Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርአንገብጋቢውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ አገርኛ ሞዴል

አንገብጋቢውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ አገርኛ ሞዴል

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ሁላችንንም የሚነካ የመሠረታዊ ፍላጎት አጀንዳ ነው፡፡ በተለይ አዲስ አበባን በመሰሉ ከፍተኛ የሕዝብ ክምችትና የተጠጋጋ ኑሮ ባለባቸው ከተሞች ደግሞ ቤት ማግኘት እጅግ ፈታኝና አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ነዋሪ ቤት ተከራይቶ የሚኖር ሲሆን፣ የቤት ኪራይ ጣሪያም እየጋሸበ ኑሮን ማክበዱ ተደጋግሞ የሚታይ ነው፡፡

ለዚህ ችግር መባባስ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የቤት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተለይ ከየክልሉም ሆነ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቤት የማግኘት ፍላጎታቸው እያየለ በመምጣቱ፣ ከነዋሪዎቹ ፍላጎት ጋር ተደማምሮ ጫና ማሳደሩ አልቀረም፡፡

- Advertisement -

ይህን ችግር ለማቃለል ቀደም ባለው ወቅት (የኢሕአዴግ መንግሥት) የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በድጎማ ጭምር ለማስተላለፍ ሞክሯል፡፡ እንዲሁም በመንግሥት፣ በነዋሪዎችና በማኅበራትም ሆነ በሪል ስቴት ኢንዱስትሪው በተሰማሩ ጥቂት ባለሀብቶች እየተሠሩ ያሉ ቤቶች ከቤት ፈላጊው ቁጥር ጋር አይጣጣሙም እንጂ ችግሩን ለማቃለል መርዳታቸው አልቀረም፡፡

መንግሥት ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ባለሀብቶችን እያስተባበረ ጭምር የደሃ ቤቶችን ሲያድስ፣ በመጠኑም ቢሆን ቤት ሲገነባ መታየቱም አልቀረም፡፡ ለወደፊትም የሚገነባውንም በዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ የመንግሥት ጥረት የሚደነቅና የሚደገፍ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን በታሰበው ልክ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት እጥረት ሊያቃልል አይችልም፡፡ ‹‹መንግሥት መቶ ሺሕ ቤቶችን ቢገነባ፣ ሌላ ሁለት መቶ ሺሕ ቤት ፈላጊዎች ወረፋ ይይዛሉ›› እንደሚባለው ነው፡፡ 

የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም ብሎም ነዋሪዎችን በየአቅማቸው የቤት ባለቤት ለማድረግ መንግሥት የግል ባለሀብቶች በግንባታ፣ በፋይናንስ አቅርቦትም ሆነ በብድርና መሰል ሥራዎች ላይ የሚሰማሩበትን መንገድ የማመቻቸቱ ሥራ ላይ ማተኮሩ ግን እንደ ብልኃት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በተለይ መሠረተ ልማት አሟልቶ በመሬት ማስተላለፍና አቅርቦት ላይ ያለውን ቢሮክራሲ አሳጥሮ፣ በግንባታ ግብዓትና ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን አቃሎ፣ እንደ ሞርጌጅና አመቻች ድርጅቶችን ፈቃድ ለመስጠት ቢተጋ ተግዳሮቱን ለማቃለል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋጋጥ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት የሪል ስቴት አልሚዎችን በፖሊሲ ጭምር በማበረታታት የጀመረው ጥረት ብቻ ሳይሆን ከባለሀብቶች፣ ከማኅበራትና ከቤት ባለቤቶች ጋር በተቀናጀና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በመሥራት የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል እያደረገ ያለው ጥረት በርካቶችን እያበረታታ መሆኑም በመስኩ በተሰማሩ ሙያተኞች ሲነገር ይደመጣል፡፡

ይህን ተከትሎ አዳዲስ ሐሳብና የችግር መፍቻ ሥልት ያላቸው ግለሰቦች ወደ ኢንዱስትሪው የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ለዕለቱ ኪሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽንን እንደ አብነት መጥቀስ እወዳለሁ፡፡ ይህ ድርጅት የዜጎችን ቤት የማግኘት ፍላጎትን ለማቃለል የሚረዳ የፋይናንስ አማራጭን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ገና ከመነሻው ዋነኛ ችግራችን የቤት መግዣ ፋይናንስ እንጂ የቤት እጥረት እንዳልሆነ በጥናት አረጋግጦ የተነሳ ነው፡፡

ድርጅቱ በአጭር የሥራ ጅማሮ ጊዜ ውስጥ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤት ፈላጊዎችን መዝግቧል፡፡ በመጀመሪያው ዙር አፈጻጸሙም 60 ባለዕድለኞችን በትንሽ ቁጠባ የቤት ባለቤት አድርጓል፡፡ የቁጠባ ሥርዓቱ በባንክ አሠራር፣ ዋስትናውም በኢንሹራንስ አጋርነት የታመነ እየተባለ በነዋሪዎችና በባለድርሻ አካላት ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥት አካላትም ሲበረታታ ሰማሁና ሒደቱን ልዳስሰው ወደድኩ፡፡

የኪሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ይልማ እንደሚያስረዱት፣ በውጭ አገር በኖሩባቸው ሦስት አሠርት ዓመታት ተሞክሮና በተሰማሩባቸው ልዩ ልዩ የቢዝነስና የሥራ ፈጠራ መስኮች እንደደረሱበት ግኝት ንግድም ሆነ ማንኛውም ቢዝነስ የማኅበረሰብን ችግር ማቃለል ካልቻለ ትርጉም የለውም፡፡ ይህን በመረዳት ወደ አገር ቤት መጥተው ለመሥራት ሲያስቡ፣ አንገብጋቢ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የበኩላቸውን አሻራ ለመወጣት በመነሳሳት ነበር፡፡

‹‹ከድርጅቱ መሥራች አባላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን ያልቻሉበትን ምክንያት በቅድሚያ በጥልቀት በማስጠናት ጀምረናል…›› የሚሉት አቶ ግሩም፣ በጥናቱ መሠረትም ዋነኛው ችግር የቤት እጥረት ሳይሆን የቤት መግዣ ገንዘብ እጥረት መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ይህን ችግር በልዩ አስተሳሳብና መንገድ ለመፍታት በመታሰቡ ነው የማኅበረሰቡን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ የሚረዳ ሞዴል ለመፍጠር የታቻለው ብለው፣ አካሄዱም በአገራችን ባህል ውስጥ ያሉት እንደ ማኅበር፣ ዕቁብ፣ ኪራይና በሌላው ዓለም የሚታወቀው የባንክ ብድር (Mortgage) በአንድ ላይ በማዋሀድ ኪ-የቤቶች የጋራ ፈንድ (Key – Common Housing Fund) (KEY CHF) ሞዴልን ለመፍጠር የተቻለው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ ግሩም ማብራሪያ ሐሳቡ ዕውን ሆኖ ድርጅቱ ከተመሠረተ አጭር ወራት ወዲህ 17 ሺሕ አነስተኛና መካካለኛ ገቢ ያላቸው ቤት ፈላጊ ዜጎች ተመዘግበዋል፡፡ በቀጣዮቹ ወራት እስከ 100 ሺሕ ቤት ፈላጊዎችን በመመዝገብ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀጣይ የቤት ባለቤት የሚሆኑ ዕድለኞችን የመለየት መርሐ ግብር ለማከናወን ታቅዷል፡፡ ይህን ዕቅድ ለማሳካትም ከማኅበራት፣ ከአጋር ተቋማትና ከግለሰቦች ጋር ተባብሮ ለመሥራት አስፈላጊው ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የተለያዩ ባንኮች፣ ቡና ኢንሹራንስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አቢጃታ ሻላ ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር፣ ትረስቴክ አይቲ ሶሉሽንስ፣ ስካይ ፕሮፕርቲስ ኪሃውሲንግ አብረዋቸው ከሚሠሩ ድርጅቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡

እነዚህን ሒደቶች ካስተዋልኩ በኋላ ነው የኪሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን ዋና ዋና ተግባራት ምንድናቸው ስል መፈተሸ የፈለግሁት፡፡ በእርግጥ ከተለያዩ መግለጫዎችና የአጋር አካላት ማብራሪያዎች መረዳት እንደተቻለው የኪ-ሲኤች ኤፍ ሞዴል በአገራችን የመጀመሪያና በተለይ የፋይናንስ እጥረት ላለባቸው ዜጎች ፍቱን የቤት ችግር መፍቻ መድኃኒት ሆኖ የቀረበ ነው፡፡

ይኸውም ገና እየተገነቡ ያሉ ቤቶችን ብቻ ሳይሆን ተገንብተው በገንዘብ እጥረት ነዋሪዎች ተረክበው ሊጠቀሙባቸው ያልቻሉ ቤቶችን፣ በተመጣጣኝ ቅድመ ክፍያና በአነስተኛ ወርኃዊ መዋጮ የግላቸው እንዲያደርጉ መላ የፈጠረና ዕቅድ ዘርግቶም በተግባር ቤት ማስረከብ የጀመረ መሆኑን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ግሩም አስረድተውኛል፡፡ በ83,145 ብር ቅድመ ክፍያና ከ2,000 ብር በሚጀምር ወርኃዊ ቁጠባ የቤት ባለቤት መሆን የሚያስችል ሞዴል መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በከተማችን ውስጥ የፋይናንስ እጥረት እንጂ የቤት እጥረት የለም በሚል ዕሳቤ ለኑሮ ምቹ የሆኑ መኖሪያ ቤቶችን ከአልሚዎች ላይ ለመጀመሪያዎቹ አራት ዙሮች በመግዛት፣ በዕቁብ መልክ በሚሰበሰብ ተዘዋዋሪ ፈንድ ቤቶችን በመግዛት ለባለዕድለኞች መስጠት ጀምሯል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ኪሃውሲንግ ዜጎች መኖሪያ ቤት የሚያገኙበትን መንገድ በመቀየር የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ባለአንድ፣ ባለሁለትና ባለሦስት መኝታ ቤቶች ከአልሚዎች ጋር በፈጸመው ስምምነት በማስገንባት ለቆጣቢዎች ተደራሽ እንደሚደርግም ነው ያረጋገጡት፡፡ እያንዳንዱ ተመዝጋቢ ለሚከፍለው የካፒታል ክፍያ ቡና ኢንሹራንስ የመልካም አፈጻጸም ዋስትና ሽፋን የሚሰጠውም ይሆናል፡፡

የኢንሹራንስ ሽፋኑን አስመልከተው ሐሳባቸውን ያካፈሉኝ የቡና ኢንሹራንስ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው አካሉ እንደሚሉት፣ የቡና ኢንሹራንስ ደንበኞች ለሚከፍሉት ክፍያ ዋስትና በመስጠት የእያንዳንዱን ቤት ፈላጊ ተመዝጋቢ ሥጋት ለመቀነስ ተችሏል፡፡

የኪሃውሲንግ ዕድለኞችን የመለየቱ ሥራም ቢሆን እጅግ ፍትሐዊና ግልጽ አካሄድን የተከተለ መሆኑን ነው ታዘቢዎች የሚናገሩት፡፡ በተለይ በሆቴል ዲሊኢፖል ታኅሳስ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. የተካሄደውን የመጀመሪያው ዙር የቤት ዕድለኞችን የመለየት ሥነ ሥርዓት የተከታተሉት አቶ ዳዊት በላይ የተባሉ ቁጠባ የጀመሩ ደንበኛ፣ ባለዕድለኞች ሲለዩ ከከተማ አስተዳዳሩ ቤቶች ልማት ቢሮና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች የመጡ ታዛቢዎች፣ የሪል ስቴት አልሚ ተወካዮች፣ ቆጣቢዎችና የሚዲያ ሰዎች በተገኙበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው ዕድለኞችን መለያ ሶፍትዌር መሆኑ፣ ቅሬታ የማይጥር ዓይን ገላጭ ጅምር እንዲታይ አድርጓል፡፡

በእርግጥም የመጀመሪያው ምዕራፍ 60 የቤት ዕድለኞች በዲጂታልና በግልጽ አሠራር በታገዝው ዕድለኞችን የመለየት መርሐ ግብር ተጠቃሚ በመሆናቸው፣ የመረጡት ቤት ተገዝቶላቸው፣ ውል ተዋውለው፣ የቤት ካርታ በስማቸው ተሰናድቶላቸው ዓይተናል የሚለው ወጣት ዳዊት፣ ከድርጅቱ ሪፖርት እንደተረዳው በ83 ሺሕ ብር የመመዝገቢያ መዋጮና በጥቂት ወራት የቁጠባ ተቀማጭ በአሁኑ ወቅት እስከ 13 ሚሊዮን ብር  የሚገመት ቤት ባለቤት መሆን የቻሉ ዕድለኞች ናቸው ብለዋል፡፡

ሌላው የኪሃውሲንግ መልካም ገጽታም ዕድለኞች ቤቱን የመግዛትም ሆነ አስፈላጊ የሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሥራ ሒደቶችን የሚያስፈጽምና ቤቱን ለባለዕድለኞች የሚያስረክብ ራሱን የቻለ የፕሮፐርቲ ማኔጅመንት አጋር ያለው መሆኑ ነው፡፡ ይህም ተጠቃሚዎች በቢሮክራሲው ውስጥ ሊያጋጥማቸው የሚችልን ውጣ ውረድ እንደሚቀንስ ይታመናል፡፡

የኪሃውሲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ጠቅለል አድርገው ሲያስረዱ ሞዴሉ የቤት ፈላጊውን ውጣ ውረድ ቀንሶ፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች በአንድ ጊዜ ገንዘብ ከፍለው ቤት መግዛት ስለማይችሉ ከ84 ሺሕ ብር ባልበለጠ የመመዝገቢያ ክፍያ፣ በ30 ዓመታት በተሠራጨ የአከፋፋል ዘዴ ጫናው ሳይሰማቸው ከፍለው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡ በ30 ዓመታት የሚከፍሉት ገንዘብም ከአሁኑ የቤት ዋጋ አንፃር ሲሰላ ከ65 በመቶ የሚበልጥ አይደለም፡፡

ኪሃውሲንግ በአሥር ዓመት 100 ሺሕ ዜጎችን የቤት ባለቤት አደርጋለሁ ያለ ሲሆን፣ በተመሠረተ በወራት ዕድሜ ውስጥ ለ60 ዕድለኞች ቤት ገዘቶ ማስረከቡን ብቻ ሳይሆን በሚቀጥሉት ወራትም ከፍተኛ የነዋሪዎች ፍላጎትና ሁኔታዎችን የማመቻቸቱ ሥራ እየተጠናከረ በመሄዱ ግቡን ለመፈጸም እንደሚችል እየተነገረም ይገኛል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ የቤት ማስተላለፍ ክፍል ባለሙያ፣ ‹‹የኪሃውሲንግ ሞዴል በአንድ በኩል አነስተኛ ገንዘብ ይዘው ቤት ልንገዛ አንችልም ብለው ተስፋ ቢስ ሆነው የሚኖሩ ሰዎችን በቁጠባ ባህልና በዕድል የቤት ባለቤት የሚያደርግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በመንግሥት አሠራር ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ቆጥበው ተጠቃሚ ካልሆኑ ሰዎች አንፃር ቢሮክራሲውን በሕጋዊ አሠራር አስፈጽሞ የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ሥርዓት ማካተቱ ተመራጭ ያደረገዋል፡፡ ገንዝብ የሚቆጠበው በባንክ ዝግ አካውንት፣ መተማመኛውም ኢንሹራንስ መሆኑም ተዓማኒነቱን ያሳያል…›› በማለት ነግረውኛል፡፡

ድርጅቱ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በዋና ዋና የክልል ከተሞች ውስጥም የአገልግሎት አድማሱን እንደሚያሰፋ ለመረዳ ተችሏል፡፡

ኪሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን (key-CHF) ሞዴልን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ከጠየቅኳቸው የሪል ስቴት አልሚዎች አንድ የግል አማካሪ፣ የቢዝነስ ሞዴሉ ከሥራ ፈጠራና ከተቀጣሪዎቹ ገቢ አንፃር ብቻ የሚታይ ሳይሆን፣ አዲስ አበባን በመሳሰሉ በከፍተኛ የቤት ኪራይና የኑሮ ውድነት ጫና ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የበዙባቸው ከተሞች ነዋሪዎች በአነስተኛ ቁጠባ ዋስትና ባለው የፋይናንስ አያያዝና በግልጽ ዕጣ አወጣጥ የቤት ባለቤት ለማድረግ በማስቻሉ ሊበረታታ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡

‹‹ቁጥራቸው በየዕለቱ እየጨመረ ካሉት የቤት ልማትና ሪል ስቴት ኩባንያዎች ጋር አጋርነት በመፍጠር የገበያ ትስስርን ለማሳለጥና የገበያ መተማማንን ለማሳደግ የሚረዳ ሞዴል እንደሆነ ይሰማኛል…›› ብለው፣ ኪሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ቤት ፈላጊዎች በባንክ ዕቁብ ጥለው የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ሥርዓት መሆኑንና እንደ ጀመረው ተግቶ በተግባር እያሳየ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...