Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉመልካም ጉርብትና ወይስ “ወደብ ወይ ሞት?”

መልካም ጉርብትና ወይስ “ወደብ ወይ ሞት?”

ቀን:

በአየለች ሀብቱ

እ.ኤ.አ. በ1648 ከተፈረመው የዌስትፋሊያ ስምምነት ወዲህ አገሮችም ሉዓላዊ መሆናቸውን ስምምነቱ ካበሰረ ወዲህ፣ ሉዓላዊነት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ያረፈበት መሠረታዊ መርህ ሆኖ ሲያገለግል እነሆ ወደ አራት መቶ ዓመት ገደማ ሊሆነው ነው። የኢምፔሪያሊዝም መምጣት በአንድ በኩል የቅኝ ግዛትን በማስፋፋት፣ በሌላ በኩልም እዚያው አውሮፓ ውስጥ የተነሱ ኃያላን ደካሞችን ለማንበርከክ ተነስተው የዓለም ጦርነቶች ተደርገው በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም እንደገና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን አቋቁሞ በአገሮች መሀል ስላለው ግንኙነት በቻርተሩም ሆነ በተለያዩ ኮንቬንሽኖቹና ዴክላሬሲዮኖቹ (Conventions, Declarations) የዓለም አገሮች ማክበር ያለባቸውን የተለያዩ መርሆዎችን ደንግጓል። በየአካባቢው/ክፍለ ዓለማት የተመሠረቱ እንደ አውሮፓ ኅብረት ያሉ ስብስቦችም ይህንኑ የተመድ መርሆዎች እያረጋገጡ ተመሥርተዋል። በአፍሪካም እንዲሁ ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት እነዚህን የተመድ መርሆዎት እያረጋገጡ ነው የተመሠረቱት። በአጭሩ የአገሮች ሉዓላዊነት በሁሉም አገሮች መካተት ያለበት ዓለም አቀፋዊ መርህ ነው። እነዚህን መርሆዎች መጣስ ከዓለም አቀፍ ግንኙነት አንፃር እጅግ ነውረኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ወንጀልም የሚቆጠር ነው። በተለያዩ ክፍለ ዓለም ያሉ አገሮችም ይህንን መርህ አክብረው ይኖራሉ።

በዘመነ ግሎባላይዜሽን መልካም ጉርብትና ተጨማሪ ምዕራፍ ይዞ መጥቷል። ይኼውም አገሮች የጋራ የሆኑ ችግሮቻቸውን እያወቁ በመምጣታቸው ከመልካም ጉርብትናም በላይ እነዚህን ችግሮቻቸውን በጋራ ለመቋቋም በአንድነት መሥራት እንዳለባቸው እየተረዱ ስለመጡ ነው። የዓለም የአየር ብክለትና ለውጥ ያስከተለው ምስቅልቅልና ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የጋራ ፕሮግራም መንደፍ (ለምሳሌ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዛፍ ተከላ አንደኛው ሊሆን ይችላል)፣ በወንዞች ተፋሰስ ላይ ያሉ አገሮች በተለያዩ መንገዶች (የኤሌክትሪክ ኃይል በጋራ ከማመንታት እስከ እርሻ መስኖና ሌላውም ድረስ በጋራ እስከ ማቋቋም)፣ እንዲሁም ሌሎችንም ሥራዎች በሚያካትት ሥራ መተባበር የሚያስፈልግበት ጊዜ ሆኗል። ጎረቤታም አገሮች ስለራሳቸው አገር ብቻ ሳይሆን ስለጎረቤቶቻቸውም ደኅንነትና ብልፅግና ማሰብ ያለባቸው ጊዜ ነው። የግሎባላይዜሽን መከሰት እነዚህን ትብብሮች የግድ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ መልካም ጉርብትና ትብብርንና እርስ በርስ መተሳሰብን (Interdependence) የግድ ያደርጋል። በተለይም ደሃ አገሮች ይህን ከመሰለ ትብብርና መልካም ጉርብትና ሌላ አማራጭ የላቸውም።

- Advertisement -

በአገሮች መሀል ሊኖር የሚገባው መልካም ጉርብትናም መሠረቱ ከላይ የጠቀስነው ሉዓላዊነትን ማክበር የሚለው የተመድ መርህ ነው። ጎረቤት አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ላይስማሙ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ ጎረቤት አገሮችን ችግር ውስጥ ብሎም ንትርክ ውስጥ የሚከታቸው፣ አልፎም ወደ ግጭት ድረስ የሚወስዳቸው የድንበር ጉዳይ ነው። ይህ ክስተት ቅኝ ገዥዎች እንዳሻቸው የፈጠሩት በጎረቤት አገሮች መሀል የተሰመረው ድንበር ነው። ምንም እንኳን ግጭት ወይም ንትርክ ባያስነሳም በሴኔጋልና በጋምቢያ መሀል ያለውን የድንበር ጉዳይ ብንመለከት፣ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካ እንዴት መቀለጃቸው እንደነበረች የሚያሳይ ነው። የሴኔጋልና የጋምቢያ ሕዝብ አንድ የነበረ ግን የፈረንሣይና የእንግሊዝ ቅኝ ገዥዎች ተስማምተው ሁለት አገር አድርገው የፈጠሯቸው ናቸው። የእነዚህን አገሮች ካርታ ብንመለከት ጋምቢያ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደ አንድ ሰርጥ በሴኔጋል መሀል በመሀል አልፋ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር የምትገናኝ ነች። የሴኔጋልና የጋምቢያ ሕዝብ ቋንቋው፣ ሃይማኖቱ፣ ባህሉ፣ ወዘተ አንድ ነው። ልዩነቱ ጋምቢያ እንግሊዝኛ ተናጋሪ፣ ሴኔጋል ደግሞ ፈረንሣይኛ ተናጋሪ መሆናቸው ብቻ ነው። በብዙ የአፍሪካ አገሮች መሀል ያለው ድንበር በቅኝ ገዥዎች ተሰምሮ እነሱው የተስማሙበት ስለሆነ፣ የአፍሪካ አገሮችም ከነፃነት በኋላ ይህንኑ የድንበር መካለል ተቀብለው ይኖራሉ። በዚህ ረገድ እስካሁን ያሉ ችግሮች በሶማሊያና ኢትዮጵያ ድንበር፣ ካሜሩንና ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን መሀል ያሉት ድንበሮች ናቸው።

እዚህ ላይ ስለሶሊዳሪቲና ዲፕሎማሲ በጥቂቱ ማንሳት አለብን። ድሮ ድሮ ኢምፔሪያሊዝም ደሃ አገሮችን በሚያምስበት ጊዜ ደሃ አገሮችም በራሳቸው ተነሳሽነትና በዓለም አቀፍ ድጋፍ ኢምፔሪያሊዝምን ታግለዋል። በዚህም ብዙ አገሮች ነፃ ሊወጡ ችለዋል፡፡ ቢዬትናም፣ ካምፑቲያ፣ ላኦስ፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ጊኒ ቢሳውና ኬፕ ቤርዴ፣ ኒካራግዋ፣ ወዘተ.፡፡ ያኔ ዓለም አቀፍ ሶሊዳሪቲ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነበር። ዲፕሎማሲውም እንደዚያ። ግሎባላይዜሽን የዓለምን ችግር የጋራ አድርጎታል። ባይታወቅ ነው እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ በራሱም ሆነ በሌላ አገር ውስጥ የሚያደርገው የኑክሌር ቦምብ ሙከራ፣ ፈረንሣይ በደቡብ ፓሲፊክ (በተለይም ኒው ካሌዶኒያ ውስጥ) ከባህር ውስጥ የሚያደርገው የኑክሌር ቦምብ ሙከራ፣ እንዲሁም በጎረቤትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድምታ ያላቸው ሥራዎችን መሥራቱ ጉዳቱ ሙከራው በተደረገበት አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ነው። ስለሆነም እንዲህ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት የአንድ አገር ሕዝብ ሥራ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ትብብርን የሚጠይቅ ነው። ለዚህ ነው የእነዚህ አገሮች ትብብር የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የግድ (Obligatory) ነው የሚሆነው።

ሌላም ችግር እንመልከት። በዓለም ላይ ያለው የአየር ለውጥ ካስከተላቸው ክስተቶች አንደኛው በሰሜንና በደቡብ የምድር ጫፎች (North and South Poles) የነበረው የበረዶ ተራራ በሙቀት መጨመር ምክንያት እየቀለጠ ወደ ውቅያኖሶች በመግባቱ፣ የውቅያኖሶቹ ወለል ከፍ እያለ በመምጣቱ በርካታ የፓሲፊክና የህንድ ውቅያኖስ ውስጥ ያሉ ደሴቶች እየሰመጡ ነው። በዚህ ረገድ ሞልዲቪስ የተባለችው ደሴት (አገር) እየሰመጠች በመሆኑ የአገሪቱ መንግሥት ለዓለም አቤት ሲል ስንት ዓመቱ። በዚህ ረገድ ደሃ አገሮችና ሌሎችም ተባብረው ይህንን ችግር መወጣት ይኖርባቸዋል። ችግሩ በውቅያኖሶቹ መዋጥ ብቻ አይደለም። በመላ ዓለም የጨመረው የሙቀት መጠን ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ነወ። ይህንንም ችግር በጋራ ተባብሮ መወጣት ያስፈልጋል። ይኼ ሁሉ የሚያሳየው የዓለም ችግር የአንድ አገር ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም አገሮች እየሆነ መምጣቱን ነው። የግሎባላይዜሽን ሒደት እንደ ዕድገት ወይም ሥልጣኔ እየተቆጠረ በሄደ ቁጥር እነዚህ ችግሮች እየተባባሱ መሄዳቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህም የዛሬዋ ዓለም የአገሮችንና የሕዝቦችን ኅብረት የምትጠይቅበት ጊዜ ነው። ይኼም ማለት የአፍሪካ አገሮች ችግሮቻቸውን ለማስወገድ የሚያስፈልጋቸው ትብብር በአፍሪካ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም አቀፍ ደረጃ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ነገ ሳይሆን ዛሬ ጋና ከቬትናም፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከካናዳ፣ ወዘተ. ጋር “ችግርሽ ችግሬ ነው” ብለው የሚተባበሩበት ጊዜ ነው (“Think Globally, Act Locally” እንደተባለው)፡፡ በአንድ አገር ብቻ ተወስኖ ስለልማት ማሰብ ዘመኑ አልፎበታል፣ ጊዜው የሚጠይቀውን ኃላፊነትንም አለመረዳት ነው። ከዚያ በላይ ሄዶ ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ስላለ አንድ ብሔር ብቻ ማሰብ ወይም ስለዚያ ብሔር የበላይነት ብቻ ማሰብ ደግሞ፣ ዓለም የዛሬ 200 ዓመት ወደ ነበረችበት ትመለስ እንደ ማለት ነው።

ዲፕሎማሲ

በአሁኑ የዓለም ሁኔታ ጊዜው የሚጠይቀው ዲፕሎማሲ ከላይ ከጠቀስነው ዓለም አቀፋዊ (ግሎባል) አመለካከት ጋር የተያያዘ ነው። በተለይ ደግሞ ከአገሬ አልፌ ለአኅጉሩም አንድነትና ነፃነት ሠርቻለሁ ለምትለው እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር፣ በዚህ ረገድ በእርግጥም የቀዳሚነት ሚናዋን በመጫወት ተምሳሌት መሆን ይገባታል። አገራችን ከእንዲህ ዓይነት ሚና ወርዳ እንኳን ለአፍሪካ ተምሳሌት ልትሆን ራሷን ችላ ለመቆሟ አጠራጣሪ እየሆነ ነው። እንዲህ ያለ አዘቅት ውስጥ ያወረዳትም ይህንን የጊዜውን አስተሳሰብ ባለመገንዘብ የተገላቢጦሹ እጅግ ጠባብ ወደ ሆነ አመለካከት በመውረዷ ነው። እንግዲህ ዲፕሎማሲያችን እንዲህ ካለው ዓለም አቀፋዊነት በመውረዱ፣ ዲፕሎማሲያችንም ይህንን ጠባብነት የሚያመለክት ሆኗል።

አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ካለ ጠባብ አመለካከት ውስጥ ሰምጠው መልካም ጉርብትናን የሚያመጣ ዲፕሎማሲ የሚከተሉ የሚመስላቸው ርካሽ “ፖፑሊዝም”ን (በከንቱ ተወዳጅ ለመሆን መሞከር) የሚከተሉ አሉ። ራስን የሌላውን አገር መሪ የሚወድ አድርጎ ማቅረብ፣ ወይም በናፍቆት ሞቼ ነበር በመሰለ ሲገናኙ መጠምጠምና በተለየ የመሳሳም አባዜ ማሳየት ዲፕሎማሲ ወይም መልካም ጉርብትና አይደለም። ምክንያቱም ሌላው መሪ (ወይም የእሱ መንግሥት) የሚያየው ሌላው መንግሥት በተጨባጭ የሚያደርገውን እንጂ የመሪውን የግል ‘ፍቅሩን’ ስላልሆነ። ዲፕሎማሲ ፈረንጆች ርካሽ ተወዳጅነት (Cheap Popularity) የሚሉት መሆን የለበትም። ይኼም የዲፕሎማሲ ሀ ሁ ነው። እንዲህ ያለው እንተ ፈንቶ ‘ዲፕሎማሲ’ ዘላቂም ስላልሆነ ዕድሜም የለውም።

ዲፕሎማሲ በአሁኑ ዓለም ከሶልዳሪቲም አልፎ የእርስ በርስ መተጋገዝን (Interdependence) የግድ ያደረገበት ጊዜ ነው። የአየር ሳይንቲስቶች (Climate Scientists) በቅርቡ እንዳስጠነቀቁት ‹‹ዓለም ተባብሮ የሙቀት መጠኑን ለመቀነስ መወሰድ ያለበትን ቁርጠኛ ዕርምጃ ካልወሰደ ይህች ዓለም ከአሥር ዓመታት በኋላ ሙቀት የመቀነስ አቅም አይኖራትም›› ያሉትን በማስታወስ፣ እያንዳንዱ አገር የእያንዳንዱ አገር ችግር ችግሬ ነው ብሎ ማሰብ መቻል አለበት። ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲም በአሁኑ ጊዜ የሚጠይቀው ኃላፊነት እንዲህ ያለውን ዓለም አቀፋዊነት ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ ነው።

ከላይ የጠቀስነውን የዲፕሎማሲ ዓይነት በአገሮች መሀል ያለውን የግንኙነት መርህ በቅጡ ያስቀመጡት፣ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ሕግጋትና ድንጋጌዎች በማያዳግም መንገድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድንጋጌዎች ተገልጸዋል። ከዚያም በላይ በየአኅጉሩ የተቋቋሙት ስብስቦችም (የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ወዘተ.) ይህንኑ በማያዳግም መንገድ ድንጋጌዎቻቸው ላይ አሥፍረዋል። የእነዚህ ሁሉ ድንጋጌዎች እምብርት ደግሞ የአገሮች ሉዓላዊነት መከበር ነው። እነዚህን ለአንዳፍታም መዘንጋት ወይም መጣስ የዓለም አቀፍን ሕግ መጣስ ነው። ለዚህ አንድና ሁለት የለውም። ቀደም ሲል እንደገለጽነው የአገሮች ሉዓላዊነት በተለያዩ ኃያላን መንግሥታት ተጥሷል። ይኼም ከባድ ችግሮችን ብሎም ግጭቶትን አስከትሏል። ይሁን እንጂ የአገሮች ሉዓላዊነት መጣስ የሚያስከትለው ችግር በአፍሪካ ቀንድ አገሮች እንደታየው ከባድ ሁኔታ የፈጠረ ነው። በመሆኑም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሉዓላዊነትን አለመጣስ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ቢያንስ በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው አገሮች መሀል የተነሱት ችግሮችና ጦርነቶች የሚያሳዩን የጉዳዩን ክብደት ነው። በኢትዮጵያና በሶማሊያ፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን፣ በኬንያና በሶማሊያ መሀል የነበሩትን/ያሉትን ንትርኮችና ግጭቶች የሚያሳዩን የአገሮች ሉዓላዊነት ምን ያህል መከበር እንዳለበት ነው። ይኼም በተራው በእነዚህ አገሮች ያሉ መንግሥታትም ሆኑ ፖለቲከኞች ምን ያህል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ያሳየናል። እንግዲህ በብልፅግና መንግሥትና በሶማሌላንድ ግዛት መሀል የተፈረመውን የወደብ ስምምነት ከዚህ አንፃር ማየት ይኖርብናል።

ጉርብትናና ወደብ ፍለጋ ምንና ምን ናቸው?

መቼም የብልፅግና መንግሥት ከሶማሌላንድ ግዛት ጋር ያንን የወደብ ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ፣ በተለይም በመንግሥት ሚዲያ ያልሰማነው ጉድ የለም። ‹‹ኢትዮጵያ ያለ ወደብ እንዴት ታስባ››፣ ‹‹ያለ ወደብ ዕድገት አይሞከርም›› ዓይነት፡፡ ወደብ ለአንድ አገር ልማት ብቻ ሳይሆን ህልውናም ጭምር እንዴት ወሳኝ እንደሆነ ብቻ ያልተሰማ ጉድ የለም። ፖለቲካ በስሜት እንደማይተነተነው ሁሉ ስለወደብም እንዲሁ ከስሜት በራቀ፣ ቡራ ከረዩ የሌለበት ሐሳብ ማቅረብ ተገቢ ነው። ለመሆኑ ወደብ ለአንድ አገር ዕድገትና ህልውና ወሳኝ ነው ያለው ማነው? የለሙት አገሮች ሁሉም ወደብ አላቸው? ግን የለሙት ወደብ ስላላቸው ነው? ያለ ወደብ ህልውና አይኖርም ያለው ማነው? በዓለም ላይ ወደብ የሌላቸው አገሮች አሉ። ወደብ ሳይኖራቸው ያደጉ አገሮችም አሉ። ወደብ ከሌለ ህልውና አይኖርም ከተባለ እኮ ገና በተሳለ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ያሉት እነ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ሌሎችም የሉም ማለት ነው። በአውሮፓም እነ ስዊዘርላንድና ኦስትሪያ ወደብ የላቸውም።

ሁለተኛ ወደብ ቢኖርስ ያ ወደብ ምን ያህል ነው ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ወሳኝነት ያለው ብለን መጠየቅ አለብን። የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ አትላንቲክ ውቅያኖስን በረጅሙ ሲያዋስን ያለው አንድ ወደብ ነው። ታዲያ የኮንጎ ኢኮኖሚ ምን ደረጃ ላይ ነው? ወደብ ብቻውን እኮ የሚፈይደው ነገር የለም። ወደብ ኖሮም ሰላምና መልካም አስተዳደር ከሌለ ወደብ ብቻውን ዳቦ አይሆንም። የኮንጎ ችግር እኮ ይኼው ነው። ወደብ ያለው ኮንጎና ወደብ የሌላት ስዊዘርላንድ ለመሆኑ ይወዳደራሉ? እኛም እኮ አሰብና ምፅዋ ነበሩን፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት በተነሳ የፖለቲካ ችግር አጣናቸው እንጂ። ያኔ በኃይለ ሥላሴ ወይም በደርግ ጊዜም አሰብ እያለን ኢኮኖሚያችን ለምን አልመጠቀም? ታዲያ ባለ ሁለት ወደቧ ኢትዮጵያ ከድህነትና ከረሃብ ተላቃ ታውቅ ነበር? ወደብ ብቻውን ዳቦ አይሆንም። መልካም አስተዳደርንና ዴሞክራሲን ይጠይቃል።

ስለወደብ ያን ካልን በኋላ ከተፈረመው የወደብ ስምምነት አንፃር ደግሞ በተጨባጭ የተከተልነውን ፖሊሲ ዘወር ብለን እንመልከት። ኤርትራ ነፃነቷን እንዳወቀች የኢሕአዴግ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በነበረው ወዳጅነት የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ይቻል ነበር። ኢሳያስ አፈወርቂም ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ እንድትጠቀም ሐሳቡን አቅርበን የኢሕአዴግ መንግሥት ነው ችላ ያለው ይላሉ። አሁን ከለውጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ዕርቅ ተደርጎ ፍቅርም ጠንቶ በነበረ ጊዜ አሰብን ኢትዮጵያ እንድትጠቀም ለምን አልተሞከረም? ድሮውንም እንጠቀምበት የነበረ ወደብ እያለ፣ ከኤርትራም ጋር ጥሩ ግንኙነት በነበረበት ጊዜ አሰብን ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ያልተሞከረው ለምን እንደሆነ ራሱን የቻለ እንቆቅልሽ ነው። ይኼን የመሰለ ዕድል እያለ አዲስ ወደብ ፍለጋ መሄድ ለምን አስፈለገ? ይኼ ጥያቄ በኤርትራና በኢትዮጵያ መንግሥታት መሀል ወደ ነበረው/ወዳለው የግንኙነት መሳከር ይወስደናል። እንደገና የዲፕሎማሲ ጉዳይ ነው ማለት ነው። በሰሜኑ ጦርነት የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያዎች አንድ ላይ ሆነው መዋጋታቸው የታወቀ ነው። የፕሪቶሪያው ንግግር ሲጀመር ሁለቱ መንግሥታት ምን ያህል እንደመከሩ አናውቅም። ግን ኤርትራ መመካከሯ ተገቢ ነበር፡፡ ምክንያቱም በሰሜኑ ጦርነት አያሌ ኤርትራውያንም ተሰውተዋልና። በመጨረሻ ግን ስምምነት ሲደረግ የኤርትራ አቋም የተለየ ለመሆኑ በኋላ በሁለቱ መንግሥታት መሀል የተፈጠረው የሻከረ ግንኙነት ያሳያል። ይኼ በተራው የዲፕሎማሲ ውድቀት መሆኑ ገሃድ ነው። አፍሪካ ውስጥ የሕዝብ አስተያየት (Public Opinion) የሚባለው ነገር የለም፡፡ አንድም ሕዝብን ከመጤፍ የሚቆጥር መንግሥት የለም፣ አንድም የሲቪል ኅብረተሰብ የሚባል ገና አልወጣም።

ይህ በዚህ እንዳለ የወደብ ጉዳይ እንዲህ እንቅልፍ የነሳ አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው እንዴት ነው? ኢትዮጵያ ዝንተ ዓለሟን ስትጠቀምበት የነበረው የጂቡቲን ወደብ ነው። አሁን ከጂቡቲ ጋር ምን ተፈጥሮ ነው ሌላ ወደብ ፍለጋ የተኬደው? ምን ጎደለ? እንደገና የሕዝብ አስተያየት ምንም ቦታ ስለሌለው፣ መንግሥት የፈለገውን ወስኖ በመገናኛ ብዙኃን ያሳውቃል እንጂ ሕዝቡ ምን ይላል ብሎ አያውቅም።

ይኼን ካልኩ ዘንድ አሁን ወደ ሉዓላዊነት ጉዳይ ተመልሼ የብልፅግናው መንግሥትና የሶማሌላንድ ግዛት ስለተስማሙበት የወደብ ጉዳይ በአጭሩ ላውጋ። ከሁሉ አስቀድሞ ሶማሌላንድ የተባለው የሶማሊያ ክፍል የሶማሊያ አንድ ግዛት እንጂ ራሱን የቻለ መንግሥት አይደለም። ራሱን ‘መንግሥት’ ይበል እንጂ አንድም የዓለም አቀፍ ድርጅትም/ስብስብም አንድ ነፃ አገር አድርጎ ያወቀው የለም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አያውቀውም፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ኢጋድም አያውቁትም። መላው ዓለም የሚያውቀው ይህ ግዛት የሶማሊያ ሪፐብሊክ አንድ ክፍል መሆኑን ነው። ሶማሊያ ፍርክስክሷ በወጣ ጊዜ እንኳን ሶማሌላንድን እንደ አንድ አገር ያወቀ የለም። በዚህ ምክንያት የማንም አገር መንግሥት ከሶማሌላንድ ጋር ያለ ሶማሊያ መንግሥት ፈቃድና ዕውቅና ስምምነት ያደረገ የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይኼ የሶማሌያን ሉዓላዊነት መጣስና የዓለም አቀፍ ግንኙነትም ሀ ሁ ስለሆነ። የተባበሩት መንግሥታትን፣ የአፍሪካ ኅብረትን፣ የኢጋድን ድንጋጌዎች በሙሉ የሚጥስ ነው። ከሁሉ የሚደንቀው ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መፈጠር ብሎም ለአፍሪካ ኅብረት መመሥረት አስተዋጽኦ አደረገች የተባለችው አገርም እንዲህ ያለ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሀ ሁን ስትጥስ ማየት ያስደነግጣል። በዚህም ከስንት ዘመን በኋላ ተሻሻለ የተባለው የኢትዮ ሶማሊያ ግንኙነት ተመልሶ አፈር ሲበላው በእጅጉ ያሳዝናል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...