Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምአሜሪካ ተስፋ የጣለችበት የእስራኤል ጋዛ የሰላም ዕቅድ

አሜሪካ ተስፋ የጣለችበት የእስራኤል ጋዛ የሰላም ዕቅድ

ቀን:

በአሜሪካ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አንስቶ እስከ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ወትዋቾች እንዲሁም በተለያዩ አገሮች የከተሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በእስራኤልና በፍልስጤም ሐማስ በጋዛ ምድር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት መኮነን ከጀመሩ ወራት አስቆጥረዋል፡፡ አሜሪካ ደግሞ ከየትኛውም አገር በበለጠ የእስራኤል ወዳጅ በመሆኗ እስራኤል በጋዛ ከምትፈጽመው ጥቃት ጀርባ ስሟ ይነሳል፡፡

ወታደራዊ ቁሳቁስን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍ ከአሜሪካ የምታገኘው እስራኤል፣ በጥቅምት 2016 ዓ.ም. መግቢያ ድንገት በሐማስ ለዘነበባትና 1,200 ሰዎችን ለገደለባት የሮኬት ጥቃት እየወሰደች ባለው አፀፋ፣ በሐማስ የሚተዳደረው የፍልስጤም ጋዛ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሯል፡፡ ሕፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ከ35 ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል፡፡ አፀፋው ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን የተጠለሉባቸውን ካምፖችም አልማረም፡፡ ዕርዳታ ሰጪዎች ጭምር የእስራኤል አረር ሰለባ ሆነዋል፡፡ 

አሜሪካ ተስፋ የጣለችበት የእስራኤል ጋዛ የሰላም ዕቅድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ኢትማር ቤንጊቪር (ከግራ) ቤዛለል ስሞትሪች በአሜሪካ የተደገፈውን የተኩስ
አቁም ዕቅድ አጣጥለውታል (ኢፒኤ – ኢኤፍኢ)

 

- Advertisement -

በየወቅቱ በእስራኤል ወታደሮች ተፈጽመዋል የተባሉትን ጨምሮ፣ በርካታ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ዶክመንተሪዎች በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተላልፈዋል፡፡

ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ቀድሞውንም በቋፍ የነበሩትን እስራኤልና የፍልስጤም ጋዛ ለከፋ ጦርነት መዳረጉና በጋዛ የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አሳሳቢ መሆን፣ ኃያላን አገሮች፣ የዓረቡ ዓለምና ሌሎችም እስራኤል ጦርነት እንድታቆምና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲመጣ እንዲወተውቱ አድርጓል፡፡ ሆኖም ለተወሰኑ ቀናት ዕርዳታ ለማስገባት በሚል ከተደረገ ተኩስ አቁም በስተቀር፣ በሥፍራው ሰላም ተናፋቂ ሆኗል፡፡ እስራኤልም ዳግም የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ ዘንድ የቀረበላትን ጥያቄ ‹‹በጋዛ ዕቅዴን ሳላሳካ አላደርገውም፤›› ስትል ገልጻለች፡፡

እስራኤል፣ በፍልስጤም ጋዛን የሚያስተዳድረው ሐማስ ዳግም የእስራኤል ሥጋት ወደማይሆንት ማድረስ የዚህ ጦርነት ዋና ግብ ነው ትላለች፡፡ ሥጋትነቱን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ ጋዛን የማስተዳደር አቅሙን ማሽመድመድና የታገቱ ዜጎቿን ማስለቀቅም ዓላማዋ ነው፡፡

ይህንን እስካላሳካች ደግሞ የትኛውንም ዓይነት ቋሚ ተኩስ አቁም ስምምነት እንደማትገባ መግለጿን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረጉትን ባለሦስት ደረጃ የሰላም ስምምነት ሐሳብ ተከትሎ አቋማቸውን ያሳወቁት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ፣ በጋዛ ቋሚ ተኩስ አቁም የሚኖረው ‹‹ሐማስ ሲወድም ብቻ›› መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እስራኤልንና ሐማስን ለማስማማት የቀረበው ዕቅድ ምንድነው?

ፕሬዚዳንት ባይደን ለእስራኤል ጋዛ ጦርነት መፍትሔ ያመጣል ብለው ተስፋ የጣሉበት ሐሳብ እስራኤልና ጋዛ ከተስማሙበት በሦስት ደረጃዎች የሚተገበር ይሆናል፡፡

የመጀመርያው የስድስት ሳምንታት የተኩስ አቁም ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ በጋዛ በርካታ ነዋሪዎች ከሚኖሩባቸው መንደሮች የእስራኤል ወታደሮች ይወጣሉ፣ አረጋውያንና ሴቶችን ጨምሮ በሐማስ የታገቱ የእስራኤል ዜጎች በመቶዎች ከሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞች ጋር ልውውጥ ይደረጋል፣ ሰላማዊ የጋዛ ነዋሪዎች ወደቀዬአቸው የሚመለሱ ሲሆን፣ ሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ 600 መኪኖች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

እንደ ባይደን፣ በሁለተኛነት የተቀመጠው የመፍትሔ ሐሳብ እስራኤልና ሐማስ ጦርነትን በዘላቂነት ለማቆም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረው ከስምምነት መድረስ ሲሆን፣ ስምምነቱ እየተካሄደ ባለበት ሁሉ የተኩስ አቁሙ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በሦስተኛነት፣ ቋሚ ተኩስ አቁም ስምምነት የሚከተል ይሆናል፡፡ በዚህ ደረጃ በጋዛ የወደሙ 60 በመቶ ክሊኒኮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የሃይማኖት ሕንፃዎች ዳግም የሚገነቡበት ይሆናል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ያቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳብ ተከትሎ መግለጫ የሰጠው ሐማስ፣ ዕቅዱን በአዎንታዊ ጎኑ እንደሚያየው ቢገልጽም፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠቡን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

አንዳንድ የእስራኤል ፖለቲከኖች፣ በጋዛ ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው እስራኤላውያን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕቅዱን በአዎንታዊ የተቀበሉ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ የጦር ካቢኔ አባል ቤኒ ጋንትዝ ናታንያሁና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት በቀጣይ ለሚኖሩ ሒደቶች እንዲመክሩበት ጠይቀዋል፡፡

የካቢኔ አባሉ ጋንትዝ፣ በጋዛ ያለው ጦርነት ካበቃ በኋላ በሚኖረው የድህረ ጦርነት ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ ዕቅድ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውና ይህ ካልቀረበ ከካቢኔ አባልነታቸው እንደሚለቁ ቀድመው አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በእስራኤል የሽ አቲድ የተባለውን ተቃዋሚ ፓርቲ የሚመሩት ያር ላፒድ በበኩላቸው ዕቅዱን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ዕቅዱን የተቀበሉት ሲሆን፣ ጀርመንና እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ የእስራኤል አጋሮች ዕቅዱን እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል፡፡

ሁለት የቀኝ ዘመም የእስራኤል ሚኒስትሮች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ በፕሬዚዳንት ባይደን የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት ከተቀበሉ መንግሥት እንደሚሽመደመድ አሳስበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ቢዛለል ስሞትሪችና የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትሩ ኢትማር ቤን ጊቪር፣ ሐማስ ከመውደሙ በፊት ማንኛውንም ዓይነት ስምምነት እንደማይቀበሉም አስታውቀዋል፡፡

እስራኤል የሰላም ስምምነቱን ልትቀበል እንደምትችል ተስፋ የጣለችው አሜሪካ፣ ለዕቅዱ መደናቀፍ ዋናው ምክንያት ሐማስ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ በዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ከርኪ እንደሚሉትም፣ ሐማስ በዕቅዱ ከተስማማ እስራኤል ዕቅዱን ልትቀበል እንደምትችል የአሜሪካ ተስፋ ነው፡፡  

ቤተሰቦቻቸው በጋዛ የታገቱ እስራኤላውያን ደግሞ ፕሬዚዳንት ባይደን ይፋ ያደረጉትን የተኩስ አቁም ዕቅድ የእስራኤል መንግሥት አባላት በሙሉ እንዲቀበሉት በሰላማዊ ሠልፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ እንደቀጠለ መሆኑን የገለጸው ዘገባው፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከኳታር፣ ከግብፅና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ፣ ሚኒስትሮቹ ሐማስ የተኩስ አቁሙን እንዲስማማ እንዲያግባቡ ጠይቀዋል ብሏል፡፡  ሐማስ ጊዜ ሳይወስድ በዕቅዱ እንዲስማማ፣ የዕቅዱን ጠቀሜታ ከፍልስጤማውያን ጋር እንዲወያይበት መጠየቃቸውንም አክሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...