Saturday, June 22, 2024

አገራዊ ምክክሩና ተስፋው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአገራዊ ምክክሩ ሒደት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሸጋገረ ይመስላል፡፡ የምክክሩ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) የተወካዮች (ተወያዮች) መረጣ ተገባዶ የአጀንዳ መረጣ ውይይት ሊጀመር ነው ብለው፣ ‹‹በአሥር ክልሎችና ሁለት ከተማ መስተዳደሮች፣ ከ1,000 በላይ ወረዳዎች በመድረስ የተሳታፊዎች መረጣ በማገባደድ ለውይይቶች ተዘጋጅተዋል፤›› በማለት እንቅስቃሴው የደረሰበትን ደረጃ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባም ይኸው ሥራ መገባደዱን በመጥቀስ ቅዳሜ ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ የተካሄደው ሥነ ሥርዓትም ‹‹የምክክር ሒደት መግቢያ ማብሰሪያ›› ምዕራፍ መሆኑን ይፋ አድርገው ነበር፡፡

ምክክሩ በይፋ መጀመሩን ለማብሰር በተጠራው በቅዳሜው ሥነ ሥርዓት ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ተገኝተው ነበር፡፡ የኃላፊነት ወሰኑ ምክረ ሐሳብ እስከ ማቅረብ ባለው ደረጃ የተገደበና የቆይታ ጊዜው ከሦስት ዓመት ያልበለጠ ተብሎ የተቋቋመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ከባድ አገራዊ አደራን የተሸከመ ተቋም ነው፡፡ ኮሚሽኑ የተወሳሰቡ ብዙ ችግሮች ለተጫናት ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሸክም ማቅለያ መፍትሔ ካመጣም ትልቅ ነገር ነው የሚለው ግምት ሚዛን ደፍቶ ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ የቅዳሜው የምክክር ሒደት መግቢያ ማብሰሪያ ምዕራፍ ትልቅ ነገር ይሰማበታል፣ እንዲሁም የምክክር ሒደቱን በተመለከተ የቆዩ ጥርጣሬዎችና ብዥታዎች ተገፈው በጎ ተስፋ ይፈነጥቅበታል ተብሎ ነበር፡፡

ከመድረኩ በኋላ ግን ይህ ስለመሆኑ ብዙዎች ጥርጣሬ ሲገባቸው ነው የታየው፡፡ መድረኩ በተካሄደ ማግሥት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ራሱን ከምክክሩ ማግለሉን ሲያስታውቅ፣ ሌላው በቅድመ ሁኔታ ራሱን ሊያገል እንደሚችል አስታውቋል፡፡

የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስለተፈቀደለት፣ ለከንቲባዋ በልዩ ሁኔታ ኮሚሽኑ ምስጋና ሲያቀርብ የታየበት መድረክ ነበር፡፡ መድረኩ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በኮሚሽኑ ሥራ ጣልቃ ገብቶ አያውቅም በሚል ኮሚሽኑ ያመሠገነበት ነበር፡፡ መድረኩ ከሞላ ጎደል የመንግሥት ስኬቶች ከስንዴ እርሻ እስከ ከተማ ማስዋብ ጎልተው የተሰሙበት ነበር፡፡ መድረኩ በአመዛኙ መንግሥት በምክክር ሒደቱ ምን እንደሚፈልግና እንደማይፈልግ ብቻ ሳይሆን፣ ከሒደቱ ምን እንደሚጠብቅም ጎልቶ የተነጋገረበት ነበር፡፡ በአጠቃላይ በመድረኩ የተስተጋባውና የመድረኩ ድባብ በአገራዊ ምክክሩ ሒደት ቅሬታም፣ ተስፋም ሆነ ቀቢፀ ተስፋ የነበራቸው፣ ወይም ሲደግፉትም ሆነ ሲቃወሙት የነበሩ ወገኖች ሒደቱን በተመለከተ ያላቸውን አቋም እንዲያጤኑ የሚጋብዙ ትዕይንቶች የተሞሉበት ነበር፡፡

ብዙዎች የአገር ችግር ማቅለያ ይሆናል ብለው ተስፋ ባደረጉበት ትልቅ የአገራዊ ምክክር መድረክ ላይ ገዥው ፓርቲ ብልፅግናን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያደረጉት ንግግር፣ የምርጫ ቅስቀሳ ይመስል ነበር ያሉ አሉ፡፡ በአገራዊ ምክክር መድረክ መክፈቻ ላይ ስለትምህርት ማስፋፋት፣ በስንዴ ልማት ራስን ስለመቻል፣ ስለተቋማት ግንባታና ዕድሳት፣ ስለከተማ ማስዋብ ፕሮጀክትም ሆነ ስለህዳሴ ግድብ ግንባታ መገባደድ ለ30 ደቂቃዎች ንግግር ማሰማታቸው መከራከሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ስለወሰዳቸውና ‹‹ድፍረት የተሞላባቸው ሪፎርሞች›› ስላሏቸው ሥራዎች ትኩረት ሰጥተው መናገራቸው፣ መድረኩን በተመለከተ ከአገራዊ ምክክርነት ይልቅ የመንግሥት የክዋኔ ሪፖርት ማድመጫ አስመስሎታል የሚል ትችት የጋበዘ አጋጣሚ ነበር፡፡

መድረኩን በተመለከተ መንግሥት እንደ መንግሥት ሆኖ ነው ወይስ የመሪ ድርጅቱ የብልፅግና አቋምን ለማስተጋባት ነው የተገኘው የሚለው ጉዳይም ወሳኝ የክርክር ነጥብ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡

‹‹በሞት አፋፍ ላይ የደረሱ በመሆናቸው ለትውልድና ለአገር በጎ ተስፋ አድርሶ ከማለፍ በዘለለ አይሰርቁም፣ አይዋሹም፣ በገንዘብም አይታለሉም›› የሚል ሙገሳ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጣቸው የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ግን የተለየ ሐሳብ ሲሰጡ ነው የታየው፡፡ ከአሥራ አንዱ ኮሚሽነሮች ውስጥ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮሚሽነሩ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በመድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተንፀባረቀው ሐሳብ ተጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹እንደ አንድ ባለድርሻ መንግሥትን ማሳተፍ ኃላፊነታችን ነው፡፡ መንግሥት የተገኘው እንደ መንግሥት ነው፡፡ የተንፀባረቀው ሐሳብም የመንግሥት ነው ብለን መዝግበናል፡፡ ከዚያ ውጪ የሚነሱ ሐሳቦችን ትክክል ነው አይደለም ብለን የመበየን ሥልጣን የለንም፤›› በማለት ነበር ለሚዲያዎች ምላሽ የሰጡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከልማት ስኬቶች ባለፈ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ስለሚሉትና ስለሽግግር መንግሥት ጉዳይ ጠንካራ ንግግር አድርገዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ጠንካራ ነገር ግን በሕግ የሚገዛ መንግሥት ያስፈልጋታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚናገረውን የሚፈጽም ጠንካራ መንግሥት መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የሚጠብቅ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያን የሚያስቀጥልና የሚያሸጋግር መሆን አለበት፡፡ ጠንካራ መንግሥት ሲባል እኛ የምንመራው መንግሥት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ማንም በቦታው ቢሆን በዙሪያችን የከበቡንና ቀጣናውን የሚያተረማምሱ እጀ ረዣዥሞችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ መንግሥት ሊኖረን ይገባል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት እሳቸው የመሩት መንግሥት የጠቀሷቸውን የጠንካራ መንግሥትነት መሥፈርቶች ስለሟሟላት አለሟሟላቱ ግን የገለጹት ነገር የለም፡፡ በዓብይ (ዶ/ር) ዘመን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ድንበር በተለያዩ አቅጣጫዎች በውጭ ወራሪዎች ሲደፈር መንግሥት መከላከል አልቻለም የሚል ከባድ ወቀሳ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው፣ ‹‹ከአሥራ ምናምን ጊዜ በላይ የህዳሴ ግድብን እያነሱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ከሰውናል፡፡ በዲፕሎማሲ፣ በፋይናንስና በዕርዳታ ምናመን ሊጫኑን ይሞክራሉ፤›› ብለው በቅዳሜው መድረክ ላይ እንደተናገሩት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ለውጭ ጫና ተጋላጭ መሆኗ ጨምሯል የሚለው ወቀሳም በመንግሥት ላይ ሲስተጋባ ቆይቷል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ የውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነትን አምርራ ስትታገል መኖሯን ጠቅሰዋል፡፡ ላኪና ተላላኪነት በበዛበት ቀጣና የምትገኝ ቢሆንም እናውቅልሀለን የሚሉ ኃይሎችን ስትመክት መቆየቷን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት መቶ ምናምን ዓመታት ከውጊያ የተለየ ታሪክ የላትም፡፡ አፄ ቴዎድሮስን ስናነሳ የውጊያ ታሪክ፣ አፄ ምኒልክን ስናነሳ የውጊያ ታሪክ ነው የምናነሳው፤›› በማለት በፀረ ቅኝ አገዛዝ የተደረገ ተጋድሎዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከግጭት ተላቃ እንደማታውቅ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንደሆነው እናውቅልሃለን የሚሉ ሰዎች የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት አይጽፉትም፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሚጻፈው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የድምፅ ውሳኔ ነው፡፡ እኛም፣ እነሱም አንችልም፤›› የሚል ንግግር አያይዘው አሰምተዋል፡፡

ስለአገራዊ ችግሮች፣ ስለመጓደል፣ ስለጠንካራ መንግሥት፣ ስለመላላክና ስለምክክር ከዘረዘሩ በኋላ ደግሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚወስናቸው ውሳኔዎች ለመገዛት መንግሥት መቶ በመቶ ዝግጁ ነው፤›› ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ፣ የባንዲራ ዓርማ ይኑረው አይኑረው ጉዳይ በምክክሩ ቀርበው በሕዝቡ ውይይትና በሕዝ ውሳኔ የሚፈቱ ጉዳዮች መሆናቸውን በምሳሌነት ሲጠቅሱ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹በውይይቱ ከተስማማን ተስማማን ካልተስማማን ሁሉም ሊገዛበት፤›› ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ከእኛው መካከል ተላላኪ ገዝተው እኛኑ በውስጥ ሊከፋፍሉን ያሰፈሰፉ ኃይሎች አሉ፤›› ሲሉም በግልጽ ማንነታቸውን ያልጠቀሷቸውን ኃይሎች ከሰዋል፡፡ ቀጠል በማድረግ ደግሞ ስለሽግግር መንግሥት ጉዳይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግሥት አይኖርም፡፡ በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ብቻ፣ በሕዝብ ውሳኔ የተመረጠ መንግሥት ብቻ ነው የሚኖረው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ‹‹እንኳን እንደ ዕቁብና ዕድር ተሰባስበን ቀርቶ አሁን ባለን ቁመናም የምናስበውን መከወን አቅቶናል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡ የሽግግር መንግሥት ሐሳብ የሚያቀርቡ ወገኖች ከፋፋዮች ወይም ተላላኪዎች በሚል ነው የተወገዙት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ ባያስቀምጡም ስለጣልቃ ገብነት፣ ከፋፋይነትና ተላላኪነት አጠንክረው ያነሱት ምዕራባዊያኑን ግፋ ቢልም የመካከለኛው ምሥራቆችን ሊሆን እንደሚችል ነው በአንዳንዶች የተገመተው፡፡ ሆኖም በገንዘብም ሆነ በዲፕሎማሲና በሚዲያ ሲደግፉት የቆዩትን የአገራዊ ምክክር አጀንዳ ምዕራባዊያኑ ሊያደናቅፉት ይሞክራሉ የሚለው ሥጋት ከየት የመነጨና ምን ያህል የተጨበጠ ነው የሚለው ጥያቄ እንቆቅልሽ ይመስላል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ባሰሙት ንግግር የኢትዮጵያ ችግርን በጦርነት ለመፍታት ተሞክሮ እንዳልተሳካ፣ በምርጫም ተሞክሮ እንዳልተፈታ ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ከዚያ ይልቅ በንግግርና በውይይት ለመፍታት አዲስ ጥረት መጀመሩን የጠቆሙ ሲሆን፣ ‹‹ከኢትዮጵያውያን እስከመጣ ድረስ ማንኛውንም ጠቃሚ ሐሳብ ለመቀበል ዝግጁ ነን፤›› በማለት ቃል ገብተዋል፡፡

ይህን ዕድል ሁሉም ወገን እንዲጠቀምበት ግብዣ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕድልን መጠቀም ድል እንደሚያመጣ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ካልተጠቀምንበትና አንዴ ካመለጠና ካለፈ በኋላ ብንጠይቅ ብለናችሁ ነበር የሚል ምላሽ ብቻ ነው የምናገኘው፤›› በማለትም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ምክክሩን በሚመለከት ከሰሞኑ ያሰሙት ጠንከር ያለ ንግግር ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ ምላሾችን እያስተናገደ ነው የሚገኘው፡፡ የሽግግር መንግሥት ሐሳብን የተመለከተ ሰነድ ከዚህ ቀደም ያቀረቡትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርም በቀጥታ ለእሳቸው የተሰጠ ምላሽ መሆኑ የተነገረው አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ንግግሩ እንዳላስደነቃቸው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ለሀቀኛ የዴሞክራሲ ሽግግር ያለው ቁርጠኝነትና ፍላጎት እጅግ የወረደ መሆኑን ከመድረኩ እንደታዘቡ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከሽግግር መንግሥት በመለስ መንግሥት በፈጠረው የምክክር ሒደት አገሪቱን ከችግር ማላቀቅ ይቻላል የሚል ተስፋ ያላቸው ወገኖች፣ ከዚህ መድረክ በኋላ አቋማቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ፡፡ አገራዊ ምክክሩ የመንግሥትን ሥልጣን ለማፅናት የሚደረግ መሆኑን አጋጣሚው አሳይቶናል፤›› ብለዋል፡፡

የሽግግር መንግሥት በኢትዮጵያ አሉታዊ አመለካከት የያዘ ጉዳይ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ልደቱ፣ ይህ የመጣው ደግሞ ከዚህ ቀደም የተሞከሩ የሽግግር ሒደቶች ባለመሥራታቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት ወደፊትም ትርጉም ያለው ለውጥ የሽግግር መንግሥት አያመጣም የሚሉ መኖራቸውን አውስተዋል፡፡

‹‹ገና ከመጀመሪያው በኮሚሽኑ ማቋቋም ሒደት ነው ሒደቱ የከሸፈው፡፡ ሒደቱ ከተበላሸ አዎንታዊ ውጤት አያመጣም፡፡ ስያሜው በራሱ አገራዊ ምክክር ማለት ብዙ አገራዊ ጉዳዮችን የሚያቅፍ ነው፡፡ አስገዳጅ የሆኑ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ነው፡፡ አገራዊ ምክክር ብለው ግን ከምክክር ያለፈ ሚና ኮሚሽኑ እንዳይኖረው አድርገውታል፡፡ አገራዊ የውይይትና የድርድር ሒደት ተብሎ ውይይትንም ድርድርንም ያቀፈ እንዲሆን ሊደረግ እንደሚገባ እኔ ቀድሜ ምክረ ሐሳቤን ጽፌ ነበር፤›› በማለት ከአሁኑ ሒደት በጎ ተስፋ እንደማይጠብቁ አስረድተዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የሕግ ባለሙያ ግን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አለመደንገጣቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹መንግሥት ከሥልጣን በመለስ እንነጋገር እያለ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በግልጽ እንዳሰፈረው የኮሚሽኑ ሚና ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ነው፡፡ ምክረ ሐሳቡን ደግሞ የሚፈጽመው መንግሥት ነው፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ሒደቱ የሽግግር መንግሥትን በፍፁም ታሳቢ ያደረገ እንዳልነበረም ጠቁመዋል፡፡

ሒደቱ ሲጀምር ከሰማይ በታች ለውይይት የማይቀርብ ነገር እንደሌለና ብዙ ተስፋ ሲሰጥ ነበር የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው የሕግ ባለሙያው፣ ወደዚህ ሒደት መገባቱን በራሱ እንደቀላል እንደማያዩት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሒደቱ የዴሞክራሲ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ የሚያስችል ውጤት ካመጣ፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን ፓርላሜንታዊ ለመወሰን የሚያስችል ዕድል ከፈጠረ፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ በተለይ የምርጫ ሒደቱ እንዲሻሻል ካደረገ፣ ሲቪል ሰርቪሱን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ካላቀቀ፣ መንግሥትና ፓርቲን እንዲነጣጠሉ ካደረገ፣ በአጠቃላይ ተቋማትን ካጠናከረና በአንፃራዊነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሪቱ ካሰፈነ በራሱ ስኬታማ ነው ብዬ እገምታለሁ፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሽግግሩ ወቅት በተለይም በኢሕአዴግ መንግሥት መጀመሪያ ዓመት የፖለቲካ ሥርዓቱ ምንነት ሲወሰንም ሆነ በሒደት ሕገ መንግሥቱ ተረቆ ሲፀድቅ ውይይት ይደረግ እንደነበር በማስታወስ፣ የአሁኑ ምክክር ከዚያ በምን ይለያይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ምክክርም ቢሆን መንግሥት በስተመጨረሻ የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦችን አልፈጽምም ቢል በምን ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል የሚል ጥያቄም ተነስቶላቸው ነበር፡፡

የሕግ ባለሙያው ሲመልሱም የኢሕአዴግ የሽግግር ሒደት ሙሉ ለሙሉ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር የተደረገና አሳታፊነት የጎደለው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ያን ጊዜ የፖለቲካ ንቃትም በሕዝቡ ዘንድ አነስተኛ ነበር፡፡ የአሁኑ ፍፁም በተለየ የፖለቲካ ከባቢ አየር ውስጥ የሚካሄድ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

መንግሥትን እንዴት እንመነው ለምክክር ሒደቱ መገዛቱን በምን እናረጋግጣለን የሚለውን ጉዳይ ሲያብራሩም፣ ‹‹መንግሥት ለምክክር ሒደቱ እገዛለሁ ብሎ ለገባው ቃል ከመገዛት የዘለለ ምርጫ ያለው አይመስለኝም፤›› ብለው፣ ‹‹መንግሥት ታንክም ባንክም ቢኖረው ለዘለዓለሙ ከተለያዩ ወገኖች ጋር እየተዋጋ መጓዝ አይችልም፡፡ ለአሁኑ ከሥልጣኔ ውጪ (ከሽግግር መንግሥት ውጪ) እንነጋገር ብሏል፡፡ ይህን አናምንህም ብሎ መሸፈቱና በጠመንጃ መታገሉ ይሻላል ወይስ በሒደቱ ገብቶ ውጤቱን መጠበቁ የሚለው ሁሉም ኃይሎች ሊያመዘዛኑት ይገባል፤›› በማለት ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በሒደቱ መቀጠል አልችልም ብሎ ወጥቷል፡፡ እናት ፓርቲ ከወዲሁ ሥጋቱን በቅድመ ሁኔታዎች እያነሳ ይገኛል፡፡ እንደ ኦነግ ሸኔና ፋኖ የመሳሰሉ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሒደቱ ይመጣሉ የሚለው ተስፋ የሰለለ ይመስላል፡፡ በዚህና በሌሎችም ውስብስብ ጉዳዮች የታጠረው የምክክር ሒደቱ እንዴት ይቀጥላል? ምንስ ይዞ ይመጣል? የሚለው በተደበላለቀ ስሜት ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -