Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡ ድርጅቱ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ አደጋዎች የመስማት ችሎታቸውን ያጡ ዜጎች የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሠራ ይገኛል፡፡ ሕፃናት ገና ሲወለዱ ለመስማት ችግር ተጋላጭ እንዳይሆኑና አስቀድመው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የመስማት ችሎታ ምርመራ የሙከራ ፕሮጀክትን በአራት በተመረጡ የጤና ተቋማት ይፋ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በውጭ አገሮች ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የመስማት መጠን መመርመሪያ መሣሪያዎች በዕርዳታ ወደ አገር እንዲገቡ በማድረግ በኩልም ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› ድርጅት በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የመስማት ችሎታቸውን ላጡ ዜጎችና በተለይም በጨቅላ ሕፃናት የመስማት ችሎታ ምርመራ ዙሪያ እየሠራቸው ስለሚገኙ ሥራዎች የማኅበሩን ፕሬዚዳንትና የአንገት በላይ ሰብ ስፔሻሊስት ኢስሀቅ በድሪን (ዶ/ር) የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ድርጅት ለመመሥረቱ ዋና ምክንያት ምንድነው?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- መስማት ለኢትዮጵያ በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ አገር በቀል ማኅበር ነው፡፡ በርካታ ሰዎች በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ አደጋዎች የመስማት ችሎታቸውን ያጣሉ፡፡ የመስማት ችሎታ ለግንኙነት መሠረትና ለማኅበራዊ መስተጋብር መዳበር ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ በአንፃሩ የመስማት ችግር ለትምህርትና ማኅበራዊ ግንኙነት ተግዳሮት በመሆኑና ብዙዎችም የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸውን በመመልከት፣ ችግሩን ለመቅረፍና ጫናውንም ለማቃለል በማሰብ ማኅበሩ ሊመሠረት ችሏል፡፡ ይህ ማኅበር በአገራችን ያለውን የመስማት ችግር በተቻለ መጠን በጨቅላነት ዕድሜ ለመለየትና ችግሩም ካለ በፍጥነት መከላከል እንዲቻል የሚሠራ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ለመስማት ችግር መከሰት እንደ መንስዔ የሚጠቀሱት ምንድን ናቸው?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያ ለመስማት ችግር በዋነኛነት ምክንያት ነው የምንለው የመሀል ጆሮ ኢንፌክሽን ነው፡፡ የመሀል ጆሮ ኢንፌክሽን በቀዶ ጥገና (ኦፕሬሽን) የሚድን በሽታ ነው፡፡ ይህ ሕክምና በአገራችን ካለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ወዲህ መሰጠት ጀምሯል፡፡ ከዚያ በፊት ሕክምናውን ለማግኘት ወደ ውጭ መሄድ ያስፈልግ ነበር፡፡ በሕክምናው ዙሪያ ‹‹ኢትዮ አሜሪካን ኦንቶሎጂ ፕሮግራም በመመሥረት ለጎንደር፣ ለሐዋሳ፣ ለባህር ዳር፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎችና ለቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል መምህር የሆኑ የጆሮ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን አሠልጥነናል፡፡ ይህም ችግሩን በመቅረፍ ዙሪያ የምናደርገው አንዱ ጥረት ነው፡፡ ለጆሮ ሕመም የወባ በሽታ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ይህም በሽታ አለመስማት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን በእነዚህና መሰል ችግሮች የተነሳ ያለመስማት ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች፣ ውጭ አገሮች ካሉ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር የማዳመጫ መሣሪያ እንዲያገኙ እያደረግን እንገኛለን፡፡     

ሪፖርተር፡- የግጭቶችና የጦርነት ቀጣናዎች ዜጎችን ለመስማት ችግር ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ይባላል፡፡ በእኛ አገርስ ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ችግሮቹ ስለመከሰታቸው የተደረጉ ጥናቶች አሉ?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- ከፍተኛ ድምፅ፣ ፍንዳታዎች ያለባቸውና ታንክ አካባቢ የሚሠሩ ግለሰቦች የጆሮ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በዚህ ዙሪያ በኢትዮጵያ የተጠና ጥናት ባለመኖሩ ብዙ መናገር አልችልም፡፡ በጦር ኃይሎች ሆስፒታልና በሌሎችም የሕክምና ተቋማት በምሠራበት ወቅት በከፍተኛ የጦር መሣሪያ ጩኸት የተጎዱ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ብጠቅስልህ በሶማሊያ የካራማራ ጦርነት ወቅት ጆሯቸው የተጎዳና ‹‹ኩክሊያ ኢንፕላንት›› የተደረገላቸው አንድ ግለሰብ አስታውሳለሁ፡፡ እኚህ ግለሰብ ጆሯቸው የተጎዳው መድፍ ይዘው ሲታኮሱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ሁለቱም ጆሯቸው አይሰሙም ነበር፡፡ ኩክልያ ኢንፕላንት ማለት ሙሉ በሙሉ ጆሮ መስማት በማይችልበት ሁኔታ ሴንሰርን በመተካት ጆሮ ውስጥ በቀዶ ሕክምና የሚቀበርና የሚመጣውን ሜካኒካል ዌቭ ወደ ኤልክትሮኒክ ዌቭ በመቀየር ድምፅ እንዲሰማ የሚያደርግ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ የመስማት መጠንን የሚጨምሩ የመመርመርያ የሕክምና መሣሪያዎችን ከኦስትሪያ መረከቡን ሰምተናል፡፡ ስለ እነዚህ መሣሪያዎች ምንነትና የመስማት መጠንን እንዴት እንደሚለኩ ቢነግሩን?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- በአገራችን በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና ሕክምናውን በዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ተደራሽ ለማድረግ ማኅበራችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መነሻነት ለዚህ ተግባር የሚያገለግሉ የጨቅላ ሕፃናትን ጆሮ የመስማት መጠን የሚለኩ እጅግ ውድና ዘመናዊ ኤሌክሪክ ሪስፖንስ ኦዲዮሜትሪና ብሬን ሪስፖንስ ኦዲዮሜትሪ መሣሪያዎችን ኦስትሪያ ከሚገኘው ሜድ ኤል ኩባንያ በዕርዳታ አግኝተናል፡፡ እነዚህ የሕክምና ግብዓቶች በሚሊዮን ብሮች የሚገመቱ ናቸው፡፡ ከኦስትሪያ ያገኘናቸው የመስማት መጠን መመርመሪያ መሣሪያዎች በአገራችን ከአንድ የመንግሥትና ከአንድ የግል የሕክምና ተቋም በስተቀር የማይገኙ ናቸው፡፡ ስለሆነም እዚህን መሣሪያዎች ከጀርመን በመጡ ባለሙያዎች ስለመሣሪያዎቹ ለጤና ባለሙያዎች ሥልጠና ከተሰጠ በኃላ፣ ለተመረጡ አራት የሕክምና ተቋማት የሚከፋፈሉ ይሆናል፡፡ እነኚህ የጤና ተቋማትም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ኮሪያ ሆስፒታልና ምግባረ ሰናይ አጠቃላይ ሆስፒታል ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ አራት ሆስፒታሎች የተመረጡበት ምክንያት ምንድነው?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- እነዚህ የሕክምና ተቋማት የተመረጡበት ምክንያት፣ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የመስማት ችግር ያጋጠማቸው ዜጎች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ እነዚህ ተቋማት የሚሄዱ መሆናቸውን መጠነኛ ጥናት በማድረግ በማወቃችን ነው፡፡ በተጨማሪም በአገራችን ያሉ አብዛኛዎቹ አንገት በላይ ሐኪሞች የሚገኙት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በመሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነኚህ መሣሪያዎች የመስማት መጠንን በመለካት ረገድ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- በአሁኑ ወቅት በርካታ ሕፃናት የመስማት ችግር ሰለባ እየሆኑ ይገኛል፡፡ በመሆኑም እነዚህ በዕርዳታ የተገኙ የመስማት መጠን መመርመሪያ መሣሪያዎች ችግሩን በተወሰነ ደረጃ በመቅረፍና በማቃለል በኩል ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ከእዚህም ባሻገር ለአገራችን የሕክምና ባለሙያዎች የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር በኩል የሚኖራቸው ጠቀሜታም የጎላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገራችን የመስማት ችግር ያለባቸው ዜጎች ምን ያህል ናቸው? የችግሩስ ስፋት እንዴት ይገለጻል?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- በአገራችን የመስማት ችግር ያለባቸው ዜጎችን በአኃዝ ለማስቀመጥ እጅግ ይቸገራል፡፡ ለዚህም ዋና ምክንያቱ በዚህ ዙሪያ የተደረገ በቂ ጥናት ባለመኖሩ ነው፡፡ ጤና ሚኒስቴር እስከ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች የመስማት ችግር አለባቸው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን ይህ የሚታወቀው ሙሉ በሙሉ ምርመራ ሲደረግና በጥናት ሲደገፍ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የተወሰኑ ጥናቶች ቢደረጉም፣ የተሟሉ ናቸው ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡   

ሪፖርተር፡-  የጨቅላ ሕፃናት የመስማት ችሎታ ምርመራ በውጭ አገሮችና በኢትዮጵያ ያላቸው ገጽታ ምን ይመስላል?

ኢስሀቅ (ዶ/ር)፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት የመስማት ችሎታ ምርመራ መርሐ ግብሮች በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮችም ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረጉ የጨቅላ ሕፃናት የመስማት ችሎታ የማጣሪያ (የምርመራ) መርሐ ግብሮች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ የመስማት ችሎታ ምርመራ ዋና ዓላማ የረዥም ጊዜ የሕክምና ችግሮችን ለመቀነስና በሽታን በመለየት ሕክምናው ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት፣ ወደ 32 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት በዓለም አቀፍ ደረጃ የመስማት ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከ25 በመቶ እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት በዝቅተኛና በመካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያና በሌሎች ታዳጊ አገሮች የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ዜጎች በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ያለመስማት ችግር ገፈት ቀማሾች ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ከችግሩም በላይ የጆሮ ሕመምን ለማከም፣ ቀድሞ ለመከላከልና መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችል የተሟላ የሕክምና ተቋማት ባለመኖሩም ችግሩን ያገዝፈዋል፡፡ ይህም የደሃ አገሮችና ሕዝቦች ትልቅ ፈተና በመሆን እስከ ዛሬ የዘለቀ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ በአብዛኛው ተጋላጮች ሕፃናት ናቸው፡፡ ድርጅታችን ‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› ሕፃናት ገና ሲወለዱ ለመስማት ችግር ተጋላጭ እንዳይሆኑና አስቀድመው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ በአገራችን በሁለት መንግሥታዊና በሁለት የግል የጤና ተቋማት ላይ በሙከራ ደረጃ ምርመራ የማድረግ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ...

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...