Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ተማሪዎች የባንክ ብድርን የሚፈቅድ አሠራር እንዲመቻች ተጠየቀ

በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ተማሪዎች የባንክ ብድርን የሚፈቅድ አሠራር እንዲመቻች ተጠየቀ

ቀን:

በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከፍለው ለመማር የማይችሉ ተማሪዎች፣ የባንክ ብድር እንዲያገኙ የሚረዳ ሕጋዊ አሠራር እንዲመቻች ጥያቄ ቀረበ፡፡

በ2015 ዓ.ም. ፀድቆ ወደ ሥራ የገባውና ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የሚያደርገው አዋጅ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ከስምንት ወራት በፊት ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ራስ ገዝነት ለማሸጋገር ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ምንም እንኳ ተጠያቂነቱ ኖሮ በተወሰነ ደረጃ መንግሥት በገንዘብ የሚደግፋቸውም ቢሆኑም፣ ራሳቸውን በራሳቸው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የፋይናንስ፣ የአስተዳደር፣ የአካዴሚክ፣ የሰው ሀብትና መሰል ነፃነት አዋጁ ያጎናፅፏቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ራስ ገዝ ሆኖ ሥራ በጀመረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ከፍለው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ክፍያው በከፍተኛ መጠን እንደጨመረባቸው እየተናገሩ ነው፡፡ ወደፊት ራስ ገዝ የሚሆኑ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሥራ ሲገቡ አሁን ያለው ሁኔታ ጥሩ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ከፍለው እንዳይማሩ ይገድባል የሚል ሥጋት እየተሰማ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መንግሥት አስቻይ ሁኔታዎች ካልፈጠረ ትምህርት ሎተሪ ይሆንብናል ብለዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል የሱፍ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ የትምህርት ዕድሉን ማግኘት ያለባቸው ነገር ግን የፋይናንስ አቅም የማይኖራቸው አስቸኳይ አማራጮች ሊቀመጡላቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚሰጡት ነፃ የትምህርት ዕድል በተጨማሪ በሌሎች አገሮች እንደሚሠራበት ለተማሪዎች የሚሰጥ ብድር መመቻቸት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ጀማል (ዶ/ር) አንድ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር ብቃቱ ካለውና ተወዳዳሪ ከሆነ በሚገባው ቃል መሠረት ከአበዳሪው ባንክ ያገኘውን ገንዘብ ተምሮ እስኪወጣ ድረስ መጠቀም እንዲችል፣ ተመርቆ ወደ ሥራ ሲገባም መክፈል የሚያስችለውን አሠራር መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዚህም የመማር አቅም ያለው ዜጋ የተመቻቸ ሁኔታ ከተፈጠረለት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ቢሆኑም ተማሪ ገንዘብ ስላጣ ብቻ የትምህርት ዕድሉን እንዳያጣ፣ አገሪቱም የሚያስፈልጋትን የሰው ኃይል እንዳታጣ ያደርጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት አቅም የሌላቸውን ለመርዳት ፍላጎቱ እንዳለው ማስታወቁን የተናገሩት ፕሬዚንዳቱ፣ መረዳት ያለባቸውንና የሌለባቸውን መለየት ግን ትልቅ ሥራ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር)፣ የሚስተዋለው ችግር ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን የፈተና ውጤት በትንሹም ቢሆን እያመጡ ባለመሆናቸው ዩኒቨርሲቲዎች ሊቀበሉት የሚፈልጉትን ያህል የተማሪዎች ቁጥር ለማግኘት ተቸግረዋል ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በቀጣይ ይህ እየተስተካከለ ሲሄድና የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምር ለተማሪዎች ምግብ ማቅረብ በዩኒቨርሲቲዎች አቅም የማይፈጸም በመሆኑ፣ መንግሥት በውጭው ዓለም የተለመደውን ለተማሪዎች ብድር የሚቀርብበት አሠራር ሊያስብበት ይገባል ብለዋል፡፡

ወደ ተማሪዎች ብድር አቅርቦት አሠራር መሄድ የግድ ነው ያሉት ለሚ (ዶ/ር)፣ ምክንያቱ ደግሞ የተማሪዎችን ቀለብ ለማሟላት ዩኒቨርሲቲዎች እየከበዳቸው መሆኑንና አሁን ያለው አሠራር በዚህ የማይቀጥል በመሆኑ ለተማሪዎች የሚሰጠው የብድር አሠራር ሕግ ሊወጣለት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የብድር ዕድሉን ያገኙ ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም እንዲገቡ የሚያግዝ የፋይናንስ አሠራር ካልተጠፈረ በስተቀር፣ አሁን ባለበት ለመቀጠል አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ ጉዳዩ በሐሳብ ደረጃ ቢኖርም ወደ ጠረጴዛ መጥቶ ውይይት ሊደረግበት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡

ከ1996 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ጀምሮ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡ ተማሪዎች በወጪ መጋራት (ኮስት ሼሪንግ) መመርያ መሠረት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ተመርቀው እስኪወጡ ድረስ፣ መንግሥት ለምግብና ለመኝታ ያወጣውን ወጪ በሚገቡት ውል መሠረት ከምረቃ በኋላ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ 

የወጪ መጋራት ክፍያ ለተማሪዎች እንዲፈቀድ እየተጠየቀ ካለው የተማሪዎች ብድር አንፃር በመጠኑ በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም ምሩቃኑ ክፍያውን እየከፈሉ አለመሆ ናቸውን፣ እንዲሁም በርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት መሠረት ክፍያውን ተከታትለው እንደማያስፈጽሙ የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...