Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ምሽት በረንዳ ላይ

ትኩስ ፅሁፎች

አገር ምድሩ መሽቶ

ሌቱ ምጣድ ሆኖ፥ በኮከብ ተሟሽቶ

የጎዳናው መብራት፥ ጨለማው ላይ ሲገን

ከመስኮት አምልጦ፥ የወጣ ወጋንን

ሳር ቅጠሉን ሲያሳይ

አጥብቄ ስፈልግ፥ የዕለት ያይኔን ሲሳይ

የሌት ዓይኔን ሲሳይ

በኩርማን ገላዋ፤ እራፊ ደርባ

የራሷ ሻጭ ሆና፤ ለሸመታ ቀርባ

በሌት ይፋ ሆና፥ በቀን ልትደበቅ

ያልቀጠረችውን፥ የምትጠባበቅ

አንዲት ሴት እያየሁ

አሰላስላለሁ፤

“አብረዋት ያደጉ፤ ብጤዎቿ ሁሉ

በድሜና በውበት እሷን የሚያክሉ

ተድረው እንደ ሴት፥ ተከብረው እንደ ሰው

የባሎቻቸውን ደረት ተንተርሰው

ፍቅር ሲያጣጥሙ

ወይ በንቅልፍ ሲሰጥሙ

ይች ወገን አልባ

የሌሊት አበባ

በቀትር ተኝታ ለውድቅት የነቃች

የቱን ፍሬ በልታ ለዚህ ፍዳ በቃች?”

እያልሁ አስባለሁ፥

ደሞ ከደጃፌ ትንሽ ማዶ ርቆ

የመሸበት ለማኝ፤ መንገዱ ዳር ወድቆ

በግልጥ ይታየኛል

“ረፍትን ላክልኝ፥ ወይ እንጎቻህን ጣል

በራብ እና በንቅልፍ ሰው እንዴት ይቀጣል”

የሚል ይመስለኛል፤

በረንዳ ላይ ቆሜ፥ በሌሊት ስምሪት

ከመስኮት በወጣ፥ የብርሃን ቅሪት

አይቼ ማልዘልቀው

ያገሬ ጎዳና የት ላይ ነው የሚያልቀው

መከራና ውበት የሚያፈራርቀው::

– በዕውቀቱ ሥዩም

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች