Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ያገዘው የቤጂንግ ስምምነት

የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ያገዘው የቤጂንግ ስምምነት

ቀን:

በኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጥረቶች መካከልም በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ያደረገውና ኢትዮጵያ የተቀበለችው የቤጂንግ ስምምነት ወደ ተግባር መተርጎም አንዱ ነው፡፡

የቤጂንግ ስምምነት 12 የትኩረት መስኮች ያሉት ሲሆን፣ በዋናነትም ሴቶች ከጤና፣ ከትምህርትና ሥልጠና፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ከአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ከሰላም፣ ከሚዲያ ተሳትፎ፣ ከድህነት ቅነሳና ከአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ ነው፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበላይ አስተባባሪ ሆኖ የሚመራው የቤጂንግ ስምምነት፣ የአፈጻጸም ሪፖርት በየአምስት ዓመቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚቀርብበት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ መነሻ በማድረግ የተደረጉ ጥረቶችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ባካተተ መልኩ ስድስተኛውን ዙር አገራዊ ሪፖርት ለመላክ የቅድመ ዝግጅት ሥራን አጠናቃለች፡፡

ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሐ ግብር 30ኛ ዓመት አገር አቀፍ ሪፖርት ከየተቋማቱ ለተውጣጡ ስትሪንግና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ይፋ በተደረገበት ወቅት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀረፁና በትግበራ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አኅጉር አቀፍ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ መካከል የቤጂንግ መግለጫና መርሐ ግብር በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡  

የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሐ ግብር የሪፖርት ዝግጅት ኮሚቴ አስተባባሪና አማካሪ ማርታ ነመራ እንዳሉት፣ ስድስተኛው አገር አቀፍ የቤጂንግ ሪፖርት ከፍ ያለ ሥራ የተሠራበትና አብዛኛዎቹ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተሳተፉበት ነው፡፡

እንደ አማካሪዋ፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን የሥራ አጥነት ክፍተት ለማጥበብና እኩል የሥራ ዕድል ለመፍጠር ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠራው ሥራ፣ የሥራ ዕድሉ በፊት ከነበረው የሥርዓተ ፆታ ክፍተት አንፃር መሻሻሎችን አሳይቷል፡፡

ለዚህ ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችም 41 በመቶ በሴቶች መሸፈኑ የሚጠቀስ ነው፡፡ ሆኖም የሥራ ዕድል ፈጠራው ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር አሁንም ክፍተት አለው፡፡ ካለፉት ዓመታት ከነበረው 31 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ግን፣ ትልቅ ውጤት ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በአገር ውስጥ ከተፈጠሩ ሥራዎች 35 በመቶ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሲሆን፣ በውጭ አገር ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ደግሞ 98.6 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነውበታል፡፡

በፆታ የተለዩ በሚመስሉ ሥራዎች ዙሪያ ያለውን ባህል ለመቀየር የተሠራው ሥራ ብዙ መሻሻሎች ታይተውበታል ያሉት ማርታ፣ ለአብነትም በትራንስፖርቱ ዘርፍ በወንዶች ብቻ ተወስኖ የነበረውን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን በማሽከርከር ሥራ ሴቶች ተሳታፊ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በዘርፉ ውስጥ 460 ሴቶች እየተሳተፉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችም ሌላው ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለሴቶች የፈጠሩ ስለመሆናቸው የተናገሩት አማካሪዋ፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተቀጠሩት 23 ሺሕ ሠራተኞች መካከል 80 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን፣ ይህም ሴቶች ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች በመሳተፍ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ማገዙን አክለዋል፡፡

በሴክተር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በሥራ ዕድል ፈጠራ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ እየተሠራ መሆኑን በማስታወስም፣ በግብርና ሚኒስቴር በግብርናው ዘርፍ ለ2.7 ሚሊዮን ሴቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮባቸዋል ብለዋል፡፡

የሴቶችን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሴቶችን ተጠቃሚነት ከፍ በሚያደርግ መልኩ እየተተገበሩ፣ ሴቶች ወደ ቢዝነስ  እንዲመጡና የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ኑሮዋቸውን እንዲደጉሙ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አማካሪዋ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከፍተኛ የሥርዓተ ፆታ ክፍተት ከሚታይባቸው መስኮች አንዱ መደበኛ የባንክ አጠቃቀም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት 39.7 በመቶ ሴቶች መደበኛ ባንክ አካውንት አላቸው፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎችም፣ የሴቶችን የቤት ውስጥ ጫና በመቀነስና ሴቶች ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡

እንደ አማካሪዋ፣ በሴቶች ላይ ያለውን ድህነት ከመቀነስ አኳያ በተሠራው ሥራ ለውጥ ስለመምጣቱ፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው የድህነት ምጣኔም እየጠበበ መምጣቱ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በትምህርትና በጤና ዙሪያ ሴቶችን ማዕከል አድርገው እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ከባለፉት አምስት ዓመታት በተሻለ ለውጥ እያመጡ መሆኑን፣ የሴቶች የፓርላማ ተሳትፎ በአምስት ዓመቱ 41.5 በመቶ መድረሱንና ይህ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካም ስኬት መሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...