Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች ማገገሚያ የ2.2 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ተጀመረ

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች ማገገሚያ የ2.2 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ተጀመረ

ቀን:

ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከጀርመንና ከኔዘርላንድስ መንግሥታት በተገኘ 2.2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ፣ በሰሜን ጦርነት ቀጥተኛ ተጎጂ በሆኑት በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚገኙ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ የአራት ዓመት ፕሮግራም ተጀመረ።

በሦስቱ አካላት የጋራ ፈንድ የተጀመረው ፕሮግራም ከኅብረቱ ጋር በቅርበት ከሚሠራ አንድ የልማት ባንክ፣ አንድ ዓለም አቀፍ የጀርመን ልማት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የካፒታል ልማት ፈንድ (ዩኤንሲዲኤፍ) በኩል ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል፡፡

ፕሮግራሙን የሚያስፈጽሙት አካላት ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ የድጋፍ ስምምነቱን ከኢትዮጵያ በኩል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሀሰን ሞአሊን ፈርመዋል።  

- Advertisement -

ለፕሮግራሙ ጀርመንና ኔዘርላንድስ እያንዳንዳቸው 185 ሚሊዮን ብር ሲያቀርቡ፣ የተቀረው 1.8 ቢሊየን ብር በአውሮፓ ኅብርት የተሸፈነ ነው።

ኅብረቱና አጋር አካላቱ ፕሮግራሙን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ የተጋፈጠቻቸው ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ስታስመዘግብ የቆየችውን ዕድገትና በኢንተርፕራይዞቹ በኩል ተገኝቶ የነበረውን የድህነት ቅነሳ ሥራ ሒደት አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢኮኖሚውንና በውስን ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚያስፈልጉ የሥራ ቅጥርና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን መልሶ ለማስፋፋት ሥራ ራሱን የቻለ የተለየ አካሄድ ሊበጅለት የሚገባ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ፣ የአውሮፓ ኅብረት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ሥራቸውን ያቋረጡ ወይም በከፍተኛ ደረጃ የምርት መጠናቸውን ለመቀነስ የተገደዱ፣ በተለይም የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ምርቶች አቀነባባሪ ኢንተርፕራይዞች አሁን ለሚገኙበት ሁኔታ የገንዘብ እጥረት ከፍተኛ ሚና መጫወቱም ተነግሯል።

ጉዳት የደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች ከገንዘብ እጥረት ባሻገር ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ ድርጅቶቻቸውን በተገቢ ሁኔታ ለማስተዳደርና ከሚደርስ ጉዳት ለማገገም የሚያስችል በቂ የአስተዳደር ችሎታ (managerial skills) የላቸውም የተባለ ሲሆን፣ ለምርት አገልግሎት የሚውሉ ንብረቶች ውድመትና ሠራተኞቻቸውን ማጣት፣ እንዲሁም የገንዘብ ተቋማትና አገልግሎት አቅራቢዎችም በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውና የተዘጉ በመሆናቸው የኢንተርፕራይዞቹን ገንዘብ የማግኘት አቅም ውስን ማድረጋቸው ካጋጠሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ ሆነው ተገኝተዋል።

ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ለቀጣይ አራት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው ፕሮግራም ኬኤፍደብሊው የተባለው መቀመጫውን በጀርመን ያደረገ የልማት ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋራ በመሆን፣ ኢንተርፕራይዞች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የንግድ ባንኮችና ማይክሮ ፋይናንሶች በኩል ብድር ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።

ጂአይዜድ የተባለው የጀርመን መንግሥት የልማት ዓላማዎችን ለማሳካት የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ደግሞ ኢንተርፕራይዞቹ በፍጥነትና በጠንካራ ሁኔታ ማገገም እንዲችሉ፣ እንዲሁም ለብድር ብቁ የመሆን አቅማቸውን በማሳደግ የፋይናንስ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ቀጥተኛ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያቀርብላቸው ተነግሯል።

ዓለም አቀፉ ተቋም ከዚህም ባሻገር በኢንተርፕራይዞቹና በአበዳሪ ገንዘብ ተቋማት መካከል ጥሩ የሥራ ግንኙነት ሊኖራቸው የሚችለውን እየለየ እንደሚያገናኝም ተነግሯል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...