Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየውጭ ባለሀብቶች በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው አዋጅ  ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው...

የውጭ ባለሀብቶች በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው አዋጅ  ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው  

ቀን:

  • በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የሳዲ ባለሀብቶች ልዩ ድጋፍና ዋስትና ለመስጠት ቃል ተገብቷል

የውጭ ባለሀብቶች በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚጋብዘው ረቂቅ አዋጅ በመጪው ሳምንት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ አስታወቁ፡፡

ገዥው ይህን የተናገሩት ሰሞኑን በሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ከተመራ የባለሀብቶች ልዑክ ጋር በአዲስ አበባ በተካሄደ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ነው፡፡  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ፣ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅድ የፖሊሲ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

ከብሔራዊ ባንኩ ገዥ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መሳተፍ ለሚፈልጉ የሳዑዲ የፋይናንስ ተቋማትና የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ሦስት አማራጮች ቀርበዋል፡፡ እነሱም ቅርንጫፍ መክፈት፣ በተቀጥላ (Subsidiary)፣ እንዲሁም በቀጥታ ኢንቨስት በማድረግ መሳተፍ ናቸው፡፡

- Advertisement -

አቶ ማሞ በማብራሪያቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ማንኛውም ኢንቨስተር ሀብቱን በውጭ ምንዛሪ ቀይሮ ወደ አገሩ እንዲወስድ የሚፈቅደለት ሕግ መኖሩን ጠቅሰው፣ በሕጋዊ መንገድ ኢንቨስት የሚያደርግ ማንኛውም ባለሀብት ካፒታሉን በቀላሉ በውጭ ምንዛሪ ቀይሮ እንዲሄድ ብሔራዊ ባንክ ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ለባለሀብቶቹ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ላይ መሠረታዊ ሪፎርም በመካሄድ ላይ መሆኑን የገለጹት ገዥው፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ለሚመጡና መንግሥት ስትራቴጂካዊ በሚላቸው ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የተለዩና ምቹ አማራጮች እንደሚቀርቡ አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም የሳዑዲ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ለማልማት ሲመጡ በውጭ አገሮች የሚከፈት የውጭ ምንዛሪ አካውንት (Offshore Account) እንዲከፍቱ በማድረግ፣ ወይም ከሳዑዲ ዓረቢያ ለሚመጡ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያፈሩትን ሀብት ቀይረው እንዲሄዱ ዋስትና (Convertibility Guaranty) ለመስጠት  ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ባለሀብቶች ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሪ ወደ አገራቸው ይዘው ለመውጣት እየተቸገሩ መሆኑን ስለመረዳታቸው የገለጹት አቶ ማሞ፣ አሁን ግን የተለዩ አማራጮችን በማቅረብ በተለይም ከሳዑዲ ለሚመጡ ስትራቴጂካዊ ባለሀብቶች ዋስትና ይሰጣል ብለዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ላላት የቅርብ ወዳጅነት ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን፡፡ ለግንኙነታችን ትልቅ ቦታ ስለምንሰጥ በከፍተኛ ቁጥር ኢንቨስትመንት ከሳዑዲ እንዲመጣልን እንፈልጋለን፤›› በማለት፣ ‹‹እንደ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ እንዲፈታ ሊወሰድ የሚገባው ማንኛውም ዓይነት የሕግ ድጋፍና ዕርምጃ ካለ በእርግጠኝነት ይፈጸማል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው እያደገ ነው ባሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ለመሥራት ለሚፈልጉና የውጭ ምንዛሪ ለሚያስፈልጋቸው ኢንቨስተሮች፣ በኢትዮጵያ በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲኖር ሰፋ ያሉ የሪፎርም ሥራዎችና ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ባሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ስትፈልጉ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ወደ ሥራ ከመግባት የሚያዘገያችሁ ምክንያት ሊሆን አይገባም፤›› ሲሉ ገልጸውላቸዋል።

ከሰሞኑ በሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን የተመራ 79 አባላት የያዘ የሳዑዲ ዓረቢያ የኢንቨስትመንትና የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ጉብኝት ያደረገ ሲሆን፣ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ የኢትዮ ሳዑዲ ዓረቢያ የኢንቨስትመንትና የንግድ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በውይይቱ ውቅት የብሔራዊ ባንክ ገዥ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ስለመሆኗና መሠረታዊ የሪፎርም ሥራ በማካሄድ ላይ እንደሆነች ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የኢንቨስትመንት፣ የባንክና የገንዘብ ፖሊሲዎችን እንዲሁም አስተዳደራዊ ሕጎችን ሪፎርም በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ የግል ኢንቨስተሮችን ለመሳብ መሠረታዊ በሆነ መልኩ አቅጣጫ የማስያዝ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በርካታ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ ምቹ ዕርምጃዎች በቅርብ ጊዜ ውሰጥ በመንግሥት ይፉ እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጠንካራ የባንክ፣ የኢንሹራንስና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለውጭና ለአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ካፒታል እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው በተጨማሪም የፋይናንስ ዘርፉ በጣም ቅርብ በሆነ ጊዜ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ይሆናል ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሀና አርዓያ ሥላሴ በበኩላቸው ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የተሰማሩ የሳዑዲ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቁጥር 233 መድረሱን፣ ከ75 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድሎችን መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡  ለሦስት ቀናት ለጉብኝት ኢትዮጵያ የመጡት ከ70 በላይ ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጥሩ ፍላት እንዳላቸው ኮሚሽነሯ አክለው ተናግረዋል፡፡ በግብርናና የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለጹት ኮሚሽነሯ፣ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የተለየ ፍላጎት አለማሳየታቸውን አስረድተዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሙጂብ በሰጡት ገለጻ፣ የሳዑዲ ባለሀብቶች በዋናነት በነዳጅ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በሰው ኃይል ምልመላ፣ በአጠቃላይ ንግድና በቱሪዝም ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ መንግሥት ጥሩ ነገሮች እያየን ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተቀራረበ መሆኑንና የረዥም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ‹‹በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገቡ ባለሀብቶችን ታያላችሁ፤›› ብለዋል።

ሰባ ዘጠኝ ኢንቨስተሮችን ያካተተው ልዑክ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከሳዑዲ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን፣ በኅዳር 2016 ዓ.ም. በሳዑዲ – አፍሪካ ጉባዔ ወቅት ያደረጉትን  የሁለትዮሽ ውይይት ተከትሎ የተከናወነ  መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከሳዑዲ ዓረቢያ የኢንቨስትመንት ተወካዮች ልዑክ ጋር በቤቶች ልማት፣ በቱሪዝምና በግብርና፣ በተለይም በአገር ውስጥ ማዳበሪያ ማምረት ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...