Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊኤጀንሲዎች ያልተገበሯቸው የኢሠመኮ ምክረ ሐሳቦች

ኤጀንሲዎች ያልተገበሯቸው የኢሠመኮ ምክረ ሐሳቦች

ቀን:

በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው ለተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች የሚሠሩ ሠራተኞች፣ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡

በአንድ ደመወዝ ሁለት ቦታ መሥራትን ጨምሮ፣ የሚገባቸውን ያህል ተከፋይ አለመሆን፣ የሥራ ጫና፣ በቀጣሪዎች ዘንድ ሊሟሉ የሚገቡ ግዴታዎችን በቸልታ ማለፍ፣ ተገቢው መሥፈርት ሳይሟላ ከሥራ ማሰናበት፣ እንደተፈለገ ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም ማዘዋወርና ሌሎችም ሠራተኞች የሚያነሷቸው በደሎች ናቸው፡፡

ደመወዝ አከፋፈል ላይ ቀጣሪ ድርጅቶች ለኤጀንሲው ከሚከፍሉት አብላጫውን ለኤጀንሲው ማድረግና የደመወዝ ጭማሪ ችግሮችም በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡

- Advertisement -

በተለይ ሴቶች ካልተገባ ንግግር ጀምሮ በርካታ የመብት ጥሰቶች የሚፈጸምባቸው መሆኑ፣ ሥራውን እናጣለን በሚል ችግሮቻቸውን ተሸክመው መሥራታቸው፣ ከአሠሪውም ሆነ ከኤጀንሲው ጋር ሐሳባቸውን በግልጽ ለመወያየት የሚያስችል ድባብ አለመኖርም የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡

የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞችን በተመለከተ፣ እነዚህንና ሌሎች መሠረታዊ የመብት ጥሰቶችን ለማስቆም እንዲቻል ጥናት በማድረግና ምክረ ሐሳብ በመስጠት ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሠመኮ)፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ ዓምና በኅዳር ኤጀንሲዎች ይፈጽሟቸው ዘንድ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ተግባር ላይ ስለመዋላቸው የሚተነትነውን ሪፖርት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞችን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል አሁንም ፈጣን የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ዕርምጃ ያስፈልጋል ያለው ኮሚሽኑ፣ በኅዳር 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዋናው የክትትል ሪፖርቱ፣ በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መብቶች በተለይም ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት፣ የእኩልነትና ከአድልኦ ነፃ የመሆን፣ የሥራና ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት ጥሰቶች እንደነበሩ አመላክቶ ነበር፡፡

በመደራጀት፣ ቅሬታ በማሰማት እንዲሁም ፍትሕ በማግኘት በኩል ከፍተኛ ክፍተቶች መኖራቸውንም በወቅቱ ገልጾ፣ ችግሮችን የመፍቻ ምክረ ሐሳቦች አቅርቦ ነበር።

የኤጀንሲ ሠራተኞችን በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ዋና የሕግ ማዕቀፍ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል ቀጥሮ ማሠራትን ዕውቅና ቢሰጥም፣ የሁለትዮሽ የሥራ ግንኙነትን ብቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተቀረፀ መሆኑ ለችግሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጾ፣ የሦስትዮሽ የሥራ ግንኙነትን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍንና የተሳታፊ አካላትን ኃላፊነቶችና የመንግሥትን ግዴታዎች በአግባቡ በሚደነግግ መልኩ እንዲሻሻል ወይም ራሱን የቻለ አዲስ ሕግ እንዲወጣ ምክረ ሐሳብም ሰንዝሮ ነበር፡፡

ሆኖም ኢሠመኮ አሁን ይፋ ባደረገው የትግበራ ክትትል ሪፖርት፣ የተወሰኑ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ቢሆኑም፣ አብዛኛዎቹ አለመተግበራቸውን አስታውቋል፡፡

የሕግ ማሻሻያ ዕርምጃዎች አለመወሰዳቸው፣ የኤጀንሲ ሠራተኞችን መብቶች፣ ደኅንነትና ጥቅማ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችለው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መመርያ ቁጥር 45/2013 ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመደረጉና የኤጀንሲ ሠራተኞች የሥራ ዋስትና ማጣት ሪፖርቱ ካመላከታቸው ክፍተቶች ይጠቀሳሉ፡፡

እንደ ኢሠመኮ ሪፖርት፣ የኤጀንሲ ሠራተኞች የሥራ ዋስትና አለመኖር መሠረታዊ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። ይህንን ለመቅረፍ የሠራተኞች የሥራ ውል፣ ተጠቃሚ ድርጅቱና ኤጀንሲው በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ሳይሆን በሚሰማሩበት ሥራ ቀጣይነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ደግም ምክረ ሐሳብ ተሰጥቷል፡፡

ይህን በመተግበር፣ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እንደተመላከተው፣ የሥራ ውል ዓይነቶችን በመገደብ፣ በሕጋዊ መንገድ ውል ሊቋረጥባቸው የሚችሉ ምክንያቶችን በመዘርዘርና ያላግባብ ውል ሲቋረጥ የሚያስከትለውን ውጤት በመደንገግ የሠራተኞችን የሥራ ዋስትና የማግኘት መብት ማረጋገጥ እንደሚቻልም አክሏል።

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁን የሦስትዮሽ የሥራ ግንኙነቶችን ሙሉ በሙሉ በሚሸፍን መልኩ እንዲሻሻል ማድረግ ወይም አዲስ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲን የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባ የጠቆመው ኮሚሽኑ፣ ይህ እስኪሆን፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኤጀንሲ ሠራተኞችን የሥራ ውል በሚሰማሩበት ሥራ ቀጣይነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚያደርግ መመርያ ማውጣት እንደሚኖርበትም አመልክቷል፡፡

በመንግሥት ቁጥጥርና ክትትል አካላት ሥር የሕግ ባለሙያ አለመኖር አንዱ ችግር ሲሆን፣ ይህንን ለመቅረፍ፣ የቁጥጥር አካላት ውስጥ የሕግ ባለሙያዎችን ማካተት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ከሚያዝያ 23 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲሁም ከግንቦት 24 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በባህር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በጅማና በአዲስ አበባ ከተሞች ክትትል አድርጎ፣ በቂ ክፍያ የማግኘት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት፣ በተገደበ የሥራ ሰዓት የመሥራት፣ ዕረፍትና ፈቃድ የማግኘት መብት፣ ከእኩልነትና ከአድልኦ ነፃ የመሆን፣ የሥራ ዋስትና የማግኘት፣ ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት፣ የመደራጀት፣ ቅሬታ የማሰማትና ፍትሕ የማግኘት መብቶቻቸው መጣሳቸውን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

የዘንድሮው የትግበራ ክትትል በዋናው ክትትል ከተሸፈኑት ከተሞች መካከል በአዲስ አበባ፣ ጅማና ሐዋሳ ከተሞች ላይ ብቻ የተወሰነ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባህር ዳር ከተማን ለማካተት እንዳልተቻለ የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...