Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበግጭት ወቅት ለሚከሰቱ የመሬት ዋስትና ሥጋቶች የይዞታ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ተነገረ

በግጭት ወቅት ለሚከሰቱ የመሬት ዋስትና ሥጋቶች የይዞታ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ተነገረ

ቀን:

በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተው ጦርነት በግጭት ወቅት ዜጎች የመሬት ይዞታቸውን ማስከበር የሚያስችላቸውና ከመሬት ጋር ለተያያዙ ኢንቨስትመንቶችም አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ የመሬት ፖሊሲ መቅረፅን አስፈላጊ እንዳደረገው አንድ ጥናት ጠቆመ። 

ዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት (International Food Policy Research Institute) በተባለ ተቋም ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው ጥናት፣ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ በሚገኙ 5,000 የመሬት ባለቤት ቤተሰቦችን እንደ ናሙና በመውሰድ ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በ2015 ዓ.ም. እና በተያዘው ዓመት ወደ 3,330 የሚጠጉ የቤት ባለቤቶችን በተጨማሪነት በማካተት የተከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡  

ግጭት፣ የመሬት ይዞታ ዋስትናና ከመሬት ጋር የተያያዙ ኢንቨስትመንቶች (Armed Conflict, Tenure Security and Land Related Investments) የሚል ርዕስ ያለው ይህ ጥናት ለግጭቱ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች የደረሰባቸውን ጉዳት በትክክል ለመለካት፣ ውጊያ በተካሄደባቸው አካባቢዎች 20 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ክብ (ራዲየስ) ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችንና ኢንቨስትመንቶችን ጉዳይ ማካተቱን የጥናቱ አቅራቢ አቶ ኃይለ ማርያም አያሌው ገልጸዋል። 

- Advertisement -

በጥናቱ በይዞታ ዋስትናና ኢንቨስትመንቶች ላይ የደረሱ ጉዳቶች በሦስት ክፍል ተለይተው ቀርበዋል። 

ከእነዚህ ተቀዳሚው ግጭት በዜጎች የመሬት ይዞታ ዋስትና ላይ ያደረሰው ጉዳት ሲሆን፣ በዚህ ውስጥ ግልጽ የሆነ የይዞታ መስመሮች መጣስና አለመጣስ፣ ይዞታን የተመለከቱ ክርክሮች መጠንና ዜጎች የመሬት ይዞታቸውን እንደማያጡ ምን ያህል መተማመን እንዳላቸው ተዳሷል። 

የዚህ የጥናቱ ክፍል ውጤት እንዳመላከተው፣ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የመሬት ባለይዞታዎች ከፍተኛ ይዞታቸውን የማጣት ሥጋት አለባቸው ተብሏል። መሬታቸው ግልጽ በሆነ መስመር ወሰኑ ተለይቶ ባይከበርም ሪፖርት እንደማያደርጉ፣ በይዞታ ክርክሮች ወቅትም ባለመብትነታቸውን ለማረጋገጥ በቂ የዓይን እማኞች ለማቅረብ እንደሚቸገሩ፣ እንዲሁም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት መንግሥት ለልማት ይፈለጋል በሚል የመሬት ይዞታቸውን ሊወስድባቸው እንደሚችል ከፍተኛ ሥጋት እንዳለባቸው መግለጻቸውም በጥናቱ ተካቷል። 

ሁለተኛው የጥናቱ ግኝት ከመሬት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የተመለከተ ሲሆን፣ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች 4,018 ከመሬት ጋር የተያያዙ ክርክሮች መመልከቱን ጠቅሷል። 

በዚህ የግኝቱ ክፍል እንደተገለጸው፣ ለእርሻ የሚፈለጉ ግብዓቶች ስርቆት በስፋት ታይቷል። ስርቆቱ ከግብዓት ባሻገር በሰብሎችና በቁም ከብቶችም ላይ ተስፋፍቶ መገኘቱም ተብራርቷል። 

በሦስተኝነት የቀረበው ከመሬት ጋር የተያያዙና የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንቶችን የተመለከተው ግኝት ነው። በዚህ ሥር ውጊያ በተካሄደባቸው አካባቢዎች 20 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የሚኖሩ ባለይዞታዎች የአፈር ጥበቃ ሥራዎች፣ የችግኝ ተከላዎች፣ እንደ ፍግና ብስባሽ ያሉ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎችን የማምረት ሥራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰው መገኘታቸው ተጠቁሟል። 

የጥናቱ መደምደሚያ ግጭቶች በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ዋስትናን፣ እንዲሁም ከመሬት ጋር የተያያዙ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንቶችን እንዲቀንሱ ማድረጉን ጠቅሷል። የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ የሌላቸው ዜጎችና በእማወራ የሚመሩ ቤተሰቦች በግጭት ወቅት ለደረሱ ጉዳቶች ከፍተኛ ተጋላጭ ሆነው የተገኙ ሲሆን፣ በመሬታቸው ላይ ኢንቨስት የማድረግ ደረጃቸው ዝቅ ያለ መሆኑም ተገልጿል። 

የዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይህ ጥናት ግጭት በሚፈጠርባቸው አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች የይዞታ ዋስትና የሚያረጋግጥ፣ የረዥም ጊዜ ከመሬት ጋር የተያያዙ ኢንቨስትመንቶችንም ማስተማመኛ የሚሰጥ፣ በጥናቱ የተረጋገጡ ሥጋቶችና ተግዳሮቶችን ታሳቢ ያደረገ ፍቱን የመሬት ፖሊሲ መቅረፅ ወሳኝ እንደሆነ ገልጿል። 

ፖሊሲው በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶችን አቅርቦት የሚያሻሽል፣ አርሶ አደሮች በይዞታቸው ላይ ያላቸውን መተማመን ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚያስችል፣ ከመሬት ጋር የተያያዙ ኢንቨስትመንቶችን የሚያበረታታ፣ በጦርነት ወቅት ከፍተኛ የችግሮች ሰለባ የሚሆኑ እንደ ሴቶች ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አስተማማኝ ጥበቃ የሚሰጥና የሚደርስባቸን ጉዳት የሚያሳርፍባቸውን ጫና ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበትም ተብራርቷል።

የገጠር መሬትን መሸጥ መለወጥ፣ እንዲሁም አስይዞ መበደር የሚፈቅድ አሠራር በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ውስጥ ተካቶ መቅረቡ ይታወቃል። 

በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀው የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም አዋጅ፣ የገጠር መሬትን ዋስትና አድርጎ ማስያዝን የሚመለከት የሕግ ድንጋጌ እስካሁን አለመኖሩን በመግለጽ፣ በአሁኑ ጊዜ በአሠራር እየታዩ ያሉ የአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የገጠር መሬት ይዞታ መብትን በመያዝ ብድር የመስጠት ተግባር፣ ለሕጉ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን በአዋጁ መመላከቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

የገጠር መሬት ባለቤት የመጠቀም መብቱን በየክልሉ በሚወጡ ሕጎች በሚወሰን የጊዜ ገደብ አማካይነት ለፋይናንስ ተቋማት ለብድር ዋስታና ማስያዝ እንደሚቻል በዚህ አዋጅ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ባለይዞታዎች በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ፣ የዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችና ግብዓቶችን የሚያገኙበት አሠራር ማመቻቸትን ያለመ ስለመሆኑ በረቂቁ ተብራርቷል፡፡

አዋጁ በፓርላማ የፀደቀው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ከፀደቀ አንድ ወር ገደማ በኋላ ነው። በምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ አዋጁ በፀደቀበት ስብሰባ፣ ‹‹የይዞታ መብታቸውን አርሶ አደሮቻችን በባንክ አስይዘው ገንዘብ የሚያገኙበት፣ የፋይናንስ እጥረታቸውን የሚሸፍኑበት፣ ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ዕድል የሚሰጥ አዋጅ ነው፤›› ሲሉ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡

ነገር ግን አዋጁ ለአርሶ አደሮች ከሰጠው አዲስ ዕድል ባሻገር፣ ከግጭት ጋር በተያያዙ የመሬት ጉዳዮችን በተመለከተ በተለየ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...