Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የትምባሆ ምርት አወጋገድ መመርያ አፀደቀ

የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የትምባሆ ምርት አወጋገድ መመርያ አፀደቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የትምባሆ ምርት አወጋገድ መመርያ አፀድቆ ወደ ሥራ ማስገባቱ ተገለጸ፡፡

የትምባሆ ምርት በሰውና በእንስሳት፣ እንዲሁም በአካባቢ ላይ ጉዳት ሳያደርስ በአግባቡ መወገዱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ባለሥልጣኑ፣ ‹‹የትምባሆ ምርት አወጋገድ መመርያ›› በማዘጋጀትና በዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሔራን ገርባ በማፀደቅ ከግንቦት 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር፣ የባለሥልጣኑ ተቆጣጣሪ አቶ ቶሎሳ ገመዳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት መመርያ ያልነበረ ቢሆንም በትምባሆ አምራች ድርጅት፣ በባለሥልጣኑ፣ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ የተያዙ የትምባሆ ምርቶች እንደ ጉምሩክ ኮሚሽን በመሳሰሉ ተቋማት አማካይነት ሲወገድ መቆየቱን በመግለጽ፣ በታኅሳስ ወር 2016 ዓ.ም. በትምባሆ አምራች ድርጅት እስከ 20 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ምርት መወገዱን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

በአዲሱ የትምባሆ ምርትን የማስወገድ ትግበራ የሰውና የእንስሳ ጤናን በማይጎዳ፣ እንዲሁም አካባቢን በማይበክል ዘዴና ሥርዓት ለማከናወን ይረዳል ብለዋል፡፡ አወጋገዱም መጠኑንና የማስወገጃ ቦታውን በመለየት እንደሚሆን አክለዋል፡፡  

በሕጋዊ መንገድ የተመረቱ ቢሆንም በትክክል ያልታሸጉ ወይም አስተሻሸጋቸው ሕግን ያልተከተለ፣ በምርት ማሸጊያ ላይ ያለው የጤና ማስጠንቀቂያ ሕግን ያልተከተለ፣ በሕግ ከተፈቀደው ውጪ ሌሎች ፍሌቨሮችና ያልተፈቀዱ ንጥረ ነገሮችን በውስጥ የያዙ፣ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ወደ አገር የገቡና በአገር ውስጥ የተመረቱ፣ በሕገወጥ መንገድ የተከፋፈሉና ተመሳስለው የተሠሩሰ የትምባሆ ምርቶች የሚወገዱ መሆናቸውን መመርያው ይጠቅሳል፡፡

ማስወገድ የሚፈልጉ የትምባሆ አምራች፣ አከፋፋይ፣ ሕጋዊ ወኪል ምርቱ የሚወገድ መሆኑ ከታወቀ በ15 ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ ማሳወቅና ለማስወገድ ማመልከት እንደሚጠበቅባቸው መመርያው ይገልጻል፡፡

ለማስወገድ የተፈቀደለት ተቋም ምርቶቹን መለየት፣ የምርቶቹን ብዛት መቁጠር፣ ከሌላ ምርት ጋር እንዳይቀላቀሉ የማድረግ ኃላፊነት፣ እንዲሁም ለሚወገዱት ምርቶች የተለየ ማከማቻ ቦታ በማዘጋጀት «የሚወገድ ትምባሆ ምርት» የሚል ጽሑፍ መጻፍ እንዳለበት በመመርያው ተካቷል፡፡

‹‹የሚወገደው የትምባሆ ምርትና ቦታ ከተለየ በኋላ የሚወገድበት መንገድ ምርቱ በድጋሚ ምንም ዓይነት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳይችል በማድረግ፣ ማለትም ከአፈር ጋር እስኪመሳሰል መወገድ ይኖርበታል፤›› ሲሉ አቶ ቶሎሳ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት የትምባሆ ምርቱ ቢያንስ 1,000 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ባለው የማቃጠያ ዘዴን በመጠቀም ምርቱ ወደ አመድነት እስከሚቀየር በማቃጠል፣ የቃጠሎው ጭስ ወደ አየር እንዳይለቀቅ የሚያጣራ ማሽን የተገጠመለት የኢንሲነሬሽን (የማቃጠል) ዘዴ መጠቀም፣ እንዲሁም የተቃጠለው የትምባሆ ምርት የመጨረሻው አመድ በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት በማያስከትልና አካባቢን በማይበክል ሁኔታ መወገድ እንዳለበት በመመርያው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የትምባሆ ምርት ከማሸጊያ ቁሳቁሶች፣ ካርቶንና ፓኬት በመለየት ከውኃና ከሲሚንቶ ጋር በማቀላቀል ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረግ፣ የተቀላቀለውን ምርት በኮንክሪት በተገነባ የቆሻሻ መቅበሪያ ቦታ ውስጥ በመቅበር፣ ከተወገደ በኋላ በኮንክሪት በተሠራና በቀላሉ ሊከፈት በማይችል ሁኔታ በአግባቡ መክደን ወይም መድፈን፣ ለዚህ ዓላማ በኮንክሪት የሚገነባ መቅበሪያ ቦታ አካባቢን፣ የጉርጓድ ውኃ ማጠራቀሚያዎችን፣ የውኃ መስመሮችን እንዳያገኝ ተደርጎ አካባቢን እንዳይበክል በትክክል መገንባት፣ በጥብቅ የተገነባ የቆሻሻ መቅበሪያ ቦታ ሲመረጥና ዲዛይን ሲደረግ በአካባቢ ላይ የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን በቅድመ ጥናት ማረጋገጥና አግባብ ካለው አካል ዕውቅና ማግኘት ይጠበቅበታል ሲል መመርያው ያብራራል፡፡

በመመርያ መሠረት የተመረተው ወይም የተከፋፈለው የትምባሆ ምርት መወገድ ያለበት ከሆነ የማስወገጃ ወጪውን አምራቹ ወይም አከፋፋዩ የሚሸፍን ሲሆን፣ የትምባሆ ምርት ከተወገደ በኋላ ባለሥልጣኑ ምርቱ ስለመወገዱ ዝርዝር መረጃ በሚዲያ መግለጽ አለበት ይላል።

መመርያውን በመቃረን አካባቢን በሚበክል ሁኔታ፣ የባለሥልጣኑ ፈቃድ ሳይኖረው ምርቱን ያስወገደና የተከማቸ ምርት ወደ ገበያ ያሠራጨ ተቋም ፈቃዱ በባለሥልጣኑ እንደሚሰረዝ ተጠቅሷል፡፡

ከሚወገድ የትምባሆ ምርት መለየት፣ ማከማቸትና ማጓጓዝ ድንጋጌዎችን ተላልፎ የተገኘ አምራችና አከፋፋይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በድጋሚ ተመሳሳይ ጥፋት የፈጸመ ከሆነ ልዩ ፈቃዱ የሚሰረዝ ቢሆንም፣ ዕርምጃ የተወሰደበት ግለሰብ በባለሥልጣኑ የአስተዳደር ዕርምጃ አወሳሰድና ቅሬታ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት መመርያ መሠረት ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል በመመርያው ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...