Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየአገራዊ ምክክር ዕድሎችና ፈተናዎች

የአገራዊ ምክክር ዕድሎችና ፈተናዎች

ቀን:

በገብሬ ይንቲሶ ደኮ (ዶ/ር)

መግቢያ

በዓለም ላይ አገራዊ ምክክር ማድረግ እየተለመደ መጥቷል። አገራዊ ምክክር የሚደረገው በአንድ አገር ውስጥ ሥር የሰደደ የሐሳብ ልዩነት ሲፈጠር፣ ሕዝባዊ ቅሬታና አመፅ ሲከሰት፣ ያለመግባባት ወደ ግጭትና ጦርነት ሲያመራና በእነዚህም የተነሳ የመንግሥትና የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ሲገባ፣ ግልጽ አካታችና አሳተፊ በሆነ አግባብ መተማመን ተፈጥሮ በመነጋገር ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ነው። አገራዊ ምክክር በባህሪው ከክርክር፣ ከድርድር፣ ከግልግል፣ ከዕርቅና ከሌሎች በተፅዕኖ ወይም በማሳመን ጥበብ ከሚደርጉ ስምምነቶች ይለያል። በምክክር ወቅት ተሳታፊዎች እርስ በርስ በመከባበር፣ በጥሞና በማዳመጥና የሌላውን ፍላጎትና ሥጋት በጥልቀት በመረዳት የአስተሳሰብ ለውጥ ያደርጋሉ።

- Advertisement -

በብዙ አገሮች አገራዊ ምክክር የሚደረገው በመንግሥት፣ በዋና ተቃዋሚዎች ወይም በሌሎች ወሳኝ ኃይሎች መካከል ሲሆን የሲቪል ማኅበራት፣ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የንግድ ድርጅቶችና የሃይማኖትና የባህል ተቋማት ይሳተፋሉ። ሕዝቡም በተለያየ መንገድ በንቃት እንዲሳተፍና በቅርብ እንዲከታተል ይደርጋል። የአገራዊ ምክክር ሒደት በተሳካ ሁኔታ ከተተገበረ እርስ በርስ መተማመን ይፈጠራል፣ ግጭት ተወግዶ ሰላም ይሰፍናል፣ ፍትሐዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ይጠናከራል፣ እንዲሁም ፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም ይረጋገጣል።

በሌላ አገላለጽ የቅሬታ፣ የአመፅ፣ የግጭትና የጦርነት መንስዔዎች በመደማመጥ ተቀርፈው መቀራረብና ጥልቅ መግባባት ይፈጠራል ማለት ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ የተጀመረው አገራዊ ምክክር ሒደት እንዲሰካ ጥረት ማድረግና ዕድል መስጠት ይጠቅማል እንጂ ምንም አይጎዳም። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ልይነቶችን በሠለጠነ መንገድ በምክክር ለማጥበብ ጥረት ማድረግ በራሱ በአዎንታዊነት የሚገለጽ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ ልምምድ ነው። 

የአገራዊ ምክክር ሒደት አስቻይና ገዳቢ ሁኔታዎች

የአገራዊ ምክክር ሒደት አስቻይ ሁኔታዎች (enabling factors) ወይም ገዳቢ ሁኔታዎች (constraining factors) እንዳሉት ጥናቶች ያመለክታሉ። አስቻይ ሁኔታዎች ወደ ስኬት የሚያመሩ ዕድሎች ሲሆኑ፣ ገዳቢ ሁኔታዎች ምክክሩ እንዳይሳካ የሚያደርጉ ፈተናዎች ናቸው። እንደ አገር የልሂቃን ድጋፍ ወይም ተቃውሞ፣ የሕዝብ ድጋፍ ወይም ተቃውሞ፣ የአኅጉርና ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ድጋፍ ወይም ተቃውሞ፣ የምክክር ባህል መኖር አለመኖርና የግጭት መኖር አለመኖር አስቻይና ገዳቢ ሁኔታዎችን ያጣመረ ፖለቲካዊ ዓውድ ነው። ሁለተኛው ዓውድ ከምክክር ሒደት ጋር የተያያዘ ሲሆን በውክልና፣ በተሳታፊ ቁጥር፣ በሰብሳቢ ምርጫ፣ በውሳኔ አሰጣጥ፣ እንዲሁም ለምክክሩ በሚያስፈልጉ ግብዓቶች ዙሪያ መስማማት ሳይኖር ሲቀር የሚያጋጥሙ አስቻይ ወይም ገዳቢ ሁኔታዎች ናቸው።

የአገራዊ ምክክር ሒደት አስቻይና ገዳቢ ሁኔታዎች ከላይ በተገለጸው መልክ የሚስተዋሉ ከሆነ፣ ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ የስኬት ዕድሉን ማስፋት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በምክክር ሒደቱ ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ አካላት (ልሂቃን፣ የኅብረተሰብ ክፍል፣ ተቃዋሚ ኃይል፣ ወዘተ) ካሉ ለቅሬታቸው ምላሽ በመስጠት መተማመንን መፍጠር ይገባል። በየአካባቢው የሚስተዋሉ ግጭቶችን በተኩስ አቁምና በሰላም ስምምነት ማርገብ ለመቀራረብ በር ይከፍታል። ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚሹ ተደራሽ መሆንና የፖለቲካ እስረኞችን መረጃ እያጣሩ መፍታት ለምክክር ሒደቱ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ሒደቱ ከተጀመረ በኋላ በውክልና ጥያቄም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚነሱ ጥቃቅን ቅሬታዎችን ነቅሶ አውጥቶ መቅረፍ፣ በዋናው ምክክርና በውሳኔ አፈጻጸም ወይም ትግበራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ይረዳል።

አጀንዳ ልየታና ቀጣይ ሒደቶች

የበርካታ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያመለክተው አገራዊ ምክክር ሦስት የሒደት ምዕራፎች አሉት። እነሱም የዝግጅት ምዕራፍ (preparation phase)፣ የምክክር ሒደት ምዕራፍ (process phase) እና የትግበራ ምዕራፍ (implementation phase) ናቸው። የተሳታፊ ልየታና አጀንዳዎችን ማሰባሰብ፣ መለየትና መቅረፅ በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው። በመጨረሻ ተለይተው ለምክክር የሚቀርቡት ወሳኝ አጀንዳዎች ኅብረተሰቡ በሐሳብ የተለያየባቸው ወይም በጎራ ተከፋፍሎ የሚጋጭባቸው በቁጥር የተወሰኑ ጉዳዮች እንዲሆኑ ይጠበቃል።

ከዚህ አንፃር ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በሐሳብ ከሚለያዩባቸውና ለግጭት መንስዔ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የታሪክ ትርክት፣ የመሬት ይዞታ ሥርዓት፣ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ፣ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝምና ሌሎችም በሕገ መንግሥቱ የተካተቱ አወዘጋቢ አንቀጾች ይገኛሉ።

አጀንዳው ተቀርፆ ምክክር በሚደረግበት ጊዜ ተሳታፊዎች የየራሳቸውን አቋም ሳይሆን ፍላጎትና ሐሳብ በቅንነትና በግልጽ በማቅረብ፣ እንዲሁም የሌሎችን ፍላጎትና ሐሳብ በጥሞና በማድመጥ ልዩነቸውን ያጠባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን በምክክሩ ወቅት በመግባባት ለመወሰን የሚያስቸግሩ አጀንዳዎች ሊያጋጥሙ ይችላል። አለመግባባት ሲፈጠር አስቀድሞ በተሳታፊዎች በፀደቀ የምክክር መርሆ መሠረት ይስተናገዳል። ምንም እንኳ የተሳታፊዎች ውሳኔ መግባባት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚፈልግ ቢሆንም፣ መርሆው ላይ አስቀድሞ የተካተተ ከሆነ በአብላጫ ድምፅም ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል።

በመግባባት ወይም በድምፅ ብልጫ የተወሰነውን ውሳኔ መተግበር የአገራዊ ምክክር ሒደት ሌላ ፈተና ነው። አጠቃላይ ሒደቱ ሳንካ ከበዛበት፣ በምክክሩ ወቅት ልዩነቶችን ለማጥበብ ካስቸገረ፣ ወሳኝ የሚባሉ ተሳታፊዎች የጋራ ውሳኔያቸውን ካላከበሩና የትግበራ ኃላፊነት የተሰጠው አካል አቅምና ግብዓት ካጣረው አገራዊ ምክክርን በስኬት ማጠናቀቅ ያስቸግራል። ስለዚህ የትግበራ ፈታናዎችን አስቀድሞ በመለየት ከወዲሁ መፍትሔ እያበጁና ሥጋቶችን እየቀነሱ መሄድ ይመከራል። የኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎና ግፊት ለትግበራ ስኬት ወሳኝ ነው።

ከአዘጋጁ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gebred@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...