Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሊዝ የገዛሁትን 5,000 ሔክታር የእርሻ ቦታ መረከብ አልቻልኩም አለ

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሊዝ የገዛሁትን 5,000 ሔክታር የእርሻ ቦታ መረከብ አልቻልኩም አለ

ቀን:

  • በፀጥታ ችግር እጣንና ሙጫ መሰብሰብ አለመቻሉ ተገልጿል

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በደቡብ ምዕራብ ክልል በማዤና በሱሪ ወረዳዎች መሀል ባለ የ‹‹መሬት ይገባኛል›› አለመግባባት ምክንያት፣ በአካባቢው ለእርሻ ልማት በሊዝ የገዛውን አምስት ሺሕ ሔክታር መሬት አለመረከቡን አስታወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ይህንን ያለው ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የ2016 በጀት ዓመት የአሥር ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ካሉት የእርሻ ልማት ቦታዎች በተጨማሪ አዳዲስ የእርሻ ቦታዎችን ለመግዛት በሒደት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ በቅርቡም በደቡብ ምዕራብ ክልል የገዛውን የእርሻ መሬት በሁለት ወረዳዎች መካከል ባለው የቦታው የይገባኛል አለመግባባት ምክንያት መረከብ አለመቻሉን፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

‹‹የመሬት ይዞታውን ለማልማት ኮርፖሬሽኑ ማሽነሪዎችን ቢያስገባም፣ ባለው ችግር ምክንያት ምንም ዓይነት የሥራ እንቅስቃሴ ማድረግ አልተቻለም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ጉዳዩንም የክልሉ መንግሥት እንዲፈታው ውይይት እየተደረገበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹ቦታው የማን ወረዳ ነው?› የሚለው ጥያቄ የክልሉ መንግሥት ሥራ እንጂ የሌላ ወገን እንዳልሆነና ቦታውም ኮርፖሬሽኑ የገዛው ከክልሉ መንግሥት መሆኑን ጠቅሰው፣ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመፍታት ምክር ቤቱ ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ችግሩ እስኪፈታ ድረስ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመዘዋወር ማልማቱን እንደቀጠለ ገልጸው፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የእርሻ ቦታዎችን ማልማት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መተሃራ አካባቢ ባለው የፀጥታ ችግር የተፈለገውን ያህል የእርሻ መሬት ማልማት ባለመቻሉ፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት መቀነሱን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ የዘር አቅርቦትን ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት የዘር ማባዣ መሬት ጠይቆ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ 1,500 ሔክታር መሬት ተሰጥቶት እንደነበር፣ ነገር ግን በፀጥታ ችግር ምክንያት እስካሁን ማልማት አለመቻሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ክልሉ በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ መረጋጋት ከተመለሰ በማንኛውም ጊዜ መሬቱን ተረክባችሁ ማልማት ትችላላችሁ መባላቸውን ገልጸው፣ ከጦርነቱ በፊት አማራ ክልል የገቡ የእርሻ ማሽነሪዎችንም ማውጣት ስላልተቻለ ኮርፖሬሽኑ ከባድ ችግር ውስጥ ይገኛል ብለዋል፡፡

የእርሻ ማሳ ዝግጅትን በተመለከተ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከአምስት ሺሕ በላይ ሔክታር መሬት ለማዘጋጀት ዕቅድ ተይዞ፣ 2,699 ሔክታር መዘጋጀቱንና ይህም አፈጻጸም ላይ መቀነስ ማሳየቱን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

የእርሻ ማሳን ከማዘጋጀት አንፃር ከታዩ ችግሮች ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ዋነኛ ምክንያቶች ሲሆኑ፣ ችግሩን ለመቅረፍና መፍትሔ ለማምጣት ምክር ቤቱ ዕገዛ እንዲደርግላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡      

ኮርፖሬሽኑ ለፓርላማው እንዳብራራው የተፈጥሮ ሙጫና የደን ውጤቶች ምርት በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

የተፈጥሮ ሙጫና የደን ውጤቶች ምርት የሚገኘው ድንበር አካባቢ ባሉ ሥፍራዎች እንደሆነ፣ እነሱም የፀጥታ ሥጋት ቀጣና ውስጥ ስለሚገኙ በ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት በአሥር ወራት ውስጥ 186 ኩንታል ብቻ መሰብሰቡን አብራርቷል፡፡ 

የኮርፖሬሽኑ የአሥር ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እንደሚያሳየው በአጠቃላይ 1,467 ኩንታል ምርት በግዥ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን 186 ኩንታል ወይም 13 በመቶ ብቻ መሰብሰቡን፣ ይህም ካለፉት ሦስት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 72 በመቶ ቅናሽ አለው፡፡

የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን ምርቶች የሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር በምርት አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑንና የኦጋዴን ዓይነት ዕጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤና አበከድ የሚሰበሰብበት አካባቢ ድርቁ በመቀጠሉ ለገበያ የቀረበ ምርት አለመኖሩ በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡

የተፈጥሮ ሙጫና የደን ውጤቶች የታቀደውን ያህል በግዥ ለመሰብሰብ ለምን አልተቻለም፡፡ ምን ዓይነት ችግሮች አሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ለቋሚ ኮሚቴው ቀርበዋል፡፡ ለቀረቡት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም፣ ችግሩ በአገር ደረጃ የሚታየው የፀጥታ ሁኔታ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ የተፈጥሮ ሙጫና የደን ውጤቶችን ምርት ለማምረት ቦታ ወስደው የተደራጁ ወጣቶች ምርቱን ማምረት ትተው፣ ከመንግሥት የተቀበሉትን ቦታ ለሦስተኛ ወገን በማከራየት ላይ በመሆናቸው የምርት መጠኑ ሊቀንስ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የምርቱ ግብይት ሥርዓት ባለመኖሩ ምክንያት ሕገወጥ ንግድ እንዲስፋፋ እንዳደረገው ጠቅሰው፣ ሁኔታው በዚሁ እንዳይቀጥልና ያሉትም ችግሮች እንዲፈቱ ምክር ቤቱ ጉዳዩን ማጤን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሙጫና የደን ውጤቶች ምርት አፈጻጸም አነስተኛ የሆነው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያወጣው የመሸጫ ዋጋ የምርቶቹን ዓይነት ደረጃ ያላገናዘበ መሆኑን፣ ጉዳዩም መፍትሔ እንዲያገኝ ኮርፖሬሽኑ ደብዳቤ ከመጻፍ አልፎ በቦታው ተገኘቶ ለማስረዳት ቢሞክርም መፍትሔ ባለማግኘቱ እንደሆነ አክለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ኢያሱ ሳለ በበኩላቸው፣ ተቋሙ ቁልፍ ስኬቶችንና ድክመቶቹን ለይቶ በአገልግሎት አሰጣጡ ትርፍ መሆን መቻሉን እንደ ስኬት ይታያል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ባልተሳኩ ጉዳዮች ላይ ጉድለቶችን ማረምና የተገኙ ውጤቶች ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የተፈጥሮ ሙጫና የደን ውጤቶች ምርታማነት ከመጨመር አኳያ ማነቆዎችን በመለየት ምርታማነቱ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፣ ለወጣቶቹም ግንዛቤ በመፍጠር በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም. በአሥር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ከምርጥ ዘር፣ ከተፈጥሮ ሙጫና የደን ውጤት ምርቶች ሽያጭ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ሥራዎችን ጨምሮ 717.78 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 742.38 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...