Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየተሰረዘ የፖለቲካ ፓርቲን እንደገና ሕጋዊ አድርጎ እንዲመዘግብ ምርጫ ቦርድን የሚያስገድድ ሕግ ፀደቀ 

የተሰረዘ የፖለቲካ ፓርቲን እንደገና ሕጋዊ አድርጎ እንዲመዘግብ ምርጫ ቦርድን የሚያስገድድ ሕግ ፀደቀ 

ቀን:

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕጋዊነት መዝግቦት ሲንቀሳቀስ የነበረን የፖለቲካ ፓርቲ፣ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመፃ ተግባር፣ ከሙስና ጋር ተያያዥነት ባላቸው የወንጀልና የማጭበርበር ድርጊቶች ሲፈጽም ከተገኘ እንዲሰረዝ በአዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 98 (1ረ) ላይ ተደንግጎ የነበረ ቢሆንም ትናንት ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በፀደቀው የማሻሻያ አዋጅ፣ በተጠቀሱት ድርጊቶች ላይ የነበረውን ተሳትፎን ማቆሙንና ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ሊመዘገብ እንደሚችል የሚያስገድደውን አዋጅ ፓርላማው አፀደቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው 30ኛው መደበኛ ስብሰባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ተወያይቶ የላከለትን የኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ ላይ  ተወያይቶ በአንድ ተዓቅቦ፣ በሁለት ተቃውሞና በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

ለፓርላማ የተላከውና የፀደቀው ማሻሻያ አዋጅ ላይ እንደተብራራው ከሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጭ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ሕጋዊ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት በነባሩ አዋጅ ባለመኖሩ በአዲስ መልክት ማካተት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

በማሻሻያ አዋጁ እንደተጠቀሰው አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነና ይህንን ማቆሙንና ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለማንቀሳቀስ መስማማቱን ‹‹በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ›› የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል፡፡

በዚህ መሠረት በሥራውና በሕጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ መነሻ በማድረግ ማመልከቻውና አባሪ ሰነዶችን በቀረበ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ቦርዱ ምዝገባውን እንዲፈጽም ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ምርጫ ቦርድ የቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ የማድረግ ምርጫ እንዳልተቀመጠ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ቦርዱ አመልካቹን በቀጥታ ያለምንም ማጣራት የመዘገበው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግበት ሥርዓት ስለመደንገጉ ተብራርቷል፡፡ በዚህም ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲው ላይ ልዩ ክትትል የሚያደርገው ለሁለት ዓመታት ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

ቦርዱ የመዘገበው ፓርቲ በቀሪዎቹ ጊዜያት ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ ክትትል እንዲያደርግ የተደነገገ ሲሆን፣ ፓርቲው ቦርዱ በተሰጠው ግብረ መልስ መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ካላስተካከለና ጉልህ የሕግ ጥሰት የፈጸመ ከሆነ፣ ቦርዱ የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፓርቲውን ምዝገባ የመሰረዝ ሥልጣን እንዳለው ተደንግጓል፡፡ 

በዚህ መሠረት እንደ ፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ የሚያመለክት አንድ የፖለቲካ ቡድን ከምዝገባ ማመልከቻ በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም የፖለቲካ ፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ የፓርቲው ኃላፊዎች ስምና አዳራሽ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በኃላፊነት ለመሥራት መስማማታቸውን የሚያስረዳ በፊርማቸው የተረጋገጠ ሰነድ እንዲያቀርቡ ይጠይቃል፡፡

ለፓርላማ የቀረበው ረቀቂ እምብዛም ባልተለመደ መልኩ አፈ ጉባዔው በአንድ ንባብ እንዲፀድቅ ጠይቀው አጠር ያለ ወይይት ተደርጎበታል፡፡ በማሻሻያው ላይ ጥያቄ ካቀረቡ ስምንት የምክር ቤት አባላት አብዛኛዎቹ የድጋፍ ድምፅ አሰምተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በማሻሻያው ‹‹በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ›› በሚል የቀረበው ድንጋጌ ይህ የመንግሥት አካል ማነው? የሚል ጥያቄ ከአባላቱ ተነስቷል፡፡ የመንግሥት አካል የሚለው አሻሚ ነው በግልጽ መቀመጥ አለበት ሲሉ አንድ የምክር ቤቱ አባል ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴሩ በሰጡት ምላሽ የመጀመርያ ረቂቁ ላይ ለአንድ ተቋም የማረጋገጥ ተግባር እንዲሰጥ በሚል ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ የተነሳው ጉዳይና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል በሚል ተብሎ የቀረበው ከሕጋዊነት ጋር የመጣ ብቻ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቤንሻንጉል፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልልም በተለያየ መንገድ ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር ንግግርና ምክክር ለማድረግ በተለያየ ጊዜ መሞከሩን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ የጥረት ጊዜያት ውስጥ የተሳተፉ አካላት፣ የተሻለ መረጃ ያላቸው፣ መስማማታቸውንና በስምምነቱ መሠረት ደግሞ ይህንን እንቅስቃሴ አቁመው መምጣታቸውን ለማረጋገጥ ተገቢነት ያለው አካል እንደየግጭቱ ዓውድ፣ እንደ ንግግሩ አካሄድ ይህ ተገቢነት ያለው የመንግሥት አካል የተለያየ ሊሆን ስለሚችል ነው ብለዋል፡፡ በየጉዳዩ ሁኔታ አግባብነት ያለው አካል ማረጋገጫ እንዲሰጥ ታስቦ የተቀመጠ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ አቶ ሙሉቀን አሰፋ በሰጡት አስተያየት አዋጁ በዋናነት የሚሻሻለው በጦርነት ወይም በጠመንጃ ሲዋጉ የነበሩ አካላትን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማምጣት ቢሆንም በዋናነት ግን ለሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሚያገለግል ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ‹‹ሕወሓት ዛሬም ጦርነት ላይ ነው፣ ምናልባት መሀል አገር አዲስ አበባ ስለተቀመጥን ላይመስለን ይችላል፣ ከዚያ ውጭ ግን ይህ ኃይል ዛሬም በአፋርም በአማራም ጦርነት ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሕወሓት ከመጀመርያው ጀምሮ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን የመራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ነገር ግን ይህ ቡድን አሁንም ያው ነው፣ እንደዚህ ያለውን ቡድን ደግሞ ማጥፋት እንጂ እንደገና በሰላማዊ መንገድ ተመዝግቦ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ ከአፋርና አማራ ሕዝብ መጣላት ነው፣ ምክር ቤቱ አዋጁን እንዳያያፀድቀው፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካዩ አብርሃም በርታ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የፌዴራል ሥርዓቱን አክብረው የአገርን ሉዓላዊነት ጠብቀው የበኩላቸውን አሻራ የሚያሳርፉበት አግባብ የሚኖር ከሆነ ይህን አዋጅ ማሻሻል ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሽብርተኝነት የተፈረጁ ፓርቲዎች ቀድሞ የነበራቸው ስም ጥሩ ባለመሆኑ በርካታ ችግሮችን የፈጠሩ በመሆኑ አካሄዱ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገውና ከተቻለ የርዕዮት ዓለም ለውጥ አድርገው እንዲመጡ ግፊት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

 የፍትሕ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ አዋጁ ምሕረት መስጠት፣ ይቅርታ ማድረግ ወይም ተጠያቂነትን ማስቀረት አለመሆኑን ጠቅሰው እነዚህ አካላት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ቢመለሱም በግጭት ዓውድ ውስጥ ለፈጸሟቸው ጉልህ የሕግ ጥሰቶች እንዴት ተጠያቂ ይሆናሉ? የሚለው በቅርቡ በፀደቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሕግ ድንጋጌ መሠረት ይሆናል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...