Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉአገራዊ ምክክር ዕውን እንዲሆን!

አገራዊ ምክክር ዕውን እንዲሆን!

ቀን:

በተስፋዬ ወልደ ዮሐንስ ኃይሌ

ሰሞኑን መነጋገሪ ከሆኑ ሁነቶች ውስጥ ትልቁን ሥፍራ የያዘው የአገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰቢያ ስብሰባዎችና ውይይቶች ነበሩ፡፡ በየቦታው የሕዝብ ወኪል ሆነው የተመረጡ ሰዎች አገራችን አሁን ስላለችበት ነባራዊ ሁኔታ ብንወያይበት ይበጃሉ፣ የምንፈልገውን ለውጥ ለማምጣት መንገድ ይቀይሱልናል ያላ_ቸውን ሐሳቦች ጊዜ ሰጥተው በኮሚሽኑ አስተባባሪነት ሲመክሩ ሰንብተዋል፡፡ ሁሉም ተስፋ ያደረገው ‹‹አገር በምክክር ትዳን›› የሚለው መርህ ‹‹ምንም ቢሆን እንሞክረው›› ከሚሉ ጀምሮ ‹‹ተስፋ የለውም አንሳተፍም›› እስከሚሉ ድምፆች ታጅቦ እየተገ_ዘ ይገኟል፡፡

አገራዊ ምክክር ለምን?

- Advertisement -

አገር በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ስትገባ፣ ወይም ከገባችበት ጦርነት ማግሥት ወይም ደግሞ ስፋት ያለው የፖለቲካ ሽግግር በሚደረግበት ወቅት፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦችና የፖለቲካ ኃይሎች መሀል አስተሳሰብንና አንድነትን ዕውን ለማድረግ የሚካሄድ ሰፋ ያሉ ባለድርሻዎችን የሚያሳትፍ ሒደት ማሰሪያው አገራዊ ምክክርና ውይይት ነው። አገራዊ ምክክር ግቡ አገራዊ ስምምነት በሌለባቸው ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትንና የጋራ ራዕይ በመፍጠር፣ ለሽግግር መሠረት መጣልና ቀጣይና ቋሚ ሰላም ዕውን ማድረግን ያጠቃልላል።

 የአገራዊ ምክክር ትኩረት እንደ አገሩ ታሪካዊና ተጨባጭ ሁኔታ ቢለያይም ቅሉ፣ ከፖለቲካ ልሂቃን ባሻገርም ሕዝቡን በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ በማዋቀር የማሳተፍ ሒደትን አጉልቶ የሚካሄድ፣ ረዥም ርቀት የሚጓ_ዝ፣ ትዕግሥት የሚሻ፣ ብልኃትን፣ እውነተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከአስተውሎት መሪነት ጋር የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ እውነተኛ መሆኑ ከሚንፀባረቅባቸው የሒደቱ አንደኛው መገለጫ ከፖለቲካ ልሂቃን ያለፈ ሆኖ ሲገኝ ሲሆን ውጤቱም በመንግሥትና በሕዝብ፣ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሀል ሊኖር የሚገባውን ትስስር የግንኙነት ምኅዳር፣ ወዘተ የሚወስን፣ የሕገ መንግሥት የመዋቅርና የተቋማት ለውጥንም ሊያመጣ የሚችል፣ መሠረታዊ ለውጥንና አዲስ ማኅበራዊ ውልን (ሶሻል ኮንትራክት) ዕውን ለማድረግ የሚያግዝ አካሄድ ነው። ይህም ጥልቅና ሳይንሳዊ የሆነ የትንተና ዘዴን በመጠቀም ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን ከተቻለ፣ በበርካታ አገሮች ውጤታማ የሆነ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ሲመጣ መመልከት አስችሏል፡፡

አገራዊ ምክክር በበርካታ አገሮች ውስጥ የተከናወነ ሲሆን እንደ ሒደቱ ዓይነትና እንደ ተሳታፊዎቹ አካላት ቁርጠኝነት ለአንዳንዶቹ የስኬት መንገድ ሲሆንላቸው፣ ለጥቂቶቹ ደግሞ ያመጣል የተባለው ለውጥ ይብሱኑ ወዳልታሰበ አቅጣጫ ሄዶ ለበለጠ ብጥብጥ፣ አካልና ሕይወት መጠፋት ምክንያት ሆነዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ፣ ቤኒን፣ ቱኒዝያና የመሳሰሉ አገሮች ውጤታማ የሆኑ አገራዊ ምክክር ወይም ብሔራዊ ዕርቅ ሒደት ተግባራዊ ያደረጉ ሲሆኑ፣ መነሻቸው በአገራቸው ውስጥ የፖለቲካ ሒደቱ ለውጥ ፈላጊ በሆኑ ኃይሎች ሥር ከገባ በኋላ እንደነበረ ታሪክ ያሳያል፡፡ ቤኒን ሒደቱ ዕውን የሆነው ከአምባገነን ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የፖለቲካ ሽግግር ከተደረገ በኋላ ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካም ቢሆን የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን ምሥረታውን ያገኘው በአፓርታይድ ሕገ መንግሥትና በአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ የኔልሰን ማንዴላን መፈታት ተከትሎ፣ የዘረኛው ሕገ መንግሥት በ1984 ዓ.ም. ተሽሮ የሽግግር ሕገ መንግሥት ተግባራዊ ከሆነ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር።

የዓረብ ፀደይ ተብሎ የሚታወቀው የ2011 ዓ.ም. የሕዝብ አመፅ ዕውን ያደረገውን ለውጥ ተከትሎ በ2013 ዓ.ም. በነበረው የለውጥ ጊዜ ሲሆን፣ በዚህ የለውጥ ጊዜ የተሰየመው የቱኒዝያ ብሔራዊ የሕገ መንግሥት ምክር ቤት ‹‹The Tunisian National Constituent Assembly (NCA) ባስተላለፈው ሕግ መሠረት፣ በተቋቋመው የእውነትና ክብር ኮሚሽን ‹‹Truth and Dignity Commission (TDC) for Transitional Justice›› ምሥረታ ጋር ተያይዞ ነበር፡፡

ምክክር በኢትዮጵያ ለምን?

መንግሥታት በሚሾሩባት ዓለማችንን የሕግ የበላይነትና የተጠያቂነት ወሰን በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ቁልፍ ሚናን እየያዘ ይገኛል፡፡ ደሴት ያልሆነችውም አገራችን የፖለቲካ መሪዎቿ ይጠቅማታል ብለው ያሰቡትን ርዕዮተ ዓለም በተለያዩ የአስተዳደር ሥልቶች በዜጎች ላይ ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡ በውጤቱም ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከንግግር ይልቅን ጦርነትን፣ ከሐሳብ ልዕልና ይልቅ ፍረጃን መሠረት አድርገው አስተዳደራቸውንና መዋቅራቸውን ለማጠናከርና የበላይነትን ለመጨበጥ የሄዱበት መንገድ ቁርሾን፣ ቅሬታን፣ ቂምና በቀልን አስታቅፎን አሁን ለደረስንበት ቦታ መገኘታችን ትልቁን ሥፍራ ይዟል፡፡

በታሪካችን ውስጥ ያለውና ያስቀመጥነው ቁርሾ ከትርክቶቻችን ባሻገር የፖለቲካ ልሂቃን ርዕዮተ ዓለማቸውን ለማስቀጠል የሄዱባቸውን መንገዶች ያሳዩናል፡፡ ለዚህም በሃምሳ ዓመታት ታሪካችን ውስጥ ደርግ፣ ኢሕአፓና መኢሶን የነበሩበትን የፖለቲካ ትግልና ለትውልዶች የሚተርፍ ምተራ ከማሳያዎቻችን ውስጥ አንድ አካላችን ነው፡፡

በሕዝባዊ ዓመፅ የተከሰተው ኢሕአዴግ በኋላም ብልፅግና በአገሪቱ ለሦስት አሠርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ባቀነቀነው ብሔርተኝነት ርዕዮተ ዓለም ብሔርተኝነት ከ1990ዎቹ ጀምሮ በፈጠራቸው ግጭቶች፣ የሕዝብ መፈናቀሎችና ፍጅቶች የአገር መፈራረሻ ዋነኛ መገለጫ ሆኗል፡፡ ለዚህም ሩዋንዳን፣ ዩጎዝላቪን፣ የቀድሞዎቹን የሶቪየት ሪፐብሊኮችን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ ለደረሱት አሰቃቂ የሰዎች፣ የንብረት፣ የአካልና የሕይወት መጥፋት የወሰደው የተጠያቂነት ሚና፣ ፍትሕና ይቅርታ በእውነተኛ መንገድ መጓዝ ባለመቻሉ እነሆ ለዛሬው ምስቅልቅል ሁኔታ እንድንዳረግ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡

በልሂቃኖቻችን መሀል እጅግ የሚፃረር፣ የተካረረ፣ የአጥፊና የጠፊ ባህሪ ያለው ባህል መስፈኑ በሕገ መንግሥቱ፣ በክልሎች አወቃቀር፣ በአገረ መንግሥት ምሥረታና አሁናዊ ሁኔታ፣ ወዘተ ላይ ሩቅ ለሩቅ እንዲሆን አድርጎታል። በአገራዊ ተቋሞቻችን፣ በአገር ዓርማ፣ በሰንደቅ ዓላማ፣ ወዘተ ላይ የጋራ ዕይታችን እየመነመነ መጥቷል። በአገራችን እንደ አገር መቀጠል አለመቀጠል ላይ ሰፊና የተፃረረ የአመለካከት ልዩነት ይስተዋላል። በተለያዩ ቦታዎች ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራና ጋምቤላን ጨምሮ በሚታይ የእርስ በእርስ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንገኛለን፡፡ በዚህ የተነሳ የሕዝባችን ሕይወት በድህነት፣ በመፈናቀል፣ በግጭት፣ በሥጋት፣ በረሃብና በስደት የተተበተበ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሕዝባችን በመላ አገሪቱ መሠረታዊ የመኖር ዋስትናውን እያጣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ መዘዋወር የማይቻልበት ሁኔታ በሰፊው ይስተዋላል፡፡ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ መናገር፣ መጻፍና መሰብሰብ አስፈሪ ብቻ ሳይሆን፣ የማይቻልበት ወይም ወንጀለኛ አስብሎ የሚያሳስርበት፣ የሚያሰውርበትና ለስደት የሚዳርግበት ደረጃ በሰፊው ተንሰራፍቷል።

አሁንም በየጎራው ከግለሰብ አልፎ በማኅበረሰብ ደረጃ ያሉ ሰዎችን በጥላቻ የመቀስቀስ፣ በሐሳብ ከእኔ ወይም ከእኛ ጋር አይሆኑ ብለን የማናስባቸውን ጉድጓድ ካልገቡ ድንጋይ ካልጫንባቸው በስተቀር ዕረፍት የማናገኝ እስኪመስል፣ ከእኔ ጋር ካልቆምክ ጠላቴ ነህ ብሎ ማሰብን በየዕለቱ ኑሯችን ውስጥ የምናየው ትግል ሆኗል፡፡  

ከአመሠራረቱ ጀምሮ በችግሮች የተተበተበው የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአደረጃጀቱና በምርጫ ሒደቱ የገጠሙት ችግሮች ተዓማኒነቱን ተስፋ ከማድረግ ይልቅ፣ የማይሳካበት ዕድሎች ሰፋ እያሉ የመጡ ይመስላሉ፡፡ ተገልለናል፣ አጀንዳ ለመላክ እንቸገራለን የሚሉ ከ10 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን በገለጹበት፣ በየአካባቢው መሣሪያ ያነገቡ ቡድኖች ተሳታፊ ባልሆኑበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ኮሚሽኑ ራሱ ነፃና ፍትሐዊ ነው ብለን ለማለት ይቸግረናል ባሉ ወገኖች ውስጥ ሆኖ መሳተፍ ብቻውን ለውጥ ያመጣል ብሎ ማሰብ፣ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ ተስፋና ሥጋት ያጠላ መስመር ሆናል፡፡  

ሁሉንም አሳታፊ፣ የውሳኔ ሰጪነቱንና ኃላፊነት የመውሰዱን ሚና በውይይቱ በሚሳታፉ አካላት ዘንድ እንዲሆን፣ እንዲሁም አገራዊ ውይይቱ እንዳይጠለፍና ጣዕሙንና ተዓማኒነቱን እንዳያጣ ባለቤትነቱን አገራዊ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ያለ ሁሉም አካላት ተሳትፎና ቁርጠኝነት፣ ጠንካራ ውይይት አመቻችና ቅንጅት አገራዊ ውይይቶችን ውጤታማና ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደማይቻልም ከግምት ውስጥ መክተት፣ ኮሚሽኑ በድጋሚ ሊያስቡበት የሚገባ ቁልፍ ተግባር ነው፡፡

ቢደረጉ የሚገቡ የመፍትሔሳቦች

የኮሚሽኑ ሁኔታ ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ ባስገባ ብሔራዊ ምክክር የተሰኘ ሒደት ከመቀጠል ይልቅ፣ በቅድሚያ ብሔራዊ ምክክርን ዕውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን በማሟላት ላይ ማተኮር ተገቢ ይሆናል። ውጤታማነት የሚኖረው ሁሉም አካላትን የየችግሩ ምንጭም የመፍትሔ አካልም ሆነው በልበ ሙሉነት፣ በያገባናል ስሜትና በቁርጠኝነት ሲሳተፉ በመሆኑ፣ ሁለንተናዊ የሆኑ አስቻይ ሁኔታዎችን ዕውን ማድረግ ለነገ የማይባል መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

መንግሥት በእርግጥም በዚህች አገር ውስጥ አገራዊ ምክክር እንዲኖር ቁርጠኝነት ካለው በመሣሪያ ፍልሚያ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ኃይሎችና በገዥው ቡድን መካከል መርህን መሠረት ያደረገ ድርድር እንዲካሄድ ማድረግ፣ በዚህ ድርድር ውስጥም የኢትዮጵያ ዋና ዋና ጉዳዮችን ለመፍታት ሊካሄድ በሚገባው የብሔራዊ ምክክርን በተመለከት መስማማት ላይ መድረስ ችላ ሊባል የማይገባው ጉዳይ ነው። በታጠቁ ኃይሎችና በገዥው ብልፅግና መሀል የሚደረስበትን ስምምነት ተከትሎም አገራችን አሁን ከምትገኝበት ወደ ተረጋጋ ሥርዓት ልትሄድ የምትችልበትን ጉዞ በሁሉን አቀፍ ድርድር መፍታት፣ ለዚህም ተግባራዊነት በተሳታፊዎች በስምምነት፣ በሰጥቶ መቀበልና በአካታችነት መንፈስ የጋራ ፍኖተ ካርታ ላይ መድረስ ያስፈልጋል።

 ከዚሁ ጎን ለጎን ተቃዋሚ ኃይሎች በሚያስማሟቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመቆም የሚያስችል ድርድርና ምክክር በማካሄድ ወደ ተጨባጭ ኃይልነት በአስቸኳይ ሊቀየሩ ይገባል፡፡

በተጨማሪ የተለያዩ የመተማመኛ ዕርጃዎች መውሰድ፣ በተለይም የፖለቲካ እስረኞችን ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ የዴሞክራሲ መብት አፈናን ማቆም በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች መንግሥት የሚያካሂደውን ጦርነት ማቆምና  የመሳሰሉት አስፈላጊ ዕርምጃዎች ናቸው።

ኮሚሽኑ አካሄዱን መመርመር፣ መገምገምና እስካሁን የሠራቸው በጎ ተግባራትን ለይቶ በማውጣት የኮሚሽኑን ይዘት፣ ኃላፊነትና ተግባር፣ የአሠራር ሒደት፣ የተሳታፊዎች ምልመላ፣ አጀንዳ አቀራረፅ፣ ወዘተ ላይ ሊሻሻል ወይም እንደ አዲስ ሊዋቀር የሚገባውን አካሄድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልገውን ሕጋዊ ድጋፍ ምን እንደሆነ ለይቶ ማውጣትና ስምምነት ላይ መድረስ ሌላው የተጀመረውን ተስፋ ከሥጋት አውጥቶ የሚያሻግረው ተግባር ይመስለኛል፡፡

ከአዘጋጁ:- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው twoldeyohanes@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...