Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ሠርክ አዲስ

ትኩስ ፅሁፎች

ሥራን ሠርክ አዲስ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የመስክ ጉብኝት ነው። ከለመዱት አካባቢ ራቅ የማለት ነገር ከሚፈጥረው የመንፈስ መታደስ ስሜት በተጨማሪ መረጃን ከምንጩ ለማግኘት ዕድል ይሰጣል። የሥራን ፍሬም ለማየት የተሻለ መንገድ ነው። የማይረሳ መረጃም ይተዋል። የእኔን ጥቂት ላካፍል። ወደ ሰሜን ሄድን፣ ሥራዎችን አየን፣ አርሶ አደሮቹ ያገኙትን ዕውቀት መሠረት አድርገው ያከሉትን ፈጠራም ጎበኘን፣ ተጋበዝን፣ ቤት ገብተን ያላቸውን አበሉን አጠጡንም። ይህ ግን አላረካቸውም። በደረቅ ወራት ነበረና የሄድንባቸው የሚያስቋጥሩን ነገር ስላልነበራቸው ተጨንቀዋል።

በበላን በጠጣነው ጠግበን፣ ባየነው ተደስተንና አመሥግነን የግቢያቸውን መንገድ እንዳጋመስን መልሰው ጠሩን። አባወርየው ግቢው ውስጥ ያለችው የወይራ ዛፍ ላይ በፍጥነት ወጣና ቆረጥ ቆረጥ አድርጎ ዝንጣፊ ይዞልን መጣ። ‹‹ይቅርታ የምንሰጣችሁ ምንም ስለሌለን ነው፣ ባዶ እጃችሁን አትሂዱ። ለመፋቅያ ትሆናችኋለች›› አለን በትህትና። ቃላት አቅም ስላልነበራቸው እጅ ነስተን ተቀብለን ወጣን።

ወደ ደቡብ ሄድን። ሥራ ስንጨርስ ቆጮ እንግዛ ብለን ወደ ተጠቆምነው ቤት ጎራ አልን። ሲጋገር ደረስን፣ ተጋበዝን። ከመካከላችን የቆጮውን መጣፈጥና የሾፌሩ ከጣፋጩ ማዕድ መለየት ቅር ያሰኘው ባልደረባችን ሊጠራው ወጣ። በዚህ መሀል ቀይ ዳጣ ተጨመረልን። የእሱን እግር ጠብቀን ቆጮ በስልስ በመብላታችን እየገሰጸን ከ‹‹ስልሱ›› ዛቅ አድርጎ ጎረሰ። ሁላችንም ‹‹በሥራ›› ተጠምደን ስለነበረ ያለ ሐሳብ የጎረሰው ዳጣ ያደረሰበትን ቃጠሎ ቶሎ ያስተዋለለት አልነበረም። ድምጹ ስለጠፋብን ቀና ብለን ስናየው አይሆኑ ሆኗል።

ወደ ምሥራቅ የሥራቸውን ውጤት የልፋታቸውን ዋጋ ካሳዩን፣ የማያልቁ ጥያቄዎቻችንን ከመለሱና አካባቢያቸው ያፈራውን ጣፋጭና አስደሳች ነገር በብላሽ ከጋበዙን፣ ገበያ ወስደው ምርጥ ምርጥ ዕቃዎች ካጋዙንና ከገዙልን በኋላ የከተሞቻቸውን ብርቅዬ ቦታዎች ሁሉ አስጎብኝተው ሰው አድርገው ይመልሱናል። የእኛ ነገር ደግሞ ሁሌም ሁሉ ነገር አዲስ ይሆንብናል። ባስጎበኙን ቁጥር አዲስ ነገር እናገኛለን።

ወደ ምዕራብ በጾም ወቅት ነበር የሄድነው። ከፕሮጀክቱ ያገኘቻትን ዕውቀት፣ እንዴት ወደ ተግባር ቀይራ ኑሮዋን እንዳሻሻለች አሳይታ፣ አስረድታና አስደስታን ከጨረሰች በኋላ ‹‹የማትጾሙ ግቡና ወተት ጠጡ›› ብላ ጋበዘችን። የማይጠጣ ግቢዋን መጎብኘት ያዘ። ባዷችንን ከቤቷ ልንሄድ መሆኑ ሰላም አልሰጣትም። ሁለት ሦስቴ መጣች። እንዳትጨነቅ ብናግባባትም አልሆነም። ሐሳቧን ለማስቀየር ስለ ግቢዋ ንጽህና፣ ስለ ተክሎቹ… ጨዋታ ጀመርን። በደስታና በልበ ሙሉነት ጓሮም እንዳላት ነገረችንና ማስጎብኘት ጀመረች።

የጎመኑን ቅጠል ስፋት አይተን ስንደነቅ ካልወሰዳችሁ አለች። ብዙ ቀን መስክ እንደምንቆይ ነግረን አስጣልን። ኮሰረቱን፣ በሶ ብላውን ሌላውንም እያየን ጉብዝናዋን ስናደንቅ ለቅመም የሚሆኑትን በሙሉ ካልወሰዳችሁ አለች። ከዚህ በላይ እንቢ ማለት ጨዋነት አልመሰለኝም፡፡ ነጭ ሽንኩርትን ጨምሮ አንድ አምስት ዓይነት ቅመም መሆን የሚችሉ ነገሮችን አሸክማ ላከችኝ። ‹‹ብዙ ቀን ነው የምንቆየው ምን ልታደርጊው ነው?›› ብለው ወንዶቹ አጣደፉኝ። ‹‹ቅመም›› የኮሰረቱን አንድ ግንድ ግን የደግነት ማስታወሻ ነውና እንዳይደርቅ ተንካባክቤ አቆይቼ ተከልኩት፣ ጸደቀ። ደግነት ይለምልም!

  • መሠረት ከበደ በሊንክደን ገጿ እንደከተበችው
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች