Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቅዱስ ሲኖዶስ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለተሳትፎ አለመጠራቱ ቅር እንደተሰኘ አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለተሳትፎ አለመጠራቱ ቅር እንደተሰኘ አስታወቀ

ቀን:

  • ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል

አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ አገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለተሳትፎ በይፋ ሳይጠራ በመቅረቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ቅሬታውን አሰማ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንኑ ቅሬታውንና ውሳኔዎቹን ያሳወቀው ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያካሄደውን የረክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ አማካይነት በሰጠው መግለጫ ነው።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን ቅር በመሰኘቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ‹‹ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት›› በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚመካከር የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ልዑኩ ከመንግሥት ጋር ከሚነጋገርባቸው ጉዳዮች መካከል በፌዴራል ፍርድ ቤት የተፈረደባቸው የምሥራቅ አውስትራሊያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን ጨምሮ ወደ አገር  እንዳይገቡ በተደረጉ በአሜሪካ ስለሚገኙ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ይገኝበታል፡፡

‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተከሰቱትን ወቅታዊ ችግሮች አስመልክቶ እየተላለፉ ያሉ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ መልዕክቶችን›› ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸውና በጥብቅ የሚቃወማቸው መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ወደፊትም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ለማድረግ ይቻል ዘንድ ወጥ የሆነ የመግለጫ አሰጣጥና የትምህርተ ወንጌል ተልዕኮ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለጥቅምት ምልዓተ ጉባዔ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑም ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ መሆኑ እንዳሳዘነው የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት በውይይትና በምክክር እንዲፈቱና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ሲኖዶሱ ከተወያየባቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፣ በረቂቅ አዋጁ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች በማዘጋጀት ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም እንዲላክና ረቂቅ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የተሰጡት የማሻሻያ ሐሳቦች በረቂቁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡

በተጠናቀቀውና ግንቦት 29 ቀን በተሰጠው መግለጫ ሲኖዶሱ አሳሳቢ ብሎ ያነሳውና ውግዘት ያስተላለፈበት ‹‹ግብረ ሰዶማዊነትና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ››ን የተመለከተ ነው፡፡

 ‹‹በሕገ ተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ የሰብዓዊ አኗኗር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃዱ በተገለጠባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ የተከለከለ፣ በቀኖናተ ቤተ ክርስቲያን፣ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች፣ በሥነ ልቦና ደንቦች የተወገዘ፣ ሥነ አእምሮዊ ሚዛንን የሚያዛባ፣ ግለሰባዊ ማንነትን፣ ቤተሰባዊ ሕይወትን፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ [ያወግዛል]›› ብሏል፡፡

‹የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና የግብረ ሰዶማዊነትን ኃጢአት› በተመለከተ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አቋም በሚገልጽ መልኩ ራሱን ችሎ ዓለም አቀፋዊ ይዘቱን ባገናዘበ ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑም ቅዱስ ፓትርያርኩ አስታውቀዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስን መግለጫ ተከትሎ  በዕለቱ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባዔ ለአገራዊ ምክክሩ ትኩረት በመስጠት በመምከሩና ቅሬታ ያሳደሩ ጉዳዮችንም ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት በመወያየት ለመፍታት መወሰኑን በአክብሮት እንደሚመለከተው ገልጿል፡፡

ለዚህም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ድረስ በመገኘት ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን፣ ይህ የአካታችነት መርሕ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጋር በእኩልነት የሚተገበር መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...