Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየከባድ ተሽከርካሪዎች ሾፌሮች በኦሮሚያ ክልል መሥራት ፈተና ሆኖብናል አሉ

የከባድ ተሽከርካሪዎች ሾፌሮች በኦሮሚያ ክልል መሥራት ፈተና ሆኖብናል አሉ

ቀን:

  • ‹‹ከተሞች ራሳቸውን ስለሚያስተዳድሩ ችግሩን እንዲያስተካክሉ ተነግሯቸዋል››

የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የከባድ ተሽከርካሪዎች ሾፌሮች በየአሥር ኪሎ ሜትሩ ገንዘብ ካልከፈላችሁ አታልፉም የሚሉ በመበራከታቸው ምክንያት፣ መሥራት ፈተና እንደሆነባቸው ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡

ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ባለው መንገድ እስከ ስምንት ሺሕ ብር በየኬላው ‹‹የኮቴ›› እየተባሉ በግዳጅ እንደሚከፍሉና አሽከርካሪዎቹ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የተናገረ የሲኖትራክ አሽከርካሪ ከመቂ ወደ አዲስ አበባ አሸዋ ጭኖ ለማለፍ መቂ፣ ዓለም ጤና፣ ቆቃ፣ ሞጆ፣ ቢዮና ደንብካ በተባሉ ስድስት ሥፍራዎች በአጠቃላይ ስድስት ሺሕ ብር ለመክፈል መገደዱን ገልጿል፡፡

‹‹መቂ አንድ ሺሕ ብር ከፍሎ የተሰጠው ደረሰኝ ዓለም ጤና ላይ አገልግሎት አይሰጥም፤›› የሚለው አሽከርካሪው ‹‹ከፍያለሁ ብዬ ደረሰኝ ለማሳየት ብሞክር አይመለከተንም በማለት  ድብደባና እንግልት ደርሶብኛል፤›› ሲል ተናግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እየተባለ ከ500 እስከ 800 ብር በየአካባቢው ገመድ ተዘርግቶ የከፈለበትን ደረሰኝ አሳይቶ ለማለፍ የሚሞክር   አሽከርካሪ፣ በታጠቁ ግለሰቦች የተሽከርካሪው ጎማ በጥይት ተመቶ ለተጨማሪ እንግልት መዳረጉን አክሏል፡፡

‹‹በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚያነጋግራቸውን አሽከርካሪ ያለ ደረሰኝ  ሦስት መቶና አምስት መቶ ብር እያስከፈሉ ሲያሳልፉ መመልከት ችያለሁ፤›› ሲልም ተናግሯል፡፡

ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ለኮቴ ብቻ ቢያንስ እስከ ስምንት ሺሕ ብር እንደሚያወጣ የተናገረው ሌላው የከባድ ተሽከርካሪ ሾፌር ነው፡፡

‹‹በየኬላው የሚሰጡት ደረሰኝ ሕጋዊ ይሁን አይሁን የሚታወቅ ነገር የለም፤›› የሚለው አስተያየት ሰጪው ስለደረሰኝ ሕጋዊነት መጠየቅ ሌላ ቅጣት ያስከትላል ብሏል፡፡

ከድሬዳዋና ከሐረር መስመር ወደ አዲስ አበባ መሥራት ከጀመረ ከሰባት ዓመታት በላይ እንደሆነው የሚናገረው አሽከርካሪው፣ በተለይ ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ የኮቴና የሚሊሻ በማለት በየአሥር ኪሎ ሜትሩ ከአንድ ሺሕ እስከ ሁለት ሺሕ ብር እንደሚያስከፍሉ ነው የተናገረው፡፡

ከአዲስ አበባ ተነስቶ ዱከም መግቢያ ላይ በ800 ብር የሚጀምረው ክፍያው ቢሾፍቱ መውጫ ላይ አንድ ሺሕ ብር፣ ከሞጆ አቅራቢያ በተመሳሳይ አንድ ሺሕ ብር፣ ሞጆ ሁለት ሺሕ ብር፣ አዳማ አንድ ሺሕ ብር፣ አሰበ ተፈሪ (ጭሮ) መግቢያ ላይ 800 ብር፣ ቦሮዳ 600 ብር፣ ሂርና፣ አደት የተባሉ ኬላዎች ላይ 800 ብር፣ ካራሚሌና  ደንገጎ በተመሳሳይ 800 ብር፣ እንዲሁም ድሬዳዋ መውጫ ላይ 800 ብር በየተራ በመክፈል እንደሚደርሱ ተናግሯል፡፡

አሽከርካሪዎች እንደሚሉት የተጠቀሱት ቦታዎች በደረሰኝ ብቻ የሚከፈልባቸው ቦታዎች ሲሆኑ፣ በተጨማሪ ለሚሊሻና ለልዩ ኃይል በማለት ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል መሥራት አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ወደ ትግራይና ወደ አማራ ክልሎች መሄድ መምረጣቸውን የተናገረው አሽከርካሪው፣ በተጠቀሱት አካባቢዎች አንድ ቦታ 800 ብር ከተከፈለ ደረሰኙን በማሳየት ብዙ ቦታዎችን ማለፍ እንደሚቻል አስረድ~ል፡፡

‹‹የኮቴ እየተባለ የሚከፈለው ገንዘብ ኦሮሚያ ክልል ብቻ አይደለም፤›› ሲል ቅሬታውን የሚያቀርበው ሌላው አሽከርካሪ፣ ‹‹በሁሉም አካባቢዎች እንደ አድማ የያዙት ነው የሚመስለኝ፤›› ብሏል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተመሳሳይ ችግር መኖሩን፣ ‹‹በአንዱ ወረዳ  የኮቴ ከፍለን አለፍ እንዳልን፣ የከተማ አስተዳደር ስንደርስ ሌላ ክፍያ ይጠይቃሉ፤›› ሲል ነው የተናገረው፡፡

ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ተነስቶ አሸዋ ጭኖ አዲስ አበባ ለመግባት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ መሣሪያ ይዘው በማስፈራራት ብቻ በትንሹ አምስት ሺሕ ብር እንደሚያስከፍሉ ገልጿል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል ከሁሉም የባሰ ነው፤›› የሚለው ቅሬታ አቅራቢው፣ ‹‹መንግሥት ሕጋዊ ናቸው ብሎ ባቋቋማቸው ኬላዎች በቀንና በማታ በታጠቁ ኃይሎች እየተዘረፍን ነው፤›› ብሏል፡፡

በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ የከባድ ተሸከርካሪዎች ሹፌሮች  ሥራ ማቆማቸውን የተናገረው አሽከርካሪው፣ በተለይ ተቀጥረው የሚሠሩ አሽከርካሪዎች ከሥራ ተሰናብተዋል ተብሏል፡፡

‹‹የኮቴ እየተባለ የሚከፈለው ገንዘብ ምን እንደሆነ አልገባኝም፤›› የሚለው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ፣ ከመተሐራ አሸዋ ጭኖ ሲወጣ ሁለት ቦታ ላይ ‹‹የኮቴ›› ተብሎ ከ100 እስከ 200 ብር እንደሚከፍል ተናግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለ‹‹ኦሮሚያ ወጣቶች ማኅበር የስፖርት ቡድን›› እየተባሉም 250 ብር ሲከፍል መቆየቱን ነው የተናገረው፡፡

ወለንጭቲ መግቢያ ላይ ሚሊሻ፣ የትራፊክ ፖሊስና የመንገድ ትራንስፖርት በጋራ ሆነው ለእያንዳንዳቸው መቶ ብር ያለ ደረሰኝ ካልተሰጠ ማለፍ እንደማይችል ቅሬታ  አቅራቢው አክሏል፡፡

አዳማ መግቢያ ላይም ተመሳሳይ ክፍያ እንደሚጠየቁና ተመሳሳይ ክፍያ ካልተፈጸመ አዲስ አበባ ለመግባት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግሯል፡፡

‹‹ብር በኪስ ሞልቶ ያልወጣ አሽከርካሪ መመለስ አይችልም፤›› የሚለው ቅሬታ አቅራቢው፣ ሕጋዊ ደረሰኝ አለኝ ብሎ መከራከር የበለጠ ቅጣት እንደሚያስከትል አስረድቷል፡፡

የአሽከርካሪዎቹን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ጥያቄ የቀረበለት የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ፣ ጉዳዩን የሰማው በቅርቡ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ከተሞች ራሳቸውን ስለሚያስተዳደሩ ችግሩን እንዲያስተካክሉ እንደተናገራቸው የክልሉ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የቀረበው ቅሬታ ከአንድ ሳምንት በፊት እንደሰሙ የተናገሩት አቶ ዳንኤል፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግን በየአካባቢው ያሉ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው  ብለዋል፡፡

ከተሞች የውስጥ ገቢ የሚሰበስቡበት የራሳቸው አሠራር ስላለ ጉዳዩን የበለጠ የሚያውቁት እነሱ ናቸው ሲሉም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...