Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊሶፍትዌርና ድሮንን ዕውን ያደረጉት ወጣቶች

ሶፍትዌርና ድሮንን ዕውን ያደረጉት ወጣቶች

ቀን:

በዋኖፊ ሰለሞን

ትኩረቱን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምርምር፣ በኢኖቬሽን ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም ኢንተርፕረነርሽፕ ዙሪያ በማድረግ በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ በነበረው   ኤክስፖ፣ የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

‹‹ሳይንስ በር ይከፍታል፣ ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፣ ፈጠራ ወደፊት ያራምዳል›› በሚል መሪ ቃል ተዘጋጅቶ በነበረው ስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ፣ በግልና በመንግሥት ተቋማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና አገልግሎቶች ለዕይታ ቀርበዋል።

- Advertisement -

የ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025›› ስትራቴጂ በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማት መገንባትና የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገቶች ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

በኤክስፖው በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራ ያጋጠሙ ፈተናዎችና ቀጣይ ዕቅዶች ዙሪያ የፓናል ውይይት ሲደረግ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ‹‹ቴክኖሎጂ ለአገር ልማት የሚያመጣው ትሩፋትና የዲጂታል ኢኮኖሚ በዲጂታል ቴክኖሎጂ›› በሚል ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳብ፣ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

መንግሥት በትኩረት እየሠራባቸው ከሚገኙት መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በ2025 ዓ.ም. ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት መንግሥት ያሳየው ተነሳሽነት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት እንዳለው ማሳያ ነው ብለዋል። 

በኤክስፖው የተለያዩ ድርጅቶችና ወጣቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን፣ ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል፡፡ ካቀረቡት መካከልም የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን የአመዘጋገብ ሥርዓት ወደ ኦንላይን የሚቀይረውን ሶፍትዌር የሠሩት ፌኔት ደምሴና ቃልኪዳን እሸቱ ይገኙበታል።

ሁለቱ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ስቴም ፓወር (Stem Power) ከሚባል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደመጡ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ከኬጂ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ያሉ ልጆችን የሒሳብ፣ የፊዚክስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግብዓትን በማሟላት እንዲጎለብቱ የሚያደርግ ሲሆን፣ ፌኔትና ቃልኪዳንም ድርጅቱን ከተቀላቀሉ በኋላ የሚፈልጉት ግብዓት ተሟልቶላቸው ሶፍትዌር ማበልፀግ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ስቴም ፓወርን ለማስተዋወቅ እንደመጡ የሚናገሩት ወጣቶቹ፣ ከኬጂ አስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ልጆች ያለ ምንም ክፍያ በቅዳሜና እሑድ መርሐ ግብር ወይም በክረምት ጊዜ ተምረው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

‹‹ድሮን የመሥራት ሐሳብ የነበረኝ የ12ተኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነው፤›› የሚለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ፍቅረማርያም ደጀኔ፣ የመጀመሪያውን ድሮን የሠራው የሦስተኛ ዓመት የዩንቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቆ ክረምት ላይ በነበረው የዕረፍት ጊዜ እንደነበር ይገልጻል።

ድሮን ለመሥራት ሙከራ በሚያደርግበት ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞት እንደነበር የሚናገረው ፍቅረማርያም፣ በሙከራ ወቅት ከሚከሰከሱት ድሮኖች በተጨማሪ፣ እየበረሩ ይጠፉበት እንደነበር ያስታውሳል።

በመጀመሪያ በቤተሰብ ዕርዳታ ሙሉ ለሙሉ ድሮን መሥራት ችሎ እንደነበር፣ የሠራውን ድሮን ለስፔስ ሳይንስና ለጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ካሳየ በኋላ የተለያዩ ቁሳቁሶች አሟልተውለት አሻሽሎ እንደሠራው ይናገራል።

ለዕይታ ያቀረባቸው ድሮኖች የዴሊቨሪ አገልግሎ ለመስጠት በቂ መሆናቸውን የሚናገረው ፍቅረማርያም፣ የወደፊት ግቡ በአገር ውስጥ ድሮኖች እንዲመረቱ ማድረግ እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት ሲቪል አቪዬሽን ሕግ እስኪያወጣ እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል።

ኤክስፖውን ሲጎበኙ ካገኘናቸው መካከል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው የሃያ አንድ ዓመቷ ህሊና ሰለሞንና ጓደኞቿ ይገኙበታል። የኮምፒውተር ሳይንስ የአራተኛ ዓመት ተማሪዋ ህሊና በኤክስፖው አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ማየቷን፣ ይህም ከፍተኛ መነሳሳት አንደፈጠረባት ትናገራለች።

የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራን የሚያበረታቱ ኤክስፖዎች ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ ሐሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር ዕድልና መነሳሳት ይፈጥራሉ ስትል የገለጸችው ህሊና፣ እሷና ጓደኞቿ ከተለያዩ ሥራ ፈጣሪዎችና ድርጅቶች ጋር እንደተገናኙ ተናግራለች። 

ወጣቶች ቴክኖሎጂ ነክ ዝግጅቶችን እንዲታደሙ አበረታታለሁ የምትለው ህሊና፣ ወጣቶች በቴክኖሎጂና በፈጠራ ዘርፍ ያላቸውን ዕውቀት እንዲያዳብሩና ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ትመክራለች።

ኤክስፖ መዘጋጀቱ ወጣቶችና ሥራ ፈጣሪዎች ከተለያዩ ባለሀብቶችና ተጠቃሚዎች ጋር እንዲገናኙ ማድረጉን ለገለጸው ፍቅረማርያም፣ ለወጣቶች ምን ትመክራለህ? በሚል ሪፖርተር ላቀረበለት ጥያቄ፣ ‹‹ወጣቶች አካባቢያቸውን ዞር ዞር ብለው እንዲቃኙና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ፣ በተለይ ለቴክኖሎጂ ትኩረት እንዲሰጡ  አበረታታለሁ›› ብሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...