Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትምሩፅ ይፍጠርን ያፈራው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያስገነባውን ዘመናዊ ትራክ ለፓሪስ ኦሊምፒክ መዘጋጃ...

ምሩፅ ይፍጠርን ያፈራው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያስገነባውን ዘመናዊ ትራክ ለፓሪስ ኦሊምፒክ መዘጋጃ ክፍት አደረገ

ቀን:

ከአዲስ አበባ 45 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ቢሾፍቱ በቀድሞ ደብረ ዘይት ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ከተቋቋመበት ዋነኛ ተግባር ጎን ለጎን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች አገርን ወክለው በድል የደመቁ አትሌቶችን በንብ ክለቡ አማካይነት በማፍራት ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

 የኢትዮጵያ አየር ኃይል አሁን ደግሞ በተለይም በአትሌቲክሱ በጎዳናና በጫካ ከሚደረጉ ልምምዶች በተጨማሪ ለመካከለኛና ለረዥም ርቀት ተወዳዳሪዎች እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትራክ (መም) በማስገንባት ሁሉን አቀፍ በሆነ ቁመና ላይ እንደሚገኝም በተግባር አረጋግጧል፡፡

‹‹ማርሽ ቀያሪው›› በሚል ልዩ መጠሪያ የሚታወቀው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን ያፈራው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ያስገነባውን ትራክ በትውልድ ቅብብሎሽ ታሪክ በመሥራት ለሚታወቁት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም ለፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ በፈለጉት ጊዜና ወቅት እንዲዘጋጁበት ባለፈው ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሠራዊቱ ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አማካይነት ይሁንታ ሰጥቷል፡፡

- Advertisement -

በዕለቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶችና የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ብሔራዊ አትሌቶች በተገኙበት፣ በአዲሱ ትራክ ላይ ሁሉም አትሌቶች ልምምድ አድርገዋል፡፡

ከጎዳናና ከጫካ ልምምድ በተጨማሪ በማዘውተሪያ ሥፍራ እጥረት ምክንያት የትራክ ልምምድ ለማድረግ በከፍተኛ ችግር ላይ የቆዩት ብሔራዊ አትሌቶች በትራኩ ጥራትና በተቋሙ ቁርጠኝነት መደሰታቸውን ጭምር ተናግረዋል፡፡

በአራት ዓመታት አንድ ጊዜ በታላላቅ አገሮች በተመረጡ ከተሞች አስተናጋጅነት ሲከናወን የቆየው ኦሊምፒክ፣ ተረኛዋ ፓሪስ ዝግጅቷን ከ50 ቀናት በኋላ በይፋ ታስጀምራለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኦሊምፒክ አድማቂዎች አሁን ላይ ዝግጅቶቻቸውን ከሞላ ጎደል በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸው፣ በተለይም በአትሌቲክሱ የኢትዮጵያውያን ብርቱ ተፎካካሪ በሆነችው ኬንያ የኦሊምፒክ አመራሮች የአገሪቱ ፓርላማ ለኦሊምፒክ ልዑካኑ ሊያደርግ የሚገባውን ሁሉ እንዲያደርግ ዕቅዶቻቸውን በይፋ ሲያቀርቡ መታየታቸው ተዘግቧል፡፡

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምን እያደረጉ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ይደመጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያስገነባውን ትራክ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ልምምድ ፈቃድ በሰጠበት ዕለት የሁለቱ ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፣ መንግሥት ከበጀት ዝግጅት ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መዘጋጀቱ ቃል እንደተገባላቸው ጭምር ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከልምምድ መርሐ ግብሩ በኋላ፣ አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ በተለይም በኦሊምፒክ ተሳትፎው ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ ዋና አዛዡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም የትግራይ አትሌቶች፣ የፌደራል መንግሥትና የክልሉ መንግሥት ግጭት ላይ በነበሩበት ወቅት በተደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለአገራቸውና ለራሳቸው ያስመዘገቧቸው ድሎች ለእሳቸው ሁሌም የልብ ኩራት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ የኢትዮጵያን ስምና ሰንደቅ በዓለም አደባባይ ከፍ እንዲል ያደረጉ በርካታ ጀግኖች መኖራቸው እንደተጠበቀ ቢሆንም፣ በዚያ ሁሉ ወጀብና አለመረጋጋት ውስጥ ሆነው ያንን አኩሪ ድል ያስመዘገቡት የትግራይ አትሌቶች እሳቸው ለሚመሩት ተቋም ከጀግናም በላይ ጀግና ስለመሆናቸው ጭምር ተናግረዋል፡፡

የሚመሩት ተቋም ‹‹ሰማዩ የእኛ ነው›› በሚለው መሪ ቃል የሚታወቀውን ያህል አትሌቶችም በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ በሚሳተፉባቸው የውድድር ዓይነቶች ‹ሜዳሊያው የእኛ ነው›› በሚል ሕዝባቸውና አገራቸውን እንደሚያኮሩ የተናገሩት ዋና አዛዡ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ያስገነባውን ዘመናዊ ትራክ አትሌቶቹ በፈለጉት ጊዜ እና ወቅት እንዲጠቀሙበት ቃል ገብተውላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዚህ ልክ የመሮጪያ ትራኩን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃው በጠበቀ መልኩ ስታዲየሙን ለማስገንባት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ብቻ እንዳስፈለገው የተናገሩት የአየር ኃይል ምህንድስና መምርያ አስተባባሪ ሌተና ኮሎኔል ያሬድ ንጉሤ ናቸው፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ የተጀመረው መስከረም 2016 ሲሆን፣ ስታዲየሙ በአጠቃላይ በአትሌቲክሱ የሜዳ ተግባራቱን ጨምሮ ዘመናዊ ትራክ፣ እግር ኳስ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ እጅ ኳስና ሌሎችም ስፖርቶች የሚዘወተርባቸው መሠረተ ልማቶችን የያዘ ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

እንደ አስተባባሪ መሀንዲሱ ከሆነ፣ ተቋሙ ለስታዲየሙ ግንባታ በግብዓትነት የተጠቀመው በአብዛኛው በራሱ በተቋሙ ባለሙያዎች ዕውቀትና አቅም በተዘጋጁ ቁሳቁሶች እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ከስፖርት መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ ትኩረት ባለመስጠታቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳና ትችት ሲቀርብባቸው የሚደመጡ በርካታ ብሔራዊ ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ተቋማቱ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ተሞክሮ በመውሰድ ከምክንያት ይልቅ የውስጥ አቅምን በመጠቀም በተለይም ከማዘውተሪያ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ክፍተቶች የመፍትሔው አካል ሊሆኑ እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎች አጋጥመውናል፡፡

ከልምምድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ በኋላ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሸነር ደራርቱ ቱሉ፣ ከግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በኋላ ማንኛውም አትሌቶች ለግል ውድድር በሚል ከውጭ ጉዞ እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡

አትሌቶቹን በመወከል አስተያየቱን የሰጠው የዓለም አገር አቋራጭን ጨምሮ በተለያዩ የኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ከሁለት አሠርታት በላይ የዓለም ክብረ ወሰኖችን በማስመዝገብና የወርቅ ሜዳሊያዎች በማግኘት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ በፓሪስ ኦሊምፒክ ካለው ልምድ አንፃር ከአትሌቶቹ ጋር በመቀናጀት ውጤት ለማምጣት በመግባባት እንደሚሠራ ተናግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...