Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከወጣው 192 ቢሊዮን ብር ውስጥ 95 በመቶው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር መሸፈኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከተደረገው ጠቅላላ ወጪ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተገኘ ብድርና ድጋፎች የተሸፈነ መሆኑ ተገለጸ። ባንኩ ለግድቡ ግንባታ ከሰጠው ብድር በተጨማሪ በብድሩ ላይ ማስከፈል የነበረበትን የወለድ መጠን በእጅጉ ዝቅ በማድረግ በየዓመቱ ሊያገኝ የሚችለውን ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የወለድ ገቢ ማስቀረቱም ታውቋል። 

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (የኢትዮጵያ ዲያስፖራ) ለማሰባሰብ የሚያስችል አዲስ መተግበሪያ በተጠናቀቀው ሳምንት ይፋ በተደረገበት ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም. (ማለትም ላለፉት 13 ዓመታት) ድረስ ለግድቡ ግንባታ 192 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ 

ከዚህ ጠቅላላ ወጪ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር ያቀረበው የገንዘብ መጠን 136.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህም ሌላ ባንኩ ከ9.6 ቢሊዮን ብር በላይ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመሸጥ ገቢ አድርጓል፡፡ ይህም እስካሁን ለፕሮጀክቱ ከወጣው ወጪ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው በባንኩ በተገኘ ብድርና ድጋፍ የተሸፈነ መሆኑን ያመለክታል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፣ ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ በብድር ከማቅረብ በተጨማሪ ለሰጠው ብድር እጅግ አነስተኛ የወለድ ምጣኔ ብቻ እንደሚያስከፍል ተናግረዋል። ባንኩ ለተመሳሳይ ብድሮች የሚጠየቀው የብድር ወለድ ምጣኔ 16.5 በመቶ ቢሆንም ለግድቡ ግንባታ ላቀረበው ብድር የሚያስከፍለው የወለድ መጠን ዘጠኝ በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ባንኩ ለመሰል ፕሮጀክቶች በሚሰጠው ብድር ላይ የሚያስከፍለውን የ16.5 በመቶ የወለድ ምጣኔ በዚህ ፕሮጀክት ላይም ተግባራዊ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ የወለድ ገቢ ያገኝ እንደነበር ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል። ባንኩ ለግድቡ ግንባታ በሰጠው ብድር ላይ ለመሰል ፕሮጀክቶች የሚያስከፍለውን የ16.5 በመቶ የወለድ ምጣኔ ተግባራዊ አድርጎ ቢሆን ኖሮ በየዓመቱ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የወለድ ገቢ ያገኝ እንደነበር ተናግረዋል።

በተጨማሪም ባንኩ እስካሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ የሰጠው ብድር መመለስ አለመጀመሩን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ በኋላም ቢሆን ባንኩ ለግድቡ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማቅረብ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ባንኩ ከሰጠው ብድር በተጨማሪ የባንኩ ማኅበረሰብ 319.7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ ለዚህ ግድብ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱም ተጠቅሷል፡፡ ከሁሉም በላይ ፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ በማቅረብም ድጋፍ ማድረጉ ጠቅሰዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሚሰጡትን ድጋፍ ለማሳደግ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ውሎ በነበረው መተግበሪያ ከ250 ሺሕ ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቡ ተገልጿል፡፡ በዕለቱ ይፋ የተደረገውና ተሻሽሎ የቀረበው መተግበሪያም የዚሁ አካል በመሆኑ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትና የማጠናቀቂያ ሥራውን ለማስፈጸም አጋዥ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ተሻሽሎ የቀረበው መተግበሪያ ስያሜ ‹‹It’s my Dam›› (ግድቡ የኔ ነው) የሚል ሲሆን፣ ይህንን የተሻሻለ መተግበሪያ በይፋ ሥራ ለማስጀመር በተሰናዳው ፕሮግራም ላይ የተገኙት የህዳሴ ግድብ የሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ እስካሁን በተለያዩ መንገዶች 19.4 ቢሊዮን ብር ከማኅበረሰቡ ተሰብስቧል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከዳያስፖራው የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን 1.4 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም እስካሁን ለፕሮጀክቱ ከወጣው ወጪ ከዳያስፖራው መሰባሰብ የተቻለው 0.5 በመቶ መሆኑን ያመላክታል ተብሏል፡፡ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አንፃር አነስተኛ የሚባል መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል፡፡ አጠቃላይ የግድቡ ሥራ 96 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሁሮ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ለቀረው አራት በመቶ ሥራ ወደ 49 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ ወጪው 241 ቢሊዮን ብር የሚያደርሰው ሲሆን፣ ቀሪው ሥራ ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በቀጣዩ ዓመት (2017) መጨረሻ ላይ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ የተለያዩ ሥራዎችን በተናጠል የደረሰበትን ደረጃ በዝርዝር ጭምር ያቀረቡት ክፍሌ (ኢንጂነር) ከዚህ በኋላ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የታደሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢንጂነር) በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ሥራ በጀመሩት ተርባይኖች የሚመነጨው ኃይል ገንዘብ ማስገኘት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከህዳሴ ግድብና ከሌሎች ማመንጫዎች የተገኘውን ኃይል ወደ ውጭ በመላክ 80 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም አስረድተዋል፡፡ የግድቡ ሥራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም አሁን ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ሁለትና ሦስት እጥፍ በላይ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ ከግድቡ ሊገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ ለማሳደግ ቀሪውን የአራት በመቶ ሥራ በርብርብ ለማጠናቀቅ ኅብረተሰቡ በተለይም ዳያስፖራው የበኩሉን ዕገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

ለቀሪው ሥራ የሚያስፈልጉ 49 ቢሊዮን ብር ወይም ወደ 850 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን በማስታወስም በተለይ ለቀሪው ሥራ የሚያስፈልጉ ክፍያዎች የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ በመሆኑ በውጭ ምንዛሪ የሚደረግ ድጋፍ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ 

ሰባት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ እስካሁን 13 ዓመት በላይ የፈጀውና በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ ወደ 241 ቢሊዮን ብር ወጪ ሊጠይቅ የቻለበትን ምክንያት በተመለከተ ክፍሌ (ኢንጂነር) ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ መጓተት በርካታ ምክንያቶች እንደነበሩ ያመለከቱት ኢንጂነሩ፣ ግንባታው ከተጀመረ በኋላ ተቋራጩ ድርጅት የግድቡ መሠረት ላይ ልል ድንጋይ እንዳጋጠመው በመግለጹና ይህንን ድንጋይ አንስቶ በኮንክሪት ለመሙላት ቢያንስ አንድ ሺሕ ቀናት ወይም ሦስት ዓመታት በማስፈለጉ ያልታሰበ የጊዜ ማራዘሚያ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ 

ይህም ግድቡ በሰባት ዓመታት ያልቃል ተብሎ ተይዞ የነበረውን ዕቅድ የኮንክሪት ሥራው ብቻ በሦስት ዓመት እንዲራዘም በማድረጉ ከሰባት ወደ አሥር ዓመት እንዲራዘም ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ ለግድቡ መዘግየት ሌላው በዓበይት ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው ከፍተኛ አቅምና ዕውቀት የሚፈልጉ ወሳኝ የግድቡ ሥራዎች በአገር አቅም ይገንባ ተብሎ ሥራው መጀመሩ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ባስከተለው ችግር እንከኖች በመገኘታቸው ይህንንም አፍርሶ መልሶ ለመገንባት ተጨማሪ ጊዜ ወስዷል፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ በራስ አቅም ለመገንባት መታሰቡ እንደ መልካም የሚታይ ቢሆንም ሥራው ላይ የፈጠረው ችግር አገርን ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በእሳቸው እምነት በራስ አቅም ሥራውን ለመሥራት መነሳት በጎ ዕሳቤ ቢሆንም ድርጊቱ ግን ‹‹መሪ ጨብጦ የማያውቅ ሰው መኪና አሽከርክር እንደማለት የሚቆጠር ነው፤›› ብለውታል፡፡ በራስ አቅም ተሠርቶ የነበረው ሥራም ቢሆን የጥራትና ስኬት ችግር በማስከተሉ እንደገና መሠራት ስለነበረበት ይህም የፕሮጀክቱን የጊዜ ሰሌዳ እንዲገፋ ከማድረጉም በላይ ተጨማሪ ወጪ ጠይቋል፡፡ 

እንዲህ ያሉት እንቅፋቶች የፕሮጀክቱን የሥራ እንቅስቃሴ አስተጓጉሎት ቢቆይም ከለውጡ በኋላ የታዩትን ችግሮች መሠረት በማድረግ የማስተካከያ ዕርምጃዎች በመውሰዳቸው ፕሮጀክቱ ዳግም ነፍስ ዘርቶ አሁን ላለበት ደረጃ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል ለፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት የሆኑ ኮንትራክተሮችን በዓለም ላይ ልምድ ባላቸው እንዲተኩ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህ ባይሆንና በነበረው አካሄደው ቢሄድ የግድቡ ግንባታ 20 ዓመታት እንኳን  ስለመጠናቀቁ እርግጠኛ መሆን ካለመቻሉም በላይ ፕሮጀክቱም ጥራት ጥያቄ  ሊያስነሳ ይችል እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

ግድቡ ዛሬ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው እጅግ የበዙ ፈተናዎችን በመቋቋም እንደሆነ በማስታወስም፣ በእስከዛሬው ጉዞ ገጥመው የነበሩ ችግሮችና አሁንም ድረስ ተግዳሮት ሆነው የዘለቁ ክስተቶችን አብራርተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ቀዳሚ ተግዳሮት የነበረው ግድቡ እንዳይገነባ የሚሹ ወገኖች በዲፕማሎሲው ረገድ የከፈቱት ጦርነት አንዱ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የግድቡ ግንባታ በተቀዛቀዘበት ወቅት ድምፃቸውን እንዳላጠፉ ሁሉ ደግም ሥራው መጀመሩና ተገንብቶ እንደሚያልቅ ሲረዱ በዲፕሎማሲው ከሚደርጉ ጦርነት ባሻገር በማስፈራራት ጭምር ሥራው እንዲስተጓጎል ሲያደርጉ እንደነበር በዚሁ ማብራሪያቸው አመልክተዋል፡፡ 

የነበሩት ተግዳሮቶች በዚህ ብቻ ተገልጾ የማያልቅ ስለመሆኑ ያወሱት ኢንጅነሩ እነዚሁ የግድቡን ግንባታ የማይሹ ወገኖች ሥራውን ለማስቆም ግንባታውን የሚያካሂዱት  ኮንትራክተሮችን ለማባበል ረዥ ርቀት ሄደዋል፡፡ ይህ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ በሌላ አገር ሥራ እንደተገኙ እናደርጋለን በሚል ሲያስፈራሩዋቸው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ 

እንዲህ ያሉትን አደናቃፊ ሁኔታዎች በሕዝብ፣ ዳያስፖራውና መንግሥት ባካሄዳቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ማርገብ ቢቻልም እንደገና በሌላ መንገድ የግድቡን ሥራ ለማስተጓጉል የዘረጉት መረብ አሁንም ድረስ ተግዳሮት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ግድቡ እንዳይገነባ በሚሹ ወገኖች አዲስ የተዘረጋው መረብ አንዱ መገለጫ ወደ ግድቡ የሚሄዱ ግብዓቶችን መንገድ እንዲቀር የሚደረጉ ጥቃቶች ናቸው፡፡ ህዳሴ ግድብ ግብዓቶች እንዳይደርሱ መንገድ ላይ የተልዕኮ ጦርነቶች በመክፈት የተደረጉ ሙከራዎች በተደጋጋሚ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ግብዓቶች የሚጓጓዙበትና አሁንም እየተጓጓዙ ያሉት በእጀባ ነው፡፡ መከላከያ በማሰማራት እየተታኮሰም ጭምር ገልጸዋል፡፡ ሥራው እንዳይስተጓጉል መስዋዕት እየተከፈለ ሥራውን ማስቀጠል መቻሉን ጭምር የተናገሩት የጥቃቶቹ መደጋገም ወደ ህዳሴ ግድብ ግብዓት ይዘው የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎች እየተፈጠረባቸው በነበረው ጥቃት ምክንያት በመከላከያ እጀባ የሚሸፈነው የጉዞ መስመርንም እስከ ማራዘም መድረሱን አመልክተዋል፡፡   

በዚህ ምክንያት ቀደም ብሎ ግብዓቶች በእጀባ የሚሄዱት ከግልገል ጊቤ ጀምሮ ሲሆን፣ አሁን ግን እጀባውን ሽፋን በማስፋት እስከ ፍቼ ድረስ ደርሷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የግብዓት ማምረቻዎች ድረስ በመሄድ ጥቃት እስከመፈጸም ደርሰው ነበር፤›› ያሉት ክፍሌ (ኢንጂነር) ፋብሪካዎች ድረስ በመሄድ ማቃጠላቸውንም ተናግረዋል፡፡ 

ለዚህም በምሳሌነት የጠቀሱት ለህዳሴ ግድቡ ሊሆን የሚችለውን ሲሚንቶ የሚያመርተውን ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የደረሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት ነው፡፡ ጥቃቱ ፋብሪካው ድረስ በመሄድ ማቃጠል፣ የፋብሪካው ጥሬ ዕቃዎች ሲጓጓዙ መንገድ ላይ ጠብቆ ጥቃት መፈጸምና የመሳሰሉት ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ይህም ዋነኛ ዓላማ የግድቡን ሥራ ማስተጓጎል ነው፡፡ አሁንም ግን እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ያለመቆማቸውንና አሁንም በየጊዜው ለፋብሪካው የሚቀርብ የማምቻ ዕቃዎች እንዳይደርሱ ደባዎች የሚፈጸሙ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

በመሆኑም በብዙ መስዕዋትነት እዚህ የደረሰውን የግንባታ ሥራ ለማጠናቀቅ የቀረው ሥራ ጥቂት በመሆኑ በርብርብ እንደተጀመረ ሁሉ በርብር እንዲያልቅ የሁሉም ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለህዳሴ ግድብ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ከዳያስፖራው ለማሰባሰብ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መተግበሪያ በይፋ መጀመሩ በተገለጸበት ፕሮግራም በሁሉም አገሮች ያሉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በቀጥታ ብዙም ተሳታፊ የነበሩበት ሲሆን፣ በአጋጣሚውም የገቢ ማሰባሰቡ ሥራ በእነሱ ተጀምሯል፡፡ በዕለቱ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ከአንድ መቶ ዶላር ጀምሮ እስከ ሁለት ሺሕ ብር ድረስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ግለሰቦችም እስከ አምስት ሺሕ ዶላር አዋጥተዋል፡፡ በተለይ አምባሳደር ባጫ ደበሌና ሌሎች ሦስት ዲፕሎማቶች የወር ደመወዛቸውን ገቢ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን፣ ሌሎች አምባሳደሮችም በተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ኢንጂነር) በኤምባሲው በኩል ለግድቡ ግንባታ በተለያዩ መንገዶች ከ200 ሺሕ ዶላር በላይ መሰብሰቡንና ተጨማሪ በማከል ገቢ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡ በዱባይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት በበኩላቸው አምስት ሺሕ ዶላር በዚሁ ፕሮግራም ላይ ለግሷል፡፡ 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 15,780 ጊጋ ዋት ሐወር ኃይል በዓመት ይመነጫል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እንደ ክፍሌ (ኢንጂነር) ገለጻ ይህ የኃይል መጠን በዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ይሆናል፡፡ 

ይህ ብቻ ሳይሆን ከግድብ የሚመነጨው ኃይል ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲገባ የነፍስ ወከፍ ገቢን (ፐር ካፒታል) መጠናችንን ያሳድጋል ብለዋል፡፡ የማምረት አቅም ስለሚያሳድግና የኢነርጂ ሽያጭ ብቻ ከሦስት እጥፍ በላይ ፐር ካፒታል ገቢን በማሳደግ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ 

በውጭ የሚገኙ ዜጎች በታላቁ ህዳሴ ገንዘብ በማዋጣት ሌሎችም ገንዘብ እንዲያዋጡ ለመቀስቀስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትና ላደረጉት አስተዋጽኦ የምስክር ወረቀት የሚያገኙበት ነው፡፡

በዕለቱ በክብር እንግዳነት የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለህዳሴው ግድብ እዚህ መድረስ የዳያስፖራው በገንዘብም በዲፕሎማሲያዊ ትግሉም ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል ያለመሆኑን ገልጸው፣ አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ አቅናም ዳያስፖራው እስካሁን በተለያዩ መንገድ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፣ አዲስ የተተገበረው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መተግበሪያ ብዙዎችን ተሳታፊ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች