለው ክፍተት ምን ይመስላል?

አቶ አበባው፡- እኛ አገር የሕግ ችግር የለም፡፡ የኢንቨስትመንት ሕጉ አለ፣ የወንጀል ሕጉ አለ፣ በየክልሉ ደግሞ የማስፈጸሚያ ሕጎች አሉ፡፡ መታየት ያለበት ጉዳይ ግን የሰዎች ሰብዓዊ መብት፣ ሰብዓዊ ክብርና ነፃነት በአደባባይ የሚጣስበት አግባብ መኖር አለመኖሩ ነው፡፡ በእኛ አገር ሕገ መንግሥት ማንኛውም ሰው የውጭ ዜጋም ጭምር በፈለገበት ቦታ የመንቀሳቀስ፣ ሠርቶና ንብረት አፍርቶ የመኖር መሠረታዊ መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ አንድ ክሊንተን ዋሽንግተን የተባሉ እንግሊዛዊ ጉዳይ ይዤ አውቃለሁ፡፡ ሰውዬው ሙከ ጡሪ አካባቢ ከብት እያረቡ ይሠሩ ነበር፡፡ የወተት ምርት እጥረት ለመፍታት ከሚሠሩት የግብርና ሥራ በተጨማሪ ለአካባቢያቸውም የበኩላቸውን ሲደግፉ ኖረዋል፡፡ ጊደር የሚባሉ የወተት ላሞችን ለሌሎች እየሰጡ ሰዎችን ያበቁም ነበር፡፡ በትንሹ በዚያ ወቅት 40 ሺሕ ብር የምትሸጥ ጊደር ነው ሲሰጡ የኖሩት፡፡ የተሻሻሉ የመኖ ዘሮችንም ለገበሬዎች ያቀርቡ ነበር፡፡ በለውጡ ዋዜማ የቄሮ አመፅ ሲነሳ ግን በአንድ ቀን ኢንቨስትመንታቸው ቆሞ ከቦታው እንዲነሱ ተደረገ፡፡ ንብረታቸው ብቻ ሳይሆን የራሳቸውም ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ ሰውዬው በፍትሕ አደባባይ የነበራቸው እንዲመለስ ለማድረግ ጥረት ጀምረን ነበር፡፡ ነገር ግን አቤቱታችን ሙሾ ሆኖ ነው የቀረው፡፡ ዛሬ በየአካባቢው ያሉ የውጭ ኢንቨስተሮችን ሁኔታ መገምገም ይቻላል፡፡ ሕግ እኮ የሚፈጸመው በሰዎች ነው፡፡ አስፈጻሚዎቻችን በየተቋማቱ ያሉት ብቁ ናቸው ወይ የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ለዜጎቿም ለውጭ ኢንቨስተሮችም በቂ ከለላ የምትሰጥ አገር ናት የሚል ዓለም አቀፍ ስምና ዝና እንድታተርፍ የሚያስችል አሠራርና አስፈጻሚዎች አሉን ወይ የሚለው ክፍተት የሚታይበት ነው፡፡ ሕጎቹ ቢኖሩም ነገር ግን ልል ናቸው፡፡ ሕጎቹ ቢላሉ እንኳ በአሠራር ሥርዓት ማጥበቅም ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ለውጭ አገር ዜጋ ለእኛ ለዜጎቹም ዋስትና የሚሰጥ አይደለም፡፡ አንተ አንድ የሆነ ክልል ሄደህ ለመሥራት የዚያ አካባቢ ብሔር ካልሆንክ አትችልም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ የሆነ ሰው ሆነህ የሆነ ክልል ችሎት ስትቀርብ ፍትሕ ታገኛለህ ወይ የሚለው ከባድ ነው፡፡ አንድ የሙዚቃ ተሰጥኦ ፕሮግራም ላይ ልጁ በደንብ አሳምሮ የጥላሁንን ዘፈነ፡፡ ነገር ግን ዳኛው በዚህ ዓይነት ቋንቋ ብትዘፍንልኝ ላሳልፍህ እችላለሁ ብሎ ነበር የነገረው፡፡ ዛሬ የፍትሕ አደባባይ ስትቆም ዳኞቹ በሚጥማቸው ቅላፄና ቋንቋ ከሌለህ ሰው በመሆንህ ያገኘኸው መብት እንዲከበር የሚያደርግ ብይን አይሰጡህም፡፡ በክልል፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በዞን፣ በወረዳ፣ በቀበሌ፣ እያልን በተዋረድ እየጠበብን እንድንሄድ የሚያደርግ ሥርዓት ነው የገነባነው፡፡ አገርን በብዙ ሊቀይሩ የሚችሉ ብዙ ገንዘብና የመሥራት አቅም ያላቸው ሰዎች በአንድ ብር ደረጃ ተፈትነው ከአገር አልወጡም ወይ?

ሪፖርተር፡- የፍትሕ ሥርዓቱን እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ አበባው– ሕግ የሚፈጸመው በሰዎች ነው፡፡ የመንግሥት መዋቅራዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ሰዎች አንዱን ቅዱስ ሌላውን እርኩስ እያረጉ የሚሠሩ ከሆነ የፍትሕ ሥርዓቱ ይዛባል፡፡ የእኛ አገር ሕግ እኮ ከስዊዘርላንድና ከፈረንሣይ ተቀድቶ የመጣ ነው፡፡ ወደ 90 በመቶ በምትለው ደረጃ ከአውሮፓ የተቀዳ ነው፡፡ በሕግ ሳይንስ የሚጠቀሱ ሊቃውንት እነ ፕሮፌሰር ሬኒ ዴቪድ የሠሩት እኮ ነው፡፡ ስዊዘርላንድ ግን በዓመት አንዴ ነው ፍርድ ቤት የሚከፈተው ይባላል፡፡ እኛ ጋ ግን አንድ ዳኛ በሳምንት መቶ ጉዳዮችን ይመለከታል፡፡ እዚያ ሕጉን የሚያስፈጽመው ፖሊስ ነው፣ እኛምጋ ሕጉን የሚያስፈጽመው ፖሊስ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፖሊስ ሕጉን የሚጥስበት ሁኔታ እዚያም እዚህም ምን እንደሚመስል ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዳኞቹ እዚያም ሆነ እዚህ እኛ ጋ ሕግ የሚያሰፍኑበት ሒደት ያለውን ልዩነት ማነፃፀር ተገቢነት አለው፡፡ ሕግን ቀድቶ ማምጣት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ቀድተህ ስታመጣ ሕጉን ቀድተህ የምታመጣበት መንፈስ ግን ወሳኙ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ፖሊስ ሕግ ያስከብራል፡፡ ሆኖም ሕግ ለማስከበር የወንጀል ሥርዓት ሕጉን የሚያጠናበት አግባብ መኖሩ መታየት አለበት፡፡ የፖሊስ ዕድገት የሚገመገመው ተቋማዊ ዓላማውን ጠብቆ በሠራ፣ ሕጉን በአግባቡ በማወቁና በመተግበሩ፣ ሰብዓዊ መብትን በመጠበቁነው ወይ የሚለውን ስንገመግም ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይወድቃል፡፡ ፖሊስ ለመሆን በሆነ አካባቢ የሆነ ብሔር አባል መሆን አለብህ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ አንፃር የፍትሕ ሥርዓቱ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠበቆች አሁን አሁን በፍትሕ ሥርዓቱ ተስፋ በመቁረጥ ደንበኞቻቸውን ተደራድረው ጉዳያቸውን እንዲጨርሱ ወደ መምከር እያጋደሉ ሄደዋል ይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ አበባው፡- የእኛ አገር የፍትሕ ሥርዓት የማይገመት ነው፡፡ የወንጀል ጉዳይን መያዝ ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይ መንግሥት ተሳታፊ የሆነባቸውን ኬዞች መያዝ ለጠበቆች ፈታኝ ሆኗል፡፡ የዳኞች ገለልተኝነትና ነፃነት ስለሚፈተን እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን መውሰድ ከባድ ነው፡፡ ፍትሕ የፖለቲካ ውሽማ ናት፡፡ ዳኞች ደግሞ ፍትሕን ከፖለቲካው ጋር ለማስታረቅ የሚሠሩ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ የመንግሥት ፍላጎት አለባቸው በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ይህ በጉልህ ይታያል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ለመሆን ስትመደብና ከቦታው ስትነሳ ምን ዓይነት ሒደት እንዳለው አይተናል፡፡ ከዚህ አንፃር ጠበቆች ተደራድረው እንጂ ተከራክረው የሚያሸንፉበት አግባብ ወደ ዜሮ እየወረደ ነው፡፡ ሁለት ዓይነት መልክ ያላቸው ባለሙያዎች በዘርፉ እየተፈጠሩ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሕግ አዋቂዎች ሌሎቹ ደግሞ ዳኛ አዋቂዎች፡፡ ምንድነው ጉዳይህ ይልሃል ደረቱን ነፍቶ፡፡ የዛሬ 40 ዓመት እንዲህ ዓይነት የስድስት ወር ሥልጠና ወስጄ ነበር፣ በዳኝነት አገልግያለሁኝ፣ አሁን ደግሞ ጠበቃ ነኝ ሊልህም ይችላል፡፡ ጉዳይህ ምንድነው ማን ጋ ቀረበ ብሎ ይጠይቅህና ዳኛ እከሌማ የእኔው ሰው ነው/ናት ችግር የለውም እፈታዋለሁ ይልሃል፡፡ እውነትም ይሁን ውሸት ከዳኛ እከሌ ጋር ምሳ ወይም እራት አብሮ እንደነበር የሚያወራ፣ ከዳኞች ጋር ተነጋግሮ ጉዳይን ለመፍታት ቃል የሚገባ በርካታ ሰው ነው ያለው፡፡ ይህን ደግሞ ልደታ ፍርድ ቤት በር ላይ የቸገረው መስሎ ጠጋ ያለ ሰው በአንዴ ይረዳዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹ስለፍትሕ ለማውራት ብዙ ሩቅ ነን ይህን ደግሞ በብዙ ማስረጃዎች ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፡፡ ዳኛው ሌባ፣ ዓቃቤ ሕግ ሌባ፣ ፖሊስ ሌባ፣ ኦዲተር ሌባ…› ብለው ቃል በቃል ተናግረዋል፡፡ ይህ ባለበት አገር ላይ ምሬት የምታቀርበው ታዲያ የት ነው? አሁንማ በቴሌግራም ገጽ ለምትፈልጉት ጉዳይ ይህን ያህል እናስፈልጋለን ከሚል ማስታወቂያ ጋር የዋጋ ዝርዝር አውጥተው ሕግን መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቃ ነን የሚሉ ጉዳይ ገዳዮች ተበራክተዋል፡፡ ለዚህ ክስ ይህን ያህል ብለው ዋጋ አውጥተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ ከዳኛ ጋር ተደራድሮ ፍትሕን ለመሸቀጥ ቀርቶ ሙያን መናቅ አይሁንብኝና ሱቅ በደረቴ ይዘው መስቲካ ለመቸርቸርም የማይመጥኑ፣ ሙያውም ሆነ ሥነ ምግባሩ የሌላቸው ተራ ደላላዎች ናቸው፡፡ ይህን ዓይነት ምግባር ያላቸው ሰዎች ድራፍትና አረቄ ቤት ተቀምጠው ዳኛን የሚያህል ከፈጣሪ በታች ፍትሕን የሚወስን ባለሙያ ሲደራደሩ ማየት ከባድ የሞራል ድቀት የሚያስከትል ነው፡፡ በአንድ መስመር ውሳኔ በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከባድ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል የፍትሕና የርትዕ ምልክት የሆነ አንቱ የተባለ የዳኝነት ሙያን እነዚህ ደላሎች አርክሰውታል፡፡ ዳኛ እኮ አይከሰስም፣ የሕግ ከለላ አለው ሲባል ያለምክንያት አይደለም፡፡ ያም ቢሆን ግን አይቀጣም ብሎ በዘፈቀደ ሙያውን ያለ ቁጥጥርና ያለሚዛን ማስጠበቂያ ሥርዓት መልቀቅ በአገር ላይ ከባድ ድቀት የሚያስከትል ነው፡፡ ልጓም ሊኖር ይገባል፡፡ የሥነ ምግባር ቁጥጥር አስፈላጊ ነው፡፡

ዳኛ በዜሮ ዓመት ልምድ ነው የሚቀጠረው፡፡ በአምስት ዓመት ልምድ ነው ጠበቃ የሚኮነው፡፡ አንድ ሰው ከዩኒቨርሲቲ በወጣበት ዕድሜ ዳኛ ቢሆን ፍትሕን ምን ያህል ሊበድል እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው፡፡ በዚያ አፍላ ወጣትነት ምክንያታዊነትን መላበስ ከባድ ነው፡፡ በዳኞች በኩልም ቢሆን በርካታ ምሬት መኖሩን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የሞት ፍርድን ያህል ከባድ ውሳኔዎችን በሰዎች ላይ የሚያሳልፍ ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ ዳኛ በእግሩ ከሥራ ወደ ቤት እንዲሄድ ማድረግ የህልውና አደጋ የሚጋብዝ ነው፡፡ የዳኞች ዋስትና በሁሉም በኩል መጠበቅ አለበት፡፡ አንድ ዳኛ 30 ሺሕ ብር የወር ደመወዝ ይከፈለው ይሆን? ይህ ገንዘብ ቤት ለመከራየት፣ ልጆች ለማስተማር ወይም ሦስት ኩንታል ጤፍ ለመግዛት ይበቃ ይሆን፡፡ እንዲህ ባለው ውስብስብ ችግር ነው የፍትሕ ሥርዓቱ እየተፈተነ ያለው፡፡ የዳኞችን የኑሮ ዋስትና መጠበቅ፣ አሠራራቸውን መቆጣጠሪያ መንገድ መዘርጋት፣ አጥፍተው ሲገኙ ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆነ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፍትሕ ለማውራት ብዙ ርቀናል ያሉት እኮ ወደው አይመስለኝም፣ ያዩትና በተጨባጭ የተገነዘቡት መኖሩ አይታበይም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...